ሊነጋጋ ሲል ጨለምለም ያለ ይመስላል!

Wednesday, 20 June 2018 13:04

ከተፈሪ ብዙአየሁ ዶርሲስ (ዶ/ር)

ይህች ሀገር የትላንቷ ኢትዮጵያ ቁመና እንደሌላት የተጀመሩ ለዉጦች ፍጥነት ያስገርመኛል። ትላልቅ ሀገራዊ ለውጦችን በረጅም ርቀት እየናፈቅን ሳናገኛቸዉ ለነበርን እጆቻችንን በአፋችን ላይ እንድንጭን የሚያደርጉን ታላላቅ አይደፈሬ ለዉጦችን እያየን ሰለሆነ ብንደነቅ አይፈረድብንም። ከዚህ የተነሳ ጅማሬያቸዉ ያማረ እና የሚያበረታቱ ልዩነቶችን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ድባብ እያስተዋሉ እንደሆነ ወዳጆቼ ነግረዉኛል።በዚህ ዙሪያ ሶስት ዓይነት ወዳጆች ገጥመዉኛል። ለዛሬ እስቲ ከሶስተኛዉ ቡድን ሃሳብ ልነሳ።

ይህ ሶስተኛዉ ቡድን በተለይ ባለፈዉ ጊዜ ጠ/ሚኒስትሩ ‹ታሪካዊ ስራ ሰርተዋል!› ይላል። እጅግ እየፈነደቁም ከደስታቸዉም ብዛት የሚያደርጉትን እስከማጣት የደረሱት በቤተመንግስታቸዉ ያደረጉትን የአቶ አንዳርጋቸዉ ጽጌን አቀባበል፤ ግብጽ ሄደዉ እስረኞችን በመፍታት እና የቀደሙ የፖለቲካ አጋሮቻቸዉን ኦቦ ዮናታን ድቢሳ እና ኮሎኔል አበበ ገረሱን ማምጣታቸዉን፤ በዲፕሎማሲው መስክ የተባበበሩት አረብ ኢሚሬት ልዑልን ልብ እና መንግስታቸዉን በመማረክ በልዩነት የሃገራቸዉን ፋይናንስ ለመደጎም ያስመዘገቡአቸዉን የጀግንት ስራ ያወሳሉ። በዚህ ሰዓት ‹ምነዉ እንደ ግብጽ እስረኞች ሆነን ጠ/ሚኒስትሩን ብናገኛቸዉ እና ጭምቅ አድርገን መሳም ብቻ አይደለም ከሰሩት ‹ጀግንነት› የተነሳ ዋጥ አድርገን በልባችን ብናስቀራቸዉ› አሉኝ። ‹በኢትዮጵያ ታሪክ አይተንም ሰምተንም የማናዉቀዉን አዲስ ልምምድ አሳዩን› ይላሉ። ምናልባትም ‹ኢትዮጵያን ለመዋጀት ከእግዚአብሔር የተሰጡን ሳይሆኑ አይቀሩም› በማለት የቀደመዉ የኢትዮጵያ ትዉልድ ይህንን ድርጊት በእዉን ስለማያዉቀዉም በዚህኛዉ ትዉልድ በመገኘታችን ታድለናል ይላሉ። የትላንቶቹ ልሂቃኖቻችን በቀልን፤ ቁርሾን፤ እና መጠላለፍን፤ ሌብነትን ያስተማሩን ዓይነት በተቃራኒ በማድረጋቸዉ በግላቸዉ ሊወደሱ ይገባል የሚል አመለካከት አላቸዉ። እርሳቸዉን በወለደዉ፤ በራሳቸዉ ፓርቲ፤ እርሳቸዉ ዛሬ በሚመሩት መንግስት አሸባሪ ተብለዉ በሌሉበት በሀገር ክህደት ሞት የተፈረደባቸዉን ኮሎኔል አበበ ገረሱን፤ የእነ አቶ ሰለሞን ጢሞን የኦሮሚያ ሞግዚት አስተዳደር በግልጽ የተቃወሙትን ኦቦ ዮናታን ዲቢሳን፤ እርሳቸዉ በሚሳፈሩበት አዉሮፕላን አጠገባቸዉ አስቀምጠዉ ሲያመጡአቸዉ በብዙ አጀብ እና ዋጋ ከየመን አስመጥተዉ የሞት ፍርድ የፈረዱባቸዉን አቶ አንዳርጋቸዉ ጽጌን፤ ከእስር ፈተዉ በክብር በv8 መኪና ወደ ቤተመንግስት ወስደዉ አቅፈዉ በመሳም አቀባበል በማድረግ የማንም በጎ ፈቃድ እና ይሁንታ ወይንም ትዕዛዝ ሳይሆን የጠ/ሚኒስትሩ የግል ዉሳኔ መሆን አለበት ይላሉ ወዳጆቼ። ማስፈታት የቄሮ-ፋኖ ትግል የወለደዉ የኦሮማራዉ ፕሮጀክት ሂደት ሊሆን ይችላል። በጎ አቀባበል እና አቅፎ መሳም ግን የግል ዉሳኔና ለለዉጥ ቁርጠኝነት ማሳያ አልፎም ታሪካዊ ትምህርት ነዉ ብለዉኛል። ‹ነገ ኢትዮጵያን ለመምራት ያሰፈሰፋችሁ ፖለቲከኞች ከዚህ በጎ ምግባር ተማሩ› ይላሉ ወዳጆቼ። ይህ ቡድን እንዲህ ብለህ ጻፍ አለኝ፡- ‹እናንተ ትላንት ከትጥቅ ትግል በኋላ እንቆምለታለን ያላችሁት ህዝብ ማንነት ስታወርዱ ሲያይ የተቃወማችሁን አካል በመፈረጅ፤ በፖለቲካ አቋማቸዉ ብቻ የሞት ፍርድ የፈረዳችሁባቸዉን፤ በእስር ቤቶቻችሁ ያሰቃያችኋቸዉን አይዞአችሁ እኛ ዛሬ እናንተን ጡረታ እናስወጣለን፤ ይቅርታን እናስቀድማለን፤ ከቁርሾ የፀዳች የነገይቷን ኢትዮጵያ ለማስረከብ እንጥራለን እንጅ አንበቀልም› በማለት ሃሳባቸዉን እንደካፍል ነግረዉኛል። ከዚህ የተነሳ ‹በግሉ ዉሳኔ ምሳሌ የሚሆን ተግባር የፈጸመ መሪ ትግላችን ስላፈራ ከትላንት ዛሬ ይሻለናል!› ብለዉኛል።

