ለውጡ ሁሉንም ዜጎች የሚያካትት ይሁን!

Wednesday, 06 June 2018 14:05

 

በጥላሁን ኤርዱኖ (ዶ/ር፣ ኢ/ር)

 

በመልካም አስተዳደር ችግርና በጥልቅ ተሀድሶ ሰበብ
ሙሰኞችን በማጋለጣቸውና ብልሹ አሠራራቸውን በመተቸታቸው
ብቻ ቂም ተይዞባቸው ከሥራቸው የታገዱና የተባረሩ እንዲሁም
ከደረጃቸው ዝቅ የተደረጉ ቅን የመንግሥት ሠራተኞች በሙሉ
በተቻለ ፍጥነት ሙሉ ጥቅሞቻቸው ተከብሮላቸው
ወደሥራቸው እንዲመለሱ መደረግ አለበት።

 

አዲሱ ጠ/ሚ ከተመረጡ ጊዜ ጀምሮ እሰየው የሚያሰኙ አስተማሪ ለውጦች እየታዩ ነው። በተለይ በፖለቲካዊ አመለካከታቸው የተነሳ ብቻ ታስረው የነበሩትን ዜጎች እንዲፈቱ ማድረጋቸው ትክክለኛና ትልቅ ታሪካዊ ርምጃ ሊባል የሚችል ነው። ነገር ግን በሙስና የታሠሩትን ሲፈቱ የታሰሩበት ሰበብ ሙስና ሳይሆን ሌላ ስለመሆኑ ጠንካራ ምክኒያትና ማስረጃ ሊኖርና ለህዝቡም ሳይዘገይ ሊነገረው ይገባል የሚል እምነት አለኝ። አለበለዚያ በሙስና ስለመታሠራቸው በህዝቡ ብዙ የተባለባቸውንና የብዙኋን መገናኛዎችም እጅጉን የዘገቡባቸውን ሙሰኞችን/ሌቦችን ሁሉ በይቅርታ ስም የሚፈቱ ከሆነ በምላሹ ከህዝብ እየተገኘ ያለው ድጋፍ ሳይውል ሳያድር እንዳይሸረሸር ያሰጋል። በዚህ ዙሪያ እየተወሰዱ ያሉት እርምጃዎች ከወዲሁ በንጹኋን የተመከረበት፣ የታሰበበትና ማስረጃ ሊቀርብበትና ለህዝብ ጥያቄ አጥጋቢ መልስ ሊሰጥበት የሚችል መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ሰዎቹ ታስረው የነበረው ሙስና የሚለው ታፔላ እንደሰበብ ተለጥፎባቸው ከሆነም ለአላስፈላጊ ሀሜት ሳይዳርግ በፊት ከወዲሁ ተገቢ ማብራሪያ ሊሰጥባቸው ግድ የሚል ይመስለኛል።


