ሰሜን ጎንደር ከአብነት ትምህርት ቤት እስከ ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ፤

Wednesday, 11 April 2018 14:34

 

ሔኖክ ሥዩም

 

"ምንኛ ደግ ነው ሰሜነኛ መሆን
ከወገራ አልፌ አገኘሁ እንደሆን" ይላል የሀገሬ ሰው።


ከወገራ ታልፎ ያለ ምድር በረከቱ ብዙ ነው። ኢትዮጵያ በዓለም ቅርስነት ያስመዘገበችው የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ይገኛል። ብርቅዬዎቹ የሚኖሩት እዚህ ሥነ ምህዳር ነው። የተደበቁ አያሌ ቅርሶች የሚገኙበት ምድር ከኢትዮጵያ የሺ ዓመታት የታሪክ ጉዞ ጋር አብሮ የነበረ መቼት በመሆኑ ብዙ ተጽፎለታል።


‘ሰሜን’ የሚለው ቃል ከአራቱ አቅጣጫዎች አንዱን የሚገልጽ ሲሆን ይኼውም የዞኑን በሰሜናዊ የጎንደር ክፍል የሚገኝ እንደሆነ ይጠቁማል። በሌላ በኩል ስሜን በሚል የሚገለጸው ቃል ከታላቁ ንጉሥ ከዐፄ ቴዎድሮስ ንግሥና በኋላ በስፋት የመጠሪያ ስያሜ ሆኖ ማገልገሉን የሚገልጹ የታሪክ ሰነዶች አሉ። ይኼውም ገና መይሳው ካሳ ተብለው በደጃዝማችነት ማዕረግ በሚጠሩበት ወቅት ድል አድራጊነታቸው እየገነነ ሲመጣ የሚከተላቸው ህዝብ "ስምህን ማን እንበል?" ብሎ የጠየቀውን ጥያቄ ተከትሎ "ስሜን ሰሜን እነግርሃለሁ" በሚል የሰጡትን ምላሽ መሠረት በማድረግ የወጣ ስም ነው። ንጉሡ ደረስጌ ማርያም ላይ ሲነግሱ ዳግማዊ ቴዎድሮስ ተባሉ። ስማቸው ስሜን ይፋ ሆነ። ስሜን የሰሜን መጠሪያ ሆኖ ከአቅጣጫ መጠቆሚያነት ባለፈ መገለጫ ሆነ።


የቀድሞው ሰሜን ጎንደር ዞን ሦስት ቦታ ተከፍሎ እንደ አዲስ ሲዋቀር ነባሩ ስያሜ የሰሜን ጎንደር ሆነ። 8ሺህ 393 ነጥብ 3 ካሬ ኪሎ ሜትር ቆዳ ስፋት ላይ ያረፈውና 897 ሺህ 468 የሚደርስ ህዝብ የሚኖርበት ይህ ሰሜን ጎንደር በሚል አዲስ የተዋቀረው ዞን ዋና መዲናው ደጋማዋ ምድር ደባርቅ ሆና ዳባት፣ ጃናሞራ፣ አዲ አርቃይ፣ በየዳ፣ ደባርቅ ለተባሉ ወረዳዎች መዲና ሆነች።


የኢትዮጵያ ረዣዥም ተራሮች የሚገኙበት ሰሜን ጎንደር ትልቁ የራስ ደጀን ከፍታ ወክሎ በስሜን ተራሮች ስር ስማቸውን የሚያስጠራቸው ከአራት ሺ ሜትር በላይ የሚረዝሙ ተራሮች ብዙ ናቸው። የስሜን ተራሮች የታሪክ አውድ በመሆን ስማቸውን ከታሪካችን ጋር አቆራኝተዋል።


የአይሁድ እምነት ተከታዮች ክርስትናን ከተቀበለችው አክሱም ከተማ ሲወጡ እና ሲፈልሱ ወደ ስሜን ተራሮች አናትና ወደ ጠለምት ምድር ነበር የተጓዙት። ዛሬ በጠለምት የሚገኙት የቤተ እስራኤላውያን መታሰቢያዎች ይህንን ድንቅ አሻራ ይመሰክራሉ። ይህ እንግዲህ በአራተኛው ክፍለ ዘመን የጀመረው የስሜን ታሪክ ነው።


ቅዱስ ያሬድ የመጨረሻውን የምነና ዘመን ያሳለፈበት ስፍራ በተራሮቹ አናት፤ ከስሜን ተራሮች አንዱ በሆነው በስሙ የሚጠራ ተራራ ላይ ነበር። ዛሬ ቅዱስ ያሬድ የሚባለው ተራራ የዜማው ሊቅ ኢትዮጵያዊው ጥበበኛ ወንበር ዘርግቶ ያስተማረበት ከዚያም የተሰወረበት ስፍራ ነው።


