የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርሻ በአፍሪካ ቀንድ!

Wednesday, 04 July 2018 12:49

 

ከተፈሪ ብዙአየሁ ዶርሲስ (ዶ/ር)

የኢትዮጵያ ሰላም ለአፍሪካ ቀንድ ቀጠና እጅግ ወሳኝ ነው። ከሁሉ የሚበልጠው ደግሞ ኢትዮጵያውያን ከሌሎች የአፍሪካ ቀንድ ህዝቦች ጋር እንደ የጉርብትናቸው የደም፣ የባህል የቋንቋ እና የሃይማኖት ትስስር አላቸው። በሌላ በኩል ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ለአፍሪካ ቀንድ ሀገራት እምብርት ናት።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ከእነዚህ ሀገራት ጋር ባላት የመልካም ጉርበትና ትስስር ብቻ ሳይሆን በእነርሱ የውስጥ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ሁኔታ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ይወሰናል።

ፖለቲካቸው፣ ሃይማኖታቸው፤ ኢኮኖሚያቸው እኛን ባይወክል የኛን የመወሰን አቅሙ የማይካድ ነው።

እነዚህ ጎረቤት ሀገራት ለኢትዮጵያ ህልውና ወሳኝ ባይሆኑም እንኳን በስኬትዋም ሆነ ውድቀትዋ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ይኖራቸዋል። በመሆኑም የትላንት ማንነታቸውን እና የዛሬ ፍላጎታቸውን መለየት ለኢትዮጵያ መጻኢ የዉስጥ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ እና የዉጭ ግኑኝነትዋ   ወሳኝ ነው።

ለዚህ ነዉ ኢትዮጵያ ለራስዋ ስትል እነርሱን የማቀፍ ስራ መስራትዋ የግድ ነው የሚባለዉ።

ኢትዮጵያን ጨምሮ የእነዚህ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ቀጠና በውስብስብ ፖለቲካ የተሞላ ነው። ሁሉም የቀጠናው ሀገራት ማለትም ኢትዮጵያ፣ኤርትራ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ ሁለቱ ሱዳኖች፣እና ኬኒያ ከውስጥ በሚነሱ የጎሳ ፖለቲካን ጨምሮ እስከ አለም አቀፍ ሃያላን ሀገራት የጥቅም ፖሊሲ ጥግ ድረስ ከሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራት በተለየ መልኩ በአንጻራዊነት በተከታታይ ግጭቶች እና ቡራቡሬ ትርምስ ይታወቃሉ።ለ150 አመታት ያላባራውና ጊዜ እና ክስተትን ጠብቆ የሚነሳው እነዚህ ሃያላን ሀገራት ለራሳቸው ጥቅሞች ሲሉ በየሀገራቱ መካከል የዘሩአቸው አረሞች አፍሪካዉያን መንግስታት በተቀያየሩ ቁጥር እንደ አዲስ ከተዳፈኑበት እየተቀጣጠሉ የዚህን ቀጠና ሀገራት በግልም በጋራም ዋጋ እያስከፈሉ፣ እድገቶቻቸውን እያሽመደመዱ ይገኛሉ። በሌላ በኩል እነዚህ የዚህ ቀጠና የአፍሪካ ሀገራት ይህንን አረም በጋራም ሆነ በግል ለመከላከል እንዳይከለከሉ የየግል እጀንዳዎቻቸውን ሳይጨርሱ ተጨማሪ የቤትም ሆነ የጎረቤት ስራዎች ይሰጣቸዋል። አፍሪካ በአጠቃላይ ምስራቃዊ አፍሪካ በተለይ በአሁኑ ዘመን ካሉት ሀያላን ሀገራት ተጽእኖ ነጻ የሆኑበት ጊዜ በታሪክ ወደ ሁዋላ ተኪዶ በራሳቸው ሀያላን በነበሩበት ጊዜ እንጅ የቅርብ ጊዜ ትዝታ የላቸውም።

ከታሪክ እንደምንረዳዉ እና እየሆነ ካለዉ በመነሳት በዚህ በ150 አመታት ውስጥ የአፍሪካ ቀንድን ያመሱአት ሀገራት የሚከተሉ ናቸዉ።

1.  የእንግሊዝ እና የጣሊያን በቀይ ባህር ላይ ያላችው ፍላጎት በኢትዮጵያና በኤርትራውያን መካከል ያላባራ ቁርሾ ጥሎ ማለፉ እና ኢትዮጵያን ወደብ አልባ ሀገር ማድረጉ፣

