የኢፌዴሪ ወንጀል ህግ አንቀጽ 556 (2(ሀ)) ድንጋጌ አተረጓጎም ልዩነት

Wednesday, 16 May 2018 13:41

 

በብሩክ አያሌው

የኢፌዴሪ ወንጀል ህግ አንቀጽ 556(2(ሀ) ደርጊቱ በወንጀል ከስ አቅራቢነት የሚያሰቀጣው እና ከስድስት ወር እስከ ሶስት አመት የሚደርስ ቀላል እስራት የሚሆነው ጥፋተኛው ጉዳት ያደረሰው በመርዝ ወይም በገዳይ መሳሪያ ወይም የአካል ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ሌላ መሳሪያ በመጠቀም እንደሆነ ነው በማለት ይደነግጋል።

በዚህ ድንጋጌ አተገባበር ዙሪያ ብዙ ጊዜ በፍ/ቤቶች አካባቢ የአተረጓጎም ልዩነት ይስተዋላል።በአንድ በኩል አጥፊው ድርጊቱን ሲፈጽም መሳሪያ ከተጠቀመ የደረሰው ጉዳት ግምት ዉስጥ ሳይገባ በዚህ ድንጋጌ ስር ሊከሰስ እና ሊቀጣ ይገባል የሚል መከራከሪያ ሲቀርብ በሌላ በኩል ደግሞ አጥፊው ድርጊቱን የፈጸመው መሳሪያ ተጠቅሞ ቢሆንም እንኳን በተጎጂው ላይ የደረሰ ጉዳት ከሌለ መሳሪያዉን በመጠቀሙ ብቻ በዚህ ድንጋጌ ስር ተከሶ ሊቀጣ ይገባል የሚል መከራከሪያ ይቀርባል።

የመጀመሪያውን አቋም የሚደግፉት ተከራካሪዎች የሚያቀርቡት ምክንያት አጥፊው መሳሪያውን ተጠቅሞ ድርጊቱን ከፈጸመ የደረሰው ጉዳት ይነስም ይብዛም ድርጊቱን ሲፈጽም ጉዳት የማድረስ ሀሳብ አለው የሚል ነው።መከራከሪያቸውን ሲያጠናክሩም ጉዳት አልደረሰም ከተባለም ቢያንስ በሙከራ ሊከሰስ ይገባል ይላሉ።ሙከራ ሲባል በኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 27(1-3) ትርጉሙና ዝርዝር ነገሮቹ የተገለጸ ሲሆን አንድ ሰው ወንጀል ለማድረግ ጀምሮ የወንጀል ድርጊቱን እስከመጨረሻው ድረስ ያልተከታተለ ወይም ለመከታተል ያልቻለ እንደሆነ ወይም የወንጀሉ ድርጊት እንዲፈጸም እስከ መጨረሻው ድረስ ተከታትሎ የሚፈልገውን ዉጤት ለማግኘት ያልቻለ እንደሆነ በመሞከሩ ብቻ ጥፋተኛ ተብሎ ወንጀሉ ቢፈጸም ኖሮ ሊቀጣ በሚችልበት ድንጋጌ የሚቀጣበት የህግ መርህ ነው። በመሳሪያ በመጠቀም ድብደባ ተፈጽሞ አጥፊው በድርጊቱ ያደረሰው ጉዳት ባይኖርም ድርጊቱን ሲፈጽም መሳሪያ መጠቀሙ በመሳሪያው ጉዳት የማድረስ ሀሳብ ስላለው ያሰበውን ውጤት ባያገኝ አንኳን በመሞከሩ ብቻ በወንጀል ህግ አንቀጽ 556(2(ሀ)) ስር ተከሶ መቀጣት አለበት ማለት ነው። ለምሳሌ አንድ ሰው ሌላን ሰው በዱላ ጭንቅላቱን ቢመታውና በተመታው ሰው ላይ የደረሰ ምንም አይነት ጉዳት ባይኖር ደብዳቢው በወንጀል ህግ አንቀጽ 556(2(ሀ)) ስር ያለውን ድርጊት ለመፈጸም ሞክሯል ተብሎ በዚሁ ድንጋጌ ስር ያለውን ቅጣት መቀጣት አለበት ማለት ነው።

ሁለተኛውን አቋም የሚደግፉት ደግሞ አጥፊው በወንጀል ህግ አንቀጽ 556(2(ሀ)) ስር ጥፋተኛ ነው ለማለት ድርጊቱን የፈጸመው ጉዳት ሊያደርስ በሚችል መሳሪያ ሆኖ፣ሊታይ የሚችል ጉዳት ካደረሰ እንዲሁም የደረሰው ጉዳት በወንጀል ህጉ አንቀጽ 560 ስር የተገጸው የእጅ እልፊት ጉዳት ወይም በአንቀጽ 555 ስር የተገለጸው ከባድ የአካል ጉዳት ውጭ ከሆነ ነው በሚል ይከራከራሉ።እኔም የዚህ አቋም ደጋፊ ስሆን ይሄንን ክርክር ለማጠናከር የሚከተሉትን መከራከሪያዎችን አቀርባለሁ

