የአፍሪካ ቀንድ እና ጅኦፓለቲካዊ ትኩሳቱ

Wednesday, 14 February 2018 12:02

 

ኢዛና ዘመንፈስ

 

ይህ አህጉራችንን አፍሪካን ከቀይ ባህርና ከህንድ ውቅያኖስ ጋር የሚያዋስናት የቀንዱ አካባቢ ዓለም አቀፋዊ ትኩረት የሚስብ ጅኦ ፓለቲካዊ እውነታ እንዳለው ይታመናል። ለዚህ እንደዋነኛ ምክንያት የሚወሰደውም ቀጣናው በተለይም ለመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ካለው ቅርበት የተነሳ፤ እንደወሳኝ የዓለም አቀፍ ንግድ እንቅስቃሴ መናኸሪያ የሚታይ መሆኑ ነው። በእርግጥም ደግሞ ሳዑዲ ዓረቢያን ጨምሮ ሌሎቹ የዓረብ ባህረ ሰላጤ የነዳጅ ዘይት አምራች ሀገራት ከአፍሪካ ቀንድ ጅኦፓለቲካዊ እውነታ ጋር በጥብቅ የሚቆራኙበት አግባብ መኖሩ የሚካድ ጉዳይ አይደለም ማለት ይቻላል። እናም ከዚህ አኳያ ይሄ የምንገኝበት የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ዓለም አቀፋዊ ትኩረትን እየሳበ የመጣ ጅኦ ፓለቲካዊ ትኩሳት እየተስተዋለበት ስለመሆኑ ነው የታመኑ የመረጃ ምንጮች የሚያመለክቱት።


እግዲያውስ እኔ በዚህ ፅሁፍ ለማንሳት የፈለግኩት ዋነኛ ርዕስ ጉዳይም፤ ይልቁንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ምስራቅ አፍሪካን ከዓረቡ ክፍለ ዓለም ጋር በሚያዋስነው የቀይ ባህርና የህንድ ውቅያኖስ ዳርቻ፤ ወታደራዊ የጦር ሰፈሮችን ለመክፈት ያለመ የሀገራት እንቅስቃሴ ጎላ ባለ መልኩ እየተስተዋለ ስለመሆኑ የሚያትት ነው። ስለዚህም አሁን በቀጥታ ወደዋው ነጥብ አልፌ፤ ለመሆኑ ካለፈው የጎርጎሪሳውያኑ 2017 ዓ.ም ጀምሮ ወደ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ፊታቸውን እያዞሩ የየራሳቸውን ወታደራዊ የጦር ካምፕ ለመመስረት ያለመ እሽቅድምድም ላይ ተጠምደው የሚስዋሉት የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የትኞቹ ናቸው? ለምንስ ነው ሀገራቱ በአካባቢያችን የጦር ሰፈር ይዞታ እንዲኖራቸው የፈለጉት? ጉዳዩ ኢትዮጵያን የሚያሳስብበት አግባብስ አለ ወይ? ወዘተ በሚሉ ጥያቄዎች ዙሪያ የሚያጠነጥን መሰረተ ሃሳብ አነሳለሁ።


እንግዲህ አሁን ላይ ስለነዚህ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ እየተስተዋለ ስላለው ጅኦፓለቲካዊ ትኩሳቱ እየጨመረ መምጣቱን የሚያመለክት እውነታ በርካታ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን የየራሳቸውን ወቅታዊ ዘገባና ሙያዊ ትንታኔ እያቀረቡበት ስለመሆናቸው ደፍሮ መናገር ይቻላል። በዚህ መሰረትም ትኩሳቱን ስላስከተለው ዋነኛ ምክንያት አስተያየታቸውን ሲሰጡ ከሚደመጡት ታዛቢዎች አብዛኛዎቹ የሚስማሙበት ጉዳይ፤ በቅርቡ ሳዑዲ ዓረቢያና ሸሪኮቿ ከኳታር ጋር ያልተጠበቀ ውዝግብ ውስጥ ገብተው የተስተዋሉበት ክስተት በአንዳንድ የገልፍ አካባቢ ሀገራት ላይ የፈጠረው የደህንነት ስጋት ነው የሚል ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ከዚሁ ጋር በተያያዘ መልኩ እንደተጨማሪ ምክንያት የሚወሰደው ደግሞ፤ የእስልምና ሃይማኖት የተመሰረተበትን እሳቤ “የሱኒና የሺአ” በሚል ፍረጃ ከሁለት ከፍለው የሚያቀነቅኑት ወገኖች የየራሳቸውን ጎራ እየለዩ ለመስፋፋት የሚሞክሩበት አግባብ እያሳደረ ያለው ተፅእኖ ነው ማለት ይቻላል።