አንዳንድ ጥናቶች ደግሞ የዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ታሪክ ላይ የሰሜን ጎንደርን አካባቢ ሚና ዳግም ያወሱታል። ለአርባ አመት የገዛችው ዮዲት ዋና ከተማዋ ወገራ መሆኑን ይናገራሉ።


ወጣ ገባና ተራሮች የበዙበት መልከዓ ምድራዊ አቀማመጡ በርካታ ጊዜያት ተደጋጋሚ የጦርነት ታሪኮችን ያስተናገደ ስፍራ አድርጎታል። ከዚህ መካከል የጌዲዮን ታሪክ አንዱ ነው። የፈላሻው የጦር መሪን የጦር ሜዳ ውሎና የጦር ድልና ሽንፈቶች ተከትሎ ዛሬ በርካታ ተረኮች ተርፈው የብዙ ስያሜ መነሻ ነው ሲባል ይደመጣል። ለምሳሌ ጠፋሁ ለዘር የሚለው ተራራ ድል መሆንን ድል ይብዛ የሚለው የከተማ ስም ደግሞ ማሸነፍን የሚወክሉ ናቸው።


በጌዲዮን ዘመን ከወሎ የመጡት ሙስሊም አባት ከጌዲዮን ጋር በተደረገ ጦርነት ሲሞቱ የተቀበሩበት ስፍራ እንደሆነ የሚነገረው ሼህ ሃዘን /ሃዘል/ በሚል የሚታወቀው እና ትልቅ የዚያራ በዓል የሚከበርበት ስፍራ ይህንን ታሪክ ከሚያስታውሱ አሻራዎች አንዱ ነው።


በ14ኛው ክፍለ ዘመን የሚጀምው ኢስላም ጌ ታሪክ ደግሞ የሰሜንን ምድር በሌላ ገጽታው እንድናውቀው የሚደርገን ታሪክ ነው። በጃናሞራ ወረዳ የሚገኘውይህ ስፍራ በተለያየ ዘመናት የተተካኩ የበቁ ኢስላማዊ አባቶች/ዐሊሞች/ መፍለቂያ በመሆን ይታወቃል።


የኢትዮጵያ ወርቃማ ዘመን የሚባለው የዛጉዬ ሥርወ መንግስት ዘመን በሰሜን ጎንደርም የራሱን አሻራ አሳርፏል። ቅዱስ ላሊበላ ከሰራቸው ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አንዱ በጃናሞራ የሚገኘው የሰረባር ባለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው። ይህ ውቅር ቤተ ክርስቲያን ከላስታ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አስቀድሞ ከዞዝ አምባ ጊዮርጊስ በፊት የተሰራ መሆኑን ታሪኩ ያስረዳል።


ኢትዮጵያ በነገሥታት አገዛዝ ተከፋፍላ ከነበረችበት ዘመን ስትወጣ የስሜን ምድር የመጨረሻውን የሽግግር ታሪክ ያስተናገደ መቼት ነበር። በ1847 ዓ.ም. የቋራው ካሳ በቧሂት ከደጃች ውቤ ጋር ባደረጉት ጦርነት ድል አድርገው ስሜን ደረስጌ ማርያም ላይ ንጉሠ ነገሥት ዘ ኢትዮጵያ ተብለው ነገሡ። ዘመነ መሳፍንት አክትሞ ዳግም የኢትዮጵያ አንድነት ታሪክ ጀመረ። የስሜን ቁልፍ ስፍራነት በዐፄ ቴዎድሮስ የንግሥና በዓል ድግስ አልተጠናቀቀም። ከዚያም ቀጠለ።


ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ የተባሉት እቴጌ ጣይቱ በልዩ ሁኔታ ካሰሯቸው ማረፊያ ቤተ መንግስቶች አንዱ በየዳ ኢየሱስ የሚገኘው ቤተ መንግሥት ነው። ከራስ ደጀን ስር ከምትገኘው ድል ይብዛ ከተማ አቅራቢያ የሚታየው የእቴጌ ጣይቱ ቤተ መንግሥት ፍራሽ ዛሬም ይጎበኛል።


በሁለተኛው የኢጣሊያ ጦርነት ፋሽሽት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ሲወር በራስ እምሩ የሚመራው ጦር ወደ ስሜን ሲጓዝ የስሜን ህዝብ በደጃች አያሌው መሪነት የሽሬው ግንባር ላይ ታላቅ መስዋዕትነት ሲከፍል የታሪኩ ዋና ጎዳና የሰሜን ጎንደር ተራሮችና ሸለቆዎች ነበሩ።