1. የወንጀል ህግ አንቀጽ 556(2(ሀ)) ከአንቀጽ 556(1) ጋር ተያይዞ መተርጎም ይኖርበታል። በወንጀል ህግ አንቀጽ 556(1) ላይ ጥፋተኛው በአንቀጽ 555 ከተገጸው ከባድ የአካል ጉዳት ውጪ የሆነ ጉዳት ካደረስ የግል አቤቱታ ሲቀርብበት ከአንድ አመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም በመቀጮ እንደሚቀጣ ተደንግጓል።አከራካሪው የወንጀል ህግ ድንጋጌም ከአንቀጽ 556(1) የቀጠለ ሲሆን ሁለቱ ድንጋጌዎች ተያይዘው ሲተረጎሙ አጥፊው ሊቀጣ የሚችለው በንዑስ ቁጥር አንድ ላይ የተገለጸውን ጉዳት በመሳሪያ ከፈጸመው ብቻ ነው።ይሄ ማለት መሳሪያ ከመጠቀሙ ባሻገር ያደረሰው ጉዳት ሊኖር ይገባል ማለት ነው።ድንጋጌው በዚህ አግባብ ካልተተረጎመ አና የመጀመሪያውን አቋም የሚደግፉት ሰዎች አንደሚሉት ከተተረጎመ አጥፊው መሳሪያ ስለተጠቀመ ብቻ የደረሰ ጉዳት ሳይኖር በወንጀል ህግ አንቀጽ 556(1) ላይ ከተቀመጠው ቅጣት የከበደ ቅጣት ከ6 ወር ያላነሰ ቀላል እስራት ይቀጣል ማለት ነው።ይሄ ማለት ደግሞ መሳሪያ ሳይጠቀም የአካል ጉዳት ያደረሰ አጥፊ ከአንድ አመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም በመቀጮ ተቀጥቶ፣ መሳሪያ ተጠቅሞ ጥፋት ፈጽሞ ጉዳት ሳያደርስ ከ6ወር ያላነሰ ቀላል እስራት ሊቀጣ ነው ማለት ነው።

2. የወንጀል ህጉ ሊደርስበት ካሰበው ግብ እና ከህግ አውጭው ሀሳብ አኳያ መተርጎም ያስፈልጋል (የወንጀል ህግ አንቀጽ 3/4/)።ይሄ ሲባል በወንጀል ህግ አንቀጽ 556(2(ሀ)) ላይ ህግ አወጪው አጥፈው መሳሪያ በመጠቀሙ ከፍ ያለ ቅጣት እንደሚቀጣ ያስቀመጠው መሳሪያ መጠቀሙን ብቻ ለመቅጣት ሳይሆን አጥፊው መሳሪያ ተጠቅሞ ድብደባ ከፈጸመ በተበዳዩ ላይ ከፍ ያለ ጉዳት ያደርሳል በሚል ግምት ነው።ድርጊቱ በመሳሪያ ተፈጽሞ የደረሰ

ጉዳት ከሌለ ወይም የደረሰው ጉዳት የእጅ እልፊት ከሆነ በአንቀጽ 556(2(ሀ)) ስር የተገለጸውን ቅጣት መቅጣት የህግ አውጭው አላማ ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም።

3. በሙከራ መጠየቅ አለበት የሚለውን መከራከሪያ በተመለከተ አጥፊው ድርጊቱን ፈጽሞ ውጤቱን ስላገኘ ድርጊቱ በሙከራ የቀረ ነው ማለት አያስችልም። አጥፊው ድርጊቱን ሲፈጽምም ሃሳቡ ጉዳት ለማድረስ ስለመሆኑ ማወቅ አይቻልም። ስለሆነም ይሄ መከራከሪያ ብዙም የሚያስኬድ አይደለም።ለምሳሌ አጥፊው በኤርገንዶ ጫማ ወርውሮ ሰው ቢደበድብ እና የደረሰ ጉዳት ባይኖር የተወረወረው ጫማ በራሱ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል አይደለም። በዚህ ጊዜ ጉዳት የማድረስ ሀሳብ አለው ማለት አይቻልም።

ሲጠቃለል አጥፊው መሳሪያ ተጠቅሞ ድብደባ ፈጽሞ የደረሰ ጉዳት ከሌለ በወንጀል ህግ አንቀጽ 560(1) ስር ከሚጠየቅ በስተቀር በወንጀል ህግ አንቀጽ 556(2(ሀ)) ስር መጠየቁ ተገቢነት የለውም።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
313 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1031 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us