አዋጅ ዘ አጭሬ፥ ረዘምዘሜ ወ ረጅሜ

Wednesday, 21 March 2018 12:41

 

በፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ

 

የአማርኛ ስነግጥም አይነቶች በ ቤት አመታታቸው በ 8 ይከፈላሉ። ለምሳሌ ቡሄ በሉ ቤት (ሆያሆዬ ቤት)፥ አበባዬ ከሆይ ቤት፥ የወል ቤት ወዘተ። ይህ ምደባቸው የተመሰረተው ባብዛኛው በጎንዮሽ ቤት አመታታቸው እንጂ በቁመታቸው አይደለም። አንድ ደሞ ለየት ያለው ቤት የማይመታ አለ። (የባለጌ ወይም የባላገር?):-

 

አፋፍ አፋፍ ስሄድ አገኘሁ ሚዳቆ
ጅራቷን ቢይዟት ዐይንዋ ፍጥጥ አለ።

 

ወይም

 

ያውና እዛ ማዶ ቃሪያ ተከምሯል
ያንን እያነሱ ቢከሰክሱትስ?

 

ለ"አጭሬ" እኔ ስሟን ባወጣላት እና ብዙ ብጽፍባትም በቅኔ ቤትም ሆነ በህዝባዊ ቅኔ ውስጥ ህያው ነበረች። በቅኔ ውስጥ ጉባኤ ቃና ትባላለች። ባለ ሁለት ስንኞች ነች። ለምሳሌ እንደ ህብራህብር የሆነች በማህሌታዊ በቅዱስ የያሬድ የተገጠመች እኔ ወደ አማርኛ የተረጎምኳት አለች።

 

ድንጋያት ሁሉ እስጢፋኖስ ላይ ቢያልቁ
ንጉሡ ገብረመስቀል መታኝ በወርቁ።

 

ይህ ጉባኤ ቃና ታሪካዊ እና መንፈሳዊ ነው። ቅዱስ ያሬድና የንጉስ ካሌብ ልጅ ንጉሥ ገብረመስቀል ጥብቅ ወዳጆች ነበሩ። አንድ ቀን ንጉሡ ቅዱስ ያሬድን አጠገቡ በሆነው ቢጠሩት እሱ በአርምሞ፥ በተመስጦ እና በጽሞና ራሱ ውስጥ ጠፍቶ ሳይስማቸው ቀረ። በእዚህ ጊዜ ንጉሡ በወርቅ ከዘራቸው መታ አደረጉት። ባነን እንዳለ እላይ የተመለከተውን በጉባኤ ቃና ተቀኘ። እዚህ ላይ መታወስ ያለበት ከሁሉ በፊት ሰማእታት የሆነው ቅዱስ እስጢፋኖስ በኢየሩሳሌም ለአይሁዳውያን ስለ እየሱስ ክርክቶስ ስለመሰከረ በአይሁዳውያን በድንጋይ ተወግሮ ነበር። ታዲያ ያን በማስታወስ ነበር ቅዱስ ያሬድ

 

ድንጋያት ሁሉ እስጢፋኖስ ላይ ቢያልቁ
ንጉሥ ገብረመስቀል መታኝ በወርቁ

 

የምትል በጉባኤ ቃና ወይም በእኔ አባባል "አጭሬ" የተቀኘው። አጭሬ በህዝብም ብዙ ተደርሳለች። የአማርኛ የህዝባዊ ጥቅስ (proverb) ሁሉ አጭሬ ነው። የተደረሰውም በህዝብ ነው። በህዝብ የሚያሰኘውንም መጀመሪያ በገጣሚው ስልላታወቀ ነው። ከህዝባዊዉ አጭሬዎች ውስጥ ጥቂቱ እነሆ---

 

አለህም እንዳልል እንዲህ ይደረጋል
የለህም እንዳልል ይመሻል ይነጋል።


********************
እኔ የምሞተው ዛሬ ማታ

ጾም የሚፈታው በፍልሰታ።
************************
እምበላው ሳጣ
ልጄ ጥርስ አወጣ።
*****************
ሊበሉ የፈለጓትን አሞራ
ስሟን ይሏታል ጅግራ።
******************
ጎረቤትህ ሲታማ
ለኔ ብለህ ስማ።
**************
እንግዲህ የኔም አጭሬ ቅርጽን በሚመለከት የእዚህን ፈለግ የተከተለ ነው። ከኔዎቹ ውስጥ አንዳንዶቹ ጥቅሳዊ (proverbial) እንዲሆኑ ያቀድኳቸው አሉ። ለምሳሌ

