የኢትዮጵያ ፖለቲካ ድርሻ በአፍሪካ ቀንድ ሃገራት ዘንድ!

Wednesday, 18 July 2018 16:05

 

ከተፈሪ ብዙአየሁ ዶርሲስ (ዶ/ር)

…ካለፈዉ የቀጠለ

ባለፈዉ ሳምንት በአዲሱ አመራር እየተተገበረ ያለዉ የአፍሪካ ቀንድ ሃገራትን የማቀፍ እንቅስቃሴ በማድነቅ ‹የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለአፍሪካ ቀንድ ቀጠና እጅግ ወሳኝ ነው› በማለት ምክንያቱን ለማስቅመጥ ሞክሬአለሁኝ። እንዲያዉም ለሌሎች የአፍሪካ ቀንድ ህዝቦች ጋር እንደየጉርብትናቸው ከህዝብ አሰፋፈር እና ከመልክኣ-ምድር አቀማመጥ አንጻር ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር እምብርት መሆኗን በማዉሳት አንዳንድ ትንታኔዎችን ለመስጠት ሙከራ አድርጌ ነበር።

በተጨማሪም ከእነዚህ ጎረቤት ሀገራት ጋራ ኢትዮጵያ የሚኖራት መስተጋብር ለህልውናዋ ወሳኝ ባይሆኑም እንኳን በስኬትዋም ሆነ ውድቀትዋ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ስለሚኖራቸዉ የትላንት ማንነታቸውን እና የዛሬ ፍላጎታቸውን መለየት ለዛሬይቷ ብቻም ሳይሆን ለነገዋ ኢትዮጵያም እድገትም ሆነ ዉድቅት ወሳኝ ነው። ለዚህም ነዉ ኢትዮጵያ ለራስዋ ስትል እነርሱን የማቀፍ ስራ መስራትዋ የግድነው ብዬ ወደ ሌሎች ጉዳይ ያመራሁት።

የዛሬ ሳምንት ከተነሱት አስራ ሶስት ነጥቦች ዉስጥ ሁለቱን ጭብጦች በመንተራስ የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነቶች እጣ ፈንታን ለመዳሰስ እሞክራለሁ።

የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ዘርፈ-ብዙ እንደሆነ እና ብዙ አካላትን የሚያካትት ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከሰተ ያለዉ የትላንት ቁመናን ይዞ ብቅ እንዳላለ ይታወቃል። ምክንያቱም የትላንቱ ግንኙነት የአንድ ሀገር ጥቅምን የበላይነት ለማምጣት ተንተርሶ የሚመጣ ግንኙነት ወይንም በቅኝ ገዥዎቻቸዉ ስዉር ፍላጎት የሚመነጭ ግንኙነት አልያም በአካባቢዉ ላይ ጥቅም ኖሮአቸዉ ጫና ለመፍጠር በሚያንዣብቡት አካላት ተፅዕኖ የሚመጣ ግንኙነት እንደነበረ እሙን ነዉ። እንዲህ አይነቱ አካሄድ ከዚህ በኋላ እንደማቀጥል ሁሉም አካል የተረዳ ይመስለኛል። አሁን በለዉጥ ትግሉ በተፈጠረችዋ አዲሷ ኢትዮጵያ ይህ ጨዋታ እንደማያዋጣት ይመከራል። በጠ/ሚ/ሩ የሚመራዉ የአዲሱ አመራር የአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች ግንኙነት በዚህ ስሌት እንዳልሆነ ከድርጊቶቻቸዉ መረዳት አያዳግትም። በመቻቻል፤ በፍቅር እና ለጋራ ጥቅም አብረን የቀጣናዉን ሀገራት እናሳድግ የሚል እሳቤ ያለዉ ነዉ።