በሌላ በኩል የአንዳንዶችን በቅርብ እንደ ጥቁር ገበያዉ ዶላር በጥቂት በጥቂቱ እየመነዘሩ መፈታት የአዲሱ ቲም ጠንካራ ተጋድሎ አለበት ብለዉ ያምናሉ። ‹ያም ሆነ ይህ› አለኝ ይህ ቡድን በልዩነታቸዉ ተስማምተዉ ‹የአዲሱን ቲም ጥንካሬ እስረኞችን በመፍታት አንለካም፣ ይህ ቀድሞ በኢህአዴግ ግምገማ ላይ የተወሰነ ስለሆነ›። ‹ይልቁንስ› ይላል ይህ ቡድን ‹የአሸባሪነት አዋጁ ሰይሻሻል በህግ ማዕቀፍ ዉስጥ የተፈረጁትን ግለሰቦችን እና ሚዲያዎች ምህረት ማድረግ ለአዲሱ ቲም ድፍረት የሰጠ ማነዉ?› ቀዳሚዎቻቸዉን ያስደነገጠ፤ ደጋፊዎቻቸዉን ያስፈነደቀ፤ በጥርጣሬ የሚያዩአቸዉን ያስተዛዘበ ዉሳኔ ነዉ› በማለት ‹ቀጥሎ ምን ይመጣ ይሆን?› አሉኝ።