በሌላ በኩል አንድ መታወስ ያለበት ቢኖር በተለያዩ ምክኒያቶች የታሰሩትን ከማስፈታታችን በተጨማሪ የጀመርነው መልካም የለውጥ ጅማሮ ሁሉን ዜጋ የሚያካትትና ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ማረጋገጥ ወሳኝ ይሆናል። አገራችን በአጋጠሟት የመልካም አስተዳደር ችግር ውጤት በሆነው ሙስና የተነሳ የአገራችን ሰላም ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ በመሆኑ በተለይ ከ2008 ዓ/ም ጀምሮ የተለያዩ የመንግሥት መ/ቤቶች ሠራተኞቻቸውን በመሰብሰብ በመልካም አስተዳደር ችግርና በጥልቅ ተሀድሶ ስብሰባዎች ሰበብ ተወጥረው መክረማቸው የሚታወስ ነው። በእነዚህ ስብሰባዎች ወቅት የአገሪቱ ህገመንግሥት ባጎናጸፏቸው ፍትሀዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶቻቸው በመጠቀም እና ከህዝብና መንግሥት የተጣለባቸውን መንግሥታዊና ህዝባዊ ኃላፊነቶቻቸውን መሠረት በማድረግ ለአገራቸው ልማትና ለህዝባቸው ብልጽግና በመቆርቆር በተለያዩ ደረጃዎችና መዋቅሮች የየመ/ቤቶቻቸውን ሙሰኞች አድሏዊና ብልሹ አሠራሮችን ማንንም ሳይፈሩ ደፍረው አምርረው የተቹ አያሌ የመንግሥት ሠራተኞች እንደነበሩ ይታወቃል። ስብሰባዎቹ ሲካሄዱ ከፌዴራል፣ ከተቋማቱ አካባቢና ከክልል የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሳይቀር የመጡ ታዛቢ እንግዶች፣ ሚኒስትሮችና ሚኒስትር ደኤታዎች ወዘተ ነበሩ። በስብሰባው ወቅት በእነዚሁ እንግዶች ለሙያቸው፣ ለአገር ልማትና ሰላም ለሚቆረቆሩት የመንግሥት ሠራተኞች ጥበቃ ይደረግላቸዋል ተብሎ በመነገሩ ተበረታትተው ብልሹ አሠራሩን አምርረው የተቹ የመንግሥት ሠራተኞች አብዛኛዎቹ ዛሬ ከነቤተሰቦቻቸው ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠዋል። እንግዶቹም የአገር ተቆርቋሪዎቹን በኔትዎርክ ለተሳሰሯቸው ለመ/ቤቱ ኃላፊ ባለስልጣናት እብሪት አሳልፈው ከመስጠታቸው በስተቀረ በቃላቸው ጸንተው ዜጎቹን ከባለስልጣናቱ ኢ-ፍትሀዊ ርምጃ ሊታደጓቸው አልቻሉም። እነዚህ ከተለያዩ ህዝባዊ ተቋማት ተወክለው መጥተው ተናግረው አናግረው ሠራተኞቹን ለማንአለብኝና ሙሰኛ ባለስልጣናት አሳልፈው ሰጥተው ወደየመጡበት ሄደዋል። ነገሩ በጥልቀት ሲታይ የእነዚህ ታዛቢዎች አመጣጣጥ የባለስልጣናቱን ብልሹ አሠራር አጥብቀው የሚቃወሙትን ቅን ሠራተኞችን ለማስጠመድ ይመስላል።


በመሆኑም እነዚህ ቅን የመንግሥት ሠራተኞች በዚሁ አዎንታዊ አስተያየታቸው የተነሳ ብቻ በሙሰኛና ብቃት አልባ የየመ/ቤቶቹ ብልሹ ኃላፊዎች ቂም ተይዞባቸው በዲሲፕሊን ሰበብ ያለምንም የህግ አግባብ ከሥራቸው የታገዱ፣ የተባረሩ፣ ሆን ተብሎ ከኃላፊነታቸው የተነሱና ከመደባቸው ዝቅ የተደረጉ ወዘተ አያሌ የመንግሥት ሠራተኞች ከነቤተሰቦቻቸው ለከፋ ችግር በመዳረግ ላይ መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል። ከእነዚህ እጅግ በርካታ ቁጥር ካላቸው ዜጎች ገሚሶቹ በአ.ፌ.ዲ.ሪ. ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት አስተዳደር ፍ/ቤት በሌላቸው አቅም ከተራራ ከገዘፉ ባለስልጣናት ጋር በመካሰስ ላይ ሲሆኑ ብዙዎቹ ግን ወጭውንና ውጣውረዱን መቋቋም ስላልቻሉ ከሥራ ገበታቸው ለመራቅና ከነቤተሰቦቻቸው ለከፋ ችግር ለመዳረግ ተገደዋል። የሚገርመው ባለስልጣናቱ ለዚህ እኩይ ተግባራቸው ለመንግሥት የሚቆረቆረውን የመንግሥት ሠራተኛን ከህግ አግባብ ውጭ ለመጨቆን ሲሉ በማንአለብኝነት የመንግሥት በጀት (አበልና ትራንስፖርት) የሚጠቀሙ መሆናቸውና ለአገርና ለወገን በመቆርቆር ለችግር የተዳረጉት አያሌ የመንግሥት ሠራተኞች ግን ዞር ብሎ የሚያያቸው አለመኖሩ ነው።


