ለውጤታማነት አጉል ምክንያት ወይስ አማራጭ?

Wednesday, 13 June 2018 13:38

 

አረጋ ይርዳው (ዶ/ር)

ማንኛውንም ሥራ ጀምሮ ፍጻሜ ለማድረስ ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች ሊኖሩ ግድ ይላል። ግብዓት ሲባል ከብዙ በጥቂቱ ዕቅድን፣ ገንዘብን፣ ቁሳቁስን፣ ዕውቀትን፣ ጊዜን አዎ! ልድገመው በእርግጠኝነት "ጊዜ"ንም ያካትታል። ግብአቶችን ወቅቱን ወይም ሰዓቱን አውቆ በቅደም ተከተላቸው የሥራው አካል በማድረግ እውቀትን ተጠቅሞ ማቀናጀት ሲቻል የተፈለገው ውጤት፣ በተፈለገው ጊዜ፣ በታቀደለት በጀት ወይም ወጭ በዕቅድ መሠረት ሲፈጸም ስኬታማነትን ያስገኛል። በሌላ መልኩ ከግብዓቶቹ አንዱ ወይም ጥቂቶቹ በተፈለገው መጠን፣ ጊዜና ዓይነት በማይገኙበት ጊዜ፣ ሥራው በታቀደለት ጊዜ፣ በተመጠነው በጀት፣ በታቀደው የጥራት ይዘት እንዳይፈፀም ሊያደርግ ስለሚችል ስኬታማነትን አያስገኝም፣ ኪሳራንም ያመጣል።

ተምረናል ብለን በየከተማው ተሰማርተን የከተሜውን ሥራ የምንሠራ ሁሉ፣ በሀገራችን አርሶ አደር ወይም ገበሬ የአሠራር ዘይቤና ጥበብ ውጤት በተገኘ እርዳታ ታግዘን መሀንዲሶች፣ አስተዳዳሪዎች፣ የኩባንያ መሪዎች ወዘተ መሆናችንን ሳንዘነጋ በሺዎች በሚቆጠሩ ዓመታት በሥራ ላይ የዋለን የሥራ ባህል ብናጤን ከገበሬው ብዙ መማር እንችል ነበር። ለነገሩ ጥሎብን ወይም የስልጣኔ ምልክት መስሎ ስለታየን የእገሌ አገር "ተሞክሮ" በማለት መደነቋቆርን አጥብቀን ይዘናል። ነቢይ በሀገሩ . . . ሆኖብን።

አንድ ገበሬ የእርሻ ሥራውን ለማከናወን በሬዎች፣ ሞፈር፣ ቀምበር፣ ጅራፍ፣ ዘር የመሳሰሉት እንደሚያስፈልጉት ያውቃል። በተጨማሪም ተፈጥሮ የሚለግሰውን ውሀ (ዝናብ) እና የፀሐይ ብርሀንና ሙቀትም ለእርሻው እንደሚያስፈልገው ያውቃል። ከሁሉም በላይ ግን እኛ ከተሜዎች ብዙም የማንጨነቅለት "ጊዜ" የተባለው ግብዓትን በዕቅዱ ውስጥ ያስገባል። እርሻ የሚጀመረው በዚህ ወር ከማርያም፣ ከሚካኤል ወዘተ ቀን በኋላ ወይም በፊት ነው ብሎ ዕቅዱን (እኛ ከተሜዎች በቁልምጫ ስትራተጂ፣ ጥናት፣ የቅርብ የሩቅ ዕቅድ እያልን የምናቆለጳጵሰውን) ብዙ ወረቀትና ቀለም ሳይጨርስ ያወጣል። ከዚያም በየቀኑ ምን ማድረግ እንዳለበት ከማረስ ጀምሮ እስከ ውቂያና አዝመራን መክተት፣ አልፎም ወደገበያ ምርቱን መውሰድን ያካተተ ያልተጻፈ ነገር ግን በቅብብሎሽ የዳበረ ክህሎቱን በመጠቀም ሥራውን ያከናውናል።