ሁለተኛዉ ቡድን የጠ/ሚኒስትሩን እና የአዲሱ ቲም (ቲም ለማ ማለትም፡- ለማ-ገዱ፤ አብይ-ደመቀ-እንደ አወላለዳቸዉ) ጥንካሬን የሚያመላክት የዲፕሎማሲ ክህሎት የኢኮኖሚ ሪፎርም፤ የፖለቲካ ጽዳት እንዳለ ሆኖ ከአኩራፊዉ ቡድን የሚመጣዉን ስልታዊ ጫና ለመቋቋም ጥሩ ቁመና ላይ አይደሉም በማለት ምክራቸዉን መለገስ ይፈልጋሉ። ‹መቼም ቢሆን!› ይላሉ ምክራቸዉን ሲለግሱ፡- ‹የለመደዉ ዉሻ እንኳን ጥቅም ሲጓደልበት ነካሽ ይሆናል› ይላሉ። የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ስናጤን በየቦታዉ በተበታተነ እና በተደራጀ በሚመስል ሁኔታ ግጭቶች ይታያሉ። ከእነዚህ ግጭቶች በስተጀርባ ያለዉን አካል ለመገመት አዲሱን ቲም የሚጠፋዉ አይመስለንም። ነገር ግን ይህን አካል በሰለጠነ መልኩ ለመቋቋም እየተሰራ ያለዉ ስራ የተዘናጋ ይመስላል። በዚህ ሰዓት የኢህዴግ ጥርነፋ እየሰራ በሌለበት ሁኔታ ዉስጥ፤ የየክልል አመራርና ካድሬዎች፤ የጸጥታ ሃይሎች በሶስት ዓመቱ እልህ አስጨራሽ ትግል ዉስጥ በመዳከሙ፤ ሁሉም በተፈራራበት ሁኔታ፤ የሰላም ማስከበር ሃላፊነቱን የሚወስድ አካል መኖር ያለበት ወሳኝ ጊዜ እና ሁኔታ ዉስጥ ያለን ይመስላል አሉኝ።

ምክንያቱም እስረኞች ተፈትዋል ፡ የፖለቲካ ነጻነቱ ከሞላ-ጎደል ተረጋግጧል። በተጨማሪም የየእለት ኑሮን ለማከናወን ሰዎች በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ተራ ግጭቶች አይኖሩም ተብለዉ ስለማይገመቱ እነዚህን ተራ ግጭቶች በመጠቀም መስመራቸዉን ለማሳየት አሰፍስፈዉ የሚጠባበቁ፡ የተመደቡ አኩራፊ አካላት በየቦታዉ መኖራቸዉ የታወቀ ነዉ። በዚህ ሰዓት ሁሉም አካላት ከላይ መመሪያን ጠበቂ በሆነበት ደረጃ ዉስት-ዉስጡን የሚሰራ አካል ደግሞ እድል አግኝቶ የተጀመረዉን ለዉጥ ባይቀለብስ እንኳን በህዝብ መካከል ጠበሳን ጥሎ የሚያልፍ ሴራ እንደሚሰራ ታዉቆ የመደራጀት ስራዉ ላይ በፍጥነት መረባረብ የግድ ነዉ ይላሉ ወዳጆቼ። በ27 ዓመታቱ የኢትዮጵያ ታሪክ በዋናነት ህወአት-ኢህአዴግ፤ እና የሰነፍ ተማሪ ኩረጃ የሆኑት የቀድሞዎቹ ኦህዴድ-ኢህአዴግ፤ ብአዴን-ኢህአዴግ፤ ደኢህዴን-ኢህአዴግ እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች እና በዛሬ ቁመና ላይ ያሉ የሃይማት ተቋማትም ሁሉ ወደ እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ህዝብ ጓዳ ይዘዉ ያልገቡት የፖለቲካ ቁርሾ፤ የሰበዓዊ መብት መደፈር፤ የኢኮኖሚ ሰለባነት የለም። ከዚህ የተነሳ በስራዉ ከእነርሱ ጋር የነበረ በልቡ ግን በእነርሱ ወገን ያልሆነዉም በወገኑ ላይ ከተደረገበት የተነሳ ያልከፋዉ የለም። ሊነጋጋ ሲል ጨለምለም ማለቱ ስለማይቀር በጥንቃቄ መራመዱ የበለጠ ዉጤታማ ያደርጋል።