ስለዚህ ክቡር ጠ/ሚኒስትራችን የተለየ ፖለቲካዊ አመለካከት ስለተከተሉ ብቻ ታስረው የነበሩት እስረኞች እንዲፈቱ እንዳደረጉ ሁሉ እነዚህም ለሥራቸው፣ ለሙያቸውና ለአገራቸው ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና በመቆረቆር የተሻለ አሠራር ይመጣል ከሚል ቅን እምነት በመነጨ የሰጡት ቅን አስተያየት ተገልብጦ ሙሰኛ ባለሥልጣናት ሰበብ አድርገው ባዋቀሯቸው የዲሲፕሊን ኮሚቴና በኔትዎርክ በሚሠራው የየተቋማቱ ቦርድ፣ እንዲሁም ለሙሰኛ ባለስልጣናቱ መሳሪያ ሆኖ በሚያገለግለው የየመ/ቤቱ የ”ህግ ክፍል” ጋር እጅና ጓንት ሆነው በተሰጧቸው ኢፍትሀዊና ኢ-ዲሞክራሲያዊ ውሳኔዎች የተነሳ ከነቤተሰቦቻቸው በከፍተኛ ችግር ላይ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ቁጥር ከሚጠበቀው በላይ ነው።


ስለዚህ ጠ/ሚኒስትሩ የጀመሩት አጓጊ ለውጥ ከአለት የጠነከረ መሠረት እንዲኖረውና ሁሉን አካታች እንዲሆን ከተፈለገ እነዚህ ዜጎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደየሥራ ቦታቸው ተመልሰው በየመስሪያ ቤቶቻቸው ሆነው አዲሱን የለውጥ ሂደት እንዲያግዙ ማድረግ ተገቢ ብቻ ሳይሆን ወሳኝ ይመስለኛል። ይህ ውሳኔ እጅግ አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ እነዚህ ድርብ በደል የተፈጸመባቸው የመንግሥት ሠራተኞች አዲሱ ጠ/ሚ የተያያዙትን አዲስ የለውጥ ሥራ ከታች ሆነው በየ/መ/ቤቱ በማሳለጥ፣ በየመ/ቤቱ ግልጽነት፣ አሳታፊነት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ወዘተ እንዲኖር በማድረግ፣ ባለስልጣናቱም በደመነፍስ ሳይሆን በመርህ እንዲመሩና በኔትዎርክ ሳይሆን በህግ ለህግ እንዲሠሩ በማድረግ፣ ሙሰኞችን በማጋለጥ የመልካም አስተዳደር ችግሩ መልሶ እንዳያገረሽ በማድረግ ረገድ ሊኖራቸው የሚችለው ሚና ከምንም በላይ እንደሆነና በማንም ሊተካ የማይችል መሆኑን ለክቡር ጠ/ሚኒስትሩ መንገር ለቀባሪ እንደማርዳት ይሆንብኛል።


የዚህ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የመንግሥት ሠራተኛ መሠረታዊ ድጋፍና አቅም ለለውጥ ሂደቱ ከፍተኛ ብቻ ሳይሆን መሠረታዊ አስተዋጽኦ ሊያበረክት የሚችል ኃይል ያለምንም ዋስትና ከሥራ ውጭ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። በተለይ በመልካም አስተዳደር ችግርና በጥልቅ ተሀድሶ ሰበብ ስብሰባ ላይ በተነሱ የሰራተኞችና የኃላፊዎች የሀሳብ ልዩነቶችን ተከትሎ በዲሲፕሊን ሰበብ ከሥራቸው የተባረሩ ቅን ሠራተኞች ከሥራ ከተሰናበቱበት ቀን ጀምሮ የተቋረጠባቸው ደመወዝ ሙሉ በሙሉ ተከፍሏቸው በአስቸኳይ ወደሥራቸው እንዲመለሱ ቢያደርጉ የተጀመረው የለውጥ ሥራ አንድ ሳይሆን ሁለት እርምጃ ወደፊት ሊያስፈነጥር የሚችል አቅም ሊፈጥር የሚችል ውሳኔ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ክቡር ጠ/ሚኒስትር እነዚህ አያሌ የመንግሥት ሠራተኞች ከሥራቸው ለመፈናቀል የተገደዱት ዛሬ እርሰዎ በየመድረኩ ከሚያነሷቸው ቁም ነገሮች ተመሳሳይ ሀሳቦች በማንሳታቸውና ከሙሰኛ ባለስልጣናቱ ኢ-ፍትሀዊ አገዛዝ እምቢኝ በማለታቸው ብቻ ነው።


