የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ተጨማሪ የቤት ሥራዎች

Wednesday, 25 July 2018 13:24


በመኮንን ተሾመ ቶሌራ

(ዘ ገዳም ሰፈር)

ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዐብይ አህመድ ባዕለ-ሲመታቸውን በቀጥታ በቴሌቭዥን መስኮት እየተከታተልኩ ነበር። የቀጥታ ስርጭቱ ባበቃ በአስር ደቂቃዎች ውስጥ “የጠቅላይ ሚኒስትራችን እናት” የሚል ፅሁፍ ለማኀበራዊ ሚዲያ ጽፌ ነበር። ይህን ያደረኩት ከዚህ ቀደም እንደዚህ ሰውን የሚያመሰግን፣ ሰው ሰው የሚልና ለሰዋዊ ስሜት ቅርብ የሆነ መሪ አይቼ ባለማወቄ እንደሆነ በወቅቱ ገልጬ ነበረ። ይህ ፅሁፍ በጋዜጣም ታተሞ በርከት ያሉ አንባቢያን እንደወደዱት ገልጸውልኝ ነበር።

መቼም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ሰዋዊ ስሜት ያላቸው አንደበተ ርዕቱ እና የተሳካላቸው የአደባባይ ንግግር አዋቂ መሆናቸውን ሁላችንም አይተናል። በዚሁ ምክንያት ብዙዎች ተማርከውና ተደምመው የሠላም ጥሪያቸውን ተቀብለዋል።

እሳቸውም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በመላ ሃገሪቱ እየዞሩ ሠላምን ሰብከዋል፣ የታሰረ አስፈትተዋል፣ የተጣላ አስታርቀዋል በጐረቤት ሃገርና በወዳጅ ሃገሮችም በሚያስደንቅ ፍጥነት እየተጓዙ አብሮነታቸውን ለማሳመንና አጋር ለመሆን ጠይቀዋል፣ በዚህም ተሳክቶላቸዋል። በተለይ ሰሞኑን ከኤርትራ ጋር ያደረጉት የሠላም ግንኙነትና ግጭትን የመፍታት ሥራ ከፍ ያለ ዋጋ የሚሰጠው ነው። በዚህም እሳቸው ራሳቸው እንዳረጋገጡልን የኢትዮጵያ ተፈላጊነትና የአለም አቀፍ የገበያ ሁኔታ እየተሻሻለ ነዉ።

በኔ አመለካከት ባጠቃላይ የጀመሩት የሠላምና የፍቅር ዘመቻ በአለም አቀፍ ደረጃ ከሚጠቀሱት የሠላም፣ የእኩልነትና የመብት ተሟጋቾች ከነማርቲን ሉተር ኪንግ፣ ከነማህተመ ጋንዲ፣ ከነ ማልኮልም ኤክስ፣ ከነቦብ ማርሌ ተርታ እንዲሰለፉ የሚወስዳቸው መንገድ ላይ ያስቀመጣቸው ይመስለኛል። እሳቸውም ቀደም ሲል የሃገራችንን አርቲስቶች ሰብስበው በሚናገሩበት ወቅት እነ ማርቲን ሉተርን፣ እነ ማልኮልምን፣ እነ ቦብ ማርሌን እያነሱ ተምሳሌትነታቸውን ሲናገሩ የእነዚህ ሰዎች ተፅዕኖ ሊኖርባቸው እንደሚችል መገመት ችዬ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትራችን ማንንም ምሳሌ ያድርጉ፣ ከማንም በጐ ነገርን ይማሩ በዚህ ጊዜ እያደረጉ ያሉት ነገር በብዙዎች ተቀባይነትን አግኝቷል። ውጤትም እያፈራ ይገኛል።

ታዲያ ዛሬ ደግሞ ብዕሬን ላነሳ የወደድከት የተሾሙ እለት የተሰማኝን እንደገለፅኩ ሁሉ አሁንም ከዚህ በኋላ ሊያደርጉት ይገባል የምለውን በኔ አመለካከት ለመግለፅ ፈልጌ ነው።

እናም በአሜሪካን ሃገር እ.ኤ.አ. ከ1945 እስከ 1975 የሃገሪቱን የሲቪል መብቶች እንቅስቃሴ (Civil Right Movement) የመሩትን እነ ማርቲን ሉተርና እነ ማልኮልምን እንደመሰሉ ሁሉ ከዚህ በኋላ ከ1960 እስከ 1968 የኢኮኖሚ ሪፎርም እና ታላቅ ማህበረሰብ ‘’ Great Society’’ እውን ለማድግ የለፋትን ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲንና በሳቸው እግር የተተኩትን ሊንደን ጆንሰንን ቢመስሉ ተገቢ ይመስለኛል።

