የመደመር ስሌት ለኢትዮጵያ ፖለቲካ!

Wednesday, 27 June 2018 12:46

ከተፈሪ ብዙአየሁ ዶርሲስ(ዶ/ር)

በቅድሚያ በመደመር ቀን ለተፈጠረዉ አሳዛኝ ጉዳይ ያለኝን ጥልቅ ሃዘን ለመግለጥ እወዳለሁኝ። መስዋዕት ለሆኑት ቤተሰቦች መጽናናትን ለተጎዱት ደግሞ መዳንን እና ፍትህን እመኛለሁ።

በመደመር ቀን የኢትዮጵያ አምላክ ባይታደገን ኖሮ ይህች ሀገር ወዳልተፈለገ አቅጣጫ መሄዷ አይቀርም ነበር። በዶ/ር አብይ ላይ የተነጣጠረዉ አደጋ ቢሳካ ኖሮ ለመጠፋፋት ቀላል መሆኑን ይህንን ሴራ የጠነሰሱት አካላት አለመገንዘባቸዉ፤ አድራጊዎቹ ከትላንት ስህተታቸዉ አለመማራቸዉን ያመለክታል። የትዉልድ ጠባሳ የሚሆን በሁሉም ወገን እንደሚከሰት መገመት አያስቸግርም። የፖለቲካ ስሌቱ ወይንም ትርፉ የተዛባ በመሆኑ ልምዳቸዉን፤ ክህሎታቸዉን እና አቅማቸዉን ልዕለ-ተፈጥሮ ኃይል ወደ ተራና ቀላል ስህተት ቀይሮት ዋናዉን ዒላማ እንዲስቱ ተደርገዋል። ከዚህም የተነሳ የብዙሃን ዜጎች ንጹህ ነፍስ እንዲቀጠፍ፤ ደም እንዲፈስ፤ አካል አንዲጎድል ተደርጓል። በዚህ ዙሪያ ዜጋ ሲነጋገር፤ የዉጭ ወዳጆች አይዞአችሁ ሊሉን የሀብት እና የጊዜ ብክነት ተፈጥሮአል። ይህንን ጉዳይ ለማጣራት ኢትዮጵያ ያልፈለገችዉን ሌላ ዋጋ እንድትከፍል ተደርጋለች። አዲሱ አመራር ቀጣዩን የኢትዮጵያ የተሃድሶ እርምጃ እንዳያስብ ለጊዜዉም ቢሆን ተስተጓጉሏል።

ዉጤቱ ግን እያንዳንዱን ኢትዮጵዊ በእልህ እና በቁርጠኝነት ራሱን እና አከባቢዉን እንዲቃኝ እና እንዲጠብቅ አንቅቶታል። ምናልባትም ሌሎች ሙከራዎች አይኖሩም ባይባልም ግን ኢትዮጵያን ሁሉ አንድ የጋራ ጉዳይ እንዲኖረን ያደረገ ክስተት ነዉ ተብሎ መውሰድ ይቻላል።

በዚህ አጋጣሚ ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድን ‹ሃይ!› የሚል አካል መኖር አለበት ብዬ አምናለሁኝ። በማህበረሰብህ መካከል በግላጭ እንደምንትንቀሳቀስ እና ያለአጀብ፣ ያለደህንነት ልዩ ጥበቃ እንደምትንቀሳቀስ እናዉቃለን። አንተ ብትጎዳ እኮ ያንተና በዙሪያህ ያሉ በመደመር ቀን በይፋ እዉቅና ሰጥተህ ያወደስካቸዉ የስራ ባልደረቦችህ ራዕይያችሁ፤ እና የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵዉያን ተስፋ እንደሚጨነግፍ አትጠራጠር። ብንወድህም፤ አንተን በነጻነትና ያለማንም ክልከላ ብናገኝህ ደስ ባለን። አንተን ማጣት ግን አንፈልግም። የሁሉንም ባይባል የአብዛኛዉን ኢትዮጵዊ ፍላጎት እየተገበራችሁ ስለሆነ ከአንተ መጎዳት ጋር በተያያዘ ጉዳይ ማንም ሀገሩን ወዳድ ኢትዮጵያዊ እንደማይደራደር አዉቀህ በማህበረሰቡ ዉስጥ በግላጭ የምታደርገዉን እንቅስቃሴ በደህንነት ሳይንሱ እንድትዳኝ በኢትዮጵያ ህዝብ ስም አጥብቄ እለምንሃለሁኝ። በግላጭ በነጻነት በህዝብህ መሃል የምትንቀሳቀስበት ቀን ገና ነዉ! ወደፊት ግን ይመጣል!