ከላይ የተጠቀሰውን ተግባር አርሶ አደሩ ወይመ ገበሬው ሲያከናውን ባቀደው መሠረት ግብአቶቹ ላይመቻቹለት ይችላሉ። ለምሳሌ አንድ ዓይነት የእህል ዘር ዘርቶ ዝናብ ማጠሩን ሲያውቅ ያካበተውን ልምድ በመጠቀም እርሻውን እንደገና በማረስ ወይም በመገልበጥ ሌላ የእህል ዘር በመዝራት ወቅቱ እንዳያልፍበትና ምርት እንዳያጣ አቅሙ እስከፈቀደለት ድረስ በመጣር ውጤታማ ይሆናል። በዚህ ተግባሩ የዝናብ እጥረት ስላጋጠመ ምንም ሳያደርግ ተቀምጦ፣ ለምን እንደተቀመጠና ምርት እንዳላመረተ አጉል "ምክንያት" (excuse) በመደርደር ጊዜውን አያጠፋም። ላድርግ ቢልም ከታክስ የተሰበሰበ ብር የሚሰጠው የለም፣ ኑሮው ውስን ስለሆነ እሱም ቤተሰቡም ይቸገራሉ። ከእሱ ታክስ ወይም ታክስ የምትፈልገው ሀገርም፣ ታክስ በመሰብሰብ ፋንታ እሱን ወደ መርዳት ልትሠማራ ትችላለች።

አርሶ አደሩ ዝናብ አጠረ ብሎ አጉል "ምክንያት" በመደርደር ፋንታ፣ በአስቸኳይ ወደ "አማራጭ" መንገድ (Option) ፍለጋ መሄዱ እንደፈለገው ባይሆንም እንኳ መጠነኛ ምርት በማግኘት ህይወቱን ይመራል። የሀገራችን አርሶ አደሮች ያላቸውን ውሱን የእርሻ መገልገያ፣ ዘር ወዘተ በመጠቀም ጊዜንና አማራጭ የሥራ እርምጃዎችን ሳይዘገዩ ተጣድፈው በመፈጸም ብዙ አስተምረውናል።

ከላይ የጠቃቀስኩት ሁናቴ ወደፈለኩት ፍሬ ነገር ይወስደኛል። ይኸውም በስንፍና፣ በግዴለሽነት፣ ባለማወቅም ሆነ በማወቅ አጉል "ምክንያት"ን (excuse) በመደርደር ለምን አንድ የታቀደ ሥራ እንዳልተሠራ ወይም ፍጻሜ ላይ እንዳልደረሰ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ውድቀትን ከማስተዳደር (Managing excuses) ይልቅ አማራጮችን በዕቅድ በማስገባት ወይም ችግር ሲፈጠር ፈጥኖ መንገድ በመፈለግ ውጤት የማግኘት አሠራርን (Managing Options) የተሻለ መሆኑ ሊሠመርበት ይገባል። ይህን ከአጉል "ምክንያት" ይልቅ "አማራጭ" ላይ አተኩሮ በመሥራት ውጤታማ መሆን ሲለመድ ብዙ ውጤታማ ያለመሆን ችግሮችን ሊያስወግድልን ይችላል። ለምሳሌ:-

- አዲስ አበባ ውስጥ ስብሰባ በተባለው ሰዓት ያለመጀመር ምክንያት በአብዛኛው የትራፊክ መጨናነቅ እንደሆነ ሁሉም ይዘምራል። በቂ ጊዜ መስጠት፣ ትራፊክ ክፍት በሆነበት ጊዜ ስብሰባ እንዲጀመር ማድረግ፣ የጉዞ መስመርን መቀየር፣ ለስብሰባ የሚያስፈልጉት ግብአቶች ሁሉ ከስብሰባው በፊት መዘጋጀታቸውን ማረጋገጥ ወዘተ ለስብሰባ ዘግይቶ መጀመር "ምክንያት" ሲፈልጉ ጊዜ ከማጥፋት ይልቅ "አማራጭ"ን በመተግበር ውጤታማ መሆን ይቻላል።