በማዕከል ደረጃ ማለትም ከጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ ጀምሮ በሁለቱ የፖለቲካ ምህዳሩ ዘዋሪዎች ብአዴን እና ኦህዴድ የሚመሩ ክልሎች ደረጃ በይቅርታ እና ተቻችለን አብረን እንስራ ስሜት የተፈታ ነገር ቢታይም እታች በዞን በወረዳ እንዲሁም የለዉጡ አካል ለመሆን ፈቃደኝነታቸዉ እምብዛም ባልሆኑት ክልሎች የተፈታ ነገር ባለመኖሩ ከላይ የተጀመረዉን ለዉጥ እታች እስኪወርድላቸዉ እየተጠባበቁ ይመስለናል። ሁሉንም አካላት ያሳተፈ በጥንቃቄ ላይ የተመሰረተ የሠላም እና የመግባባት ኮንፈረንስ የሚያስፈልጉበት ደረጃ ላይ ያለን ይመስለናል አሉኝ። የሠላም የመቻቻል ኮንፈረንሱ መነሻም የተፈቱትን ከማስተዋወቅና እና የተጀመሩ ለዉጦችን ታሳቢ ያደረገ ቢሆን ይህች ሀገር እስከሚቀጥለዉ ምርጫ ድረስ የተረጋጋች ትሆናለች ብለን እናምናለን ይላሉ ወዳጆቼ። ተስፋ እንዳለቸዉም ነግረዉኛል ልበል?

አንደኛዉ ቡድን ደግሞ እስከነአካቴዉ ‹ይህ የኦቦ ለማ ቲም ራሱን ችሎ አልቆመም› ይላል። ምክንያቱን ሲያስቀምጥ አኩራፊዉ ወገን አዘናግቶ ያለ የሌለ ሃይሉን አስተባብሮ ዘርፈ ብዙ የማስመለስ ሙከራ ሊያደርግ የተዘጋጀ የሚመስል ምልክቶች እያየን ስለሆነ የማይጠበቁ ጉዳቶች ሊከሰቱ ይችላሉ አሉኝ። ‹ለምሳሌ መቐለ ላይ የነበረዉ ቁልጭ ያለዉ መልእክት ኢህአዴግ በሁለት አንጃ ስር መዉደቁን ያመላክታል› ይላል ይህ ቡድን። አዲሱ ቲም ከአንድ አቅጣጫ ሆኖ ‹እኛ የኢህአዴግ መርህን ተከትለን እየሰራን እንጅ ምንም አዲስ ነገር አልሰራንም። ይልቁንም በጥልቅ ግምገማችን የወሰንናቸዉን እየመነዘርን በመተግበር ላይ እንገኛለን› ሲል በጡረታ የተገለለዉ ቡድን ደግሞ ከማዶ ሆኖ ‹የፔይሮል ጡረተኛ እንጅ የትግል ጡረተኛ የለም፤ ቀደምት ታጋዮችን ያገለለ ተልእኮም አንቀበልም! እያለ ማስፈራራቱን ቀጥሏል። የትግል ጡረተኛ የለም ሲባል አሁንም በትግሉ ሜዳ ላይ አለሁ ማለት ነዉ ይላሉ ወገኖቼ። አዲሱን ቲም በአትኩሮት እየተከታተለ ከተሰመረለት መስመር ቢወጣ ለማረም የሚፈልግ አካል መኖሩ ይህ አመለካች ነዉ ይላሉ። የዚህ የአንደኛዉ ቡድን ጓደኞቼ የሚሉት ‹አዲሱ ቲም በቄሮ-ፋኖ ዘርማ መራራ ትግል ዉስጥ ራሱን ገልጦ ከባርነት ነጻ ወጣ እንጅ ያላወራረደዉ እዳ አለበት ሲሉኝ አንድ በልጅነቴ የማዉቀዉን ገጠመኜን ነገርኳቸዉ።

