ኢትዮጵያዊው ጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በኔልሰን ማንዴላ የፍቅር እና የዕርቀ-ሰላም መንገድ ላይ …!!

Wednesday, 04 July 2018 13:00

 

በተረፈ ወርቁ (ምንጭ ግዮን መጽሔት)

1. እንደ መንደርደሪያ


የደቡብ አፍሪካው የነጻት ታጋይ፣ አርበኛና የዓለም ሰላም የኖቤል ተሸላሚው፣ ኔልሰን ሮሂላላ ማንዴላ፣ ከ27 ዓመታት የወኅኒ ግዞት ወጥተው፤ እርሳቸውና ሕዝባቸውን እጅግ አሰቃቂ ለሆነ ግፍና መከራ የዳረጋቸውን የአፓርታይድ ዘረኛ መንግሥትንና የሥርዓቱ ቀንደኛ አቀንቃኝ ለሆኑ መሪዎችና ደጋፊዎች- ከልብ የሆነ ይቅርታ ማድረጋቸውን ባወጁበት፣ ለሕዝባቸው ባደረጉት ታሪካዊ ንግግራቸውም፤ ‹‹ለነገይቱ ደቡብ አፍሪካ ብሩሕ ተስፋ ያለን ብቸኛው መንገድ ወይም አማራጭ ‹‹የፍቅር፣ ‹የመደመር› የዕርቀ-ሰላም መንገድ ብቻ›› መሆኑን ባወጁ ማግሥት የለንደኑ ታይምስ/Times መጽሔት በፊት ሽፋን ገጹ ላይ የኔልሰን ማንዴላን ትልቅ ምስል ያካተተ አንድ ወቅታዊ ዘገባ ይዞ ወጥቶ ነበር።


‹ታይምስ› የኔልሰን ማንዴላ የካርቱን ምስል ይዞ የወጣበት መንገድ በወቅቱ ብዙዎችን ያስገረመና ያነጋገረ ጉዳይ ሆኖ ነበር። መጽሔቱ የማንዴላን የራስ ቅል በጣም አግዝፎ የተቀረው አካላቸውን ደግሞ ትንሽ አድርጎ ነበር በካርቱን ምስሉ ያወጣቸው። የዚህ የማንዴላ የካርቱን ምስል አንድምታም፤ “በኃይላቸው፣ በሰራዊታቸው ብዛትና በጠብመንጃ ኃይል ሳይሆን በአእምሮአቸው ታላቅነትና ብስለት፣ በፍቅር፣ በቅን ልቦ እና በማስተዋል ሕዝባቸውን፣ ሀገራቸውን የሚመሩ፣ ብልህና ታላቅ የሆነ መሪን አፍሪካ አሁን ገና አገኘች፤” የሚል መልእክትን ለማስተላለፍ ነበር ይህን የማንዴላን የካርቱን ምስል የተጠቀመበት።


በእርግጥም ሥልጣን የፈጣሪና የሕዝብ አደራ መሆኑን የዘነጉ፣ ሥልጣን ርስተ-ጉልት በሆነባት አፍሪካችን፣ ኢትዮጵያችን- ለሥልጣናቸው ሲሉ በገዛ ሕዝባቸው ላይ ጦር ለማዝመት ወደኋላ የማይሉ፣ የአፍሪካን በደም አበላ እንድትዋኝ፣ ምድራችን የደም-ምድር/አኬል-ዳማ እንድትሆን ያደረጉ፣ ከአውሬ ያልተለዩ አምባገነን መሪዎችን ባየንባት አኅጉራችን/ኢትጵያችን፣ የምርጫ ኮሮጆ ገልብጠውና የሕዝብን ድምፅ ወዲያ ብለው ‹‹ሥልጣን ወይም ሞት!›› በሚል መፈክር ሕዝባቸው ላይ የጥይት ውርጅብኝ የሚያዘንቡ ቡኩኖችን፣ በሙስና፣ በሌብነት ላይ የነገሡ አልጠግብ ባይ፣ ‹‹የቀን ጅቦችን››፣ ግብዞችንና አስመሳዮች፣ የእውነትና የፍትሕ ጠላቶች ነፍስ ሥጋችንን ባስጨነቁባት ኢትዮጵያችን- የአፍሪካዊውን፣ ታላቅ ጀግና የማንዴላን/የማዲባን፤ ‹የእውነት፣ የፍቅር፣ የዕርቀ-ሰላም መንገድ የሚከተል በፍቅር ልብ፣ በአእምሮ ብስለትና በማስተዋል ሕዝባቸውንና ሀገራቸውን የሚመሩ መሪዎችን ማግኘት እንደ ታላቅ የምስራች የሚቆጠር ነው።


