የሚጽፉ እጆች ይበርክቱልን!

Wednesday, 02 May 2018 12:46

 

“የመተቸት መብት የዴሞከራሲ መፈተኛው ነው።”

(ቀዳማዊው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ቤንጎሪዮን)

ሪያድ አብዱል ወኪል (በጉራጌ ዞን የወለኔ ወረዳ ዓቃቤ ህግ)

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

ይህንን ጽሁፍ ስታነቡ በአለም ዓቀፍ ደረጃም ሆነ በኢትዮጵያ በተለያዩ ሁነቶች ታስበው ከሚውሉት በርካታ ዝክረ ቀናት አንዱ የሆነው “የዓለም የህትመት መገናኛ ብዙሃን ቀን” እየተከበረ ይሆናል። ወይም ደግሞ ተከብሮ ያለፈ ቢሆን እንኳ በእነዚሁ የዝክረ ሰሞን ቀናት “ድባብ” ውስጥ ትሆኑ ይሆናል ብዬ ስለምገምት የዚህ ጽሁፍ መነሻና መድረሻ ሃሳብም ይህንኑ ቀን ምክንያት በማድረግ “የሃሳብና ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት” ላይ ያተኮረ ስለመሆኑ ከወዲሁ እንድትረዱልኝ ይሁን እላለሁ። ከሃገር ውጪም በሀገር ውስጥም ላሉ “እውነተኛ” ጸሃፊያን የቀረበ ልባዊ መወድስ አድርጋችሁ ልትወስዱትም ትችላላችሁ።

ሰሎሞን ሞገስ (ፋሲል) የማደንቀው ገጣሚ ነው። ይበልጥ የሚታወቀው ደግሞ “እውነትን ስቀሏት!” በሚል ርዕስ ባስነበበንና የበኩር ስራው በሆነው የግጥም መድብሉ ውስጥ ባካተታት “ስንቅ የሚያቀብሉን እስረኞቹ ናቸው” በተሰኘችው ግጥሙ ነው። ለዚህ ጽሁፍ መግቢያ ይሆነኝ ዘንዳ ከዚያችው መድብሉ ውስጥ “መንገዱን አጥቼ - መንደዱን አገኘሁ” በሚል ርዕስ የቆዘመባትን አንድ “መንገደኛ” ግጥም ልጋብዛችሁና ወደ ነገረ ጉዳዬ እገባለሁ።

“አገር ካልሆነችኝ የትውልድ አገሬ፣

እኔም ልጅ አልሆናት ከእሷው ተፈጥሬ፣

“ኑ! ኑ!” እያላችሁ የሄደ አትጣሩ፣

ጨርቄን አቀብሉኝ በየት ነው ድንበሩ?!”

ሰሎሞን ጎበዝ ገጣሚ ብቻ ግን አይደለም በማህበራዊ ህየሳ ጽሁፎቹም የተዋጣለት ተመልካችና ንቁ ታዛቢ (Observer) ጭምር ነው። የጽሁፍም የንባብም ደንበኛ በነበርኩባት የ “አውራ አምባ ታይምስ” ጋዜጣ አምደኛ ሆኖ ከጻፈባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ (ለላይኛው ግጥምም “መነሾ ስብራት” የሚመስለኝ ጉዳይ) በሃገራቸው “ነገር” እየተመረሩ የሚሄዱ ሰዎችን ለመጥራት “ኑ! ኑ!” ብሎ ከመዝፈን ይልቅ እዚህ ያለውን አስመራሪ “ነገር” እንዲስተካከል መዝፈኑ አልያም ደግሞ ቀድሞ ማስተካከሉ ይበጃል በሚል የያዘው አቋም ይመስለኛል።

በአንድ የጋዜጣዋ እትም ላይ “እሰደዳለሁ!” በሚል ርዕስ ሲጽፍ የመሰደዴ ምክንያቶች ናቸው ያላቸውን ጉዳዮችም በዝርዝር ጽፎ ነበር። አሁንና ዛሬ ላይ ያኔ እንዳለው ይሰደድ ይኑር ባላውቅም በዚያው ሰሞን እዚያው ጋዜጣ ላይ ባስነበበን የመጨረሻ መጣጥፉ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ወዳጆቼን፣ ጓደኞቼንና የሙያ ባልደረቦቼን ሁሉ ብዙ ዋጋ አስከፍሏልና ከአሁን በኋላ “ብዕሬን ሰቅያለሁ!” ብሎ መድረኩን በሃዘን መሰናበቱን ግን በደንብ አስታውሳለሁ። ይህንን አለማስታወስስ እንዴት ልችል እችላለሁ?! እንዴትስ አንድ ብዕረኛ ከንባብ ማዕዱ ላይ ጎደለን ስነገር “መንገዱን ጨርቅ ያድርግለት!” ልል ይቻለኛል?! እንዴትስ ቢሆን “ካሻው በሊማሊሞ በኩል ያቋርጥ!” ብዬ ላሾፍ እችላለሁ?! እንዴት… እንዴት?!?!

