የአካውንቲንጉ አባት አበርክቶ ሲታሰብ…

Wednesday, 14 March 2018 13:08

 

                                                                                   

በደረጀ ትዕዛዙ

በተለያዩ ሙያ ውስጥ ሆነው አገራቸውንና ወገናቸውን በመደገፍ በግብራቸው ስማቸውን ያገነኑ ሊቃውንቶቻችን ጥቂት ናቸው። እነዚህ ጥቂቶቹም ቀስ በቀስ በማይመክቱት ተፈጥሯዊ ህግ እየተወሰዱ «ነበሩ» እንድንል ተገደናል። ባላቸው ሳይንሳዊ ዕወቀትና ምጥቀት ለአገር፤ ብሎም ለዓለም ባበረከቱት አስተዋጽኦ የሎሬትነት ማዕረግን የተቀዳጁት እንደነ ፀጋዬ ገብረ መድህን እና አፈወርቅ ተክሌን የመሳሰሉት የጥበብ ሰዎች ህልፈታቸው ምን ያህል ልባችንን እንደሰበረው እንረዳለን።

እንዲህ አይነት ሰዎች የማንነታችን ማሳያ፣ የክብራችን መገለጫዎችም ጭምር ናቸው። ነበሩ። ማንነታቸው ሲነገር፣ እንዲኖር የሚያስገድድ ተግባር ፈጽመው አልፈዋልና ተከታታዩ ትውልድ ምንግዜም ሲያስባቸው ይኖራል።

ባለፈው ዓመት ልክ በዛሬው ዕለት በሥጋ ሞት ያጣናቸውን ምሁር (ኤሚሪተስ ፕሮፌሰር) ዮሐንስ ክንፉን ዛሬ በዚህች አጭር ጽሑፍ ልናስባቸው ወደድን። እናም ማንነታቸውን፣ የነበራቸውን ሙያዊ አበርክቶና ስብዕናቸውን እንዲህ ጥቂቱን ጨልፈን እንደሚከተለው አሰፈርነው።

ከአንጥረኛው ባለጸጋ ደጃዝማች ክንፉ ኪዳኔ እና ከወ/ሮ ዋጋዬ ገ/ሚካኤል ሰኔ 23 ቀን 1928 ዓ.ም ከወደ ትግራይ አክሱም ውስጥ ተወለዱ። ታሪክ አክባሪ፣ ባህል ጠባቂ፣ ወግ አጥባቂ (Conservative) ከሆኑ ቤተሰብ ውስጥ ያለ ችግር ሲያድጉም፤ ከቤተሰቡ ውስጥ በልዩ ትኩረት ትምህርትን አጥብቀው እንዲይዙ በበጎ ተጽዕኖ ውስጥ ሆነው ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ውስጣቸው እየሰረጸ የሄደው ትምህርት ኋላ ላይ ማደጊያቸው፣ መከበሪያቸው፣ አገራቸውንም ማስጠሪያ ጭምር ሆነ።

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በኤርትራ አስመራ ከተማ ኮምቦኒ ት/ቤት፤ የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሱዳን ካርቱም ኮምቦኒ ት/ቤት ሲማሩ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በኮተቤ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ት/ቤት ነው የተከታተሉት።

እ.ኤ.አ. በ1960 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አገኙ። ጥሩ ውጤት በማምጣታቸው ባገኙት ስኮላርሺፕ ዕድል በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1963 በአካውንቲንግ ዘርፍ ከአሜሪካው ኡታህ ዩኒቨርሲቲ የማስትሬት ዲግሪያቸውን ተቀብለው ወደ አገራቸው ተመለሱ። በመቀጠልም እ.ኤ.አ. በ1970 ዓ.ም. በዚያው በአሜሪካን ሀገር ከሚገኘው ከሚቺጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አስተዳደር ዘርፍ የዶክትሬት (DBA) ዲግሪያቸውን ይዘው ተመለሱ።

ከዚህ በኋላ የበቁ ምሁር ሆነው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ኋላም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፈረንጆች ብቻ ያስተምሩት የነበረውን የአካውንቲንግና ሌሎች ተያያዥ ትምህርቶችን ተረክበው በቋሚነት ማስተማር፣ መምራት ቀጠሉ።