2.  የግብጽ በአባይ ወንዝ ላይ ባለት ጥቅም የበላይነትዋን ለማስጠበቅ የምታደርገው እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ አለማባራቱ፣

3.  የፈረንሳይ በጂቡቲ ላይ የመቆየትዋ እና አወጣጥዋም የወቅቷን ኢትዮጵያ እንጅ የነገይቷን ሁኔታ ያላገናዘበ ዉሳኔ በማድረግ አዳፍና የሄዴችው እሳት ኢትዮጵያ በጅቡት ጉዳይ ላይ መቼም አቅም እንዳይኖራት ማድረጉ፣

4.  የእንግሊዝ፣ የጣሊያን፣ እና የፈረንሳይ በሱማሊያ በነበራቸው ትንቅንቅ ውስጥ ለታላቋ ሱማሊያ መፈጠር ጽንሰ ሀሳብ ማኖር እና የኢትዮ ሶማሌ ያልበረደለት ጫና፣  

5.  በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የሶቪዬት ህብረት/የሩስያ እና አሜሪካን መር ምእራባውያን የተቃራኒ አይዶሎጂ ፍትግያ ውስጥ የተፈጠረው ቂርሾ አለማባራት፣

6.  ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ የአሜሪካን መር አለም አቀፍ የሽብርተኝነት ቁጥጥር ዘመቻ ለኢህአዴግ መር ኢትዮጵያ መንግስት በቀጠናው ላይ እንድተፏንን እድል ማግኘት፣

7.  በደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ጉዳይ የአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ከኢትዮጵያ የተነሳ ግልጽ አቋም አለመያዝ እና ገለልተኛ አካል መሰየም አለመቻል፣

8.  የቻይናዎች የንግድ እና የኢኮኖሚአቸዉ ተጽእኖ በቀናነዉ መስፋፋት ብሎም ገበያውን የመቆጣጠር አዝማሚያ የአሜሪካን እና የምዕረባዉያንን ትኩረት መሳብ፣

9.  የሀብታሞቹ እስላማውያን ሀገራት የራሳቸው የሆነ ርእዮተ አለም አልባዎቹ ሱማሊያውያን እና ባልተረጋጋችው የደቡብ ሱዳን ጉዳይ ውስጥ ሃይማኖታዊ ተጽእኖ የመፍጠር ፍላጎት፣

10.የሰሜናዊ ሱዳን ርእዮተ አለም ጠንካራና ላለመበግር ተጋድሎነ ተመረኩዘዉ ሌሎቹ ሃብታም ሙስሊም ሀገራት ድጋፍ መቀጠል ቀጠናውን ለመቆጣጠር መሞከር ለምትተጋዉ አሜሪካ የትንኮሳዎች ምከንያት መሆን፣

11.የኬንያዉያንን የሊበራሊዝም ተጽእኖ ኢኮኖሚ መንግስት መር ፓርቲዉ እና በተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል ምእራበዉያን ለራሳቸዉ ፍጆታ በሚመች መልኩ ለመቅርጽ የሚፈጥሩት የዉስጥ ጫና፣

12.በቀጠናዉ ገናና ከመሆን ፍላጎት የመነጨ ዉሉ የጣፋበት የኢህአዴግዋ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ኢኮኖሚ ባለቤቷ አቅጣጫ ለሊበራል ዲሞክራቶች አለመመቸት ከዚህም የተነሳ የራሷን ሳታበስል የሌላዉን ለማማሰል ስትሞክር ብዙ ጠላቶችን በቀጠናዉ ማፍርቷ፣ እና የመሳሰሉት ናቸዉ።

እነዚህን ነጥቦች ወደፊት አንድ በአንድ በመንሳት በኢትዮጵያ አዲሱ አመራር አቅጠጫ ዉስጥ ያላቸዉን ተጽእኖ እንደምቹ ሁኔታነት እና የስጋት ምንጭነታቸዉ ከመነፍትሔ አቅጣጫቸዉ ጭምር ለመዳሰስ ይሞከራል።