ከዚህ አኳያ የሚስተዋለውን የሁለትዮሽ ጎራ ለይቶ በእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ፉክክር ምክንያት የመፋጠጥና የመጠላለፍ ሽኩቻ በፊታውራሪነት የሚመሩት ሀገራት ሳዑዲ ኣረቢያና ኢራን ስለመሆናቸውም ተደጋግሞ የተነገረ ጉዳይ ነው። ለአብነት ያህልም የመካከለኛው ምስራቅ ብቸኛዋ ድሀ ሀገር ተደርጋ የምትወስደውን የመንን ወደ ለየለት ምድረ በዳነት እየቀየራት ያለውን የእጅ አዙር ጦርነት የሚያካሂዱት ሃይሎች፤ በአንድ ፊት ኢራን በሌላ ፊት ደግሞ ሳዑዲ ዓረቢያ የተሰለፉበትን የሺአና የሱኒ ጎራ እንደሚወክሉ ይታመናል። ከዚህ ስር የሰደደ የሁለቱ ሀገራት (የሳዑዲ ዓረቢያና የኢራን) እስላማዊ መንግስታት መካከል የሚስተዋል ቅራኔ እየተካረረ መምጣት ጋር በተያያዘ የባላንጣነት ስሜት የመን ውስጥ እየተካሄደ ያለው ጦርነት፤ ለዚያች ሀገር ህዝብ የዕልቂት ምንጭ ከመሆኑም ባሻገር፤ ጦሱ ለመላው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ጭምር እንዳይተርፍ መሰጋቱን ምንጮች ያመለክታሉ። እናም ይሄው የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት እነዚህን ከመሳሰሉት የዕርስ በርስ ግንኙነታቸውን የሚያሻክሩ ምክንያቶች ጋር በተያያዘ መልኩ እየፈጠሩ ያለው ጎራ ለይቶ የመፋጠጥ አዝማሚያ እየተካረረ ከመምጣቱ የተነሳ፤ የፍጥጫው መሪ ተዋኒያን የሆኑት የነዳጅ ሀብት ባለፀጋ መንግስታት የየራሳቸውን ወታደራዊ ጡንቻ ለማሳየት ወደ የአፍሪካ ቀንድ ቀጠና የጦር ሰፈር ይዞታቸውን በማስፋፋት ላይ ተጠምደዋል ነው የሚባለውም።


ከዚህ አኳያ የወቅቱ ዓለም አቀፋዊ መነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ እስከመሆን የደረሰውን የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ጅኦፓለቲካዊ ትኩሳት በሚመለከት የየራሳቸውን ትንተና ሲሰጡ የሚደመጡ ምሁራን ምን እንደሚሉ ማስታወስ ጠቃሚ ይመስለኛል። ስለሆነም ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉ አጠቃላይ እውነታውን ከመገምገም የሚመነጭ ሙያዊ ገለፃ በማቅረብ ረገድ የሚወቁት የፓለቲካ ተንታኞች እንደሚያስረዱት፤ አሁን ላይ በአፍሪካ ቀንድ የቀይ ባህርና የህንድ ውቅያኖስ ዳርቻዎች ለወታደራዊ የጦር ሰፈር የሚሆን አንድ ጥግ መርጦ በኮንትራት መልክ ስለመያዙ የማይነገርለት የመካከለኛው ምስራቅ ዓረባዊ ሀገር የለም። በዚህ ረገድ ሶማሊያ፤ ሶማሊላንድ፤ ጅቡቲ፤ ኤርትራና ሱዳን ለመካከለኛው ምስራቅ ዓረባዊ ሀገራት የጦር ሠፈር የሚሆን የወደብ አካባቢ ቦታ ሳይፈቅዱ እንዳልቀሩ ነው መረጃዎቹ አክለው የሚያመለክቱት። ለአብነት ያህልም ሳዑዲ ዓረቢያን ጨምሮ፤ ሌሎች የአካባቢው ባለፀጋ ሀገራት “ኢስላማዊ የፀረ ሽብርተኝነት ጥምረት” በሚል ስያሜ ያቋቋሙት ወታደራዊ ሃይል ኤርትራ ውስጥ ከአሰብ ወደብ አቅራቢያ የሚገኝ ስፍራን በካምፕነት ስለመያዙ ጉዳይ ከተነገረ ዓመታት ተቆጥረዋል።