በዚህ አጋጣሚ የፖለቲካ ምህዳሩን፤ የኢኮኖሚ እና ነጻ የእዉቀት ሜዳዉን ለ27 ዓመታት የቀድሞዉ ኢህአዴግ አጠበበዉ እንጂ፤ ኢትዮጵያችን ተፈላስፈንባት፤ ሃብት አፍርተንባት፤ አስተዳድረንባት ያላለቀች በመሆኗ የቀደመዉን ጭቆና እና አፈና ልትመልሱብን የምትፈልጉ አካላት ለእናንተም ምህረት እና ይቅርታ ለማድረግ እድሉን ስጡን። በተዘጋጃችሁበት ጉዳይ ልዕለ-ተፈጥሮ የሆነዉ እግዚአብሔር ከባድ ዋጋ ሊያስከፍለን ለነበረዉ ለእኩይ ስራችሁ እንዲከሽፍ ማደረጉን ተገንዝባችሁ ሌላ አሳይመንት እየጨመራችሁብን የይቅርታና የምህረት ልብ እንዳይኖረን አታደርጉን። ነገም ሌላ ቀን ነዉ!  

ወደ ተነሳንበት ርዕስ ስመለስ ይህ የመደመር ስሌት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዓይነተኛ ጉዳይ ነዉ። መደመር ቀመር ነዉ። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ባልተጠበቀ ሁኔታ ብቅ ያለ የክቡር ጠ/ሚኒስትር ዶር/አብይ አህመድ የግል ፍልስፍና እና አመለካከት ነዉ። የእርሳቸዉ መሆኑ የሚታወቀዉ ስልጣን ከተረከቡ ጊዜ ጀምሮ ከእያንዳንዱ ንግገሮቻቸዉ ዉሰጥ መደመር አትታጣም። ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ ወዶላቸዋል።

የመደመር ቀመር ሳይንሳዊ ሲሆን ለሂሳብ ሳይንስ ብቻ የማይሰራ ነገር ግን ለሁሉም ሴክተር ልንጠቀምበት የሚገባን ሳይንስ ነዉ። መደመር በአራት ባህሪያት ይገለጻል። እነዚህን የመደመር ባህሪያት ደግሞ በፖለቲካ እና አስተዳደር ዘርፍ፤ በልማት እና ኢኮኖሚዉ ዘርፍ፤ በማህበራዊዉ ዘርፍ ሁሉ አመጣጥነን ልንጠቀምባቸዉ እንችላለን።

የሂሳብ ሊቆች በሳይንሱ ዓለም የመደመር ባህሪያት (Additive Property) በአራት ይከፈላል ይላሉ። እነርሱም

1.   Commutative Property: When two numbers are added, the sum is the same regardless of the order of the addends. E.g.:- 2+3=3+2

2.   Associative property :when two numbers are added the sum is the same regardless of the groupings of the addends .E.g.:- (2+3) +4=2+(3+4)

3.   Additive Identity Property: the sum of any number and zero is the original numbered.

E.g.:- 5+0=0+5

Distributive Property: The sum of the two numbers times a third number is equal to the sum of each addend times the third number. E.g.:- 3*(4+2)=4*6+4*2

እንግዲህ ጠ/ሚኒስትሩ ያሉት ‹ስንደመር አንድ እንሆናለን› ማለታቸዉ 2+3=1 አለመሆኑን እንዲታወቅ ይፈለጋል። በየትኛዉም አራቱ የመደመር ባህሪያት (የሂሳብ ህግ) የሚደመሩ አካላት አንድ ሊሆኑ ሳይሆን ራሳቸዉን ችለዉ የድምሩ ዉጤት እንዲሆኑ ነዉ። በዚህ ቀመር የሚደመሩ አካላት ተጨፍልቀዉ አንድ አይሆኑም። ምናልባትም ራሳቸዉን ችለዉ ዉህድ ወይንም የቁጥር ብርካቴ ይሆናሉ እንጅ አንድ ሊሆኑ አይችሉም።

ወደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ስናመጣዉ እና እያንዳንዱን የመደመር ባህሪያት እንደሚከተለዉ ይተነተናሉ።

“Commutative property፡-“ ይህ የመደመር ባህሪ የሚያሳየዉ ጭብጦች መሰረታዊነታቸዉ ተጠብቀዉ አቀማመጣቸዉን ብንቀያይር ድምር ዉጤታቸዉ አይቀየርም ነዉ። ለምሳሌ ያህል “Commutative right & Justice” (መብት እና ፍትህ)ን ብንወስድ ሁለቱም ጉዳዮች በአንድ በተወሰነ የፖለቲካ አምድ እና የማህበረሰብ መስተጋብር ዉስጥ ግለሰቦች/ቡድኖች እንዴት ሊስተናገዱ እንደሚችሉ የምናይበት ባህሪ ነዉ። እነኚህ ሁለቱ መብት እና ፍትህ የሚባሉ ጉዳዮች የጊዜ ፡ ቦታ እና ሁኔታ ተጋላጮች በመሆናቸዉ በሁሉም ማህበረሰብ ዉስጥ ያለቀለት እና የተቋጨ አንድ አይነት ትርጉም የላቸዉም። ከዚህ የተነሳ ይመስላል ታላቁ የግሪክ ፈላስፋ አሪስቶትል ‹ፍትህ ማለት በሁለት ተፏጭ ጭብጦች መካከል ያለ ነዉ› የሚለዉ። ሁለት የሚፋጩ ጭብጦች ካሉ ሁለቱንም ሊዳኝ የሚችል ፍትህ በሁለቱም ጭብጦች መካካል ይገኛል ማለት ከሁለቱ ጭብጦች አይወጣም ማለት ነዉ። ይህ ስለ ዉጤት የሚያመለክት ነዉ። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዉስጥ ሁለት ጽንፎች ቢኖሩ መፍትሔዉ በሁለቱ ጭብጦች መካከል ስለሚኖር ያለን አማራጭ የሁለቱን ጽንፎች መሰረታዊ ዉክልና (አቀማመጥ፤ አመጣጥ፤ ወዘተ) መስተጋብር ሳናፋልስ እንደምራቸዉ ነዉ።  

ለምሳሌ ዶ/ር ኢቢይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የኦሮሞን ህዝብ የመገጠንል ጥያቄ ቢያነሱ በዚህ ስሌት መሰረት ቀድሞዉንም ይህንን አቋም ነበራቸዉ ሊባል ይችላል። አቶ ደመቀ ደግሞ ከቀደመዉ ተጽዕኖ ነጻ ከወጡ እና አዲሱን አመራር ከተቀላለቀሉ በኋላ ኢትዮጵያ በምንም መልኩ አትበታተንም ካሉ እርሳቸዉም ቀድሞዉንም የነበራቸዉ አቋምነዉ ስለሚባል   የሁለቱንም አቋም መደመር የሚቻለዉ በመገንጠል እና በጋራ መኖር መካካል ያሉትን ጭብጦች በመደመር ነዉ። የዚህ ዓይነት የመደመር ባህሪ የሁለቱም ጽንፎች ባለቤቶች እስካሉ ድረስ ቦታ ፤ዘመን ፤ ሁኔታ ቢቀያየር ድምር ዉጤቱ ያዉ ይሆናል። ድምር ዉጡቱ ግን ለሁለቱም እኩል በመካከለኛ እንዲሰራ ማድረግ በጋራ መደመርን እዉን ያደርጋል ተብሎ ይታመናል።