ጎረቤቶችዋን ያላማከለ ስራ ኢትዮጵያን እንደማያዋጣት አዲሱ አመራር የተገነዘበ ይመስለኛል። ለዚህም ነዉ የዉጭ ግንኙነቱን ከጎረቤት ሀገራት በተለይም በደም፣ በሃማኖት፣ በባህል እና በኢኮኖሚ የተሳሰሯትን ጎረቤቶችዋ የጀመረችዉ። አዲሱ አመራር በሳልነቱን የሚያመላክቱ ጉዳዮች ኢትዮጵያ ከጎረቤቶችዋ እንድትታረቅ እና ከዚህ በፊት ባጠፋቻቸዉ ጉዳዮች ካሉም የማባበል ስራ ለመስራት ብሎም የአዲሱን አመራር የወደፊት አቋም እና አቅማቸዉንም ጭምር ለማሳየት የተሰራዉ ስራ እነርሱን ብቻ ሳይሆን አለምአቀፍ ማህበረሰቡንም አስደምሟል። የዚህ ጽኀሁ ማጠንጠኛ ይህ ከቶ በኢትዮጵያ ታሪክ ያልተሞከረ ስልት በጥንቃቄ እና በብስለት መመራት ያስፈልገዋል ነዉ። የኢትዮጵን ትንሳዔ የማይፈልጉ ጠላቶቻችን በዉስጥም በዉጭም ዓይናቸዉ የሚቀላ ወዳጆች ሞልተዉናል። ጥንካሬዎቻችንን በመለየት ድካሞቻንን/ስህተቶቻቸን በማወቅ በተፈጠሩ አጋጣሚዎች በድል ሲቃ ሳንዘናጋ ስጋቶቻችን ላይ መስራት የግድ ነዉ።

ከዚህ የተነሳ የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ እንደ ከዚህ በፊቱ እንደማይቀጥል እስክናረጋግጥ ድረስ ምሁርን፣ ተመራማሪዎች በብዕሮቻችን ፖለቲካኞቻችንን ማንቃት የግድ ነዉ እላለሁኝ።

የአዲሱ ጠ/ሚ/ር የለዉጥ ፍጥነት በኢህአዴግ ዉስጥ ብቻ ሳይሆን መላዉን ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵዉያንን እያካለለ ይገኛል። ኢትዮጵያ በለዉጥ ጎዳና ዉስጥ ናት የሚያስብሉ በጎ ጅምሮች ከዉስጥም ከዉጭም ይታያሉ። የለዉጡ አቅጣጫ እና ፍጥነት በተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ዉስጥም አብዮት አስነስቷል። የጠ/ሚ/ሩ የለዉጥ እርምጃዎች የተፎካከሪ ፓርቲዎችን ሃሳብ/አጀንዳዎች በተግባር ወስደዉባቸዋል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እንታገልለታልን ሲሉ የነበሩትን የዲሞክራሲ አቅጣጫዎች ሳይቀር በተግባር እየመለሱ የሚሉትን እያሳጡአቸዉ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን ዓላማቸዉን ወስደዉባቸዉ ኢህዲጋዊ አድርገዉታል። ማጋነን ካልሆነ በቀር የአንዳንዶችን የፖለቲካ ማኒፌስቶ በእርሳቸዉ በተግባር እርምጃ ያለቀ እስኪመስል ድረስ አዲሱን ኢህአዴግ ተቀላቀሉ የሚሉ ይመስላል። በዚህ ሁኔታ ጠንክሮ ከቀጠለ፣ ኢትዮጵያ ከዉስጥም ከዉጭም ከሰከነች፣ የተፎካከሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ብዛት ሳያስፈልገን በሁለት ጽንፍ ቢደራጁ ኢትዮጵያን ወደፊት ማራመድ ይቻላል ብዬ የግሌን አስተያየት እሰጣለሁኝ።

በዚህ አጋጣሚ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በሚቀጥለዉ ምርጫ እንድንመርጣቸዉ ካሰቡ አሁን በተፈጠረላቸዉ አጀንዳቸዉን የማቅለል ስራ በአዲሱ የኢህአዴግ አመራር ከተሰራላቸዉ መጪዋን የኢትዮጵያ ሁኔታ የሚወስን የበሰለ ፖለቲካ የአፍሪካ ቀንድ ተሳትፎዋን ጨምሮ ለኢትዮጵያ በሰከነ መልኩ ያለማንም ጫና ግንባር ፈጥረዉ ትዉልድን ያሳተፈ ስራ ሰርተዉ ቢያቀርቡልን ታሪክ አይረሳቸዉም ብዬ እገምታለሁ።

መጪዉ ጊዜ ብሩህ ነዉ!¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
39 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 923 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us