ሆኖም ግን የቀደመዉ አፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ለአሁኑ ዘመን ድርሻ አይኖረዉ ማለት የዋህነት ነዉ። ምክንያቱም ቢያንስ አሁን ላይ ያሉት የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት መሪዎች እና የሚከተሏቸው ርዕዮቶቻቸው የዚያን ዘመን አሻራ ሰለባዎች እንደሆኑ የሚታወቅ ነዉ። ምሳሌ ብንወስድ ኤርትራ ለ40 ዓመታት ለነጻነቷ ስትዋደቅ የኖረችዉ እና ከኢትዮጵያ በመገንጠል ራሷን የቻለችዉ የቀደሙት የቅኝ አጋዛዝ በእነርሱ ላይ የፈጠሩት ተጽእኖ እንደሆነ እሙን ነዉ። ሌላዉ የዛሬይቷ ኢትዮጵያ የምትከተለዉ ብሄርን መሰረት ያደረገዉ (Ethnic Federalism)ከእርስ በርስ ጭቆና እና የብሔሮች የባላይነት ተጽዕኖ ጋር ስትዋደቅ የኖረችዉ ተረጋግታ ይህን የዉስጥ ጉዳዮቿን ለማስተካከል እንዳትችል በየጊዜዉ በዉጭ ሃይላት በሚሰጧት የቤትስራዎች በመወጠርዋ ነዉ። ከዚህ ከብሔር ጭቆና ጋር ስትዋደቅ ስለኖረች ዘመናዊዉን ዲሞክራሲ ልታጣጥም አልቻለችም።

በመሆኑም ሁለቱም አካላት የዉጭ ሃይላት በሰጡአቸዉ ባሻከሙአቸዉ አጀንዳዎች የየግላቸዉን የቤት ስራ ባለመጨረስ ሲንገዳገዱ ኖረዋል። የሁለቱን ሀገራት ጉዳይ ጠርንፈዉ የያዙት ሀገራት ፍላጎቶቻቸዉ የተለያዩ ቢሆንም የተገለጡባቸዉ መንገዶች ጥቅሞቻቸዉን ለማስከበር ሲሉ በድካሞቻቸዉ እና በብርቱ ፍላጎቶቻቸዉ ቀዳዳ ገብተዉ ሀገራቱን ማቃቃር፤ ብሎም ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንዲያመሩ ማድረግ ነበር። ባለፈዉ ጊዜ እንደነሳሁት እነዚህ አካላት የተጠቀሙባቸዉ ስልቶች የሚከተሉትን ዉጤቶች ሀገራቱ እንዲያስመዘግቡ ዳርጎአቸዋል፡-

$1·         የእንግሊዝ እና የጣሊያን በቀይ ባህር ላይ ያላችው ፍላጎት በኢትዮጵያና በኤርትራውያን መካከል ያላባራ የነጻነት እና የድንበር ቁርሾ ጥሎ ማለፉ እና ኢትዮጵያን ወደብ አልባ ሀገር ማድረጉ፣

$1·         የግብጽ በአባይ ወንዝ ላይ ባለት ጥቅም የበላይነትዋን ለማስጠበቅ የምታደርገው እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ ተከትሎ ኤርትራ በግብጽ እንድትደገፍ እና የሁለቱም ትንኮሳ አለማባራቱ፣

ከዚህ የተነሳ ኤርትራ ነጻ ከወጣች ወዲህ እንኳን ሁለቱም ሀገራት የየግላቸዉን የዉስጥ ስራ ባለማጠናቃቅ የእርስ-በርስ ትንኮሳቸዉን ሲሰሩ ቆይተዋል። እንግዲህ ኤርትራ ህዝቦችዋን የምታኖርበትን ስታሰላ ከኢትዮጵያ ውጭ ሌላ የተሻለ አማራጭ ላይኖራት፤ ኢትዮጽያም ለወድብ ፍላጎትዋ ከኤርትራ ወደቦች ሌላ አማራጮች ቢታዩአትም ከፍቅር ይልቅ ምክንያቶችን በመደርደር ለኤርትራ ብርቱ ፍላጎት በርዋን ከመዝጋት ባለፈ ለመተሳሳብ የሰራችዉ አልነበረም። ትላንት ኤርትራውያን በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ የመንግስት መዋቅሮች፣ እና የደህንነት ተቁዋማት የነበራቸውን የበላይነት ከነጻነት በኋላ በእጃ-ዙር ለማስቀጠል ሲፈልጉ ኢትዮጵያ ከመገበያያ ገንዘብ ልዩነት ጀምራ እምቢተኝነት ማሳየት ስትጅምር ፍጥጫው ወደ ጦርነት አምርቶ ዘርፋ-ብዙ ኪሳራን አምጥቶአል። ውጤቱም ሲጨመቅ ኤርትራ ስለድንበር ኢትዮጵያ ደግሞ ስለወደብ ይሰሩት የነበረው ስዉር እና ግልጽ መናቆሮች 27 ዓመታትን ፈጅቶባቸዋል።