ይኸው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሶሎሞንን ብቻ ሳይሆን ለቁጥር የታከቱ ጋዜጠኞቻችንን ብዕር የበላ ጅብ አልጮህ ብሏል። እነሆ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሃሳብ ገበያው ላይ ከጥቂት ጋዜጣና መጽሄቶች በቀር አልበረክት ብለዋል። እዚህ ጋር የሃሳብ ጸር የነበረውንና ምናልባትም ዛሬም ከበሽታው ያልተፈወሰውን የዕድሜ አዛውንቱ “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ የገጽ 3ቱን “ቱባ ሰው” ማስታወሱ አስፈላጊ ነው። ይህ የጋዜጣ ገጽና ይህንን የዚህ ገጽ ሰው በዚህ የሃሳብና የንግግር ነጻነት ሰሞን “ደስ አይበልህ!” አለማለት ህገ-መንግስታችን ያወቀልንን መብት በአግባቡ አለመጠቀም ይሆናል። የ “ገጽ 3ቱ ሰው” እነሆ የሃሳብና የንግግር ነጻነት ጸሃይ መቦግ ጀምራለችና “ደስ ይበለን!” እልሃለሁ!!!

 

አራተኛው የመንግስት አካል!

በብዙ ሃገራት የህትመት ዘርፉም ሆነ ይህ የሃሳብና ንግግር ነጻነት የሚገለጽባቸው ማንኛቸውም አይነት ሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ዘርፎች ከሶስቱ ተለምዷዊ የመንግስት ምሶሶሰዎች ተጨማሪ ሆኖና እንደ አራተኛው ምሰሶ (‘Fourth Estate’) ተደርጎ ይቆጠራልና የትኛውም መንግስት ለዘርፉ ህጋዊ ጥበቃና ከለላ ይሰጠዋል። መገናኛ ብዙሃኑም የህዝቡ መተማመኛ፣ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቱ ጠባቂ፣ ለሃሳብ ነጻነቱ ልዕልና እንዲሁም ለጥቅሙ የሚዘብ፣ ለድምጽ አልባዎች ድምጽ፣ ዓይንና ጆሮ ሆኖ ስለህዝቡ የሚያይ የሚሰማ በመሆን የራሳቸውን አበርክቶ ያቀርባሉ። የፕሬስ ሚና በዚህ ብቻ ግን አይገደብም መብቱን ጠንቅቆ ያወቀና ባወቀው ልክም በመብቱ የሚጠቀምን ዜጋም ይፈጥራል።

ለመገናኛ ብዙሃንና ለየትኛውም አይነት የሃሳብ ልዩነቶች ተገቢውን ክብር የሚሰጥ ህብረተሰብ መፍጠር ያስፈልገናል፣ ለየትኛውም አይነት የሃሳብ ልዩነቶች ተገቢውን ቦታ የሚሰጡና ራሳቸው ሃሳብን ከማፈን ነጻ የወጡ ነጻ መገናኛ ብዙሃን ያሰፈልጉናል፣ ለየትኛውም አይነት የሃሳብ ልዩነቶች ዕውቅናና ህጋዊ ጥበቃ (በነቢብም በገቢርም!) የሚሰጥ መንግስትም ያሻናል። የሃሳብ ልዩነትን መታገስና መቀበል የማይችል መንግስት፣ ይህንንም ልዩነት እንደ መርገምት ወስዶ ለማጥፋት ቀን ከሌት የሚታትር መንግስት፣ የራሱንና የራሱን ሃሳብ ብቻ እየሰማና እያሰማ መኖርን የሚያልም መንግስት፣ በኢትዮጵያ እንደታየው ሃገሪቱን ወደ ትልቅ እስር ቤትነት ይቀይራታል። አሳቢዎቿንም የስደትን ጥርጊያ እንዲከተሉ ያደርጋል።

ያለነጻ ፕሬስ ዴሞክራሲን አሰፍናለሁ ብሎ ቃል መግባት በራሱ ቃለ-አባይነት ነው፣ ያለነጻ ፕሬስ ማህበረሰባዊ ለውጥን መናፈቅም ከንቱ ነው፣ ያለነጻ ፕሬስ መልካም አስተዳደርን አሰፍናለሁ ቢባልም የማይመስል ነገር ነው። ምክንያቱም የነጻ ፕሬስ መኖር ለእነዚህ ሁሉ ትልሞች ቀዳሚ ለነገር (Pre-requisite) ነውና። እንድ የእንግሊዝ ፍርድ ቤት ከርዕሰ ጉዳያችን ጋር በተገናኘ ውሳኔው ላይ “የንግግር ነጻነት የዴሞክራሲያዊ ህብረተሰብ አስፈላጊው መሰረት ነው። ለዚሁ ህብረተሰብ ስልጣኔና ዕድገትም ሆነ ለእያንዳንዱ ዜጋ መታነጽ መሰረታዊ ቅድመ-ሁኔታ ነው።” በማለት ነበር ፍርዱን ያሳረገው።

