ከበውቀቱ ስዩም ዘለፋ ሰውረነ!

Wednesday, 28 March 2018 12:23

 

በመኮንን ተሾመ ቶሌራ - ዘገዳም ሠፈር

 

ሰውረነ!

ከአላዋቂ አጉራሽ፣

ከአፍ አበላሽ፡፡

 

ጉርሻን በቅጡ የማይችሉ ሰዎች ጎራሽን የጠቀሙ ይመስል በወጥና በቅባት አፉን፣ አንዳንዴም ልብሱን ሁሉ አበላሽተው ነገሩን ሁሉ እንዳይሆን እንዳይሆን ያረጉታል፡፡


ሰነፍ መምህርም ለተማሪዎቹ ያላዋቂነት ትምህርት ሲሰጥ እንደዛው ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ በተለይ ተማሪው ብዙም በእድሜና በእውቀት ያልጎለመሰ ሲሆን፣ ጥፋቱ የከፋም ይሆናል፡፡ ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ ያነበብኩት ነገር እንደዚሁ “አላዋቂ ለባሽ ልብስ አበላሽ” ሆኖብኝ ነው፡፡ እንደ ዘርያዕቆብ ፈላስፋው ተደብቄ ከኖሩኩበት ዋሻ ብቅ እንድል ያደረገኝ፡፡


በውቀቱ ስዩም የተባለው “የሥነ-ፅሁፍ ጠበብት” እንደለመደው “ሰውረኝ” በምትል አላጋጭ ፅሁፍ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳን መወረፉን ሳይ እቺን ምላሽ (reaction) ልሞነጫጭር ወደድኩኝ፡፡


ለነገሩ የሥነ ፅሁፍ ልምድ እንጅ የሥነ-ፅሁፍ ትምህርት በዋለበት ያልዋለውን ትንሹ ብላቴና በውቀቱ ላይ ብቻ ያየሁት ችግር ስላልሆነና በአብዛኛው የኛን ትውልድ የሚመለከት የ“አላዋቂ አልባሽ…” ትችት መብዛቱን ያስተዋልኩ ስለመሰለኝ ነው፡፡ ይህችን አጭር ፅሁፍ ለመጻፍ የተነሳሁት፡፡- ቢሆንም ማሳያ እንዲሆንልኝ በአብዛኛው የዚሁኑ “ብላቴና” ችግሮች አነሳለሁ፡፡ እርግጠኛ ነኝ እሱ ከዚህ የበለጠ ጭቃ ለቅላቂ ስለሆነ እኔን ስም አጥፊ አይለኝ፡፡


ምንም እንኳን የሸክስፒርን ቦታ ባልሰጠዉም የራሱ ቀለም ያለዉ ፀሃፊ በመሆኑና ልጅእግር አስተዉን ስለምረዳ በዉቀቱን ስነ-ፅሑፍ ባለመማሩ ብቻ በተለምዶ “የልምድ አዋላጅ”/“Traditional Midwives”/ እየተባሉ ከሚጠሩት ፀሀፍት አልመድበዉም።