ምዕራባውያኑ ታላላቅ ሚዲያዎች ለዚህም ይመስላል ‹የሰላም፣ የዕርቅ ሰው› የሆኑትን ኔልሰን ማንዴላን እንዳሞጋገሷቸው፣ ከፍ እንዳደረጓቸው ሁሉ በተመሳሳይም ሰሞኑን እንደ ዋሽንተግተን ፖስት፣ ዘጋርዲያን ያሉ ጋዜጦችና ታላላቅ የመገናኛ ብዙኃን የሀገራችንን፣ የኢትዮጵያን ጠቅላይ ሚኒስትር የዶ/ር ዐቢይ አሕመድን ‹የፍቅር፣ የዕርቀ-ሰላም ጉዞ› ከግምት ውስጥ በማስገባት ‹‹ዳግመኛው አፍሪካዊው ማንዴላ›› ሲሉ ለመጥራት የተገደዱት።

2. ጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በማንዴላ የፍቅር እና የዕርቅ መንገድ…!!


“Ethiopia always has a special place in my imagination and the prospect of visiting Ethiopia attracted me more strongly than a trip to France, England, and America combined. I felt I would be visiting my own genesis, unearthing the roots of what made me an African.” (Long Walk to Freedom Nelson Mandela/1994)


‹‹ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት በእኔና በሕዝቤ ልብና ማንነት ውስጥ ያለው ሥፍራ እጅጉን ክቡርና የተለየ ነው፤ በዓለማችን ከሚገኙ ታላላቅ ሀገራት መካከል ከፈረንሳይ፣ ከኢንግላንድና ከአሜሪካ ሀገራት ጉብኝቴ ይልቅ፤ የመላው ጥቁር ሕዝቦች ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ ቅርስና የአፍሪካዊ ማንነቴ ሥርና መሠረት የሆነችውን ሀገረ ኢትዮጵያን መጎብኘት በእኔና በሕዝቤ ልብ ውስጥ ልዩ ትርጉም፣ ልዩ ስፍራ አለው።›› (ኔልሰን ማንዴላ)


በውድ ሀገራቸው ኢትዮጵያ፣ በሕዝባቸውና በአፍሪካ ምድር ፍቅር፣ ዕርቀ-ሰላም፣ ብልጽግና ይሰፍን ዘንድ ምኞታቸው የሆነው የሀገራችን አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፤ ቅዳሜ ዕለት በተጠራው ታሪካዊና ታላቅ የድጋፍ ሰልፍ በለበሱት ካኔተራ/ቲሸርት ላይ የደቡብ አፍሪካውያን፣ የፀረ-አፓርታይድ ታጋይና የነጻነት አርበኛ፣ ኔልሰን ሮሂላላ ማንዴላ ምስል እንዲሆን መፍቀዳቸው የእኚህን ታላቅ አፍሪካዊ አድናቂያቸው ብቻ ሣይሆኑ በተግባርም የእርሳቸውን የዕርቀ-ሰላም መንገድ ለመከተል መወሰናቸውን የሚያሳብቅ ነው።


ደቡብ አፍሪካውያን ‹‹ታታ ማዲባ (ታላቁ አባታችን)›› በሚል የሚጠሯቸውና የሚያሞኳሽዋቸው ኔልሰን ሮሂላላ ማንዴላ የሀገራቸውን፣ የሕዝባቸውንና የእርሳቸውን እንደ መርግ የከበደ የመከራ፣ የግፍና የጭቆና ታሪክ፣ የአፍሪካንና ሕዝቦቿን ዘመናት የባርነትና የቅኝ ግዛት አሰቃቂ፣ የመከራ ዘመናት- በፍቅር፣ በይቅርታ ዘግተው፣ ለ27 ዓመታት ከቀዝቃዛው የአትላንቲክ ውቅያኖስ ማዶ- በሮቢን ደሴት ወኅኒ ቤት ተግዘው፣ በዘረኛው የአፓርታይድ መንግሥት የውድ እናታቸውንና የበኩር ወንድ ልጃቸውን እረፍተ-ሞት ላይ እንኳን እንዳይገኙ ማእቀብ ተጥሎባቸው፣ እንደ መርግ የከበደ የእናታቸውን ህልፈት ለብቻቸው ሆነው በኀዘንና በቁጭት በትር እንዲገረፉ የፈረደባቸውን፤


