መራሩን ፖለቲካ በቀልድ ያዋዛው መረራ

Wednesday, 31 January 2018 13:18

 

በጌትሽ ጎችቭስኪ

 

...መረራ ቦተሊካ የጀማመረው አምቦ ሁለተኛ ደረጃን ሲማር ነው። ያኔ አምቦ በራስ መስፍን ስለሺ አስተዳደር ስር ትናጥ ነበር። ቄሮው መረራ በዚህ ጊዜ ለሰላማዊ ሰልፍ አምቦ ላይ ከፍሬንድስ ጋር ተቃውሞ ወጣ። /የወንዙ ልጅ ፀጋዬ ይሄኔ ሳይሆን አይቀርም ለአምቦ የተቀኘላት፤
ምነው አምቦ?


እንዳልነበርሽ የደም ገንቦ


እንዳልነበርሽ ንጥረ ዘቦ


ከጠበልሽ ሲሳይ ታልቦ...


ዛሬ እንደዚህ ምነው አምቦ?/


...አአዩ ሲገባም ፖለቲካል ሳይንስ መረጠ። የመኢሶን ወጣት ክንፍ አመራር ሆነ። በመኢሶን እና ደርግ ፍቅር መሃል ንፋስ ሲገባ፤ በ1970 ዓም ታሰረ። ደርግ አስረኛውን የአብዮት በአል ሲያከብር፤ መስከረም ሁለት 1977 ዓ.ም ላይ በምክትል ፕረዘዳንቱ ፍስሃ ደስታ በኩል፤


"አብዮታችን ለተጎናፀፈው ዘላቂ ድል የደስታው ተሳታፊ እንድትሆኑ ምህረት ተደረጎላችኋል" ብሎ እስረኞችን ለቀቀ። ከነዚህ መሀል አንዱ ሰባት አመታት ማእከላዊ የነጠቀበት እና እድሜው 28 ዓመት የደፈነው መረራ ጉዲና ነበር።


በአአዩ ትምህርቱን ቀጠለ። የመጀመርያ ዲግሪውን በማእረግ ያዘ። ግብፅ- ካይሮ ከሚገኝ የአሜሪካን ዩኒቨርስቲ ሁለተኛ ዲግሪው የመማር እድል አገኘ። በፖለቲካል ሳይንስ ኤም ኤውን ጨርሶ ተመልሶ አአዩ በመምህርነት ቀጠለ። ፒኤችዲውን ከሆላንድ ዘሄግ ያዘ።


ፖለቲካል ሳይንስን ጥግ ድረስ ተምሮ ጥግ ድረስ አስተማረ። ...የኢህአዴግን የጫወታ ህግ ተከትሎ የፖለቲካ ፓርቲ አቋቁመ። በፖለቲካ ሰበብ ሰባት አመታት ቢሰረቅበትም፤ "ፖለቲካና ኮረንቲን በሩቁ" የሚለውን ተራ ብሂል የሚቀበል ተራ ሰው አይደለም። "ከፖለቲክስ በሸሸህ ቁጥር ካንተ ባነሱ ድንዙዞች እየተመራህ የበለጠ አሳርህን ታያለህ "ይልሃል እንጂ። ...በፖለቲካና ታሪክ አቋሙም፤ የኦሮሞ ብሔር ባለፉት ስርአቶች የተገፋ ነበር እያሉ ለሚያላዝኑትን መስሚያ ጆሮ የለውም።


"ኦሮሞ በአሮጌዋም ሆነ ባዲሲቱዋ ኢትዮጵያ ምስረታ ላይ ተገፊ ሳይሆን ተሳታፊ ነበር" የሚል ነው።


ነው! ...በሠላምም ጊዜ የበይ ተመልካችነት፤ በጦርነት ጊዜ ደሞ የተጨፍጫፊነት ታሪክ አይደለም ያለው ኦሮሞ። አብሮ በልቶ-ተበልቶ አብሮ ጨፍጭፎ-ተጨፍጭፎ ነው የዘለቀው። ስልጣን ሹዋሚም ሻሪም ሆኖ ነበር። የባህሉንም አሻራ ኢትዮጵያ ላይ አትሞ ኖሯል።