በመጀመሪያ ላነሳ የምወደው አንድ ሰው በተለይ እንደ “በውቄ” ዓይነት የሥነ-ፅሁፍ ጠበብት ሌላው ላይ ትችት ለመስጠት በሚናገርበት ወይም በሚፅፍበት ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያለውን እውቀትና ልምድ እንዲሁም አካዳሚያዊ ተአማኒነት (Authority) ማየት ይገባዋል፡፡ እዚህ ላይ “በውቄ” ግጥምን መግጠም እንጂ ስለግጥም ለመናገር የትኛው ደብር ነው የመሪጌታነት ማዕረግ የሰጠው፡፡ እኔን ሁል ጊዜ የሚገርመኝ “ብላቴናው” እኛው በሰጠነው አድናቆትና የፌዝ ሥነ-ፅሁፍ ጭብጨባ ቱባ ባህላችንን፣ ሃይማኖታችንን እና ለሰማይ ለምድር የከበዱ የሥነ-ፅሁፍ ሰዎቻችንን ለመተቸት ጉልበት ያገኘ ይመስለኛል፡፡ መተቸት መብቱ ቢሆንም ፀጋዬ ገብረ መድህንን የሚያክል የሥነ-ፅሁፍ ሊቅ (gaint) አዲስ አለማየሁን የሚያክል ፈር ቀዳጅ በበሰለና በሰላ ምሁራዊ አይን ሳይሆን በፌዝ እያዋረዱ የራስን ስም ለመገንባት መጣርን የመሰለ ከራስ ጋር ያለ ስህበት (Ego) ያለ አይመስለኝም፡፡ አንዳዳድ ጊዜ ደግሞ ትምህርታዊና አመራማሪ ባልሆነና አናዳጅ በሆነ መልኩ ከምድር አልፎ በሰማይ ያሉ ጻድቃንንና ሰማዕታትና ማንጓጠጥ አለዋቂ እንጅ አሰላሳይ የሚያስብል አይመስለኝም፡፡


በመሆኑም ጎራሽ ስላገኘን ብቻ የሰውን አፍና ልብስ ማበላሸት ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡ በመጀመሪያ ማጉረስ ያለብን ማጉረስ ያለብንን ያህል ብቻ መሆን ይገባዋል፡፡ በሌላም በኩል የአጎራረስ አዋቂ መሆን ያስፈልጋል፡፡


ለምሳሌ ሰሞኑን “በውቄ” ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ እሳቸውና በሳቸው ደረጃ ብቻ ያሉ ሰዎች የሚግባቡበትንና ጠለቅ ያለ እውቀትን የሚጠይቀውን “ጉባዔ ቃና” ለኔና ለበውቄ ትውልድ እንደወረደ ስላመጡት ነገሩ ምንድን ነው ብሎ ከመመርመር ይልቅ ወደተለመደው ፌዝ ሮጦ አዋቂዎችን አላዋቂ ለማስመሰል መሞከሩ አሳዝኖኛል፡፡


ፕሮፌሰሩ እንኳን አንድ ቤት የማይመታና ቤት የሚመታ ግጥምንና ሌላውን የሥነ-ፅሁፍና የታሪክን ስንክሳር ለመረዳት የሚያስችል ልምድም ትምህርትም ያላቸው ይመስለኛል፡፡


እኔ እንደሚመስለኝ የሳቸው ዓላማ ቤት የሚመታ ሥነ-ፅሁፋዊ ውበት ያለው ግጥም ለኛ ለማስተማር ሳይሆን “ጉባዔ ቃና” ስለተባለው መንፈሳዊ፣ ሥነ-ግጥም ማስታወስ ነው፡፡ ሰውየውማ ከፈለጉ ያማረና ልብ የሚነካ ግጥም እንደሚጽፉ እናውቃለን፡፡ ለምን ቢሉ እሳቸው እንደብላቴናው ”ጆሮ ጠገብ” ብቻ ሳይሆኑ የሥነ-ፅሁፍ ትምህርት በዋለበት የዋሉ በልምድም ቢሆን ብዕርና ወረቀትን በማገናኘት የባተሉ ስለሆኑ፡፡


ለማንኛውም “ቧልተኛ ሰው አንቱ ሳይባል ያረጃል” እንዳይሆን ወደ ቁምነገሩ እንምጣና “ጉባዔ ቃና” ምንድን ነው የሚለውን ለመመርመር አዋቂዎች ከዋሉበት ለመዋል እንሞክር፡፡

 

“ጉባዔ ቃና”


ፕሮፌሰሩ እንዳሉት በአብዛኛው ሁለት ስንኞች ያሉት የአምላክ መወድስ ወይም የአንድ ምጡቅ ሃሣብ መግለጫ መንፈሳዊ የሥነ ግጥም ዓይነት ነው፡፡