ከትግል አጋራቸውና ከውድ ሚስታቸው ጋር እንኳን በስድስት ወር አንድ ጊዜ ለሠላሳ ደቂቃ ብቻ እንዲገናኙ የወሰነባቸውን … ያን በእርሳቸውና በሕዝባቸው ላይ አስከፊ የሆነውን የዘረኝነት ቀምበር የጫነባቸውን፣ መራራና አሰከፊ፣ የሰቆቃ ሥርዓት ይቅር ብለው በአፍሪካ፣ በዓለም ፊት አዲስ ታሪክ የጻፉት፤ የአፍሪካ ጥቁር አፈር ውድ ልጅ የሆኑት ማንዴላ የዶ/ር ዐቢይ ሕያውና ታላቅ ተምሳሌት ሆነው በቅዳሜው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ደምቀው ታይተዋል።


እኚህ የሀገራችን ጠቅላይ ሚ/ር የዶ/ር ዐቢይ ታላቅና ሕያው ተምሳሌት የሆኑ፣ የዕርቅና ሰላም ሰው፣ ደቡብ አፍሪካዊው የነጻነት ታጋይና አርበኛ፣ ኔልሰን ማንዴላ ከ27 ዓመታት ግዞት ነጻ በተለቀቁበት እ.ኤ.አ. የካቲት 11 ቀን 1990 ደስታቸውን ለመግለጽ ለተሰበሰቡ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ደቡብ አፍሪካውያን ሕዝባቸው፣ በኬፕታውን ከተማ ባደረጉት ንግግራቸው እንዲህ ነበር ያሉት፤


I stand here before you not as a prophet but as a humble servant of you, the people. Your tireless and heroic sacrifices have made it possible for me to be here today. I therefore place the remaining years of my life in your hands.


ደቡብ አፍሪካውያን ሕዝቤ ሆይ! በፊታችሁ የቆምኩት እንደ ነቢይ ሳይሆን እንደ ትሑት አገልጋያችሁና ታዛዣችሁ ሆኜ ነው፤ የእናንተ ድካም የለሽ፣ ጀግንነታችሁና መሥዋዕትነታችሁ የዛሬ የነጻነት ቀን ዕውን እንዲሆን አድርጓል፤ ስለሆነም እናንተን በታማኝነትና በቅንነት ለማገልገል ቀሪ የሕይወት ዘመኔን በእጃችሁ አደራ እተዋለሁ።


እንደ አፍሪካዊው ጀግና ኔልሰን ማንዴላ ሁሉ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድም በሔዱበትና በተገኙበት የተለያዩ መድረኮች ሁሉ በሚያደርጓቸው ንግግሮቻቸውና ተግባራቸው የሕዝብ አገልጋይነታቸውን ለማስመስከር፣ በፍቅር፣ በቅን ልቦና እና ትሕትና ተግተው በመሥራት ላይ ናቸው። አይሁዳዊው፣ ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን፣ ‹‹ትጋት ለሰው የከበረ ሀብት ነው፤›› እንዲል ጠቅላይ ሚ/ር ዐቢይ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ- ሀገራቸው፣ ኢትዮጵያን ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ በመጓዝ የፍቅርን፣ የሰላምንና የዕርቅን ዘር ለመዝራት እየደከሙ፣ እየተጉ ነው። ‹‹ፍቅር ያሸንፋል!›› በሚል መርሕም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላለፉት ረጅም ዓመታት ጥላቻና መከፋፋት፣ መበላላትና መለያየት ለነገሠበት የሀገራችን የፖለቲካ የጨለማ መንገድ ላይ ፍቅር ብርሃን ይበራበት፣ ይቅርታ ጎሕ ይደምቅበት ዘንድ እየተጉ፣ ሕዝባቸውን፣ የሥራ ባልደረቦቻቸውንና ፓርቲያቸውን ኢሕአዴግን ጭምር እያተጉ ነው።

3. ፍቅር ያሸንፋል!