እንዲሁም ደግሞ አውሮፓዊቷ ሀገር ቱርክና እንደ ኳታር ያሉት የመካከለኛው ምስራቅ ሸሪኮቿ ሶማሊያ ውስጥ በተናጠል የያዙት ወታደራዊ የጦር ሰፈር እንዳለ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንደ ሀገር ዕውቅና ባይሰጣትም የራሷን ሉዓላዊ ግዛት ፈጥራ ማስተዳደር ከጀመረች ከ26 ዓመታት በላይ ያስቆጠረቺው ሶማሊላንድ እንኳን በአቅሟ፤ ለተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ተመሳሳይ ዕድል የሰጠችበት ሁኔታ ስለመኖሩ ነው ምንጮቹ የሚገልፁት። ጅቡቲ ራሷም ከዚሁ የአፍሪካ ቀንድ ጅኦፓለቲካዊ ትኩሳት መገለጫ እውነታ የፀዳች ናት ተብሎ አይታመንም። እንዲህም ሆኖ ግን እንደ ሻዕቢያ መራሹ የአስመራ አገዛዝ የኤርትራን ቆላማ አካባቢዎች ለመካከለኛው ምስራቅ ባለ ፀጋ መንግስት የጦር ካምፕነት መቸብቸቡን የቀጠለ የአፍሪካ ቀንድ ሀገር የለም ማለት ይቻላል። ለዚህም ደግሞ አሁን ሰሞኑን በስፋት እያነጋገረ ስለሚገኘው፤ ቱርክና ግብፅ ኤርትራ ውስጥ በምዕራባዊ የቀይባህር ዳርቻ የየራሳቸውን ወታደራዊ የጦር ስፈር ለመመስረት ከሻዕቢያ መንግስት ጋር መስማማታቸውን ተከትሎ በአካባቢው ውጥረት መስፈኑን የሚያወሱ ዘገባዎች እየወጡ መሆናቸውን ማንሳት ብቻ ይበቃል። ለነገሩ የፕሬዘዳንት ኦማር ሐሰን ዓል በሽር ሱዳንም ከኤርትራ ጋር በሚያዋስናት የምዕራባዊ ቀይ ባህር አካባቢ የሚገኝ አንድ ደሴቷን ለቱርክ መንግስት ለዘጠና ዓመት የሚቆይ ኮንትራት ፈርማ ሰጥታለች ሲሉ እንደ ሳዑዲ ዓረቢያ ያሉ ሀገራት የሚያሰሙት ቅሬታ እንዳለም መረጃዎች ያሳያሉ።


እንግዲህ ስለወቅታዊው የአፍሪካ ቀንድ ጅኦፖለቲካዊ ትኩሳት ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሲያነሱ የሚደመጡት ከሞላ ጎደል ይህን እንደሚመስል ደፍሮ መናገር ይቻላል። ስለዚህም ቀጥሎ መነሳት የሚኖርበት መሰረታዊ ጥያቄ፤ ታዲያ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ልዕለ ሃያሏ ሀገር ኢትዮጵያ ይህን ጉዳይ እንዴት ታየዋለች? የሚል ይሆናል። እናም ባለፈው ሳምንት ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ስለወቅታዊው የሀገራችን አጠቃላይ እውነታ መግለጫ የሰጡት የኢፌዴሪ መንግስት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሃላፊ ሚኒስትር ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ፣ የአፍሪካ ቀንዱን ጅኦፖለቲካዊ ትኩሳት በሚመለከት ጥያቄ ቀርቦላቸው “ሁኔታው ኢትዮጵያን የሚያሳስብ ነው የሚል እምነት የለንም” ሲሉ መልሰዋል። ሌሎች የኢፌዴሪ መንግስት ባለድርሻ አካላትም ቢሆኑ በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡበት ሲጠየቁ ከዶክተር ነገሪ እንብዛም የተለየ አቋም ላይ አለመደረሱን የሚያመለክት ተመሳሳይ ምላሽ እንደሚሰጡ ነው እኔ በግሌ ያረጋገጥኩት።