በመሆኑም እርስዎ የአገሪቱ ከፍተኛው ባለስልጣን ባይሆኑና ዛሬ የያዙት አቋም ይዘው በአንዱ የመንግሥት መ/ቤት ሠራተኛ ሆነው ተቀጥረው በሚሠሩበት መ/ቤት ለስሙ ብቻ የ”መልካም አስተዳደር ችግርና ጥልቅ ተሀድሶ” ስብሰባ ተብሎ በተጠራ ጉባኤ ላይ ልክ ዛሬ ከሥራቸው የተፈናቀሉት የመንግሥት ሠራተኞች እንዳደረጉት ሁሉ የዛሬውን አቋምዎ ይዘው ቢሳተፉ ኖሮ እርስዎም ያለምንም ጥርጥር ከሥራዎ የመባረር/የመፈናቀል እድል ሊያጋጥምዎ ይችል እንደነበር ሊጠራጠሩ አይገባም። ስለሆነም እነዚህ ከአድርባይነት የጸዱ ትክክለኛና ቅን የመንግሥት ሠራተኞች ለተያያዙት አዲስ ሥርዓት ስምረት ሲሉ ሊታደጓቸው ይገባል። እንደእኔ ሙስና የአድሏዊ አሠራር ውጤት ሲሆን አድሏዊ አሠራር ደግሞ የመልካም አስተዳደር ችግር ውጤት ይሆናል። በአንጻሩ የመልካም አስተዳደር ቸግር ደግሞ የመልካም አስተዳዳሪ አለመኖር (አለመፍጠር/አለመምረጥ/አለመሾም) ችግር ውጤት ነው። የመልካም አስተዳዳሪ ችግር ደግሞ የአስተዳዳሪዎች/ተሸሚዎች መምረጫ መስፈርቶች ችግር ውጤት ይሆናል። ስለሆነም በአረጀና በአፈጀ ችግርና አስተሳሰብ የተተበተበና የቆሸሸን አስተዳዳሪ ከሥራ ብቃት፣ ከተገቢ ት/ደረጃ፣ ከበቂ የሥራ ልምድ፣ ከተቋሙ ህ/ሰብ ተቀባይነት፣ ከአገራዊ ራዕይ ወዘተ ውጭ በጎሳና ፖለቲካ ኔትዎርክ መርጠን/ሹመን የመልካም አስተዳደር ችግርና ጥልቅ ተሀድሶ ያለህ በሚል ብልሹ ስብሰባ ጊዜ ማጥፋት ከአሁን በኋላ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማብቃት አለበት። የህዝብንና የመንግሥትን አደራ ተቀብለው በተገቢው ሁኔታ በብቃት ማስተናገድ የሚችሉ አያሌ ባለሙያ ዜጎች ባልጠፉበት አገር ለጎሳና ለፖለቲካ ቡድን ኔትዎርክ ጥቅም ሲባል ብቻ አገር የምትታመስበት ምክኒያት መኖር እንደሌለበት ሊሠመርበት ይገባል። ከህዝብና መንግሥት የተሰጠውንና የተጣለበትን አደራና ኃላፊነት መወጣት ያልቻለውንና በህግ አግባብ መሥራት ያቃተውን ኃላፊ ለመጠገን ሲባል ብልሹ አሠራርና ቡድንተኛ አስተሳሰብ ሙጥኝ ያለውን ባለስልጣን እንደ ሳር ቤት እያደስን ለማዝገም ከአሁን በኋላ ጊዜ ማጥፋት የለብንም። ያረጀና የፈጀ አስተሳሰብ ባለቤት የሆነው የሥራ መሪ በመጣበት እግሩ ያመጣው ኃይል እስከ ጡረታ እድሜው ሳይጠብቅ በጊዜ ሊሸኘው ይገባል የሚል እምነት አለኝ።


