ከትላንትናው ዛሬ ይሻለናል!

Wednesday, 06 June 2018 14:02

 

ተፈሪ ብዙአየሁ ዶርሲስ (ዶ/ር)

ዛሬያችን ከትላንትናችን የሚሻለው ከስህተቶቻን ስንማር ብቻ ነው። ቀዳሚዎቻችን የሰሩትን ስህተት በተመሳሳይ መልኩን ቀይረን ዛሬ ዕዳን በህዝባችን ላይ እየጨመርን አለመሆናችንን እርግጠኞች መሆን አለብን። ትላንት በእጃችን የገቡትን ድሎቻችንን ያስነጠቁን እና 27 ዓመት ሙሉ የሰውን ሁለንተና እንድንገብር የዳረጉንን አካላት በአዲሱ ቲም አሰራር ውስጥ ሆነን ለመውቀስ እንኳን ዕድል ሳናገኝ የዛሬዎቹ አመራሮቻችን ድሎቻችንን እንደማያስነጥቁን በምን እርግጠኞች እንሆናለን?

በእጃችን የገባውን እድል ሊናጠቁን፤ የተስፋን ጭላንጭል ያሳዩንን አመራሮቻችንን መንገዳቸውን በማሳትም ሆነ በማስፈራራት ወይንም በእጅ አዙር ለማስገደድ እየተጉ ያሉት

1.    የራሳቸው አመለካከት እና የእስካሁኑ ተሞክሮአቸው

2.    በዙሪያቸው ያሉ አማካሪዎቻቸው

3.    ጥቅማቸው የጎደለባቸው

4.    የወደፊት ተስፈኞች ናቸው።

አዲሱ ቲም ወደ ቤተመንግስት ከመግባቱ በፊትም ሆነ ከገባ በኋላ ኦቦ ለማ መገርሳ ብዙ አደራ ስላለባቸው ዋጋ እየከፈሉ እንደሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ ይረዳል ብዬ እገምታለሁኝ። በቲም ለማ (የኦሮማራዎቹ) ፕሮፖዛል እና የተቀናጀ አሰራር አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ወደስልጣን ስለመጡ ለሁለቱም ስፍራ ተግተው መስራታቸው ‹የኢትዮጵያ ተስፋ› የሆነውን የአዲሱን አመራር ማቅናት፣ መደገፍ እና መገምገም እንደሚጠበቅባቸው ለማንም የታወቀ ነው። በክልላቸው ባላቸው ኃላፊነት እና በእርሳቸው መንገድ ጠራጊነት እና በጎ ፍላጎት የመጣውን አዲሱ የኢትዮጵያን አመራር የመደገፍ ኃላፊነት እንደተወጠሩ ሁሉም ኢትዮጵያ ሊረዳላቸው ይገባል ብዬ አምናለሁኝ። ሁለቱም ቦታ ላይ ቢበላሽ ከታሪክ ተወቃሽነት አያመልጡምና። ኦቦ ለማ ግን ይህንን ድርብርብ ሃላፊነት ለመወጣት ሲወስኑ በክልላቸው ብቁ ረዳት እንዳለቸው እኔ በግሌ እርግጠኛ አይደለሁም። እምነት የሚጣልባቸው ብቁ ረዳታቸውን ወደፌዴራል ሲያመጡአቸው ሰውየው የተመደቡበት ቦታ በራሱ ለኢትዮጵያ ህዝብ ወሳኝ ስፍራ እንደሆነ እሙን ነው። “ራሱ” ጤነኛ የሆነለት ሰው ሌላው የአካል ክፍሉ ቢታመም ቶሎ ሊድን ይችላል የሚል እሳቤ ከሆነ እሰየው ነው።

ምናልባት ደግሞ ከጠ/ሚኒስትሩ ንግሮች እንደሚደመጠው እና እርሳቸውም ግንቦት 20ን አስመልክተው ንግግር ሲያደርጉ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ሲሉ አጋንነነው መናገራቸው ከዚህ ከአዲሱ አመራር በስተጀርባ ሆነው ታላቂቷን ኢትዮጵያን ለመገንባት ቆርጠው የተነሱ ይመስላል።