በአንፃሩ የምስራቃዊ አፍሪካን ጅኦ ፖለቲካዊ እውነታዎች የሚመለከት ጥናትና ምርምር በማካሔድ ረገድ የሚታወቁ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ምሁራን፤ በቀንዱ አካባቢ እየተስተዋለ ያለው ውጥረት እኛን የሚያሳስብ አይደለም የሚባል እንዳልሆነ ሲያስገነዝቡ ይሰማሉ። ለዚህ አስተያየቴ በዋቢነት ልጠቅስ የምችለውም ደግሞ አቶ አብዱል መሐመድን ነው። አቶ አብዱል መሐመድ “ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ” በመባል የሚታወቀውን ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስርዓት ግንባታ ሂደት መፋጠን የሚያግዙ ቅድመ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ጥረት የሚያደርግ የስቪክ ተቋምን ከመሰረቱት የሀገራችን ምሁራን አንዱ ሲሆኑ፤ በቅርቡ የአፍሪካ ቀንድን ወቅታዊ ጉዳይ አስመልክተው ምን እንዳሉ ልንገራችሁ።


በዚህ መሰረትም አቶ አብዱል መሐመድ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከሸገር 102.1 ኤፍ ኤም.ሬዲዮ ጣቢያዋ አንጋፋ ጋዜጠኛ ከመዓዛ ብሩ ጋር ቆይታ ባደረጉበት ውይይት ላይ በተለይም እንደ ሳዑዲ ዓረቢያ ዓይነቶቹ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በገፍ የሚገዙትን ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ሲያስቡ ጦሱ ለኛም ይትርፍ ይሆናል የሚል ስጋት እንደሚሰማቸው መግለፃቸውን አስታውሳለሁ። ምሁሩ ለዚህ ስጋታቸው እንደዋነኛ ምክንያት ያቀረቡት የመከራከሪያ ነጥብም “ሳዑዲ ዓረቢያውያኑ ሀብት ስላላቸው ብቻ፤ ከምዕራቡም ከምስራቁም ዓለም ዘመኑ ያፈራውን የጦር መሳሪያ በመግዛት የሚታወቁትን ያህል ይሄን የረቀቀና የመጠቀ የጦር መሳሪያ ቴክኖሎጂ ለመታጠቅ የሚያስችል ዕውቀት ያለው ወታደራዊ ሃይል ይኖራቸዋል ተብሎ አይታመንም። እናም አሁን በጎረቤት የመን እየተካሔደ ያለው ጦርነት ተባብሶ በቀጠለ ቁጥር ሳዑዲዎቹ ያከማቹት የጦር መሳሪያ ከእነርሱ እጅ እየወጣ በሌሎች የሽብርተኝነት እንቅስቃሴ ላይ በተሰማሩ ቡድኖች እጅ ውስጥ ሊገባ የማይችልበት ምክንያት ስለማይኖር ነው ጉዳዩ ለአፍሪካ ቀንድ ሀገራትም ጭምር ስጋት ተደርጎ መወሰድ ያለበት” ብለዋል።