ፕሮፌሰር በዩኒቨርሲቲው በአካውንቲንግ የትምህርት መስክ በማስተማር የሙያ ጉዞአቸውን «ሀ» ብለው የጀመሩት እ.ኤ.አ. በ1963 ዓ.ም። እ.ኤ.አ. በ1970 ዓ.ም. በዩኒቨርሲቲው የረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ያገኙ ሲሆን፣ በ1974 የተባባሪ ፕሮፌሰርነት እንዲሁም በ1995 ዓ.ም. በአካውንቲንግ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግን ተቀብለዋል። በመደበኛ አስተማሪነትና ተመራማሪነት እንዲሁም የድህረ ምረቃ ተማሪዎችን በማማከር በአጠቃላይ በዩኒቨርሲቲው ከ47 ዓመታት በላይ እንዳገለገሉ የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል።

ኃላፊነትን በትጋት የመወጣት አቅማቸውና ትጋታቸው ስለሚታወቅ በዩኒቨርሲቲው ከማስተማሩ ጎን ለጎን በየዘመናቱ የተጣለባቸውን የአመራር ኃላፊነት ተወጥተውታል። በዚህም መሰረት ከ1963-66 ዓ.ም. የቢዝነስ አስተዳደር ኮሌጅ ዲን፣ ከ1970-74 ዓ.ም ደግሞ የአካውንቲንግ ዲፓርትመንት ሊቀመንበር፣ ከ1970-74 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ልማት በምክትል ፕሬዝዳትነት ባላደራ በመሆን አገልግለዋል።

በሙያቸው ያላቸው ቀና አገልግሎት ቀጥሎም እ.ኤ.አ. ከ1991-1995 ዓ.ም. የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋኩሊቲ ዲን በመቀጠልም ከ1995 እስከ 1997 ዓ.ም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሀገር የልማት መካነ ጥናት ተቋምን በዳይሬክተርነት መርተዋል።

ፕሮፌሰር ዮሐንስ በሙያቸው ላይ ተጨማሪ ምርምር ለማካሄድ እ.ኤ.አ. ከ1985-86 የዳላስ ቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ የሂሳብ አያያዝ ልማት ማዕከል የፉል ብራይት ስኮላርሽፕ የሰጣቸው ሲሆን፤ በጀርመን ሀገርም ክያል ዩኒቨርሲቲ የፍሬድሪክ ኤበርት ፋውንዴሽን የከፍተኛ ደረጃ ተመራማሪ ተሸላሚ (የሲኒየር ሪሰርች ፌሎሽፕም) በመሆን ምርምራቸውን አካሂደዋል።

እኚህ ጎምቱ ምሁር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጡረታ ቢወጡም የድህረ ምረቃ ተማሪዎችን ከማማከር እራሳቸውን አላቀቡም። የአዛውንትነት ዕድሜያቸው ስራን አልገፋም። ከሐምሌ 1988 ዓ.ም ጀምሮ ሚድሮክ ኢትዮጵያን በሰው ኃይል ሥልጠናና ልማት ዳይሬክተርነት እስከ ህልፈተ-ህይወታቸው አገልግለዋል። ለሚድሮክ ኢትዮጵያ ኩባንያ ብቻም ሳይሆን የሀገራችን ኢትዮጵያ ብሎም የአህጉራችን የአፍሪካ ባለውለታ ነበሩ።

በተለይም ለሚድሮክ ኢትዮጵያና ለእህት ኩባንያዎቹ አመራርና ሠራተኞችን ለሃያ ዓመታት ሙያዊ ብልፅግና እንዲያድግና እንዲጎለብት ስልጠና በመስጠት እንዲሁም በአማካሪነት ላበረከቱት አስተዋፅዖ ከፍተኛ አድናቆት ሲቸራቸው እንደኖረ ይነገርላቸዋል።

ወደ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ የተቀላቀለውን የሚድሮክ ኢትጵያን የትምህርትና ሥልጠና ተቋምንም ያቋቋሙት ፕሮፌሰሩ፤ የተለያዩ ካምፓኒያዎችን በማማከር፣ ግዙፍ ለሆኑ የመንግስትና የግል ተቋማት፣ ድርጅቶች እና ሙያዊ ማህበራትን በመደገፍ እንዲሁም የቦርድ አባልና ሰብሳቢም ጭምር በመሆን አገልግለዋል።