ደቡብ አፍሪካዊው የነጻት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ፤ ‹‹ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት እርሳቸው፣ የሕዝባቸውና የመላው ጥቁር ሕዝቦችና በአጠቃላይ የሰው ልጆች ሁሉ ግዙፍ ታሪክና ገናና ሥልጣኔ መነሻ፣ የሰው ልጆች የነጻነት የተጋድሎ ክቡር ተምሳሌት… ወዘተ መሆኑን ባወጁበት ‹Long Walk to Freedom› በሚል ረጅሙን የትግል ሕይወታቸውን በተረኩበት መጽሐፋቸው፤ ‹‹ፍቅር በማንኛውም ልብ ውስጥ በተፈጥሮ አለ፤ በተቃራኒው ጥላቻ ግን በትምህርት እንጂ በተፈጥሮ አይገኝም።›› እንዳሉት ሁሉ ጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር ዐቢይ ይህን የፍቅር፣ የዕርቀ-ሰላም መንገድ ለመጓዝ ረጅሙን ጉዞ ተያይዘውታል።


ዶ/ር ዐቢይ ባሳለፍነው ቅዳሜ በመስቀል አደባባይ በተጠራው ታሪካዊ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የማንዴላ ምስል ያረፈበትን ካኔተራ ለብሰው መምጣታቸው እኔም ለውድ ሀገሬ፣ ለዚህ ባለ ታሪክና ታላቅ ሕዝብ ‹የማንዴላን/የማዲባን የፍቅር፣ የሰላም፣ የእርቅ መንገድ እከተላለሁ!› በሚል መርሕ፤ የኢትዮጵያዊነትን የፍቅርና የአንድነት ቃል ኪዳን ከሕዝባቸው ጋር አብረው ለማደስ ቃል የገቡበት፣ ለውድ ሀገራቸውና ለውድ ሕዝባቸው ምኞታቸውና ሕልማቸው ‹‹ፍቅር፣ ሰላም፣ አንድነት፣ መደመር›› መሆኑን ዳግመኛ ያረጋገጡበት ታሪካዊ፣ ታላቅ ዕለት ነው ማለት ይቻላል።


ጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ማግሥት ጀምሮ ፍቅርን፣ ይቅርታን፣ ሰላምንና ዕርቅን በማወጅ ሀገራቸው ኢትዮጵያ በቀደመ ታሪኳ ወደነበራት ገናና ሥልጣኔ፣ የታላቅነት፣ የክብር ሰገነት ላይ ትመለስ ዘንድ መወጣጫ መሰላሉ፣ እንደ ሀገር ለመቀጠል ያለን ብቸኛ አማራጭ፤ ‹አንድነት፣ ኅብረት፣ መደመር ነው፤ በአንድነት እጅ ለእጅ ተያይዘን በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ፍቅር፣ ሰላም እንዲናኝ ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናድርግ!› በማለት ደጋግመው ጥሪያቸውን ለሕዝባቸው አስተላልፈዋል።


ጠቅላይ ሚ/ሩ በዚሁ ፍቅርን፣ ሰላምንና ዕርቅን ባስቀደሙበት ጉዞአቸው ከሀገራችን ኢትዮጵያ ውጪም ከምሥራቅ አፍሪካ እስከ ሰሜን አፍሪካና መካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ድረስ ተጉዘው ለሕዝባቸው ያላቸውን ፍቅርና ክብር በተግባር ጭምር አሳይተውናል።

 

4. ቅዳሜ ሰኔ 16ን በጨረፍታ፡-


የቅዳሜው ሰኔ 16 ቀን የድጋፍ ሰልፍ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የፍቅር፣ ዕርቀ-ሰላም ጥሪ፣ ግብዣ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ዘር፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት ድንበር ሳይለያቸው፣ ሳይከፋፍላቸው በአንድነት ሆነው፤ ‹‹እኛም ከጎንህ ነን፣ ኢትዮጵያና ሕዝቧን ታላቅ የማድረግ ክቡር ራእይህም ተካፋዮች ነን። ጠቅላይ ሚኒስትራችን፤ ‹‹ሕልም ሕልማችን፣ ቁጭትህ ቁጭታችን፣ ናፍቆትህ ናፍቆታችን፣ ተስፋህ ተስፋችን ነው!›› በሚል የዘመናት ናፍቆት፣ ታላቅ ስሜትና ጉጉት- ኢትዮጵያውያን ሁሉ በፍቅር የታደሙበት ነበር የቅዳሜው ዕለት የመስቀል አደባባዩ ታሪካዊ ሰልፍ።