በሌላ በኩል ያ የቀደመው በውጭ አካላት የተፈጠረው የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ የተነሳ የኤርትራ ህዝብና መንግስት ነፃነት አልባ ሆነዉ በመኖራቸዉ ነፃ መሆን የሚሰጠዉን ጥቅም ማጣጣም ፈለጉ። በተፅእኖ ስር መሆን እና በነፃነት ስር ሆኖ ማቀድ እንዲሁም ሀገርን መምራት መካከል ከፍተኛ ልዩነት እንዳለዉ የታመነ ነዉ። ስለዚህ ይህንን ልዩነት ማወቅና በመፈለግ ከኢትዮጵያዉያን ወገኖቻቸዉ በሪፈረንደም ተለዩ። በዚህ 27 ዓመታት በነጻነት ኖረዋል። ከኢትዮጵያ ተለይተዉ ሲኖሩ 20ዉን አመታት ደግሞ በመንግስታት ጥላቻ ስር ስለኖሩ የነጻነቱ ልክ እና ስኬቱ ይለያይል። በእነዚህ ጊዜያት ዉስጥ ያሳለፉአቸዉን ብሎም ያሳኩአቸዉን እና ያጡአቸዉን መሰረታዊ እሴቶች ተለይተዉ መታወቅ አለባቸዉ ብዬ እላለሁኝ። ለነጻነታቸዉ የተዋደቁት ኤርትራዉያን ናቸዉ፤ ተለይተዉ የሄዱትም እነርሱ ናቸዉ።

በመሆኑም ከትጥቅ ትግሉ ጅማሬ አንስተዉ እስከነጻነነቱ ዘመን የነበረዉን ስኬቶቻቸዉን እና ያጡአቸዉን እሴቶች በሳይንሳዊ እና ዘመናዊ ጥናት በማስደገፍ ትርፋቸዉን እና ኪሳራዎቻቸዉን በመለየት ለቀጣዩ ዘመኖቻቸዉ እና ለትዉልዶቻቸዉ የወደፊት አቅጣጫ ማስቀመጥ ያለባቸዉ ይመስለኛል። ይህንን ጉዳይ ምርምር ማድረግ ከኤርትራዉያን ምሁራን እና ተመራማሪዎች ይጠበቃል። ኤርትራ እንደ ሀገር ከኢትዮጵያ ጋር ተደምራ ለመቀጠል የሚነሱ ስጋቶች እና ግልጽ መሆን ያለባቸዉ ጉዳዮች ነጥረዉ መዉጣት አለባቸዉ።

በአንዲት አረፍተ ነገር ‹ከአንግዲህ በኢትዮጵያ እና በኤርትራዉያን መካከል ድንበር አይኖርም› ብሎ የኢትዮጵያ ጠ/ሚ/ርዶ/ር አቢይ ሲናገሩ ከነፃነት በፊት 30 ዓመታት ከነጻነት በኋላ 27 ዓመታት የፈጀዉ መናቆር እና መገፋፋት በአንድ አረፍተ ነገር ሲቋጭ ስለድንበር፤ የነበረንን አመለካት ከሰዉልጅ መሰረታዊ ሰብዕና በላይ አለመሆኑን ሀገራቱን ለዚህ የዳረጉት በህይወት ላሉም ለሌሉም መሪዎቻችን የምላቸዉ ነገር ቢኖር ‹ይህ ሩህሩህ እና የፍቅር ሰባኪ ወጣት መሪ ትላንት በኖረላቸዉ› እስካሁን የባከነው የሰዉ የገንዘብ እና የጊዜ ሃብቶቻችን ሀገራትን ወደፊት የሚያስኬድ ስራ በተሰራበቸዉ ያስብላል።

በኢትዮጵያ አነሳሽነት አሁን የተደረገዉ እርቅ እና የጉርብትና መተሳሰብ ጉዳይ የኤርትራዉያን ፈጣን የሆነ ምላሾቻቸዉ ከልብ መሆኑ አንድ ነገር ያጭራል። የኤርትራ መንግስት እና ሕዝቦች የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝቦቻቸዉ እንደሚያስፈልጉአቸዉ ብቻ ሳይሆን ከዚህ ህዝብ ዉጭ መኖር እንደማይፈልጉ ዓይነተኛ ማሳያነዉ።