“Associative property” ይህ ሁለተኛዉ የመደመር ባህሪ ደግሞ የሚያመለክተዉ የችብጦች መለዋወጥ ድምር ዉጤታቸዉን አይቀይርምየሚል ነዉ። ይህንን ሃሳብ በትክክል ሊገልጥልን የሚችለዉ ጠ/ሚ/ሩ ራሳቸዉ ያሉት የፍልስፍና ዓረፍተ ነገር በተሻለ ያብራራዋል የሚል እምነት አለኝ ። ‹እኛ ኢትዮጵያን ስንኖር ኢትዮጵዊያዊያን ስንሞት ኢትዮጵያ ነን›አሉ። ኢትዮጵዊነት እና ኢትዮጵያ በፖለቲካ አመለካከታችን ሊቀየር አይችልም። ለምሳሌ ያህል ብሔርን መሰረት ያደረገ ፌዴራሊዝም ምርጫችን ቢሆን ወይንም ጂኦግራፊን መሰረት ያደረገ ፌዴራሊዝም ብንመርጥ ‹ፌዴራሊዝም› የሚለዉ ድምር ዉጤት በእኩልነት ላይ እስከተመሰረተ ድረስ ያስደምረናል። ኢትዮጵዊነትን ማንም ለማንም የማይሰጥ ወይንም ማንም ማንንም የማይነፍግ መደመር ሲሆን፤ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ደግሞ በሁሉም ህዝቦቿ በጎ ፈቃድ እንጅ በማንም የተናጠል ተጽዕኖ የምትፈርስ ወይንም የማትገነባ ናት የሚለዉ አይነት የመደመር ቀመር ባህሪ ነዉ።  

“Additive Identity” የዚህ የሶስተኛዉ ዓይነቱ የመደመር ባህሪ ደግሞ የሚያመለክተዉ የአንድ ዋና ጭብጥ ከምንም ወይንም ባዶ ነገር ጋር ሲደመር የሚገኘዉን ዉጤት ያመለክታል። ይህ አይነት የመደመር ቀመር ከኢህአዴግ የቀደሙት የኢትዮጵያ መንግስታት የጭፍን አንድነት መደመር ምሳሌ ነዉ። ከምንም ጋር ሳይደመር ሁሉም በአንድነት ተጨፍልቆ አንድ ሃይማኖት፤ አንድ ህዝብ፤ አንድ ሃገር፤ አንድ ባንዲራ ወዘተ ሲባልለት፤ ሲዘመርለት የነበረ የመደመር ፖለቲካ ነዉ።

“Distributive property” አራተኛዉ የመደመር ባህሪ ሲሆን የሁለት ራሳቸዉን የቻሉ ጭብጦች ድምር ከሶስተኛ ወገን በሚመጣዉ ማንነት አይቀየርምየሚል ነዉ። በዚህ ድምር ስሌት አሪስቶትል ‹የምጣኔ መስተንግዶ› ይለዋል። እኩል መስተናገድ ተገቢነት ያለዉ ጉዳይ ሲሆን ለመደመር ምጣኔ ግን ወሳኝነት አለዉ።

ለምሳሌ በዚህ ስሌት መሰረት 3*(4+2)=3*4+3*2 4እና 2 ቁጥር ምጣኔን ሲያመለክቱ 3 ቁጥር ግን ለሁሉም እንደ ምጣኔአቸዉ እኩልነታቸዉን ወይንም በእኩልነት መስተናገዳቸዉን ያመለክታል። ልዩነትን የሚያመጣዉ የምጣኔ ቀመሩ ነዉ። የድምራቸዉ ዉጤት ግን ያዉ ኢትዮጵዊነት ነዉ።

እንግዲህ መደመር የሚለዉ ቃል እና ፍልስፍና የክቡር ጠ/ሚ/ሩ ሲሆን ሳይንሱን ተከትዬ በኢትዮጵያ ፖለቲካ አዉድ አዋዝቼ ማቅረቤ ከግምታዊ ፖለቲካኛነት እና ከልማዳዊ ማብራሪያ ሰጪነት አልፈን ምሁራን ለሃገራችን የሚጠቅመዉን ባላቸዉ ነገር ጀባ እንዲሉበት የመነሻ ሃሳብ ማቅረቤ ነዉ። በሚቀጥለዉ እትም ይህንን ሃሳቤን የሚያዳብር የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ሊያስተሳስር የሚችል ዳሰሳ ይዤ ለመቅረብ እንደምሞክር በመግለጽ በዚሁ እሰናበታለሁ።

በየራሳችን ማንነት ዉስጥ ለኢትዮጵዊነት እንደመራለን!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
226 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 916 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us