ባካበቱት የዳበረ የሙያ ዕውቀትና ክህሎት መነሻነት፤ ፕሮፌሰር ዮሐንስ ከአስር የማያንሱ ሀገራዊ፣ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ሙያዊ ማኅበራት አባል ነበሩ።

በልዩ ልዩ የምርምር እና በጎ አድራጎት ማኅበራት በመሥራችነትና በአባልነት እንዲሁም አመራር በመስጠት ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርገዋል። በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የተመረቁ ኢትዮጵያውያን ማኅበር ከመሥራቾቹ አንዱ በመሆንና የማህበሩ ፕሬዝዳንትም ሆነው አገልግለዋል። በኢትዮጰያ በትምህርትና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሀሳብ አፍላቂ ማህበር (Ethiopian Think Tank on Education and Society) ከመሥራቾች አንዱ ነበሩ፤ የመጀመሪያውም ፕሬዝዳንት ሆነው አገልግለዋል።

የኢትዮጵያ የአካውንቲንግና የኦዲቲንግ ሙያተኞች ማህበር ከመሥራች ኮሚቴ አባላት አንዱ ነበሩ። ይህንን ማህበርም በፕሬዝዳንትነት አገልግለዋል። የአንበሳ ባንክ አክሲዮን ማኅበር የቦርድ ሊቀመንበርም በመሆን ዉያዊ አሻራቸውን አኑረዋል።

የአካውንቲንግ መማሪያ መጽሐፍትን እንዲሁም ሙያቸውን የተመለከቱ ከ54 በላይ የምርምር ጽሑፎችን በጆርናሎች ያሳተሙና በኮንፈረንሶች ላይ ያቀረቡም ምሁር ነበሩ‐ ፕሮፌሰር ዮሐንስ።

በዚህም በተለያዩ ጊዜያት በርካታ አገራዊና ዓለም-አቀፋዊ ሽልማቶችን ሲቀበሉ ኖረዋል። የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ሽልማት፣ የፓን አፍሪካን የኮርፖሬት ገቨርናንስ ሽልማት፣ ከኢትዮጵያ አካውንቲንግ ማህበር ከፍተኛ ደረጃ የክብር ሽልማት አንዱ ነው።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአገልግሎት ዘመናቸውን፣ ትጋታቸውን፣ ችሎታቸውን እና ለዚህች አገር ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ግምት ውስጥ በማስገባት ከሽልማት ጋር «የአካውንቲንግ አባት» የሚል የክብር ስያሜ ሰጥቷቸዋል።

በፈረንጆቹ 2013 ሞሪሺየስ ላይ በተካሄደው የአፍሪካና የህንድ ትብብር በስራ አመራር ጉባኤ ላይ የኤሚሪተስ ፕሮፌሰር ማዕረግ (Emeritus professor award) ተሸልመዋል። ይህ ከፍተኛውን የእውቀት ደረጃ ለያዘ የሚሰጠው የእድሜ ልክ መጠሪያ ነው። ከዚያ ሌላ ማዕረግ የለም። በኢትዮጵያም ይህን ማዕረግ የተቀዳጁት እርሳቸው ብቻ ናቸው።

ኤሜሬተስ ፕሮፌሰር ዮሐንስ ብዙ ናቸው። በኢትዮጵያ የአካውንቲንግ ትምህርት ፈር ቀዳጅ (pioneer) ናቸው። የዚህም ሙያ ጠርዝ የነኩ ብቸኛ ሰው። በሙያቸው ከ47 ዓመታት በላይ ሲያገለግሉ በርካታ ሊቃውንትን አፍርተዋል። ዛሬ በትላልቅ ካምፓኒዎች፣ ኢንሹራንሶች፣ ባንኮች፣ ከፍተኛ የመንግስትና የግል ተቋማት በኃላፊነት ላይ ያሉ ምሁራን አብዛኞቹ የእርሳቸው ተማሪዎች ናቸው።

