“ዐይኔን ተመልከተኝ”ን እንደተመለከትኩት

Wednesday, 27 June 2018 13:08

 

መልካሙ ተክሌ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

የማነበውን ይህን መጽሐፍ በማሳየት “ኦቲዝም ምንድነው?” ስል የጠየኳት አብራኝ ታክሲ የተሳፈረች አንዲት ወጣት "የቃሉን ትርጉም አላውቅም። የአዕምሮ ዝግመት ይመስለኛል። አይደለም እንዴ?" ስትል መልሳ እኔኑ ጠየቀች። ኦቲዝም የአዕምሮ ዝግመት አይደለም ስትል እንደገና ምላሽዋን ሰጥታለች።

እንደዚህች ልጅ የጠራ እውቀት ባይኖረኝም የኦቲዝም የአዕምሮ ዕድገት መዛባት ምንነትን አስመልክቶ ያወቅኩት የዛሬ ዐሥር ዓመት ግድም በጆይ አቲስቲክ ማዕከል በተገኘሁበት ወቅት ነበር። እዚያ ያሉ ባለሙያዎች በኦቲዝም የአዕምሮ ዕድገት ችግር ያሉ ሕፃናትን አለመታከት ሲንከባከቡ ማየቴን እስካሁን አስታውሳለሁ።

ይህን ይበልጥ እንዳስታስ ያደረገኝ ሰሞኑን ለንባብ የበቃው የዶክተር ዮናስ ባሕረጥበብ “ዐይኔን ተመልከተኝ - በኦቲዝም ጥላ ሥር” ነው። መጽሐፉ በ265 ገጽ ቢገደብም ያልተገደበ ግንዛቤ ያስጨብጣል። 150 ብር ዋጋ ቢቆረጥለትም ከችግሩ ስፋት አንጻር ሲያንሰው ነው። እንደውም ቢቻል ድጋፍ ሰጪ ተፈልጎ በነጻ ቢታደል ይበልጥ ተደራሽ ይሆናል።

በመጽሐፉ ላይ አስተያየት የሠጡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አዕምሮ ሕክምና ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ዳዊት ወ/አገኝ "በሀገራችን የልጆች አስተዳደግ እና ሕክምና ሥርዓት ውስጥ ያለውን ክፍተት በማስተዋል፣ ለብዙ የኦቲዝም ኅብር የአዕምሮ ዕድገት መዛባት ተጎጂ ሕፃናት እና ቤተሰቦቻቸው መፍትሔ የሚሆን መጽሐፍ አበርክተውልናል" ሲሉ ጸሐፊውን በማመስገን የመጽሐፉን ሚና አጉልተዋል። ተገቢ ነው።

ኦቲዝም የኦዕምሮ እድገት መዛባት ችግር ከማኅበራዊ ሕይወት መገለል እና ጤናማ ባልሆነ መልኩ በራስ ዓለም መመሰጥን ያመለክታል ብዬ አስባለሁ። ከዶክተር ዮናስ መጽሐፍ ምን ያህል ርቄአለሁ? እርስዎስ ስለ ርእሰ ጉዳዩ ምን ያስባሉ?

በፍላጎታቸው የአዕምሮ ሐኪም በሆኑት ዶክተር ዮናስ የተጻፈው “ዐይኔን ተመልከተኝ” መጽሐፍ በሙያዊ ቃላት የተደረተ አይደለም። ለሁሉም አንባቢ ሊገቡ የሚችሉ፣ ከሙያዊ ውሎ የተቀዱ፣ ሰው ሰው የሚሸቱ ታሪኮች የተካተቱበት ነው። ከየምዕራፉ ጋር የሚሔዱ ግጥሞች እና ጥቅሶችም አሉት። ይህ ማንኛውም አንባቢ ላንብህ ሲለው አንብበኝ የሚያሰኘው ነው። በመሆኑም በዝቅተኛ የትምህርት ደረጃ ያለ ሰውና ከፍተኛ ትምህርት የተማሩቱ መጽሐፉን ባልተራራቀ ግንዛቤ እንዲረዱት ያስችላል። በዚህ ላይ በየምዕራፉ ማጠቃለያ ጭምቅ ሐሳብ መኖሩ መጽሐፉን ተመራጭ ያደርገዋል።