በ1963 ተወዳጁ ማርቲን ሉተር በዋሽንግተኑ ሰልፍ “March on Washington” ላይ “ህልም አለኝ” (I have a dream) የሚለውን ታላቅ ንግግሩን ካደረገ በኋላና የአሜሪካው ኮንግረስ በ1964 የሲቪል መብቶችን ህግ (Civil Rights Act) ካፀደቀ በኋላ እንዲሁም በ1960 ዓ.ም ጆን ኤፍ ኬኔዲ ከሪቻርድ ኒክሰን ጋር ዴሞክራሲያዊ በሆነ ምርጫ ተወዳድረው የኬኔዲን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ በሀገረ አሜሪካ በርካታ ለውጦችና ተስፋዎች መታየት ጀምረው ነበር።

በሰሜን አሜሪካ በዚያን ዘመን የተከሰቱ ነገሮች በሙሉ ከአሁኑ የሃገራችን ሁኔታ ጋር ፍጹም ተመሳሳይነት ነበራቸው ማለት ባይቻልም በተወሰነ መለኩ ልንማርባቸው የምንችላቸው ነገሮች በመኖሩ ባጭሩ መዳሰስ የሚያስፈልግ ይመስለኛል።

በወቅቱ በኢኮኖሚያዊና በማኀበራዊ ጉዳዩች ተሳትፎ ጥቂቶች ተጠቃሚ ሆነው ሌሎች የተገለሉበት፤ ፍትህ የተዛባበት ሁኔታ በስፋት ይታይ ነበር። በተለይም ጥቁር አፍሪካ አሜሪካውያን ከኢኮኖሚያዊና ከፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች የተገሉበትና ከፍተኛ በደል የሚደርስባቸው አግባብ ይስተዋል ነበር። ጥቂቶች የሰውን ጉልበት በተለይም የጥቁሮችን እየበዘበዙ ይከብሩ ስለነበር ብሶቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። ጾታዊ እኩልነትም ባለመኖሩ ምክንያት ሴቶች የአደባባይ ትግል ጀምረውም ነበር።

በዚያን ጊዜ የነበረው የአሜሪካ የእኩልነትና የፍትህ እጦት በዋነኝነት ከስርዓትና ከሕግ ክፍተቶች ጋር ይያያዝ ስለነበር በአሁኑ ሰዓት ሃገራችን ውስጥ ካለው እኩል ተጠቃሚነትና የዴሞክራሲ እጦት ችግሮች ጋር ፍፁም የሆነ ተመሳሳይነት እንደሌለው እሙን ነው።

በዚያን ዘመን በአሜሪካ ነጮችና ጥቁሮችን፣ ወንዶችና ሴቶችን፣ ሀብታሞችና ደሃዎችን እኩል ለማረግ በ1964 ዓ.ም. የፀደቀው የሲቪል መብቶች ህግ እና ሌሎችን ህጐች አርቅቆ ማፅደቅ ተገቢ ነበር። ከዚህ አንፃር በኛ አገር በአሁኑ ሰዐት ብዙም በህግ ክፍተት ባናሳብብም በዚያን ዘመን በአሜሪካ ፖለቲካዊ፣ ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን ለማምጣት የተጠቀሙበትን ዘዴች መመልከተ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

የምርጫ ህግ፣ የእስረኞች መብትና የፍትህ ስርዓት

በ1960ቹ በአሜሪካን ከተደረጉ ጠቃሚ እርምጃዎች በከፍተኛ ፍርድ ቤቱና በአቃቤ ህጉ የተወሰዱት ዋነኞቹ ናቸው። በወቅቱ ዋና አቃቤ ሕግ በነበሩት በኤርል ዋረን አማካኝነት የሲቪል መብቶችን እና ነፃነቶችን፣ የምርጫ ህጐችን እንዲሁም የግለሰቦችን መብቶች የተመለከቱ የህግ እርምጃዎችና ማቫሻያዎች ተወሰዱ። በወቅቱ በሀገሬው ህዝብ የዋረን ፍርድ ቤት “Warren Court” በመባል የሚታወቀው ተቋም በማኀበራዊ፣ ሀይማኖታዊና ፖለቲካዊ የሆኑና አጨቃጫቂ የነበሩ ጉዳዩችን ባደረገው ሪፎርም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲፈቱ አድርጓል። ምርጫን በተመለከተም በተለይም ፍርድ ቤቱ “አንድ ሰው አንድ ድምፅ” የሚለውን ዐብይ ፍልስፍና አፅድቆ በሀገሪቱ የምርጫ ስርዓት እንዲሰራበት አድርጓል።”

ከዚህ አንፃር በአሁኑ ጊዜ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋትና የፖለቲካ ኃይሎችን በስፋት ማሳተፍ ስለሚያስፈልግ በዚሁ ዘርፍ በተለይ የምርጫ ስርዓቱ አሳታፊና አመቺ እንዲሆን መስራት ያስፈልጋል።

በአሜሪካን ሃገር በዚያን ዘመን ማለትም በ1963 ዓ.ም. ፕሬዝዳንት ኬኔዲን የተኩት ጆንሰን በቀጣዩ ዓመት በ1964 ዓ.ም. በምርጫ መሳተፍና ማሸነፍ ይጠበቅባቸው ነበር። ጆንሰን ያሰቧቸውን ትላልቅ ዕቅዶች ለማሳካትና ዳር ለማድረስ ይችሉ ዘንድ ወደ ሥልጣን በመጡ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚደረገውን ምርጫ ማሸነፍ ነበረባቸዉ። እናም ተወዳዳሪያቸው የነበሩትን ባሪ ጎልድዋተርን በብልሃት አሸንፈው በድህነት ላይ የጀመሩትን ዘመቻ ለመቀጠል ችለው ነበር።