ስለ ፕሮፌሰር ምስክርነት የሚሰጡ ሁሉ እውቀትን ፈትፍተው ሲያጎርሱ ስስትን አያውቁም። ቀለል ባሉ ምሳሌዎች ትላልቁን የተውሰበሰበ የአካውንቲንግ ትምህርት በተማሪዎቻቸው ውስጥ ያስቀራሉ። በልዩ የማስተማር ጥበባቸው በተማሪዎቻቸው የሚወደዱት ፕሮፌሰር ዮሐንስ፤ የትምህርት ክፍለ ጊዚያቸው በተማሪዎቻቸው እንደሚናፈቅ ሁሉ፤ እርሳቸውም ለተማሪዎቻቸው ባላቸው አክብሮት ሰዓት አያዛንፉም። አይቀሩም። ሳይዘጋጁ ጠመኔያቸውን ከጥቁር ሰሌዳው አያዋድዱም። ተማሪዎቻቸው ለውጤት ሳይሆን ለእውቀት እንዲተጉ ሲመክሯቸው፤ ከድህነቷና ከጉስቁልናዋ በማገገም ላይ ያለችውን አገር ለማሳደግ ትልቅ ተስፋ እንደሆኑም ጭምር በመንገር ነው።

ዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከፕሮፌሰሩ ጋር ባለው ቅርበት ስለ እርሳቸው ያለው አስተውሎት ከወስጡ የሚጠፋ አልሆነም። ርሁሩህ ናቸው። አልፎ አልፎ ብልጭ የምትል ንዴት ቢጤ አለችባቸው። በአለባበሳቸው ሁሌም ዜንጠኛ ናቸው። ትህትናቸው ይገዛል። መጽሐፍትና የተለያዩ የማስተማሪያ መርጂያዎችን የሚያጭቁበት ትልቅ የእጅ ቦርሳ (ሳምሶናይት) ምንግዜም አይለያቸውም።

መንፈሳዊ ሕይወታቸው የጠነከሩ ናቸው። በውሃ ዋና እና ዮጋ ስፖርት ጤንነታቸውን የሚጠብቁ ሸንቃጣም ነበሩ። በአነጋገር፣ በአረማመድ፣ በአመጋገብና በአቀማመጥ ጭምር ጠንቃቃ መሆናቸው የሚታወቅላቸው ፕሮፌሰር፤ ከስራና ከማህበራዊ ኑሮ ጋር በተያያዘ ከሰዎች ጋር ያላቸው ግንኙነትም በዚያው መጠን ፍፁም የሆነ ስርአትን የጠበቀ ነው። ለጊዜ የሚሰጡት ዋጋ ከፍተኛ ነው። የቀጠሮን ሰዓት ሰከንድ መታገስ አይችሉም። ስራን አያሳድሩም። ሁሉንም ነገር የሚመሩት ባወጡት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ነው። በእንዲህ ሁኔታ በራሳቸው የኑሮ ዘይቤ ሲመሩ፤ ብቸኝነትን በአንድ በኩል፤ ነጻንትን በሌላ በኩል በእኩሌታ ይዘው በመጓዝ ነው።

አገራቸውን ይወዳሉ። ከውጪ ዜጋ ባለቤታቸው የወለዷቸውን ሁለት ልጆች እና ባለቤታቸውን ተለይተው ወደ አገራቸው በመመለስ በሙያዊ አበርክቷቸው የጸኑትም ለዚሁ ነበር።

ከሦስት ዓመት በፊት ከአንድ መጽሔት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልሰ «አሁን ባለሁበት ዕድሜዬ ላይ እየሰራሁ ገንዘብ ማካበት ቀርቷል፤ አይቻልም። ዋናው ለዚህ ደረጃ መድረሴ ተመስገን ያስብለኛል፤ ከዚህ በኋላ ምን ልሰራ እንደምችል እያሰብኩ፣ በተቻለኝ መጠን ያሰብኩትን እየፈጸምኩ በሠላም መኖር ነው። ዕድሜዬ እስከፈቀደ ልሰራ ያሰብኩትን እሰራለሁ። ጤነኛ ነኝ፤ የነቃ አዕምሮ አለኝ ብዬ አስባለሁ። በኢትዮጵያ ፋይናንስና አካውንቲንግ እንዴት ሊያድግ እንደሚችል የራሴን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ ነኝ …»ብለው ነበር። ይህ ህልማቸውና ምኞታቸውን ብዙም ሳያሳኩ ግን ህልፈታቸው ተሰማ።

አዎ! እኚህን ጎምቱ ምሁር የዛሬ ዓመት ልክ በዛሬው ቀን ነው፣ በድንገተኛ አደጋ በ81 ዓመታቸው ያረፉት። ነፍስ ይማር።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
153 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1036 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us