ከስብሰባ መቅረት - እጅግ በጣም በተደጋገመና አሰልቺ በሆነ የስብሰባ ጋጋታ፣ ከፍተኛ ባለስልጣን እንደሚኖር በጥሪ ወረቀቱ ይገለጽና ለዚያ ስብሰባ ለተባለው ባለስልጣን በሚመጥን መልኩ የስብሰባ ነጥቦች ይዘው የሚገኙ ታዳሚዎች፣ የክብር እንግዳው ወይም ባለስልጣኑ ባለመገኘታቸው "እጅግ ከፍተኛና ያልታሰበ ጉዳይ፣ ስብሰባ ወዘተ ስላጋጠማቸው ሊገኙ ባለመቻላቸው ይቅርታ ጠይቀዋል፣ መልእክት ልከዋል ወዘተ" ይባልና ስብሰባው በአሉታዊ የስብሰባ ድባብ ተከቦ ይጀመራል። ጉዳዩ ባለስልጣኑን የሚያስፈልግ ካልሆነና ከሳቸው በታች ባለ ባለሥልጣን ወይም ተወካይ ማካሄድ የሚችል ከሆነ መጀመሪያውኑ ለተወካዩ ሥራውን መስጠቱ ይተሻለ አማራጭ (Option) ስለሆነ ይህን ማድረግ ሲቻል አጉል "ምክንያት"ን (excuse) ማቅረቡ ለታዳሚው ድርብ በደል ይሆናል።

- በተለያዩ የግልም ሆነ የመንግሥት ተቋማት የሚገኙ የሥራ ክፍሎች ከ"አማራጭ" ፍለጋ ይልቅ "ምክንያት" በመደርደር ሥራን ሲያደናቅፉ በብዛት ይስተዋላሉ። ለምሳሌ በአንድ ኩባንያ የፋይናንስ ክፍልን የሚመራ ኃላፊ ኩባንያው ለደንበኞቹ በዱቤ ምርቶች ሸጦ ብዙ ያልተሰበሰበ ገንዘብ (receivables) ከደንበኞቹ በወቅቱ በስንፍናው ባለመሰብሰቡ ኩባንያው የጥሬ ገንዘብ (cash) እጥረት አጋጥሞት ደመወዝ ለመክፈልና አስፈላጊ ግዥ ለመፈጽም ቢቸገር፣ እጥረቱ ወይም ችግሩ የተፈጠረው ገንዘቡ በደንበኞች እጅ ስለሆነና በተሰብሳቢነት ተመዝግቦ ስላልተከፈለ ነው የሚል አጉል "ምክንያት"ን (excuse) እየደረደረ የ"ምክንያት" ደርዳሪነት ወይም አስተዳዳሪነት ሥራ (Managing excuses) የሚተገብር ከሆነ ኩባንያውን እየጐዳው መሆኑን ሊያውቅ ይገባል። ይኸው ኃላፊ ለተጠቀሱት ክፍያዎች ጥሬ ገንዘብ ከሌለውና ተሰብሳቢዎችን አፋጥኖ ለማግኘት የማይችል ከሆነ አማራጭ (Option) መፈለግ ያስፈልገዋል። ለመሰብሰብ ያጋጠመውን ችግር የሚፈታበትን መንገድ ቀይሶ ለጊዜው ከፊቱ ለተጋረጠው የደመወዝና የግብዓት መግዣ የገንዘብ ችግር አማራጮች (Options) ለአለቆቹ ይዞ መቅረብ ይኖርበታል። የፋይናንስ ክፍል መሪ መሆኑም ይህን እንዲተገብር ግድ ይለዋል።

- አንድ ተቋም በምርት የማምረት ጠባዩ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱ የማምረቻ መሣሪያዎቹ ቢቆሙ ምርቱ ላይ ችግር የሚፈጥር ከሆነ፣ ምርታማነቱ ወይም የምርቱ ጥራትና ብዛት ከዕቅድ በታች የሆነበትን ሁናቴ ለመግለጽ አጉል "ምክንያት" ሲደረድሩና ሲፈጥሩ ጊዜ ከማጥፋት፣ መጀመሪያውኑ የኤሌክትሪክ ኃይል ባለመኖሩ ሊበላሹ የሚችሉ የሥራ ክፍሎችን በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ሊያሠራ የሚችል ተጠባባቂ ኃይል (standby generators) እንዲኖር የማድረግ አማራጭ (Options) ሥራ ከምክንያት ይልቅ አማራጭን ማስተዳደር (Managing Options rather than excuses) ስለሚሆን አዎንታዊ ውጤትን ያመጣል።