ለምሳሌ አጤ ሱስንዮስን ውሰድ። ኦሮሞ አምቦ አቅራቢያ ግንደበረት ውስጥ በጉዲፈቻ አሳድጎ ጎንደር ቤተ መንግስት ላይ ለንግስና አብቅቶታል። ...በየጁ ዳያናስቲ ብትልም አንጋሽም-አውራሽም-አውራጅም ነበር ኦሮሞ። ጦረኞቹ የየጁ ኦሮሞ መሳፍንት የያኔውን ጫወታ ህግን-ክብረ ነገስትን ተከትለው ለ80 አመታት አስተዳድረዋል። ከራስ አሊ ጉዋንጉል እስከ ትንሹ ራስ አሊ።


...የአጤ ምኒሊክ የጦር መሪዎች እና የቅርብ አማካሪዎችም የኦሮሞ ተወላጆች ነበሩ። የቅርብ ወዳጆችም ናቸው።አባ መላ የምንሊክን ተዝካር ሳይቀር በድብቅ ያወጡ ነበር። ራስ ጎበና እና ምኒልክ ልጅህን ለልጄ ተባብለው፤ ሸዋረጋ ምኒልክን/ለራስ ሚካኤል ከመዳራቸው ቀድሞ/ ለወዳጆ ጎበና አጋብተዋል። ከጋብቻው የተገኘው ልጅ ደጃዝማች ወሰንሰገድ ወዳጆ ጎበዝ የጦር አለቃ ነበር። እንደውም በምኒልክ የልጅ ልጅነቱ ለስልጣን ሁሉ ቀርቦ ነበር። ግን ወዳጆ በተፈጥሮ ድንክ ስለነበር መኳንንቱ ለመሪነት አይመጥንም ብለው ዘለውታል።


አዎን ! ኦሮሞ በሞደርን ኢትዮጵያ ግንባታ ወደ ዳር ተገፊ ሳይሆን ዋና ተሳታፊ ነበር። ነበር! ልክ እንደ ቄሮው መረራ፤ አምቦ ሁለተኛ ደረጃን ሲማር ሸቤ የተዶለው ቄሮው ሃጫሉ ሁንዴሳ፤ ባለፈው ቦሌ ላይ በጌሬርሳ "የፈረሶቻችንን ዱካ የአድዋ ተራሮች ላይ አለ "እያለ ሸልሏል። ልክ ነው! ሃጫሉ የአያቱን ወንድም የፀጋዬ ገ/መድህንን ግጥም እያነበበ ስላደገ ይህ አይጠፋውም...


/ዋ...አድዋ!


የአለት ምሰሶ አድማስ ጥግዋ፤


...እያለ ስለ አባ ጎራው፣ አባ ቃኘው፣ አባ መቻል/


ጎራው የገበየሁ፣ መቻል የፊታውራሪ ኃብቴ፣ ነፍሶ የደጃዝማች ባልቻ፣ ቃኘው የራስ መኮንን ፈረሶች ናቸው። የአድዋን ድል ያለነሱ እንዴት ማሰብ ይቻላል ታዲያ?


ባገር ውስጥ አመፅም፤ ከሚያምፁትም ሆነ ከሚያከሽፉት የኦሮሞ ተወላጅ በስፋት ተሳትፏል። በኢጆሌ ባሌ አመፅ በእነ ዋቆ ጉቱ የሚመራውን አመፅ ያከሸፈው ጄ.ጃገማ ኬሎ ነው። የ1953ቱ መፈንቅለ መንግስት ካከሸፉት ዋናው ጄ. ታደሰ ብሩ ነው። ደርጎች አጤው ስልጣን እንዲለቁ የፃፉትን ደብዳቤ ያደረሰውና ያነበበው ሻለቃ ደበላ ዲንሳ ነው። ቀይ ሽብርና ነጭ ሽብርም ላይ አሸባሪም ተሸባሪም ሆኖ ታሪክ ሰርቷል። ጄ.ተፈሪ በንቲ ሲገደል አስገዳዩ መንጌም የሸገር የጨርቆስ ልጅ ቢሆንም ኦሮሞ መሆኑን መፃፉ ላይ ያምናል። በ1981መፈንቅለ መንግስቱ ላይ እነ ጄ.ደምሴ ቡልቶን ቡድን ለማክሸፍ እነ ሻምበል መንግስቱ ገመቹ ተሳትፈዋል። በ1983 ግንቦት ላይ ከወያኔ እና ኦነግ መሪዎች- ከመለስ እና ሌንጮ ጋር ለመደራደር ተስፋዬ ዲንቃ ለንደን ነበር።