በአንፃሩም ደግሞ ‹‹የእውነት፣ የፍትሕ፣ የፍቅር፣ የሰላም ጠላቶችን ያስደነገጠ፣ ያስበረገገና የክፋት ምክራቸው የተናደበት፣ ታሪክ በወርቀ ቀለሙ የከተበው ደማቅና ታሪካዊ ሰልፍ ሆኖ ነው ያለፈው። ጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር ዐቢይ በቅዳሜው የድጋፍ ሰልፍ ላይ በደረሰው የቦምብ ጥቃት አደጋ በኋላ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በቀጥታ ባስተላለፉት መልእክታቸው እንዳሉትም፤


‹‹የጥፋት፣ የክፋት ኃይሎች ሆይ፡- ከብረት በጠነከረ በኢትዮጵያዊነት የፍቅር፣ የአንድነት ቃል ኪዳን፣ ብርሃን የፈነጠቀበት ጎዞአችንን ለማጨለም፣ ደስታችንን ለመረበሽ ያደረጋችሁት ሙከራ አልተሳከላችሁም፤ ደግሞ መቼም አይሳካላችሁምም። በዚህ ክፋታችሁ፣ ጥፋታችሁ መካከል እንኳን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ለፍቅር፣ ለሰላም፣ ለአንድነት የዘረጉት ክንዳቸው አልታጠፈም፤ አይታጠፍምም። በሀገራችን የጀመረው የፍቅርና የአንድነት ጠል፣ ዝናብ መዝነቡ ይቀጥላል፤ በጭራሽ ወደኋላ አንመለስም!!››


ዕለቱ ይቅርታ ከፍ ያለበት፣ ፍቅር የነገሠበት ነበር። በጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን የነጻት ተጋድሎ፣ በክቡር ደማቸው ከፍ ያለው አረንጓዴው፣ ቢጫውና ቀዩ ሰንደቀ ዓላማችን በክብር ከፍ ብሎ የታየበት ነበር። በአጭሩ የሰልፉ ኅብረ ብሔራዊነት፣ ታላቅ ትዕይንት ግን ቃላት ከሚገልጸው በላይ እጅግ ልዩ ነበር። ያልተሰማ የመፈክር ዓይነትና ያልተሰማ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የድል ዜማ አልነበረም። ላለፉት ሃያ ዓመታት የታሰሩ መፈክሮችና ዜማዎች በነጻነት አዲስ አበባን ጎዳናዎች አድምቀውት ነበር የዋሉት። ሕፃን፣ ወጣት ወንዶችና ሴቶች፣ አርበኞች፣ አርጋውያን፣ ካህናት፣ መነኮሳት፣ ሼኽዎች... ብቻ ምንም የቀረ የኅብረተሰብ ክፍል አልነበረም ማለት ይቻላል። ፍቅር ያሸነፈበት፣ ደማቅና እጅግ የተዋበ ሰልፍ ነበር!!


በኢትዮጵያ ፍቅር ነፍሳቸው የተማረከ፣ በእናት ምድራቸው የአንድነት የተጋድሎ ታሪክ ብሔራዊ ኩራት መንፈሳቸው ከፍ ያለ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በፍቅር ሸማ ጥበብ ደምቀው በደስታ እንባ የታጠቡበት ቀን ሰኔ 16 ዕለት ቅዳሜ!! በዚህ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የእናት ሀገራችንን ሰንደቀ ዓላማ በክብር ከፍ አድርገው የተሸከሙና የሚያውለበልቡ አርጋውያን አባቶችና እናቶች በእንባ እየታጠቡ የኢትዮጵያን አምላክ በደስታ ሲቃ ተውጠው ሲያመሰገኑ ማየት ልዩ የሆነ ስሜትን የሚያጭር ነበር። ይህ ፍቅር፣ ሰላም እና የይቅርታ መንፈስ በሀገራችንና በሕዝባችን መካከል ጸንቶ ይቀጥል ዘንድ የሁላችንም ኢትዮጵያውያን ጸሎትና ምኞት ነው።


‹‹Let Unity, Discipline and Peaceful Action become the Hallmark of Everything We Do! Viva Peace! Viva Democracy!›› (Nelson Mandela/Madiba)


‹‹አንድነት፣ ጨዋነትና ሰላምን መርሕ ያደረገ የለውጥ እንቅስቃሴ፤ በምናደርጋቸው በማንኛውም ድርጊታችን ዋና ቁልፍ ጉዳይ ይሁን! ቪቫ ለሰላም! ቪቫ ለዲሞክራሲ!››
ሰላም ለኢትዮጵያ! ሰላም ለሀገራችን!

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
48 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 921 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us