ይህም በዓለማቀፍ ደረጃ በታሪካዊነቱና ዜማን በምልክት (ኖታ መሰል) ሁኔታ በማስቀመጥ አስገራሚ ስራ ከሰራው ከቅዱስ ያሬድ ጋር የሚገናኝ እንደሆነ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ ቅዱስ ያሬድ የአስገራሚ ቅኔ ፈጣሪ በመሆኑ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ዋናው የቅኔው ዓላማ አምላካዊ ምስጋና መስጠት በመሆኑ አንዳንድ ጊዜ የያሬድ ቅኔ ቤት ሲመታ አይታይም ይባላል፡፡ በሌላ በኩል ደሞ እንደአስፈላጊነቱ ቤት የሚመታበትም ሁኔታ አለ፡፡


ይህን በተመለከተ በርካታ ፀሃፊዎች የሚጠቀሱ ቢሆንም ለጊዜው “ባህልና ክርስቲያናዊ ትውፊት በኢትዮጵያ” ከተሰኘው የካህሳይ ገብረ እግዚአብሔር መፅሐፍ አብነት እንጠቃቅስ፡፡


በዚህ መፃህፍ ፀሃፊው፡-


“የአገራችንን የግዕዝ ቅኔን በተመለከተ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት በአንድነት የሚስማሙበት ነገር ቢኖር የቅኔ ጀማሪ ቅዱስ ያሬድ መሆኑን ነው፡፡ ይሁንና ብዙዎቹ የቅዱስ ያሬድ ግጥም ቤት አልባ ወይም ጎት ግጥም ነው ሲሉ፣ ከፊሎች ደሞ የለም ከሞላ ጎደል የተሟላ ነው ይላሉ ሲሉ፣ ከፊሎች ደሞ የለም ከሞላ ጎደል የተሟላ ነው ይላሉ” ሲል ፅፏል፡፡


ይህንንም ቤት ያለመምታት ጉዳይ አስመልክቶ አንድ ሌላ ባለቅኔ የተከበረው ያሬድ ለቅኔዎቹ ቤት ባለመስራቱ እንደተዋረደ ገልጾ መቀኘቱንም ይገልጻል፡፡ እንዲህ ብሎ፡-
ተትሕተ ያሬድ ዘኢተትሕተ፣


ለቅኔያቲሁ ደቂቅ እስመ ኢሐነጸ ቤተ፡፡


ይህ ባለቅኔ የሱን “ጉባዔ ቃና” ቤት መምታቱን ብቻ ስላየ ልክ በውቄ ፍቅሬ ቶሎሳ የተዋረዱ እንደመሰለው ሁሉ እሱም ያሬድ የተዋረደ መሰለው፡፡ ነገር ግን ትውልዱ ለቤት መምታት ሳይሆን አምላካዊ መወድስነቱን ይበልጥ አክሮ ለሺህ ዓመታት በያሬድ የተጀመረውን ቤት የማይመታ የሚመስለውን ያሬዳዊ ዜማ አክብሮ ይዞ ሲያወድስበት ሲያመሰግንበት ኖረ፡፡ በመሆኑም ባህላችን ታሪካችን ቅርሳችን ሆነ “ጉባዔ ቃና” እኛ ግን አላወቅነውም እንድናውቀው ያህል በካሕሳይ ገብረ እግዚአብሔር የተፃፉትን ጥቂቶቹን ለአብነት እንይ፡፡


እም ፈልፈለ ብዕል ገነት ንጉሥ ሰቀዩ፣
እምነቅዐ ወንጌል ገራህተ አርወዩ፡፡


ይህ ቅኔ ያሬዳዊ ሲሆን፣ ባለቅኔው “አርአያም” ብሎ ካስቀመጠው መደብ የተወሰደ ሲሆን፣ ወደ አማርኛ ሲመለስም ቤት የማይመታ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡


ከፏፏቴ የንጉሥን (የክርስቶስን) ጓሮ አጠጡ፣
ከወንጌል ምንም እርሻውን አርኩ፡፡


የሚል ይሆንና ቤት ሳይመታ ቢቀርም መንፈሳዊ መልዕክቱ ግን እንደተጠበቀ እናገኘዋለን፡፡ ይህንን ሁኔታ ነው እንግዲህ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ጉባዔ ቃናን እያሰቡ ሊያስተምሩን ያሰቡት ይሁንና በእሳቸው በቂ ማብራሪያ አለመስጠት ይሁን በኛ ትችት ወደጅነት መደነቋቆሩ የመጣው ለነገሩ፣ ቅኖች ብንሆን ኖሮ ችግር ያለው ለሚመስለን ነገር ጠይቀን መረዳት እንችል ነበር፡፡ ይሁንና ፈጥነን እውቀት ያላቸውን ቀደምቶቻችንን ወደመተቸት እየሮጥን የእውቀት ቀዳዳችንን እየከፈንን እንኖራለን፡፡


ለማንኛውም ጉባዔ ቃናን ይበልጥ እንረዳው ዘንድ በፀሃፊው ለአብነት ከተጠቀሰው ባለሦስት ስንኞች ቅኔያት አንዱን ደግመን እንይና ወደ አማርኛ ሲመለስ እንዴት ቤት መምታት እንደማይችል አስተውለን ፕሮፌሰር ፍቅሬን ለመርዳት እንሞክር፡፡


ሀገረ ክርስስ ሐዳስ ንድቅ፣
ዘበ ውስቴታ የኅድር ጽድቅ፣
ጻድቃን ኪያሃ አብደሩ እምወርቅ፡፡
ይህ ቅኔ የጾመ ድጓ ክፍል ከሆነው ከያሬድ ቅኔ የተወሰደ ሲሆን፣ እንደተነጋገርነው ወደ አማርኛ ሲመለስ ቤት ላይመታ ይችላል፡፡ ነገር ግን ግዕዙን ለሚያውቅና ለመረመረው ሥነ-ፅሁፋዊ ምጥቀቱን ያውቀዋል፡፡ (ለኔና ለበውቄ ባይገባንም)፡፡
ለማንኛውም ትርጉሙን በአማርኛ ስናየው፡-
የክርስቶስ አገር አዲስ ቤት፣
ጽድቅ/እንግዳ የሚያድርባት ናት፣
እውነተኞቹ ጻድቃን ከወርቅ አርሷን መረጡ፡፡


የሚል አተረጓጎም ሊኖረው የሚችል ሲሆን፣ ፕሮፌሰር ፍቅሬም ጉባዔ ቃናን ወደ አማርኛ ሲመልሱልን በግዕዙ እያሰቡ ግዕዝ የሚሸከመውን እምቅ ቅኔያዊ ምስጢር ተሸክመው ሳይሆን አይቀርም፡፡ በርግጥ ይህን አስቀድመዉ ቢያብራሩልን ጥሩ ሊሆን ይችል ነበር።


“በላ ልበልሃ” እየተባለም የሚዘረፈዉን የሙግት ቅኔና ሌሎችን ስነ ቃላዊ ትዉፊቶቻችንን (Oral Traditions) መዘከሩና ለአዲሱ ትዉልድ ማስተዋወቁም ሌላ የሚያስመሰግን ቁም ነገር እንጅ ማህበረሰባዊ እና ሀይማኖታዊ አፈንጋጭ (Deviant/Atheist) ነኝ በሚል ሊቧለትባቸዉ የሚገባ አልመሰለኝም።


በመሆኑም የእኛ የብላቴናዎቹ ተግባር ፊትለፊት የምናየውነን የታላላቆቻችንን ጎዶሎ ሳይሆን ውስጠ ሚስጥሩንና ታሪከ ነገሩን መሆን ይገባዋል ባይ ነኝ፡፡ ይህንን ስል ግን “ውሃ ሽቅብ አይፈስም” በሚል ብሂል ቀዳሚዎቻችን ሲሳሳቱ እርምት አንሰጥም ማለት አይደለም፡፡ ይሁንና ”አላዋቂ አጉራሽ…” ሆነን ግን ከታላላቆቹ መማር የሚገባቸውን ታናናሾቻችንን እንዳናስት እንጠንቀቅ!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
112 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 914 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us