ታዲያ ኦሮሞ የሌለበትን የኢትዮጵያ ታሪክ እንዴት መፃፍ ይቻላል? ኦሮሞ የሌለበትን የሃገር ግንባታ ማውራትስ ቢሆን!? ለዚያ ነው መረራ ስለ ኦሮሚያ መገንጠል ሲጠየቅ የሚስቀው እና
"ኦሮሞ ግንድ ነው። ቅርንጫፎቹ ልገንጠል ቢሉ ነው የሚያምረው" የሚለው።


...ይህን አመለካከቱን ይዞ ታግሏል።


ዶር በ1997 የፓርላማ አባል ሆነ። ዶር መረራ በቀልድ እያዋዛ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ የሚመታ ፖለቲከኛ ነው። ነገር አያንዛዛም። ለምርጫው ዋዜማ የፓርቲዎች ውድድር ላይ ከአባዱላ ጋር ባንድ መድረክ ተገናኝቶ ነበር።


"አቶ ወይም ጄኔራል አባዱላ ዛሬ ስለ ኦነግ ሲያወሩ ስሜን ዘንግተውታል።መፃፋቸው ላይ ግን ሪፈረንሳቸው የኔ መፃፍ ነበር።"


/...በጫወታው ህግ መሰረት ወታደር የመከላከያ ሚኒስተር መሆን አይችልም። ጄኔራሉ ግን አቶ ተብሎ ሆኗል/


ከክርክር መድረኩ ሲወጡ አባዱላ መረራን እንዲህ አለው፤


"አቋምህ ምንድነው ?"


"ያው እንዳንተ ስፋቅ ኦነግ ነኝ።"


/መለስ ኦህዴዶችን ያላቸውን ጠቅሶ በነገር ሲወጋው ነው/


...ፓርላማ ውስጥ አንዴ አፈጉባኤዋ ለአስተያየት እድል ስትሰጠው፤


"እሺ ዶር መራራ ይቀጥሉ..."


"አመሰግናሎ ክብሪት አፈ ጉባኤ!"


/እሱ "መራራ" ከሆነ እሷ" ክብሪት" የማትሆንበት ምክንያት የለም።/


...መረራ አውሮፓ ደርሶ ይመለሳል። መለስ መረራን ፓርላማ ሲያገኘው እንዲህ አለና ሸነቆጠው፤


"እንደነ ብርሃኑ በዚያው የምትሸፍት መስሎኝ ነበር "


"ለመሸፈትማ ከአውሮፓ ይልቅ አምቦ ይቀርበኛል እኮ!"


...አሁን ዶር መረራ የሚኖርበት አሸዋ ሜዳ የአምቦ መውጫ ነው። ሜዳው ደሞ አሸዋ ሜዳ የሚል ስያሜ ያገኘበት ጉዳይ የመረራን ታሪክ አካል ነው። ለ10ኛ አብዮት በአል ታጠቅ የተሰበሰበው ሰልጣኝ ወታደር እዚህ ሜዳ ላይ ነበር የሰልፍ ልምምድ ያደረገው። ክረምት ላይ ጭቃው ሲያስቸግር ሬድ አሽ-ቀይ አሸዋ አፈሰሱበት። ስሙም በዚያው እሸዋ ሜዳ ተባለ። እዚህ የተለማመደው ሰልፈኛ ትርኢት ያቀረበ እለት ነው ወጣቱ መረራም በምህረት ከእስር የተፈታው።


...ዶር መረራ በ2002 ምርጫ ሲሳተፍ የውጭ ሚዲያ "ታሸንፋለህ ወይ ?" ብሎ ጠየቀው። መረራ የስታሊንን ንግግር ጠቅሶ፤ "People vote, we count." ብሎ ጋዜጠኛውን አዝንናናው። ቆጠራውን እንጂ ምርጫውን አሸንፋለው፤ ማለቱ ነው።እውነቱን ይመስላል። ትናንት አምቦ የወጣው ህዝብ፤ ምርጫውን አሸንፎ ቆጠራው ላይ መሸነፉን ይመሰክራል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
162 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1061 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us