ይልቁንም ደግሞ የመላው ምስራቅ አፍሪካን ቀጣና ሰላምና መረጋጋት በማስጠበቅ ረገድ ቁልፍ የሚባል ግንባር ቀደም አወንታዊ ሚና ስትጫወት የምትስተዋለው ኢትዮጵያ፤ የአካባቢው ልዕለ ሃያል ሀገር እንደመሆኗ መጠን፤ አሁን አሁን በዚሁ የቀይ ባህርና የህንድ ውቅያኖስ ዳርቻ (የቀንዱ አካባቢ) እየተፈጠረ ያለውን ጅኦፖለቲካዊ ውጥረት ጥንቃቄን በሚጠይቅ ክትትል ልትመለከተው እንደሚገባ ነው አቶ አብዱል መሐመድ ያስገነዘቡት። ሀገራችን እንደ ሱዳንና ጅቡቲ ካሉት ጎረቤቶቿ ጋር የፈጠረችውን በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ግንኙነት እንደሚያደንቁ ያልሸሸጉት የኢንተር አፍሪካ ግሩፕ ዋና ዳይሬክተሩ፤ ግን ደግሞ የኤርትራው መንግስት ኢትዮጵያን በበጎ መንፈስ እንደማይመለከታት ከታመነ ዘንዳ፤ በተለይም ከአፍሪካ ቀንዱ ጅኦፖለቲካዊ እውነታዎች አኳያ መደረግ የሚኖርበትን ተገቢ ጥንቃቄ የማድረግ ጉዳይ ቸል መባል እንደሌለበት ነው ያሰመሩበት። የኢፌዴሪ መንግስት የሚከተለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ስትራቴጂ ሀገራችንን ለክፉ የሚሰጥ ነው የሚል እምነት እንደሌላቸው የገለፁት አቶ አብዱል መሐመድ፤ ይህ ኢትዮጵያ የምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ዓለም አቀፋዊ የመርከብ ንግድ እንቅስቃሴ ከሚካሔድበት የቀይ ባህርና የህንድ ውቅያኖስ ቀጣና ጋር የሚዋስን በመሆኑ ምክንያት ጭምር የተለየ ጥንቃቄን የሚጠይቅ ጅኦፖለቲካዊ እውነታ መኖሩን ያገናዘበ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ መክረዋል።


ሌላው በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት መካከል ስላለው ጅኦ ፖለቲካዊ እውነታ የጥናትና ምርምር ስራዎችን በመስራት ረገድ የሚታወቁት ኢትዮጵያዊ ምሁር ደግሞ ፕሮፌሰር መድህኔ ታደሰ ናቸው። እናም ፕሮፌሰር መድህኔ ታደሰ የአካባቢውን ሀገራት በእጅጉ ሊያሳስባቸው የሚገባ የጋራ ስጋት ስለመሆኑ አበክረው የፃፉለት የአፍሪካ ቀንድ ጅኦ ፖለቲካዊ ርዕሰ ጉዳይ፤ በተለይም “ሱኒና ሽዓ” ከሚል መፈራረጅ እንደሚመነጭ የሚነገርለትን የመካከለኛው ምስራቅ የእስልምና እምነት ተከታይ መንግስታት ከሚያራምዱት የሁለትዮሽ አቋም ጋር በተያያዘ መልኩ ሊዛመት የሚችል ፅንፈኝነትን ነው። እንዲያውም እውነቱን እንነጋገር ከተባለማ፤ ይህ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የአለም አቀፋዊ ፅንፈኛ ቡድኖች አፍራሽ እንቅስቃሴና የሽብር ጥቃታቸው ግንባር ቀደም ኢላማ የመሆን ዕድሉ የሰፋ ነው ሲሉ ገና ከዛሬ 20 ዓመት ጀምሮ በአፅንኦት ያስገነዘቡ ብቸኛ ኢትዮጵያዊ ምሁር እኚሁ ፕሮፌሰር (ያኔ ዶክተር እንደ ነበሩ ልብ ይሏል?) መድህኔ ታደሰ እንደሆኑ ማስታወስ ይቻላል። ለማንኛውም ግን ይህ የምንገኝበት የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና በተለይም ለመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ቅርበት ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንደሚስተዋል የሚገመት ጅኦፖለቲካዊ ውጥረትና ትኩሳት የማይለየው አካባቢ ስለመሆኑ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ይመስለኛል። ለዚህም ደግሞ አሁን ላይ መላውን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በስፋት እያነጋገረ ካለው ወቅታዊ እውነታ የተሻለ ማሳያ እንደማያሻን ነው የሚሰማኝ። በተረፈ የዛሬውን ሐተታየን እነሆ እዚህ ላይ አብቅቻለሁ። መዓ ሰላማት!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
120 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 841 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us