የመኪና አደጋ፣ ኤችአይቪ ኤድስ እና የወጣቶቹ ጥረት ከአክሱም እስከ …..

Wednesday, 09 May 2018 13:23

 

በይርጋ አበበ

ወጣት ዳንኤል የማነ እና አማኤል ኪዳነ ላለፉት ሁለት ዓመታት የመኪና አደጋን እና የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭትን በተመለከተ በእግራቸው እየተጓዙ የአገራቸውን ህዝብ ሲያስተምሩ ቆይተዋል። ሁለቱ ወጣቶች በራሳቸው ተነሳሽነትና ያለማንም ደጋፊ ወገናቸውን ከአደጋ ለመታግ ሲያስተምሩ ቆይተዋል። በቅርቡ በአዲስ አበባ ራስ ሆቴል አዳራሽ ‹‹የኛ ድንበር ተሻጋሪ ደረጃ 2 ለ የደረቅ ጭነት ማመላለሻ ባለንብረቶች ማህበር›› ለረጅም ዓመት አሸከርክረው ምንም ጉዳት ያላደረሱ አሽከርካሪዎችን የመሸለምና እውቅና የመስጠት ፕሮግራም አዘጋጅቶ ነበር። በዚያ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው ሃሳባቸውን እና ልምዳቸውን ለታዳሚዎች ያካፈሉት ሁለቱ ወጣቶች እስካሁን ያለፉበትን እና ወደፊት የሚሄዱበትን የህይወት ጎዳና ለሰንደቅ ጋዜጣ እንዲህ ሲሉ ነግረውታል።

 

 

የእቅዱ ጅማሮ

በኢትዮጵያ ያለው የተሸከርካሪ ቁጥር ከሌሎች አገሮች ጋር ሲወዳደር በጣም አነስተኛ የሚባል ቢሆንም እያደረሰ ያለው ጉዳት ግን ከዓለም የመሪነቱን ደረጃ ይዟል። በያመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ኢትጵያዊያንን በወጡበት የሚያስቀረው ይኸው የመኪና አደጋ በንብረት ውድመት በኩል የሚያደርሰው ጉዳት ደግሞ እንደ መንገዶች ባለስልጣን መረጃ ከሆነ በቢሊዮን ብር የሚገመት ነው።

ኤችአይቪ ኤድስን በተመለከተ በቅርቡ የወጣ አገር አቀፍ መረጃ እንደሚያመለክተው ደግሞ በያመቱ ከ24 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ይያዛሉ። ከዚህ ቁጥር ውስጥ አብላጫውን የሚይዘው በወጣቶች በተለይም በሁለተኛ እና አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ላይ መሆኑ ችግሩን የከፋ ያደርገዋል።

የመኪና አደጋ እያደረሰ ያለውን ጉዳት አስመልክቶ በፓርላማ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ኃይለማሪያም በአንድ ወቅት በሰጡት ምላሽ ‹‹የመኪና አደጋ ላይ እንደ ኤችአይቪ ኤድስ አገር አቀፍ ዘመቻ ሊከፈትበት ይገባል›› ሲሉ መናገራቸው የቅርብ ሩቅ ትዝታችን ነው። በኢትዮጵያ ሺዎችን ለሞት እና የድሃ አገር በጀት ላይ ቢሊዮንን ለውድመት የሚዳርገው የመኪና አደጋ ካደረሳቸው የህይወት ጉዳቶች አንዱ በወጣት አማኑኤል ኪዳኔ ወላጆች ላይ ያደረሰው የሞት አደጋ ነው። ልጃቸውን ለማስመረቅ ከቤታቸው የወጡት የአማኑኤል ወላጆች የተሳፈሩበት መኪና በሀሰተኛ መንጃ ፈቃድ ያሽከረክር የነበረ ሾፌር ነበር የምትሽከረከረው። ሾፌሩ አምስት ሰዎችን እንደያዘ መኪናዋ ገደል ስትገባ የተመራቂው ወላጆችም ህይወታቸው ሊያልፍ ቻለ። የወጣት ዳንኤል ወላጆች ደግሞ በኤችአይቪ ነበር የሞቱት።