ይህ ሊሆን ‹ኢትዮጵያ ኤርትራን ማቀፍ› እና ‹ኤርትራ ደግሞ ኢትዮጵያን ማክበር› መቻል በሚባሉ ስሌቶች መካከል ስልታዊ አቅጣጫዎች ከእንግዲህ እንደሚያስፈልጉ መታወቅ አለባቸዉ። ምክንያቱም ሁለቱም መንግስታት እና የሁለቱም ህዝቦች ሀገራት በመተቃቀፍ እና በመከባበር የጋራ ጥቅም መርህ ላይ የተመሰረተ የሀገራት ግንኙነት እጅግ ያስፈልጋቸዋል። እነዚህ ማቀፍ መታቀፍ፤ ማክበር እና መከበር የሚባሉ ስሌቶች ሰፊ ትንታኔ ቢፈልጉም ስልት ሊበጅላቸዉ ይገባል።

ትላንት ኤርትራዉያን እንደ ኢትዮጵዊ ዜጋ በኢትዮጵያ ሲኖሩ በነበረበት ዘመን በታላላቅ የኢኮኖሚ፤ የፖለቲካ፤ የትምህርት ተቋማት ዉስጥ በነበራቸዉ የበላይነት ሌላዉ ህዝብ ወደ እነርሱ ሊጠጋ በማይችል ሁኔታ አቅም የማሳጣት ስራ ዛሬ ላይ ቆመን መደገም እንደሌለበት ለኢትዮጵያ ህዝብ ዋስትና ያስፈልጋል። በደም የተሳሰሩ ህዝቦች በሚል እሳቤ ሌላዉን አቅም የማሳጣት ስራ ዛሬ ላይ ከደረሱበት ተምረዉ የመለሱ ከሆነ እሰየዉ። አለበለዚያም ሁለቱ ህዝቦች ዳግም ሌላ ድንበር እንዳይፈጥሩ በመተቃቀፍ እና በመከባር ስሌት ከወዲሁ ሊዳኛቸዉ የሚችል አቅጣጫ መጠቆም   የግድ ነዉ።  

ኢትዮጵያ የራስዋን የዉስጥ ስራ ሰርታ ባትጨርስ ሁለቱንም በአንድነት የማስኬድ አቅም አለኝ፤ እችላለሁኝም በማለት የጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ግንኙነትን ከቀጠናዉ ሀገራት ጋር ለመስራት ፈር ቀዳጅ እና ምሳሌነቱ አለምን ያስደመመ ስራ መስራት ጀምራለች። በዚህ ጉዳይ ላይ ጠ/ሚ/ሩን ጨምሮ አዲሱ አመራር ሊመሰገንም፤ ሊበረታታም ይገባል። ኢትዮጵያ የቀጣናዉን ሀገራት የማቀፍ እና የማስተሳሰር አቅም አላት ወይ የሚያሰብል ጥያቄ ቢያጭርም ቀድሞዉኑ ቀጣናዉን በማመስ፤ በማስፈራርት እና በመደለል የኖረችበትን አቅሟን ወደዚህ ላይ በማዞር ብትሰራ የበለጠ ዉጤታማ የምትሆነዉ በሁለት ምክያቶች ነዉ።

1.  አማራጭ የባህር በሮችን በኤርትራ በኩል በማግኘት ኢኮኖሚዋን ታደላድላለች።

1.1. ብዙ ሩቅ ሳትሄድ ለምርቶችዋ ሰፊ የገበያ እድል ታገኛለች

1.2.ምርቶችዋን ለማሰራጨት ሰፊ የስራ እድሎችን ትከፍታለች

1.3.ከቀጠናዉ ሀገራት ርቃ ሳትሄድ ሌሎች አቅርቦቶችን ታገኛለች

1.4.ሰጥቶ በመቀበል መርህ ራስዋንም ኤርትራንም ተጠቃሚ ታደርጋለች

2.  የቀጠናዉ ሠላም ይጠበቃል

2.1. ለመቻቻል እና ተቀባብሎ አብሮ መኖርን ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትን ታስተምራለች