ይህች ኢትዮጵያ እያሉ ያቀነቀኑላት የትኛዋ እንደሆነች ለጊዜው ግልጽ ባይሆንም የትላንቱን ስህተት ለመድገም እየተንደረደሩ ያሉ የሚያስመስል አመላካች ነገሮችን አስተውላለሁኝ።

በአሁኑ ወቅት ትኩስና የወቅቱ ጥያቄ እየሆነ የመጣው ‹ጠ/ሚኒሰትሩ መቼ ነው ቁጭ ብለው የሚሰሩት?› የሚል ነው። ይህ ጥያቄ በሰው ሁሉ ልብ አለ። ሚዲያውንም እያጣበበ ያለውም እውነታ ይህ ነው። ከተሾሙ ሁለተኛ ወራቸውን ደፍነዋል። መሰረታዊ ጅማሬዎች ይታያሉ። ከአጓጊ ንግግሮቻቸው በስተጀርባ ሆነው የአካሄዳቸው አቅጣጫ ግን በጥርጣሬ የሚያዩ ተበራክተዋል። ቢሮ ባለመገኘታቸው የተነሳ በጥርጣሬ እንዲሞሉ ያደረጋቸው አንዳንዶች የለውጥ ናፍቆት ስላላቸው ነው ያስብላል።

እነኚህ ለውጥ ናፋቂዎች ገሚሶቹ አብዮታዊነት ይታይባቸዋል። ጠ/ሚኒስትሩ ልክ ወደስልጣን ሲመጡ የተመኙት እና እንዲሆንላቸው የፈለጉት ወዲያውኑ እንዲሆን የሚናፍቁትን ነው፡፤ አይፍረድባቸውም ይሆናል። ካሳለፉት ሁኔታ አንጻር ምናልባት ልክ ናቸው ሊያስብል ይችል ይሆናል። ፈጣን ለውጥ አብዮት እንጂ ሂደት አይሆንም። ኢህአዴግ ደግሞ የስልጣን ሽግሽግ አደረገ እንጂ የስርዓት ለውጥ አላደረገም። ምክንያቱም የስርኣት ለውጥ ነው የሚያስብል እርምጃ አላደረገም። ከዚህ የተነሳ አብዮታዊ ለውጥ ሊያሰብል የሚችል አልታየም።

ሁለተኞቹ ለውጥ ናፋቂዎች በሂደትም ቢሆን የሚመጣውን ለውጥ ቢናፍቁም ምልክቶቹን እየገመገሙ በጥርጣሬ ውስጥ ገብተዋል። ጥርጣሬያቸውን ያጎሉት ሁኔታዎችም

·         ጨከኞች በጭካኔአቸው እስከቀጠሉ ድረስ፤

§  የተወሳሰበው የገበያ ትስስር አሁንም አላፈናፍን ብሎ ኢኮኖሚውን እየጎዳ አስካለ ድረስ፤

§  ኢህአዴግ በአዲሶቹ ሹመቶቹ ሰዎችን ቀያየረ፤ ቦታቸውን ለዋወጠ እንጂ ከራሱ ክልል ወጥቶ የእይታ አድማሱን ለማስፋት ሌሎችን ለማቀፍ ስርዓቱ እስካልፈቀደለት ድረስ፤

§  ሙሰኞች ዛሬም ቢሮክራሲውን በተሻለ አሰራር እስካወሳሰቡ ድረስ፤

§  ቅድመ - ሁኔታዎችን ያላገናዘበ በውጭ ያሉ ተፎካከሪ የፖለቲካ ድርጅቶችን እና ታዋቂ ፖለቲከኞችን እና ሚዲያዎችን በአፍ ብቻ ጥሪ ከማቅረብ በህግ ማዕቀፍ እስካለተደገፈ ድረስ፤

§  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አቅም ማሰፈራሪያ ሆኖ እስከቀጠለ ድረስ ለውጡ መቼና እንዴት ይመጣ ሆን ብለው አዝጋሚውን ሂደት በአንክሮ እየተከታተሉ ይገኛሉ።