እነዚህ ሁለት ወጣቶችም ይህን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በራሳቸው ወጪ እና ጉልበት የሚሰሩት ከዚህ በኋላ መሆኑን ወጣት ዳንኤል የማነ ለሰንደቅ ጋዜጣ በሰጠው አስተያየት አስታወቋል። የጉዟቸውን መጀመሪያም አክሱም ከተማ አድርገው ከ200 በላይ ከተሞችን በእግራቸው በመዞር ‹‹በትምህርት ቤቶች፣ በቤተ አምልኮዎች፣ በዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች፣ በእስር ቤቶች እንዲሁም በመንግስት ተቋማት›› ወስጥ እየተዘዋወሩ ስለ መኪና አደጋ እና ኤችአይቪ ኤድስ ያስተምራሉ።

በተለይ የመኪና አደጋ እንዲደርስ አንዱ ምክንያት የአሽከርካሪዎች የብቃት ማነስ መሆኑን የሚገልጸው ወጣት ዳንኤል ‹‹በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ መንጃ ፈቃድ ስልጠናዎች ቢሰጡ፤ በአንድ ጊዜ አራተኛ እና አምሰተኛ መንጃ ፈቃድ መሰጠቱ ቀርቶ በሂደት እንዲሰጥ ቢደረግ እና የመንጃ ፈቃድ አሰጣጡ ላይም በጥናት እንዲመሰረትና የአገሪቱ ህግ አውጭ ክፍልም ትኩረት እንዲሰጠው›› የሚሉ ጥናታዊ ጸሁፎችን ያቀርባሉ ያስተምራሉ። በዚህ ስራቸው ድካምና ወጭ ቢበዛባቸውም ‹‹ህዝብን ማዳን ቅድሚያ አድርገን ስለተነሳን ድካሙ አይሰማንም፤ አገሬ ምን አደረገችልኝ ሳይሆን ለአገሬ ምን አደርኩላት ብለን ሁላችንም ልንሰራ ይገባል›› የሚል አቋም አላቸው።

ወጣቶቹ ትምህርት የሚሰጡት በአሽከርካሪዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በህብተሰብ ግንዛቤ ላይም መሆኑን ይናገራሉ። በትራፊክ አጠባበቅ በኩል ከትግራይ ኮረም፣ ከአማራ ጎጃም እና ከኦሮሚያ ክልል ደግሞ አምቦ ህብረተሰቡ ቀድሞ ግንዛቤ ያለው መሆኑን ታዝበናል የሚሉት ወጣቶቹ፤ ‹‹ልናስተምር ገብተን ተምረን ወጣን›› ብለዋል። የእነዚህ አካባቢዎች ተሞክሮ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ቢተላለፍ የጉዳቱን መጠን ይቀንሰዋል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

በኤችአይቪ/ኤድስ ላይም ቢሆን በተለይ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ያለው ተስፋፊነት የከፋ መሆኑን እንደታዘቡ ገልጸዋል። ይህን በተመለከተም መንግስት የቤት ስራውን እንዲሰራ እያሳሰቡ መሆኑን ተናግረዋል።

 

 

የገቢ ምንጭ

ወጣቶቹ ከአክሱም ተነስተው ከ200 በላይ ከተሞችን ሲያዳርሱ ሁለት ዓመታትን አስቆጥረዋል። አብዛኛውን ጉዞ በእግራቸው የሚያካሂዱ ሲሆን ከአንድ ወረዳ ወይም ከተማ ቢያንስ ለአስር ቀናት ያድራሉ። ከትግራይ ክልል ተነስተው ደቡብ ኢትዮጵያ ድረስ የተጓዙት እነዚህ ወጣቶች በጉዟቸው የሚያስፈልጋቸውን ወጪ እንዴት ይሸፍኑ እንደሆነ ላቀረብንላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ‹‹በራሳችን ስሜት እና ወጪ ነበር ስራውን የጀመርነው ነገር ግን በምንሄድባቸው አካባቢዎች ትምህርታችንን የሚሰሙ ወገኖቻችን በራሳቸው ተነሳሽነት ድጋፍ ያደርጉልናል›› ሲሉ ተናግረዋል።

