50 የመተሳሰብና የመፈቃቀር ዓመታት

Wednesday, 28 February 2018 12:59

 

50 ዓመት ስንኖር ክፉ ደግ ተነጋግረን ጎረቤት ጣልቃ ገብቶ አያውቅም (አቶ አበራ ውርጌሳ)
ተቻችለንና ተደጋግፈን እዚህ ደርሰናል (ወ/ሮ ዝናሽወርቅ በቀለ)

 

በጋዜጣው ሪፖርተር

 

አቶ አበራ ውርጌሳ የዛሬ 68 ዓመት በአዲስ አበባ ነው የተወለዱት። አዲስ ከተማ ክ/ከተማ ያደጉት አቶ አበራ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በንግድ ሥራ ላይ የቆዩ ሲሆን እድሜያቸው ከፍ ሲል ቤተሰቦቻቸው ለልጃቸው ውሃ አጣጭ ፍለጋ ጀመሩ። ፍለጋውም ሶዶ ላይ ማረፊያውን አግኝቶ በቤተሰባቸው ጨዋነትና በልጅት ቁንጅና አማካኝነት የወ/ሮ ዝናሽወርቅ በቀለ ቤተሰብ በአቶ አበራ ቤተሰብ “ልጅህን ለልጄ” ተብሎ በአገር ባህልና ወግ ልጆች ሳይተዋወቁ ሁለት ቤተሰቦች ስምምነት ላይ ደረሱ።


እናም የካቲት 10 ቀን 1960 ዓ.ም የ18 ዓመቱ አፍላ ወጣት የ16 ዓመቷን ኮረዳ በትዳር ጠቅልለው ከሶዶ ወደ አዲስ አበባ በማምጣት ሶስት ጉልቻ ተጀመረ። እርግጥ ነው እንደዛሬው ቢሆን አቶ አበራ እድሜዋ ለጋብቻ ያልደረሰችን ልጃገረድ በማግባት ለእስር ይዳረጉ ነበር።


እነዚህ የሰርጋቸው እለት አይን ለአይን የተያዩት ጥንዶች በጋብቻና በፍቅር ተሳስረው 50 የመተሳሰብ የመፈቃቀርና የመደጋገፍ ዓመታትን ዘልቀው ከሁለት ሳምንት በፊት ኮልፌ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው 50 ዓመት የጋብቻ የወርቅ ኢዩቤልዩ በዓላቸው ተደግሶ ነበር።


ጥንዶቹ በአሁኑ ወቅት ስድስት ሴት እና ሶስት ወንዶች ልጆችን አፍርተው 11 የልጅልጆችን ያዩ ሲሆን አሁንም ፍቅራቸው ሳይቀዘቅዝ በልጅ ልጅ በጥሩ ጤናና በባለፀግነት ተባርከው የደስታ ኑሮ እየመሩ ይገኛሉ።


“ያየኋት የሰርጋችን ቀን ነው፤ ካየኋት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ በፍቅርና በመተሳሰብ ኖረናል። የተካረረ ጠብ ተጣልተን ጎረቤትም ሆነ ዘመድ አዝማድ በመካከላችን ገብቶ አስታርቆን አያውቅም ይላሉ አቶ አበራ። ወይዘሮ ዝናሽ ወርቅ በበኩላቸው “አንድን ትዳር እንዲፀናና በሰላም እንዲቆይ የሚያደርገው መቻቻል እና አንዳንድ ነገሮችን አይቶ እንዳላዩ በመሆን ማለፍ ነው” ይላሉ። ጥንዶቹ ዛሬ ላይ ባልየው 68 ዓመት ወ/ሮዋ 66 ዓመት፣ ቢሞላቸውም አሁንም የ50 እና የ45 ዓመት ጎልማሳ እንጂ ወደ ሰባዎቹ የተጠጉ አይመስሉም። አባወራው ጭምትና ዝምተኛ ሲሆኑ ወይዘሮዋ ንቁ ፍልቅልቅና በፈገግታ የተሞሉ ናቸው።


እስከ 1980ዎቹ በአዲስ ከተማ አካባቢ መኖሪያቸውንና የንግድ ስራቸውን አድርገው የቆዩት ጥንዶቹ በአሁኑ ሰዓት ኮልፌ አጠና ተራ አካባቢ በገነቡት G+1 ቤት ውስጥ በሠላምና በፍቅር ይኖራሉ።


አክሊሉ አበራ ለነዚህ ጥንዶች 3ኛ ልጅ ነው። የቤተሰቡ ፍቅር መቻቻልና የተረጋጋ ህይወት እጅጉን እንደሚደንቀው ይናገራል። “እናትና አባቴ የፍቅር ተምሳሌቶች ናቸው። እኛ ከነሱ የተማርነው በርካታ ቁምነገር ለህይወታችን በጣም ጠቅሞናል” በማለት አንጋፋዎቹ ተምሳሌቶች ያሳለፉትን የመቻቻልና የፍቅር ጊዜ ለልጆቻቸው እንዳስተላለፉ ይናገራል።