የኦቲዝም የአዕምሮ ዕድገት ችግር በኢትዮጵያ በበቂ ደረጃ አልተጠናም። የሕዝቡም ግንዛቤ አጥጋቢ አይደለም። ስለዚህ ችግሩን በቀላሉ ለመቅረፍ አስቸጋሪ ያደርገዋል። ዋና መንስዔው አለመታወቁም ሊያባብሰው እንደሚችል እሙን ነው። ለዚህም ይመስለኛል ዶክተር ዮናስ በመጽሐፉ ገጽ 29 “የችግሩ ስፋት እና ጥልቀት ላይ ጥናቶች ቢደረጉ፤ ፖሊሲዎች ለማውጣት፣ ውሳኔ ሰጪ አካላትን ለማሳመን፣ ችግር ፈቺ ሰፋፊ ፕሮጀክቶችን ቀርጾና በጀት መድቦ ተፈጻሚ ለማድረግ በእጅጉ ይረዳል” ያሉት።

ለኦቲዝም የተለያዩ መነሻዎች ሊኖሩት ቢችሉም አካላዊ መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው ከሚታሰቡት ውስጥ በእርግዝና ወቅት የሚያጋጥም ሕመም፣ በወሊድ ጊዜ ሕፃኑን የሚታመማቸው ሕመሞች እና ሌሎች ጉዳቶች የኦቲዝምን ችግር እንደሚያባብሱ በመጽሐፉ ተወስቷል።

እንዳይባባስ ከሚደረግባቸው መንገዶች አንዱ ግንዛቤ መጨበጥ ነው። ሌሎቹን መጽሐፉን ሲያነቡ ያገኙዋቸዋል።

ከመጽሐፉ እንዲህ አይነት መረጃ ብቻ ሳይሆን በርዕሰ ጉዳዩ ዙርያ የሚሰሩ ድርጅቶች አድራሻም ያገኛሉ። መረጃ የሚሰጡ ትክክለኛ የኢንተርኔት አድራሻዎችንም እንዲሁ።

የኦቲዝም ኅብር የአዕምሮ ዕድገት መዛባት ችግር ማከሚያ ዘዴዎች ሲሉ ዶክተር ዮናስ በመጽሐፉ የጠቀሱዋቸው ዘዴዎች አሉ። ከእነዚህም አንዱ ወላጆች የመፍትሔው አካል እንዲሆኑ በሥልጠና መታገዝ እንዳለባቸው ያትታል። (ገጽ 156) ከዚህ የተያያዙ የመድሃኒት አጠቃቀም፣ አመጋገብ ወዘተ በመጽሐፉ ተብራርተዋል።

ወላጆች ብቻ ሳይሆኑ ሁላችንም መጽሐፉን አንብበን የመፍትሔው አካል መሆን እንችላለን። ስለዚህ መጽሐፉ ከመጻሕፍት ቤታችን ወይም መደርደርያችን ሊኖረን ይገባል። በዚህ ርእስ ዙርያ ሌሎች መጻሕፍትም ሊፃፉ የግድ ነው- ከጉዳዩ አሳሳቢነት አንጻር።

ለሁሉም ታማሚ ባይሆንም ጥሩ ሕክምና ካለ ከኦቲዝም መፈወስ እንደሚቻል ተስፋ ይሰጣል- "ዐይኔን ተመልከተኝ"።

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ኅብረተሰብ ከባድ ችግሮችን በሃይማኖት ይፈታልኛል በሚባልበት ሃገር የፀበል እና የሃይማኖት ቦታዎች በኦቲዝም የአዕምሮ እድገት ችግር ውስጥ ያለ ልጅን መውሰድ በሌሎቹ ልጆች ላይ ተጽእኖ እንዳለው መጥቀሱ ብዙም አያስኬድም። በሌላ ገጽ ደግሞ ዐውዱ ቢለይም ሕሙማኑን ሃይማኖታዊ ቦታ መውሰድን የመፍትሔው አካል ሊሆን እንደሚችል መገለጹ ግራ ሊያጋባ ይችላልና የዶክተር ዮናስን ማብራርያ ይፈልጋል።

በሌላ በኩል በመጽሐፉ ብዙ ቦታ ባይሆንም ሐሳብ መደጋገም ይታያል። ድግሞሹ ለአጽንዖት ከሆነ ይበጃል። ካልሆነ ግን ያሰለቻል። ለምሳሌ በማውጫ (Table of contents) የተጻፈ መጽሐፍ በመግቢያ ስለ ሁሉም ምዕራፎች መጠቀሱ ድግሞሽ ነው።

ያም ሆኖ ግን በመግቢያው እንደተጠቀሰው "ዐይኔን ተመልከተኝ በኦቲዝም ጥላ ሥር" ለመጽሐፍ ሕክምና (bibliotherapy) ጥሩ ምሳሌ በመሆኑ እኔም እስማማለሁ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
84 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 917 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us