ነገር ግን በመንግስትም ሆነ በተቋማት በኩል የሚደረግላቸው ወጥ የሆነ ድጋፍ አለመኖሩን የገለጹት ወጣቶቹ፤ ‹‹አንዳንድ የመንግስ ተቋማት ትብብር ሊደረግልን እንደሚገባ ስለሚያምኑ የቻሉትን ድጋፍ ያደርጉልናል፤ አንዳዶቹ ደግሞ የድጋፍ ደብዳቤ ይሰጡናል፤ ቀሪዎቹ ግን ምንም አይነት ድጋፍ አያደርጉልንም›› በማለት ለጉዟቸውና ለስራቸው የሚያስፈልጋቸውን ወጪ እንዴት እንደሚሸፍኑ ተናግረዋል።

ከዚህ በተረፈ ደግሞ ድጋፍ ስላገኙ ብቻ ሳይሆን ድጋፍ ባላገኙባቸው ወቅቶችም ቢሆን ስራቸውን ያለመታከት እንደሚሰሩ የሚገልጹት እነዚህ ወጣቶች ‹‹ብዙ ጊዜ ተቸግረን እናውቃለን የምናድርበት አጥተን ጫካ ውስጥ ያደርንበት ጊዜም አለ›› ብለዋል። ሰውን በመኪና አደጋ እና በኤድስ እንዳይሞት የሚያስተምሩት ወጣቶቹ ራሳቸውን ለዱር አውሬ አሳልፈው እስከመስጠት የደረሱበትን አጋጣሚ ያስታውሳሉ። ተቋማት ድጋፍ ሊያደርጉልን ቢፈልጉም በራሳችን ፍላጎት እንጂ ህጋዊ ሰውነት ስለሌለን ሊደግፉን አልቻሉም። አንዳንዶቹ ደግሞ እኛን በመገናኛ ብዙሃን ሽፋን የሰጠልን ስለሌለ ከናካቴውም አያውቁንም። በዚህ የተነሳ በበጎ ፈቃዳቸው ልቦናቸው ያሳሰባቸውን ከሚደርጉልን ሰዎች በምናገኘው ድጋፍ ነው ስራችንን የምንሰራው›› በማለት የገጠማቸውን ፈተና ተናግረዋል።

ይህም ሆኖ ግን ተስፋ ቆርጠው ወደኋላ እንደማይሉ የሚናገሩት ወጣቶቹ ወደፊት ብዙ ወጣቶችን አብረውን እንዲሰሩ በማድረግ በሁሉም የአገራችን ክፍሎች በማህበር ተደራጅተን ትምህርት መስጠታችንን እንቀጥልበታለን›› ብለው የወደፊት እቅዳቸውን ተናግረዋል።

 

 

የፖለቲካ ውሳኔ የሚሹ ጉዳዮች

ወጣቶቹ በየሄዱበት ከተማ እና በደረሱበት ቦታ ሁሉ በአገሪቱ ያሉ ችግሮችን ከማስተማር ጋር በተያያዘ ትኩረት የሚደርጉት የመፍትሔ ሃሳቡ ላይ መሆኑን ይገልጻሉ። የመፍትሔ ሃሳብ የሚሹ ጉዳዮችን የተመለከቱ ጥናታዊ ጽሁፎችን ሲያቀርቡ የመፍትሔ ሰጪዎቹ አድራሻ ‹‹አራት ኪሎ ያለው ነጩ ህንጻ›› ሆኖ ያገኙታል። ለዚህ ደግሞ የአገሪቱ ህግ አውጭ ክፍል ህጎችን ሲያወጣ ህብረተሰቡን ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን፣ የማያሰሩ ከሆነም የሚሻሻሉበትን መንገድ እንዲያመቻች ብሎም እንዲቀየሩ በማድረግ በኩል ቁርጠኛ እንዲሆን ጠይቀዋል። ለዚህ ደግሞ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጡን በተመለከተ የህግ ማሻሻያ እንዲደረግ የተደረሰበትን ውሳኔ እንደ ጥሩ ጅምር ተመልክተው በሌሎች ህጎች ላይም እንደዚህ አይነት ውሳኔዎች እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
62 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 885 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us