‹አባቴ እናቴን ሲያገባት ከአባቷ ቤት የተሰጣት ባሪያ/አገልጋይ ነበረዉ። እናቴ እና አባቴ ተጣልተዉ ሲለያዩ እርሷ እስከነበረችበት ጊዜ ድረስ ታማኝ ሆኖ ሲያገለግለዉ የነበረዉን ይህን ሰዉ አባቴ እቁብ እንዲከፍል ወደ እርሷ ቤተሰቦች ሲልከዉ ብሩን ይዞ በዚያዉ ጠፋ። ይህ ሰዉ ራሱን ከአባቴ ቤት ባርነት ነጻ አወጣዉ እንጅ ከእዳ ነጻ አልወጣም› አልኳቸዉ። እነዚህ በዚህኛዉ ጎራ ዉስጥ ያሉ ወዳጆቼ ገጠመኜ ስለተመቻቸዉ ሃሳቤን በሏት!። እንዲህ አሉኝ ‹አዲሱ ቲም ፊቱን ወደ ማህበረሰቡ ቢመልስም ከኢህአዴግ ጋር ያላወራረደ ብዙ ሂሳብ ስላለበት ዛሬም ነጻ አይደለም› ያን ሰዉ አባትህ ለገንዘቡ ብቻ ሲል መልሶ ባሪያ ሊያደርገዉ ባይችልም ከተቀበለዉ ነገር የተነሳ በእርሱ ላይ የገንዘቡን ያህል መብት አለዉ። ኢህአዴግ ወዶም ባይሆን ተገዶ ‹በኢህአዴግ የህግ ማዕቀፍ ስር› ለአዲሱ ቲም ስልጣን አስረክቧል። ‹የኢህአዴግ የህግ ማዕቀፍ› የሚባለዉ አዲሱ ቲም በሜዳዉ ላይ እንዲጫወትበት የታሰረበት ገመድ ነዉ ይላሉ ወገኖቼ። አዲሱ ቲም ጨዋታዉን የሚጫወተዉ በተፈጠረለት ሜዳ ዉስጥ፤ በረዥሙ በታሰረበት ገመድ ልክ ነዉ፤ እየተጫወተበት ያለዉ ብለዉ ሊያሳምኑኝ ይሞክራሉ ወዳጆቼ። ‹ቢሆንም› አሉኝ ‹ይህ ቲም አንድ ቀን የታሰረባትን ገመድ መበጠስ የሚያስችለዉ አቅም ሲያጎለብት እንደሚበጥሳት እና ራሱን ከእዳ ነጻ እንደሚያወጣ ተስፋቸዉን ነግረዉኝ፤ ከትላንት ዛሬ ይሻለናል!› አሉኝ።

እኔ ግን ከሶስቱም ቡድን ወዳጆቼ የተሻለ ተስፋ አለኝ!

አዲሱ ቲም እስከዛሬ የሄደባቸዉ ጎዳናዎች ላይ የጣላቸዉ አሻራዎች በብዙዎች ዘንድ ሙገሳን ያስገኘላቸዉ ቢሆንም ከአንዳንድ ጉዳዮች በስተቀር ቃል በገቡት መሰረት ማህበረሰቡ የሚጠብቅባቸዉን እና በኢህአዴግ የተፈቀደላቸዉን ብቻ አይደለም የሰሩት፤ እንዲያዉም ከታሰበዉ በላይ ልቀዉ ሄደዋል። ስለዚህ የተጋነነ ሙገሳም ዉዳሴም ሳያስፈልጋቸዉ አይቀርም። ሆኖም ግን ይህ ሙገሳ የትግሉን ክሬዲት ለራሳቸዉ ለመዉሰድ እንዳይሞከሩ አደራ እላለሁኝ። እስካሁን ባደረጓቸዉ ነገሮች ሁሉ ዉስጥ ጥቃቅን እንከኖችንም አይቻለሁኝ። በአንጻሩ ግን ስልታቸዉን አደንቃለሁ። የሚጠበቅባቸዉንም ሆነ ተሰፍሮ የተሰጣቸዉን እንደተራበ ሰዉ ዘግነዉ አላበሉንም፤ ወይንም አጥቶ እንዳገኘ ተንሰፍስፈዉ አላንበሸበሹንም። ለዉጥን ለናፈቀዉ ለዚህ ህዝብ በየእለቱ ዛሬ ደግሞ ምን አዲስ ነገር አለ እያልን በጉጉት እንድንጠባበቅ ሲያደርጉን ስልታዊ በሆነ ሁኔታ በሰከነ መንፈስ ቆጥበዉ ሲመነዝሯት የምታልቅባቸዉ እየመሰለኝ ሌላስ ኢህአዴግ ከፈቀደላቸዉ ሌላ ምን ሊሰሩ ይሆን እላለሁኝ። ይህ አብዮተኛ ላለመሆን አቅማቸዉን እያጎለበቱ በጥንቃቄ የሚያደርጓቸዉን ስልታቸዉን አደንቅላቸዋለሁ። ይህ የዉጤታማ መሪ ባሳል ስልት እና ባህሪ ነዉ።