2.2.ያኮረፈ ፖለቲከኛ በሚያብበዉ መቀባበል ዉስጥ ይዋጣል

2.3.የጎሳ ፖለቲካ ጫናዉ ይቀንሳል

2.4.የባህል ዉርርስ ይካሄዳል

የሁሉም የቀጠናዉ ሀገራት በአንድም በሌላም የኢትዮጵያ ተጽዕኖ አለባቸዉ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ፖለቲካ እድገት ያበረከተችዉ አነስተኛ ሳይሆን ይልቁንም አደገኛ ነዉ። በተለይ ሁለቱም መንግስታቶቻቸዉ ተቀናቃኞቻቸዉን በማዳከም እና ለማጥፋት የሚያዉሉት የገንዘብ፤ ጊዜ እና የሰዉ ሃብት ለአፍሪካ ዲሞክራሲ ግንባታ ቢያዉሉት የተሻለች የተመረጠች ሀገራቸዉን መፍጠር በቻሉ ነበር። ጠላታቶቻቸዉን/ ተቀናነቃኞቻቸዉን ብለዉ የፈረጁአቸዉን ለማሳደድ ሲሉ በሌላ ሀገር ህልዉና ዉስጥ ጣልቃ ሲገቡ ይታዩ ነበር። በሌላ በኩል እነዚህን ተቀናቃኞቻቸዉን ያስጠልላሉ የተባሉትን ተቀናቃኞች እነርሱም አደራጅተዉ ያሰማራሉ። ኤርትራ አርበኞች ግንቦት 7 እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር መጠለያ በመስጠት ስትደግፍ የቀድመዉ ህወአት ኢህዴግ መር የኢትዮጵያ መንግስት በአንጸሩ የኤርትራን መንግስት ለማዳከም የማትፈነቅለዉ ድንጋይ አልነበራትም። ከዚህ ጫና የተነሳ ኤርትራ በሁሉም አቅጣጫ በማዕቀብ ስር ወድቃ ከአለም አቀፍ ማህበረ-ሰብ እንድትገለል ተደርጋ ፍዳዋን ስታይ ነበረ። ከእንግዲህ በኢትዮጵያ የዉስጥ ጉዳይ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከኢትዮጵ ህዝብ እና መንግስት ፍላጎት ዉጭ ፍላጎት መሄድ አይጠበቅባትም። ኢትዮጵም እንዲሁ። ሁለቱም ሀገራት እና መንግስታት ከዚህ ስህተቶቻቸዉ መማር ያለባቸዉ ነገር በሳይንሳዊ ምርምር መታገዝ አለበት እላለሁኝ።

ይህ ድርጊት ለዚህ ርእስ ለተመረጡት ኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የነበረዉ ክስተት ብቻ ሳይሆን የሁሉም የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ችግር ነዉ። አሁን ግን በሁለቱም ሀገራት መካከል የመተቃቀፍ እና የመተሳሰብ ደረጃ ላይ ሲደርሱ ማየት ለአፍሪካ ቀንድ እዉነትም ኢትዮጵያ እጅግ ታስፈልጋለች ያስብላል። ጅማሬዋ የሚበረታታም ነዉ። እንግዲህ ከዓመታት የከረረ ጥለኝነት በኋላ፤ የሰዉ እና የንብረት ዉድመት በኋላ ለመተራረም እና ያለፈዉን ቁርሾ መዘከር የሚደረግ ሙከራ ሌላ ስህተት ይፈጥራል። ሆኖም ግን ወደ ፊት አብሮ ለመስራት በሚያስችሉ እና ጠ/ሚ/ሩ ሁሌም እንደሚሉት በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ በማተኮር ጥቃቅን ልዩቶቻችንን እና ችግሮቻችንን ላለማጉላት አይኖቻችንን ከትላንትናዎቹ ስህተቶቻችን በማንሳት የበለጠ ልንሰራበት የሚያስችሉንን ሆኔታዎችን ማመቻቸት የግድነዉ። ስለዚህም ከሁለቱም ወገን መንግስታት ፓርቲዎች ነጻ የሆኑ የሁለቱን ህዝቦች አብሮነት የሚደግፉ በመተቃቀፍ እና በመከባበር ስሌት ላይ የሚሰሩ ገለልተኛ አካላት ያስፈልጉናል።

በኢትዮጵያ እና በኤርትራውያን መስማማት የማይደሰቱ ጥቅማቸዉ የተጓደለባቸዉ ጎረቤት ሀገራትም ሆኑ በቀጠናዉ ላይ በተጽዕኖ ፈጣሪነት የሚታወቁት የሚያመጡትን ጫና ሁለቱም ተቋቁመዉ ስምምነቱ መሬት እንዲረግጥ የሚከላከልለትን እንዲሁም ሃይ ባይ አካልም ያስፈልጋል።

መጪዉ ጊዜ ብሩህ ነዉ!¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
57 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 942 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us