እንደእኔ የሚዳሰሱ፣ የመጨበጡና በአደባባይ የሚታዩና በየቀኑ ለ24 ሰዓታት ተለይተውን ለማያውቁ ችግሮች በጀት መድቦ ምርምር ማድረግ አስፈላጊ ነው ብዬ አላስብም። እናም በአገራችን ተሀድሶ፣ ጥልቅ ተሀድሶ፣ የመልካም አስተዳደር ችግር ወዘተ በሚሉ ሰበብ አስባብ ስብሰባዎች ጥሪ የተነሳ ከአድርባይነት ጸድተው ለአገራቸውና ለህዝባቸው በመቆርቆር ሙሰኛ ባለስልጣናትንና ብልሹ አሠራራቸውን በታዛቢዎች ፊት በአደባባይ በማጋለጣቸው አያሌ የመንግሥት ሠራተኞች ከህግ አግባብ ውጭ ከሥራቸው ታግደዋል፣ ተበርረዋል፣ ከደረጃ ዝቅ ተደርገዋል። የመልካም አስተዳደር ችግርና በጥልቅ ተሀድሶ ስብሰባ ምክኒያት በእነዚህ ቅን የመንግሥት ሠራተኞች ላይ የተወሰደውና በሰበብ አስባቡ እየተወሰዱ ያሉ እነዚህ ኢ-ፍትሀዊና ኢ-ዲሞክራሲያዊ ርምጃዎች በራሳቸው በሠራተኞቹ፣ በሌሎች ቀሪ የመንግሥት ሠራተኞችና ዜጎች ላይ እያስከተሏቸው ካሉ ችግሮችና ከሚፈጥሯቸው አሉታዊ ተጽዕኖዎች የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል። እነዚህም፡-


• የአገር ጉዳይ የእኔ ጉዳይ ነው የሚል ዜጋ ማሳጣትን፣
• በመንግሥትና በመንግሥት ባለስልጣናት ላይ እምነት ማጣትን፣
• ግልጽነት፣ አሳታፊነት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያለው አሠራር ማጥፋትን፣
• ለምንም ነገር ግድ የሌለውና አገራዊ ስሜቱ የላሸቀ ዜጋ ማፍራትን፣
• አድርባይነትን ማንገስንና ዜጎችን ተጠራጣሪ ማድረግን፣
• በተመሳሳይ ስብሰባዎች ላይ አለመሳተፍን፣ ከተሳተፉም አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ሀሳብ አለማመንጨትን፣
• የዜጎችን ሞራል መገደብንና የሥራ ተነሳሽነት ማሳጣትን፣
• የዜጎችን ዲሞክራሲያዊ መብቶች መጨፍለቅንና እንዳያስከብሩ ማሸማቀቅን፣
• ዜጎችን በስጋትና በፍርሀት ማኖርና ፈሪ ዜጋ መፍጠርን፣
• የመልካም አስተዳደር ችግርን አሜን ብሎ የሚቀበል ዜጋ ማበራከትን፣
• ሙስናና ኢፍትሀዊነት እንዲነግስ ማበረታታትን፣
• የመንግሥትና ህዝብ ሆድና ጀርባ መሆንን፣ እና

• በግልጽነትና አሳታፊነት መጥፋት የተነሳ የሥራ ቡድን ይጠፋና የሙስና፣ የዘርና የፖለቲካ ቡድን መንገስን እና የመሳሰሉት ናቸው። ዛሬ በአገራችን እየሆነ ያለውም ይህው ስለሆነ ሊታሰብበት የሚገባ አቢይ ጉዳይ ነው። ስብሰባዎቹም ከላይ በተገለጸው መልኩ ቅን የመንግሥት ሠራተኞችን ከማጥመድና ከነቤተሰቦቻቸው ለከፋ ችግር ከመዳረግ ባለፈ ይህ ነው የሚባል ፋይዳ አላስገኘም። ለዚህም ነው ሁለቴ ተሀድሶ ተብሎ ለዓመታት ለውጥ ባለመምጣቱ/ የመልክም አስተዳደር ችግሩ እየባሰበት በመሄዱ በ3ኛው “ጥልቅ” የሚል ታርጋ ለመጨመር የተገደድነው። በመልካም አስተዳደር ችግሬ ላይ በጥልቅ ተወያዩ ብሎ መልሶ ሰበብ አስባብ ፈልጎ ዜጎችን አናግሮ መክሰሱና ከህግ አግባብ ውጭ ማስቀጣቱ ከአንድ መንግሥት አይጠበቅም። የዚህ ዓይነት አካሄድ መንግሠትን ከህዝብ በእጅጉ ከማራራቁም በላይ ከባድ ዋጋም ሊያስከፍለው የሚችል ነው። እያስከፈለውም ነውና በጥልቅ ሊታሰብበት ይገባል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
67 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 135 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us