የጨለማ ድንፋታ
በብርሀን እስከሚመመታ።
**********************
ትእቢት
ያከናንባል ቱቢት።**
**************
አዋቂና አላዋቂ
*************
አዋቂ አፋር
አላዋቂ ደፋር።
***********
*ቱቢት ማለት ጥቁር የሀዘን ጨርቅ ነው።
***********************************

 

ባለፉት ሶስት ዐመታት በፌስቡክ የለቀቅኳቸው አጭሬዎች ቢሰበሰቡ አንድ መጽሀፍ ይወጣቸዋል። በእነሱ ጦስ በትእቢተኞች አላዋቂዎች ብዙ ዘለፋ፥ ስድብ፥ እና ዝርጠጣ ደርሶብኛል። በገዛ ጣቶቼ ጽፌ። ዐይን ከፋች ሀሳቦቼን በነጻ


ስለለገስኩ በመመስገን ፈንታ ያ ሁሉ ውርጅብኝ ለምን ደረሰብኝ? ስለስነግጥም ጠልቆ ሳይገነዘብ እኔን ከ 12 ሰዐታት ጀምሮ የምገጥመውን፥ በስነግጥም፥ በድራማ እና በስሂሁስ MA እና Ph.D. ያለኝን ሰው፥ እነዚህኑ የትምህርት ዐይነቶች በአውሮፓ እና እሜሪካን ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ያስተማርኩትን፥ እኔን ግጥሞቼ በጀርመንኛ፥ በሩስያዊኛ እና እንግሊዝኛ ታትመው የዐለም ህዝብ ያደነቃቸውን፥ ከእዚህም በላይ እኔን ግጥሞቼ እውቅና አግኝተው ከዐለም ኖቤል ሽልማት ካገኙ ደራስያን ግጥሞች ጋር የታሙመትን ገጣሚ እንዴት ማንም እየተነሳ ግጥም አትችልም እያለ ሊዘልፈኝ ደፈረ? መልሱ ትውልዱ ሳያውቅ ያወቀ ስለሚመስለው፥ በትእቢት የተወጠረና ሰውን የሚንቅ ስለሆነ፥ ግጥም ሲባል ረጅሙ ብቻ ስለሚመስለው ነው። ከእዚህም በላይ፥ ያ ቴዎድሮስ ጸጋዬ የተባለውም ሰው የዚሁ ትውልድ አካል ስለሆነ አጭሬን ሊረዳ ሳይችል ቀርቶ በቴሌቪዥን አሹፎብኝ ለተከታዮቹ አሳልፎ ስለሰጠኝ እና እነሱ ከእሱ ተጽእኖ ተላቀው በእራሳቸው አእምሮ ለማመዛዘን ባለመቻላቸው ነው።


እኔ "አጭሬ" ብዬ በአማርኛ የሰየምኩት አሰነኛኘት (አገጣጠም) በግእዝ ትምህርት ቤት ባለ ሁለቱ ስንኞች ጉባኤ ቃና የተባለ እና በህዝቦችም ዘንድ የተለመደ ነው። ከጥንት ተጀምሮ የአለ እና የነበረ ነው።


ሀቁ ይህ የሆኖ ሳለ የአሁኑ ትውልድ የእዚህ ዐይነት የግጥም ዘይቤ ሁሌም እንደነበረ ለመገንዘብ እንዴት ተስኖት ነው እኔ በእዚህ ስልት ስፅፍ ይህ ሰው ምን አመጣብን እሪ እምቧ፥ የሚልብኝ፥ እያልኩ እራሴን ሳልጠይቅ አልቀረሁም። ቢያንስ በአማርኛ ጥቅሳዊ አነጋገሮች ውስጥ ይሄ ዘዬ አለ። ታዲያ ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልደው ያደጉ ሰዎች ይህን የህዝባዊ ጥቅሳዊ ግጥም ሰምተው አያውቁምን፥ ብዬ መደመሜ አልቀረም። ከእነሱ ውስጥ በህብረተሰቡ ገጣሚዎች ተብለው የሚታሰቡ ሰዎችም በእዚህ ቁጥር ውስጥ መደመራቸው አስገርሞኛል። እነሱም እንደ አንባቢዎቻቸው አንድ ግጥማዊ ሳጥን ውስጥ ተቆልፈዋል ማለት ነው። ታዲያ አንቢዎቻቸው የሚከተሉት እነሱ የሚያሳዩአቸውን ፈለግ አይደል? ሌላ ከየት ያመጣሉ? እርግጥ እነዚህ ገጣሚዎች እና ግለሰቦች ጥቂቶች ናቸው። ብዙሀኑ ግን የአጭሬን ታሪክ ቢያውቁም ባያውቁም የእኔን አጭሬዎች በማንነታቸው መዝነው ወደዋቸዋል። ከመውደድም አልፈው አጭሬዎች መጻፍ የጀመሩም አሉ። ይህ እጅግ አስደስቶኛል። ሁሉም በተመቸው የስነግጥም ዘርፍ ራሱን ይግለጽ። አጭሬ ታብብ፤ ታፍራ!