ቤተልሄም አበራና ፍሬ ህይወት አበራ ለቤተሰባቸው 5ኛና 6ኛ ልጆች ናቸው። “እናታችን እናት ብቻ ሳትሆን ጓደኛችንም ናት ቤትና ትዳሯን አክብራ ፍቅርና እንክብካቤ ጨምራ ለዚህ አድርሳናለች” ይላሉ። ከቤተሰባቸው የወረሱትን በፍቅርና በአክብሮት የመኖር ፀጋ እህትማማቾቹ በህይወታቸው እየተገበሩ ሲሆን፤ ሁለቱም ከ10 ዓመት በፊት በወራት ልዩነት አግብተው 10ኛ ዓመት የጋብቻ በአላቸውን ለማክበር እየተሰናዱ መሆናቸውን ነግረውናል። እያንዳንዱ አራት ልጆች አፍርተው እናትና አባታቸውን የአያትነት ወግና ማዕረግም አጐናፅፈዋል። አባታቸው አቶ አበራ ለእናታቸው ያላቸው አክብሮትና መረዳት የእናታቸው ትዕግስትና ልባዊ ፍቅር ዛሬ እነሱም ለሚመሩት የተስተካከለ ህይወት መሠረት እንደሆናቸው ይናገራሉ።


ገረመው ንጉሴ የእነ አቶ አበራን ልጅ በማግባት ቤተሰቡን በጋብቻ ተቀላቅሎ በደስታ ህይወቱን ይመራል። በንግድ ሥራ ላይ የተሰማራው ገረመው የብሩህ አዕምሮ ባለቤትና እጅግ የሚደነቅ ጠቅላላ እውቀት ያለው ወጣት ነው። ጥንዶቹ አንጋፋዎች በባህሪዋም በመልኳም የተስተካከለችና ምርጥ ሚስት ስለሰጡት አማቶቹን ያመሰግናል። “እኔ መጀመሪያ ያገኘኋት እሷን ነው፤ ቀጥሎ ቤተሰብ ነው የሚገኘው” የሚለው ገረመው፤ ቤተሰብ በጥሩም ይሁን በመጥፎ ጐን ልጆቹ ላይ ተፅዕኖ እንደሚያደርግ ገልጾ፣ ትዕግስትና ቁም ነገሯን ስመለከት የወላጆቿ ተፅዕኖ በትክክል እንዳረፈባት እገነዘባለሁ ብሏል። “እኔ ግልፍተኛ ስሆን እሷ ሁሉን በትዕግስት ታልፋለች” ሲል ያክላል። በጓደኝነታቸው ወቅት ስለቤተሰቦቿ ታጫውተው እንደነበር የሚገልፀው ገረመው በጋብቻ ከተሳሰሩ በኋላ ቤተሰቧን ሲረዳ በጣም ጥሩና መልካም ብዬ የምገልፃቸው አይነት፣ በልጆቻቸው ትዳር ጣልቃ የማይገቡ እና ልጆቻቸውንም የልጆቻቸውን ትዳርም ሆነ የልጆቻቸውን ባሎች እንደልጆቻቸው የሚቆጥሩ ብሩክ አባትና እናት ስለመሆናቸው በክብረ በዓሉ ላይ በተገኘን ጊዜ አጫውቶናል። እኛ ለስሙ አማች ብንሆንም ከልጆቻቸው እኩል የምንታይ በመሆናችን እድለኞች ነን በማለት አቶ አበራ እና ወ/ሮ ዝናሽ ወርቅን አመስግኖ እረጅም እድሜና ጤና ተመኝቷል።


ኢዮብ ታሪኩ የቤቱ አምስተኛ ልጅ የሆነችው የፍሬህይወት ታሪኩ የትዳር አጋር ነው። ባለቤቱን በሰው አማካኝነት ተዋውቆና አጥንቶ እንዳገባት ይናገራል። ከዚያ በኋላ ወደ መጠናናትና ከዚያም ወደ ጋብቻ በመሄድ 11ኛ ዓመት የትዳር ጊዜ ላይ መሆናቸውንና አራት የአብራካቸውን ክፋዮች አግኝተው ለመሳም እንደበቁ ይናገራል። “ፍሬ የተባረከች ልጅ ሆና አግኝቻታለሁ ከጋብቻችን በኋላ ከቤተሰቧ ስቀላቀል የእነሱ ውጤት መሆኗ የያዘችውን መልካም ስብዕና እንድትይዝ እንደረዳት ማወቅ ችያለሁ” ይላል። ቤተሰቡ ፍቅር፣ መቻቻልና መከባበር ያለበት ቤት በመሆኑ የቤተሰቧን አርአያ ተከትላ የወጣች በመሆኗ ከምንም በላይ ባህሪዋ ማርኮኝ ነው ያገባኋት ይላል። ቤተሰብ ጥሩም መጥፎም ፍሬ ለማፍራት አካሄዱ እና አኗኗሩ ይወስነዋል ያለ ሲሆን፤ አቶ አበራና ወ/ሮ ዝናሽወርቅ መልካም አሳቢና ቅን ሰዎች በመሆናቸው ተሳስበውና ተከባብረው እዚህ በመድረሳቸው ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢና ለጐረቤት ምሳሌ መሆን መቻላቸውን አቶ ኢዮብ ይናገራል።


ጥንዶች ረጅምና ስኬታማ የትዳር ህይወት ለመምራት ምን ማድረግ አለባቸው ስንል የጠየቅናቸው አቶ አበራና ባለቤታቸው፤ “ዋናው ነገር መቻቻል፣ መተማመንና መከባበር ነው። ወደ ጋብቻ በችኮላ ከመግባት ጊዜ ወስዶ መጠናናትና መተዋወቅ ወሳኝ ነገር ነው” ሲሉ መልዕክት አስተላልፈው በዕለቱ ድግስ ደግሰው ወዳጅ ዘመድ ሰብስበው ይህንን ክብረ በዓል በደስታ እንድናከብር ያደረጉትን ልጆቻቸውንና የልጆቻቸውን ባለቤቶችና ወዳጅ ዘመዶቻችንን እናመሰግናለን ብለዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
150 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 822 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us