በየሠርግ ዝግጅቱ ሙሽሮች እስከሚገቡ እየተባለ በሰዓቱ ተገኝቶ ከዚያም በኋላ ሙሽሮቹ በመኪና ትራፊክ መጨናነቅ "ምክንያት" በመዘግየታቸው በይፋ ወይም በሹክሹክታ እየተነጋገሩ ለሰዓታት (ፊት ለፊቱ የተቀመጠውን መጠጥ መጠጣት እያማረው ሳይቀምስ) የጠበቀው የሠርግ ታዳሚ አንድም መጠጣት እንዲጀምር ካልሆነም ሙሽሮቹ አስቀድመው ገብተው እንግዳ እንዲቀበሉ የማድረግ አዲስ "አማራጭ" መፍጠር ሁሉም ሰው እያማረረ ነገር ግን ይባስ ብሎ በመሸጋገር የሚገኝ ዝግጅት ቢለወጥ ቀልጣፋና ሁሉንም ታዳሚ የሚያስደስት ሠርግ ሊሆን ይችላል።

አዲስ አበባ ከተማችን ብዙ የመሪዎች ስብሰባ ታካሂዳለች። ይህ መታደል ነው፣ ይገባታልም። የመሪዎች ስብሰባ እንዳለ በመጥቀስ ለአሽከርካሪዎች የተከለከሉ መንገዶች በመግለጽ በአኳያው አማራጭ መንገዶችን አሽከርካሪዎች እንዲጠቀሙ በማስታወቂያ ይነገራል። ይህ ጥሩ ነው። ይህን ማስታወቂያ ሰምቶ አንድ ሠራተኛ ከሥራ ላለመዘግየት፣ ከእነአካቴው ላለመቅረት ተለዋጭ መንገዶች አጥንቶ በሥራ ገበታው ለመገኘት "አማራጭ" መምረጥን ትቶ፣ ከሥራ የዘገየንበትን ወይም የቀረንበትን አጉል "ምክንያት" ላለቃው፣ ማስረዳት ጥቅም የለውም።

በባህላዊ መንገድ የተዘጋጀ ኮሶን ለማዳን የሚጠጣ የኮሶ መድኃኒት በተፈጥሮው መራራ ነው። ነገር ግን በሽታውን ይፈውሳል ከተባለ መራራ ስለሆነ አልጠጣም ያለ በበሽታው እንደሚጠቃና ለከፍተኛ ጉዳት ሊዳርገው እንደሚችል ያውቃል። ስለሆነም መራራውን ኮሶ ይጠጣል።

የሥራ "አማራጭ"ን ለመጠቀም ማሰብና መጨነቅን የመሳሰሉ መራራ ችግሮች ሊኖሩት ይችላል። ነገር ግን ለአማራጭ ጥረት ማድረግ (እንደ ኮሶው የመረረ ቢሆንም) በተሠማራንበት ሥራ ውጤት የሚያስገኝ ፈውስ ከሆነ ልንለምደው ይገባል።

ከላይ የተጠቀሱት ጥቂት ምሳሌዎች በጠቋሚነት እንዲያገለግሉ የጠቃቀስኳቸው ሲሆኑ በተመሳሳይ ብዙ ሁኔታዎችን በተለያዩ የሥራ ረድፎች መግለጽ ይቻላል። ወደ ርዕሴ ስመለስ ለምክንያት ፈጠራ ጊዜ አባክነን ምክንያትን ተጠቅመን ሥራን ውጤታማ ካለማድረግ ይልቅ አማራጮችን በመፈለግ ውጤታማ ለመሆን ሥራን መምራት በሰፊው ቢለመድ የተሻለ ነው። Better Manage options rather than excuses.

የሥራ መሪዎች ሠራተኞች ለተሰጣቸው ሥራ አማራጭን እንደ አስፈላጊ ሂደት መጠቀም እንዲችሉ ማበረታታት ይጠበቅባቸዋል። በአኳያው ባልሆነና ተቀባይነት በሌለው ምክንያት ሥራ እንዳይደናቀፍ ማድረግም ይጠበቅባቸዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
153 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1095 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us