የሃሳብና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መሰረታዊ መብት በህግ ዕውቅና ከማግኘቱ ባሻገር ህጉ በተግባር ሲገለጽና ለመብቱም ጥበቃ ሲደረግለት ሃገር ተጠቃሚ ትሆናለች። የሃሳብ ልዩነት ዕድልና በረከት እንጂ እርግማንና መርገምት ስላይደለ። የተሳሳተና “ክፉ” የምንለው ሃሳብ ቢሆን እንኳ ልናደምጠው ካልፈቀድንና ለማፈን ከሞከርን ቀድሞ ነገር በሃሳብ ነጻነትና በአመለካከት ልዩነት አናምንም ማለት ነው። የተሳሳተው ሃሳብም ቢሆን የመታረም ዕድልን የሚያገኘው ይፋ ሲወጣና ሲነገር ነው።

ከዚህም ባሻገር እኛ “የተሳሳተ/መጥፎ” የምንለው ሃሳብ በእኛ መመዘኛ ላይ ቆመን ስለመሆኑና “እነሱ” የምንላቸው ወገኖችም የእኛን ሃሳብ በራሳቸው ሚዛን ለክተው “መጥፎ/የተሳሳተ” ሊሉት እንደሚችሉ ማወቁም ብልህነት ሲሆን እውነታው ደግሞ ሁለቱም ሃሳቦች ለሃገርና ህዝብ ጠቃሚዎች መሆናቸው ነው። “መጥፎ ሃሳብ ደግሞ ምን ይጠቅማል?!” ካላችሁ እነሆ መልሱን የሚሰጠን ዕውቁ የሃሳብ ሰው ጆርጅ በርናንድ ሾው ነው።

በሃሳብ መስመር ላይ አንዳችን የሌላችንን ሃሳብ የምናጣጥለውና የኢትዮጵያ መንግስትም በተደጋጋሚ “አንዳንድ የህትመት ዘርፉ አካላት መርዶ ነጋሪና ጨለምተኛ ናቸው” እያለ ነበርም አይደል?! ጆርጅ በርናንድ ሾው “ተስፈኛ ነኝ ባዩም ሆነ ጨለምተኛ ነው የሚባለው ወገን ለህብረተሰቡ የየራሱን አስተዋጽዖ አበርክቷል። ተስፈኛው ለመብረር አውሮፕላን ሲሰራ ጨለምተኛው በረራ ላይ ለሚፈጠር አደጋ መዳኛ የሚሆነውን ጥላ (parachute) ሰርቷልና!” ይለናል። መርገምተ-በረከት እንበለው ይሆን? አዎን! መርምሮ ላስተዋለው በመርገምት ውስጥም በረከት አለ።

 

ገደብ አልባ ነጻነት ግን የትም የለም!

ብዙዎች ስለ ታላቋ ሀገረ አሜሪካን የንግግር ነጻነት ሲጽፉ የሃገሪቱ ህገ-መንግስት “First Amendment” የሆነውን “ኮንግረሱ የዚህን መብት ትግበራ የሚከለክል ወይም የሚቀናንስ ምንም አይነት ህግ ሊያወጣ አይችልም።” የሚለውን በመጥቀስ “The best press law is no press law at all.” በማለት ነው። ምናልባት ተመሳሳይ የሆነ ባህል፣ እምነት፣ ሃይማኖትና ማንነታዊ ግብ ላለባት ሃገር ይህ ትክክል ይሆናል። ይህ እውነታ ለአሜሪካውያን ብቻ ሳይሆን በዚሁ ባህል ውስጥ ላሉትና በጅምላው “ምዕራባውያን” ለሚባሉት ሁሉ የሚሰራ ነው።