ጠ/ሚኒስትሩም ለእነዚህ ጉዳዮች መፍትሔ ለማፈላለግ በቢሮ አልተገኙምና -ጅማሬው ያላማረ ብለው ይተቻሉ። የሚያቀርቡት ሃሳብም ‹የሰው ለውጥ የስርዓት ለውጥን ለማምጣት የተሿማች ቁርጠኝነት እና ዋጋ መክፈልን ይጠይቃል›። ጠ/ሚኒስትሩ ከስራቸው ያዋቀሩአቸው ተሿሚዎች ቀድሞውንም በራሱ በኢህአዴግ የተቃኙ አፈቀላጤዎቹ በመሆናቸው ከራሱ ክልል አልወጣም እዚያው በዚያው መሿሿሙን ብንታገስም የምንናፍቀውን ለማግኘት ጥርጣሬ ውስጥ ነን የሚሉ ይመስላሉ።

እንደማሳያ የሚያቀርቡትም የሚድሮክ ለገደንቢ የወርቅ ማምረቻ ውሳኔ በጠ/ሚኒስትሩ ዘመን ሁለቴ መገለባበጡን ነው። አቶ ሞቱማ መቃሳ የማእድን እና ኢነርጂ ሚኒሰትር ሆነው ያደሱትን ፈቃድ ውሳኔውን ከማቅናት ይልቅ የመከላካያ ሚኒሰትር ሆነው ጉልቻቸውን በቀሩ ማግስት ስህተታቸውን ለመሸፋፈን የጉጂን ህዝብ ለማሳመንም ሆነ ለመለማመጥ ወይንም ለማስፈራራት (አልሆነላቸውም እንጂ) ሙከራ ማድረጋቸው አልተሳካላቸውም። ህዝቡ በጉልበቱ ውሳኔውን አስቀለበሰ። ኢህአዴግ ከስህተቱ መማር ያልቻለው እስከመገደድ ጥግ ድረስ መሄዱ የሂደት ለውጥ ፈላጊዎችን ጥርጣሬ አጉልቶታል። ጠ/ሚኒሰትሩ የሰው ሕይወት እስኪጠፋ፤ ደም እስኪፈስ መጠበቃቸው (መገደዳቸው እስከልቀረ ድረስ) አንድም አለቆቻቸው ስላልፈቀዱላቸው እየተለማመጧቸው ወይንም ራሳቸው የውሳኔው አካል ስለነበሩ ነው ያስብላል። አልያም ይላሉ የሂደት ለውጥ ፈላጊዎች እርሳቸው እስካሁን ካደረጓቸው ንግግሮቻቸው ውስጥ የትግሉ ባለቤት የሆነውን አካል በግልጽ እውቅና ያለመስጠታቸው ሀቅ ፍንትው ብሎ እየወጣ ስለሆነ ከኋላ ሆኖ ግንባሩን የሚቋጥርባቸው እንዳለ በመገመት እርሳቸው ነጻነታቸው ንግግራቸው ብቻ ይሆንን ይላሉ። ስለዚህ እርሳቸውም ሆኑ ካቢኔዎቻቸው የስርዓቱ አካል ስለሆኑ እስኪፈቀድላቸው ድረስ ደም መገበር ነበረበት ወይ?