ከደባርቅ ወጣ ብሎ የሚገኘው ውልክፊት በአምስቱ ዓመታት የአርበኝነት ታሪክ ለኢትዮጵያ ነጻነት ትልቅ ተጋድሎ የተደረገበት የማይረሳ ታሪካዊ ስፍራ ሆኖ በደማቁ ተጽፏል።
ወታደራዊን ሥርዓት ለመገርሰስ የተደረገውን የትጥቅ ትግል ያስተናገዱ በርካታ የጦር አውድማዎችመገኛ የሆነው ይህ ምድር በተለይም ትግሉን የሚመራው ሬድዮ ጣቢያ ዋና ማሰራጫ በመሆን ያገለገለ፤ የጀነሬተር ናፍጣ በረዶ ሲሰራ በእሳት ቀልጦ አገልግሎት ላይ የዋለበት ነው።


የተራሮቹ ራስ ስሜን ከባህር ወለል በላይ እስከ 4 ሺህ 620 ሜትር በሚደርሰው ከፍታው ይታወቅ እንጂ የድንቅ ሸለቆዎችም ምድር ነው። የሰሜን ሌላ ገጽታ ከሊማሊሞ በታች ያለው ሥነ ምህዳር ሲሆን 10 በመቶ የሚደርሰው የምድሩ ክፍል ውርጭ ነው። ደጋማው የአየር ንብረት 43 ነጥብ 19 በመቶ የሚሆነውን ይሸፍናል። ወይናደጋው ክፍሉ 22 ነጥብ 7 በመቶ ሲሆን ቆላማው አካባቢ ደግሞ ከአጠቃላይ የአየር ንብረቱ 34 ነጥብ 55 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ይዟል።


ከ4000 ሜትር ከፍታ በላይ የሆኑት አስር ተራሮች ደጋማው የተራሮች አናት የምንጮች ማህጸን እንዲሆን አድርገውታል። በሰሜን ጎንደር ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ 36 የሚሆኑ ትልልቅ ወንዞች ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል 13 የሚሆኑት ወንዞች ከስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የሚነሱ ናቸው።


ደገኛው ገብስ ህልውናው ነው። ኮረፌው ብርዱን የሚያሸነፍ መጠጥ በመሆኑ የባህላዊ እሴቱ መገለጫ ሆኗል። ቆለኛው ከማሽላ የተቆራኘ ነው። ሰሊጥ የምድሩ ትልቁ በረከት በመሆኑ ኢኮኖሚው ከግብርና ተቆራኝቷል።


1200 የሚሆኑ የእጽዋት ዝርያዎች የሚገኙበት ምድር አስር በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ እጽዋት መኖሪያ ነው። ከአስሩ ብርቅዬ እጽዋት ደግሞ ሦስቱ በስሜን ተራሮች ብቻ የሚገኙ ዝርያዎች ናቸው። 35 አጥቢ እንሰሳት የሚገኙበት ብሔራዊ ፓርክ አስር በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ የዱር እንስሳትን ይዟል። ብርቅዬው ዋሊያ ከሰሜን ጎንደር ውጪ በየትም ዓለም የሌለ የኢትዮጵያ መገለጫ ነው።


አካባቢው የብዙ ሥነ-ምህዳር ስብጥር ያለበት ነው። እንዲህ ያለው ስጦታ ችግር ፈቺ ተመራማሪ ለማፍራት የማይገኝ ቤተ ሙከራ ነው። የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ብቻ ለብዙ የዓለማችን ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የመስክ ትምህርት ቤት ሆኖ አገልግሏል። እጽዋቱን ፍለጋ፣ ዱር እንስሳቱን ጥናት፣ አእዋፍ ምርምር ብለው በዱር በገደሉ የሚውሉ ተመራማሪዎች ዩኒቨርሲቲያቸው አንዳች ነገር እንደሚገኝ አምኖ የሚልካቸው ናቸው።


በአብነት ትምህርት ቤት ማዕከልነት የሚታወቀው ስፍራ አሁን ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተገንብቶበታል። ዩኒቨርሲቲው ብዙ ስራዎች ይጠብቁታል። ደገኛው ገብሱን የሚታደግለት የምርምር ውጤት ይሻል። አስጎብኚው ስሜንን የበለጠ ሸጦ ዓለም የሚያንጋጋለት የቱሪዝም ስትራቴጂን የተራበ ነው። በርካታ ቅርሶች ጥናት፣ ጥገናና ልማት የሚሹ ናቸው። ብዙ ታሪኮች ተደብቀው የሚኖሩበት ምድር፣ ዓይነተ ብዙ ፈዋሽ እጽዋት ተመራምሮ ለሀገር የሚያውለን እያሉ የሚጣሩበት ቀጠና የሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ብዙ ይጠበቅበታል። እናም ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ እንደ ተራሮቹ ቁመት ከርቀት የሚታይ ስራ መስራት አለበት።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
170 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 153 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us