የብሄር፣ የሃይማኖትና እምነት ብዝሃነትን ለሚያስተናግዱና ኢኮኖሚያቸውን ፈቀቅ ማድረግ፣ ዜጎቻቸውንም በመሰረታዊ የፊደል ዕውቀት እንኳ መሞረድ ላልቻሉ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሃገራት ግን ህጋዊ ገደብ ማደረጉን በጽኑ አምንበታለሁ። በአሜሪካና ሌሎች የምዕራቡ ሃገራትም ቢሆን ገደቡ ባለሁለት ሚዛንነት ሆኖ እንጂ ገደብ አልባነት ኖሮ ስላይደለ። አለም ዓቀፍ ህግጋትም የሚነግሩን በህግ ያልተገደበ የንግግር ነጻነት ዳፋው ጨርሶ የንግግር ነጻነት አለመኖርን የሚያመጣ ስለመሆኑ ነው። መብት ከግዴታ ጋር እንጂ ለብቻው የሚቆም ነገር አይደለምና።

በኢትዮጵያችን ግን የሚሆነውና ሲሆን የነበረው ከዚህ አይነቱ የመብት ወሰንን ዳር ድንበር ለይቶ ያሰመረ ህጋዊ ገደብ (Limitation) ጋር የተያያዘ ሳይሆን መሰረታዊ የንግግር መብትን የሸራረፈ ነው። ትሬሲ ጄ ሮስ የተባለች ተመራማሪ “A Test of Democracy: Ethiopia’s Mass Media and Freedom of Information Proclamation” በተሰኘውና “PENN STATE LAW REVIEW” ላይ በታተመላትና የኢትዮጵያ የሃሳብ ገበያ ላይ ባተኮረው መጣጥፏ “የዴቪድ ቤንጎሪዮን ትንቢት ለኢትዮጵያ የሚሰራ ይመስላል። በጸጥታና በርካታ ተያያዥ ጉዳዮች ሃገሪቱ በአለም ዓቀፍ መድረኮች ከበሬታን ብታተርፍም ዴሞክራሲዋ አሁንም የሃሳብ ነጻነትን መታገስ አቅቶታል።” የሚል መደምደሚያ ላይ እንድትደርስ አድርጓታል። የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ በዚህ መብት እየተፈተነ በተደጋጋሚ ፈተናውን ሲወድቅ ኖሯል።

የጋዜጠኞች እስር፣ ማስጠንቀቂያና ማሸማቀቅ፣ የህትመት ዋጋ ጭማሪ፣ ጋዜጦች ለህትመት ሲዘጋጁ እንደ ተንኮለኛ ቤት አከራይ መብራት ማጥፋት፣ ማስታወቂያን በመከልከል በገንዘብ ማዳከም፣ ጋዜጠኞችን ከመንገድ መጥለፍና ማገድ፣ የታተመ ጋዜጣን ሙሉ በሙሉ ወርሶ ማቃጠል፣ መንግስት ይጠብቀኛል ብሎ ማመንና መተማመን ሲኖርበት መንግስት ያስረኛል ብሎ እንዲሰጋና እንዲፈራ ማድረግ፣ በተለያዩ የ “ሂድ አትበለው…!” ዘዴዎች እግሩን ከሚወዳት ሃገሩ እንዲነቅል ማድረግና ማስደረጉ… ከኢትዮጵያውያን የተሰወሩ አይደሉም። ሰው ስጋም ነብስም ነው፣ ሰው አካልም መንፈስም ነው፣ ለሰውነታችን ምግብ እያማረጥን እንደምንበላለት ሁሉ ነብሳችንም የተለያዩ ሃሳቦችን ማግኘት ያሻታል። ለዚህ ደግሞ የህትመቱ ዘርፍ ከሌሎች መገናኛ ብዙሃን የተለየ ቀለም እንዳለውና የዜጎች የሃሳብና ዕውቀት መገበያያ ቦታ (Market place of ideas) መሆኑ እሙን ነው። የሃሳብ ገበያው መርህ “ምርጥ ሃሳብ ያሸንፋል!” እስከሆነ ድረስም ሃሳቦች ሁሉ ለገበያ መቅረብ እንዳለባቸውም ግልጽ ነው።

 

በመጨረሻም…

ይህ የትግልህ ፍሬ አፍርቷልና ዳግም ብዕርህን አንሳ መወድስ ለሰሎሞን ሞገስ (ፋሲል) ብቻ አይደለም። ለእስክንድር ነጋ፣ ለውብሸት ታዬ፣ ለአበበ ቶላ ፈይሳ ለተመስገን ደሳለኝ እና ለ “አዲስ ነገር” ሰዎች ወይም ለ “ዞን ዘጠኝ” ጦማሪያንና ለሌሎች ብጠቅሳቸው ቦታ ለማይበቃኝ ለቁጥር የበዙ ብዕረኞቻችን ብቻም አይደለም…. ለእስርም፣ ለስደትም፣ ለመዘጋቱም ለተጋለጡት “የሙስሊሞች ጉዳይ” መጽሄት ባልደረቦችም ጭምር እንጂ ነው።

-ሠላም ለእናንተ ይሁን!-

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
66 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 770 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us