ሎሎች ሶስተኛ ወገኖች ጠ/ሚኒሰትሩ ወደቢሮ ተመልሰው እንዲሰሩ የሚናፍቁት እርሳቸው ስለሳሏት ኢትዮጵያ አቋማቸውን ለማወቅ የሚናፍቁት ናቸው። እነዚህ አካለት ከንግግሮቻቸው የምትደመጠዋን ምናልባት በእርሳቸው የአእምሮ ሳሎን ተስላ የተቀመጠችውን ኢትዮጵያን፤ በሙዳያቸው ሸላልመው ያኖርዋትን ሲፈልጉ አጋጣሚውን ሲያገኙ የሚመነዝርዋትን የእርሳቸውን ኢትዮጵያ ማወቅ የሚፈልጉ፤ በጉጉትም እየጠበቁ ያሉ በርካታ ናቸው። እርሳቸው የሚያቀነቅኑላት ኢትዮጵያ የቄሮ ትግል የወለዳት የኦቦ-ለማዋ ኢትዮጵያ አትመስለንም የሚሉ በርካቶች ናቸው። (ኦቦለማም በግንቦት 20 ንግግራቸው ሊቀላቀሉአቸው የሞከሩ ይመስላሉ)። ጠ/ሚኒስትሩ በንግግሮቻቸው የሚያንቆለጳጵሷት ከአንድነት መሰረተ-ሃሳብ የምትጀምረዋ ኢትዮጵያ ስለሆነች እርስዋ ካበቃለት ቆይታለች ብለው የሚሉ ሶስተኛ ወገኖች ተበራክተወል። እነዚህኞቹ ምክር ቢጤ አላቸው፡- ምናልባትም ከጫፍ ጫፍ ሲጨበጨብላቸው ድጋፍ ያገኙ እየመሳላቸው ስራው ቀሎላቸው በውስጥም በውጭውም ጉብኝቶች ያንበሸበሹን እርሳቸው የሚሏትን ኢትዮጵያ የተቀበልንላቸው መስሎአቸው እንዳይዘናጉ በማለት ይመክራሉ። ስራው የቀለላቸው ሲመስለን ይላሉ እነኚኞቹ፡- ‹ልዩነታችንን ከማግነን አንድነታችን ላይ እንስራ› የሚለው በውብ ቃላቶች የተከሸነው ንግሮቻቸው ‹እዳው ገብስ› ሆኖላቸው ተቀባይነት አግኝተው ኢትዮጵያ በቀላሉ አንድ ትሆናለች ብለው ካሰቡ የፈጠኑ ይመስላሉ ይላሉ።

በመድረኮቻቸውም በሚዲያዎቹ ዘገባዎችም ስለቀናቸው ከሁሉ በላይ እርሳቸው የሳሏት ኢትዮጵያ ልዩነትን አስወግዳ በአንድነቷ ላይ የምትሰራ በመሆኑ ከኢህዴግ የምቾት ቀጠና ባይወጡም ሰው ተቀያይሮም ቢሆን ኢትዮጵያ ትቀጥላለች ብለው ባስቡ እና ሌላ ስህተት ባይደግሙ የሚሉ አሉ። እርሳቸውም በቀጥታም ባይሆን በንግግሮቻቸው የእርሳቸው የመደመር ስሌት የማይመቻችሁ ካላችሁ ልዩነቶቻችንን አቻችለን ወደታላቂቷ ኢትዮጵያ ግንባታ ሃሳብ መቅረብ ይሻላችኋል ብለው መክረዋልና።

እነዚህ ከእርሳቸው ታላቂቷ ኢትዮጵያ ፈጣን ግንባታ ፕሮፖዛል በመለስ ያሉ ወገኖች እርሳቸውን የወለደው ትግል መሰረቱ ግን ይህ አይደለም ይላሉ። እርሳቸው ስለው ያቀረቡልንን ኢትዮጵያ ብንፈልግ ኖሮ እስከዚህ ድረስ ልጆቻችንን የቀጠፈ ደም አፍሳሽ ዘግናኝ ትግል ማድረግ ትርጉም አልባ አይሆንም ወይ? ይላሉ። እነዚህ አካላት የሳሉዋት እና የሚጠብቁዋት ኢትዮጵያ በአንድነት ላይ ሳይሆን በእኩልነት ላይ የምትመሰረትዋን ነው። መሰረተ-ሃሳባቸው ኢትዮጵያን በትላንትናም ሆነ በዛሬ ላይ ቆመን ስናስባት በእኩልነት ላይ የተመሰረተች አይደለችም ይላሉ።

የእነዚህ ወገኖኝ ሃሳብ ዘመናዊቷን ኢትዮጵያን ለማምጣት የተዋደቁላት አጼ ቴዎድሮስ የሳሏት ከአጼ ምኒልክ በኋላ እስከቄሮ ትግል ድረስ የደረሰችውን ኢትዮጵያን ከሆነ አጼ ቴዎድሮስም ተሳስተዋል ማለት ነው ብለው ሊሞግቱአቸው ይሆን?።