እኔ ከዚህ በኋላ እንደዜጋ የምናፍቀዉ ከሶስቱ ወሳኝ አካላት የህግ ተርጓሚዉ እና የህግ አስፈጻሚዉን ነጻነት በዚህች ምድር ከምንም ነገር በፊት ማየት እናፍቃለሁ። ማለቴ የፍርድ ቤቶች የመከላከያ፤ ፖሊስ እና የደህንነት ዘርፉ ነጻ እና ገለልተኛ ሆነዉ ለሀገራቸዉ ለወገናቸዉ እና ለፍትህ የቆሙ ተቋም ሆነዉ ማየት ነዉ። የትኛዉንም ምርጫ ከማድረግ በፊት የትኛዉንም የፖለቲካ ተፎካካሪ ድርጅት ያሳተፈ መድረክ ከማዘጋጀት በፊት እነዚህን ተቋማት በአዲስ መልኩ ማደራጀት ይቀድማል። ኢህአዴግን የሚዳኝ በዚህ ምድር ላይ እስካሁን ቄሮ ብቻ ሆኖ እስካለ ድረስ ቄሮ ደግሞ ተቋም እስካልሆነ ድረስ ከህግ በላይ እየሆነ ያለዉን አካል ልኩን ማሳወቅ የሚቻለዉ እነዚህ ተቋማት አስተማማኝ ቁመና ላይ ሲደርሱ ብቻ ነዉ። የኢትዮጵያ ህዝብ ለኢህአዴግ ማስፈራሪያና ልክ አስገቢ ተቋማዊ ቁመና የሌለዉን ቄሮን እስከመቼ ይደገፋል?

ባሳል የፖለቲካ አመራር ለትዉልድ የሚበጀዉን ከማስቀደም ይጀምራል። አዲሱ ቲም ይህን ለማመቻቸት የአቅም ችግር እንደሌለበት እስካሁን ካደረጋቸዉ ስልታዊ እርምጃዎቹ እና ዉሳኔዎቹ ለመረዳት አያስቸግር ይሆናል። የኢህአዴግ ፈቃድ ግን እጅግ ከባዱ ፈተና ሊሆንባቸዉ ይችላል። ነገር ግን የእስከአሁኑ ስልታቸዉ በተለይም የመድረክ ላይ ንግግሮቻቸዉ፤ በኢህአዴግ ሊቀመንበር ምርጫ ወቅት የፈጠሩት ግንባር እና መናበብ ከጀርባቸዉ ያለዉን ህዝባቸዉን በመታመን ቢገፉበት ይህችን ሀገር ወደአሰተማማኝ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ያመጧታል የሚል እምነት አለኝ። በዘመናዊቷ የኢትዮጵያ መንግስታት ታሪክ ነጻ ፍ/ቤት፤ ነጻ የመከላከያ፤ የፖሊስ እና የደህንነት ተቋማት አልታዩም። አዲሱ ቲም ያለፉት መንግስታት ታሪክ ስህተትን መድገም የሌለበት አንዱ እና ዋነኛዉ ጉዳይ ይህ ነዉ።

ኢህአዴግ በሞራል፤ በመዋቅሩ እና በአቅሙ ተሽመድምዶ ባለበት ሰዓት እነዚህን ተቋማት ሳያደራጁ እና አስተማማኝ ሁኔታ ላይ ሳያደርሱ የጋራ የፖለቲካ መድረክ ለመፍጠር ሁሉንም አካል ያሳተፈ የሚባለዉ ቁምነገር ኢትዮጵያን ለማትወጣዉ አደጋ ይዳርጋታል ብዬ መስጋት የኔ ብቻ ሳይሆን የአንዳንዶች ወዳጆቼም ስጋት ነዉ።

በሌላ በኩል እነዚህ የሚደራጁት ነጻ ህግ ተርጓሚ እና ህግ አስፈጻሚ አካላት በኢህአዲጋዊ ቅኝት መሆን እንደሌለባቸዉ አጥብቄ እለምናለሁኝ። ይህን ምክሬን በሚቀጥለዉ ጽሑፌ እመለስበታለሁ።

ነገም ሌላ ቀን ነዉ!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
69 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 925 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us