እዚህ ላይ መዘንጋት የሌለበት፥ እኔ የደረስኳቸውን የታሪክ መጻህፍት ያልወደዱ ሰዎች በአጭሬ እያሳበቡ እኔን ለመዝለፍ መጣጣራቸው ነው። እነሱን በአነጋገራቸው ቃና ስለምለያቸው ከቁብም አልቆጥራቸው። የስነግጥምን የሂስ መስፈርት አሟልቶ ስንኞቼን የሚሄስ ሰው ግን ቢገኝ እንዴት መልካም ነበር። እስከአሁን ግን በስሜት ተነድቶ የሚሳደብ ብቻ ነው ያስተዋልኩት።


የአማርኛ የግጥም ዐይነት በጎንዮሽ የቤት ዐመታቱ ለ 8 ቢከፈልም በቁመቱ አልተከፋፈለም። እንዳው በደፈናው ሁሉም ግጥም ይባላል እንጂ። ስለእዚህ እኔ በቁመቱ መሰረት ለሶስት ከፍዬው ሶስት ስሞች ሰጥቼዋለሁ።


ከሁለት ስንኞች እስከ አንድ ገጽ የአለውን "አጭሬ"፥ ከ2 ገጾች እስከ 4 "ረዘምዘሜ" እና ከ 5 ገጾች ጀምሮ ያለውን "ረጅሜ" ብዬዋለሁ። የተቀበለ ይቀበለዋል። ያልተቀበለ ይተወዋል። እኔ ግን ቢያንስ የራሴን ግጥሞች ለመከፋፈያ እጠቀምበታለሁ።


እኔ ከልጅነቴ ተጀምሮ ግጥም እጽፋለሁ። ሀኪም ወይም ኢንጂኔር ለመሆን ስችል፥ ግጥም መጻፍና ስነጽሁፍን ከመውደዴ የተነሳ እነዚህን እስከ Ph. D. ድረስ ተማርኳቸው። እንዲሁም በአውሮፓና አሜሪካ የኒቨሲቲዎች ውስጥ አስተማርኳቸው። ግጥም መጻፍ የጀመርኩት ሁሉም የሀገራችን ገጣሚ እንደሚያደርገው በረዘምዘሜ እና በረጅሜ ነው። በጣም ረጅሙ አንድ ግጥሜ ሲነበብ አንድ ሰአት ይፈጃል። ይህን "ይቺ ናት የኔ ምድር" የተሰኘውን ረጅሜ የደረስኩት የዛሬ 30 ዐመት ነው። በኢትዮጵያ ህዝብ ተደጋጋሚ ጥያቄ ባለፉት 30 ዐመታት በጀርመኑ የዶቼቬሌ ሬድዮ ተደምጧል። በቅርቡ፥ ማለትም ከፋሲካ በኋላ በመፅሀፍ እና በሲዲ (በኔ ድምጽ የተነበበ) ይለቀቃል። ከልጅነቴ ጀምሮ እስከ አሁን የጻፍኳቸው ረዘምዘሜ እና ረጅሜ ግጥሞቼ ቢሰባሰቡ በቀላሉ 10 ቅጾች ይወጣቸዋል። እግዚአብሄር እድሜ ከሰጠኝ ይታተማሉ። ካልሆነም ተበትነው ይቀራሉ።


አጭሬ ለፌስቡክ አመቺ ስለሆነችና እውነቱን እንነጋገር ካልን ከአንድ ገጽ ከበለጠ ፌቡከኞች ስለማናነብ ለሁላችንም አመቺ ሆና ተገኝታለች። አጭሬን አለአግባብ የሚተቹትን ሰዎች በጣም ታዝቤአለሁ። ከአንድ ገጽ የሚተርፉ ረዘምሜዎዋችን ወይም ረጅሜዎችን ስለቅ እረጭ ጸጥ ይላሉ። ስለማያነቧቸው ወይም የለመዱአቸው አይነቶታች ስለሆኑ ነው። እኔ ግጥም የምገጥመው እንደ የስሜት ቅኝቴ daily mood ስለሆነ ቅኝቴን እያዳመጥኩ ሲያሰኘኝ አጭሬን ጽፌ በነጻ እለጥፍላችኋለሁ። ይህ ግን ለዘላለም ይቀጥላል ማለት አይደለም። አንድ ቀን እርግፍ አድርጌ መተዌ አይቀርም።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
97 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 962 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us