በእነዚህ ጽንፍ ያሉት ወገኖች የመከራከሪያ ሃሳባቸው ጠ/ሚኒስሩን የወለደው የቄሮ ትግል ውስጥ የታለመችው ኢትዮጵያ ገና ተስላ ያላለቀች ነገር ግን ያገባኛል የሚል አካል ሁሉ ከቃላት ድርደራ ባለፈ ብሩሹን አንስቶ የሚስላት ናት ይላሉ።

ይህች የምትመጣዋ ኢትዮጵያ የቄሮን ትግል መሰረት ካላደረገች

1.  የኦሮሞ ፖለቲካ አሁንም አላደገም ማለት ነው ይላሉ።

2.  ቄሮ የታገለው ከኢህዴግ በበጎ ስጦታነት የሚቀርብለትን ሽርፍራፊ የስራ-እድል መመቻቸት ይሆናል ማለት ነው። ይህ ደግሞ የቄሮን ትግል አሳንሶ ማየት ይሆናል ይላሉ።

3.  ጠ/ሚኒሰትሩ ሳይሆኑ እርሳቸውን ወደፊት ለማምጣት ዋጋ የከፈሉ ቲም-ለማዎች ከቀደሙት ስህተቶች ባለመማራቸው የተቀዳጁትን ድል ለሌላ አካል አሳልፈው እየሰጡ ነው ማለት ነው ይላሉ።

4.  ከዚህ ሌላ ሶሶት ዓመት ደም ያፋሰሰ እልህ አስጨረሽ ትግል የአሁኗን ኢትዮጵያን እና ኢህአዴግን ይጠብቃቸዋል ማለት ነው ይላሉ።

እንግዲህ የጠ/ሚኒሰትሩን በቢሮ መገኘት የሚናፍቁ ሶስቱም አካላት መቼም ቢሆን የኦሮሞ ህዝብ መብቱን ለማስከበር ከዚህ በኋላ ምክር እንደማያስፈልገው ኢህአዲጎች ሊማሩበት የተገባቸው የሚድሮክ ለገደንቢ ወርቅ ማምረቻ ውሳኔ ነበር በማለት ይመክራሉ። ከዚህ የተነሳ በሂደት ለውጥ ፈላጊዎቹ በንቃት የሚታየው ጉዳይ የጠ/ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የትኛዋ ናት? በማለት ሰፊ ማብራሪያ የሚያሻው ጥያቄ ያቀርባሉ።

እኔ ግን የምለው አለኝ። መምራት ፈልገውም ያልሆነላቸው ነገር ግን ስለዚህች የጋራችን ስለሆነች ሀገር አሻራቸውን የጣሉ፤ በአንጻሩ ደግሞ እድሉን አግኝተው የመሯትም መሪዎች በነበሩባቸው ወቅት የተሳሳቱትን ስህተት ላለመድገም ቁርጠኞች ነን ወይ? በኪቹዎቻችን ደም ወደፊት ስትወጡ ይህችን ሀገር

·         እናንተ ወደምትፈልጉት አቅጣጫ እንድትመሩ አይደለም።

·         በዙሪያችሁ ያሉ አማካሪዎቻችሁ አስተዋችሁ ስህተት እንድትሰሩም ዋጋ የከፈለም የለም።

·         ጥቅማቸው የጎደለባቸው ከህዝቡ ፍላጎት በተቃራኒ የነበረው እንዲቀጥል እንዳያደርጓችሁ ተጠንቀቁ

·         ተስፈኞችን ትላንት ያልሆነላቸውን እናንተ ከምታሳዩአቸው ምልክቶች በመነሳት ወደሚፈልጉት እየመሯችሁ ሌላ ተጨማሪ ዋጋ የሚያስከፍለንን ስህተት እንዳትሱሩም ቆም ብላችሁ ዋጋችሁን ተምኑ።

ሰፊ ደጋፊ ህዝባችሁን አሳትፋችሁ የተሻለ ነገር በዘመናችሁ እንደምትስሩበትና፤ ያንንም ለቀጣዩ ትውልድ እንደምታቆዩ ተስፋ አለኝ።

የምሪት ዘመናችሁ ይበረክ!!

ግንቦት 2010 ዓ.ም

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
62 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 142 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us