የጆንሰን መንግስት በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን ትልቅ ርዕሰ ጉዳይ የሆነውን የእስረኞች ወይም የታራሚዎችና የተከሰሱ ሰዎችን መብት በተመለከተም ወሳኝ የሆኑ የህግ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ በማድረግ የሃገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ይበልጥ እንዲጠናከር አስችሏል።

ከዚህ አንፃር በሀገሪቱ የሚከሰስ ማንኛውም ሰው የመክፈል አቅም ቢኖረውም ባይኖረውም ጠበቃ የማግኘት መብት እንዲጠበቅለት የሚለውም ህግ በአሜሪካ ወጥቷል። በመሆኑም ማንኛውም በህግ ጥላ ስር ያለ ሰው ይህ መብቱ ሳይነገረው በፀጥታ ኃይሎች የተሰበሰበበት ማንኛውም ማስረጃ ዋጋ እንደማይኖረውም ታወጀ።

በዚያን ዘመን ከተለያዩ ህዝባዊ አመፆችና የመብት ትግሎች ወጥታ የተረጋጋች አሜሪካን ለመገንባት የተደረገው የፍትህ ስርዓት እና የዳኝነት ነፃነት ማሻሻያ ወሳኝ ሚና እንደነበረው ማስተዋሉ ለሁላችንም እንደ አንድ ትምህርት የሚወሰድ ይመስለኛል።

በተመሳሳይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በአጭር ጊዜ ውስጥ የምርጫ ውድድር የሚጠብቃቸው ከመሆኑም በላይ በአጠቃላይ ለፖለቲካ ኃይሎች አመቺ የፖለቲካ ምህዳር እንዲፈጠር መስራት ይኖርባቸዋል። ለዚህም ከምርጫ ህጉ እስከ ህገ-መንግስታዊ ማሻሻያ ማድረግ ሊያስፈልግ ይችል ይሆናል።

“ታላቅ ማኀበረሰብ” የመፍጠር ሥራዎች

በአሜሪካ በ1963 ዓ.ም ኘሬዚዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ወደ ዳላስ ቴክሳስ ግዛት በተጓዙበት ወቅት ሊ ሃርቬይ ኦስዋልድ በተባለ ግለሰብ ከተገደሉ በኋላ በእግራቸው የተተኩት ምክትል ኘሬዝዳንታቸው ጆንሰን የህዝቡን ህይወት ለመለወጥ ከፍተኛ ዘመቻ አድርገዋል። ጆንሰን በተለይ “ታላቅ ማኀበረሰብ” መፍጠር የሚል ዘመቻቸው በሃገሪቱ ታሪክ እስካሁን የሚታወስ ታላቅ ተግባር ነበር። ቀደም ሲል በኘሬዝዳንት ኬኔዲ የተጀመሩ የሲቪል መብቶች እንቅስቃሴዎችና የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራዎችን፣ ጠንካራ ሰራዊት የመገንባት እና በቀዝቃዛዉ ጦርነት (Cold War) አሸናፊ የመሆንን ኃላፊነት የወሰዱት ጆንሰን በራሳቸውም በኩል ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በድህነት ላይ ጦርነት “war on poverty” አዋጅ አውጥተው እንዲጸድቅ አስደርገው ለሀገራቸው ሕዝብ “It is time to declare an unconditional war on poverty” ሲሉ በድህነት ላይ ከፍተኛ ጦርነት መታወጁን አሰረዱ። ከምንም ነገር በላይ ድህነትን ለመዋጋት ቆርጠው መነሳታቸውን ግልጽ አደረጉ።

ከዚህ ጋር በተያያዘ እ.አ.አ በማርች 15 ቀን 1965 ዓ.ም በሃገራቸው ኮንግረስ ፊት ቀርበው የተናገሩት የሚታወስ ነው።

‘’I do not want to be the president who built empires, or sought grandeur or extended dominion. I want to be the presidentwho educated young children… who helped to feed the hungry… who helped the poor to find their own way….’’

“እኔ ኢምፓየሮችን የሚገነባ፣ ወይም ታላቅና የተስፋፋ ሃገርን የሚያልም ኘሬዝዳንት መሆን አልፈልግም፣ እኔ መሆን የምፈልገው ወጣቶችን የሚያስተምር፣ የተራቡትን የሚያበላ እና ድሆች ከችግር የሚላቀቁበትን መንገድ የሚያሳይ ኘሬዝዳንት መሆን ነው የምፈልገው” በማለት ፍላጐታቸውን ገለጹ።

ፕሬዝዳንት ጆንሰን ፍላጎታቸውን በመግለጽ ብቻ ሳይወሰኑ በርካታ የሪፎርም እርምጃዎችም እንዲካሄዱ አስቻሉ።

በተለይም አሁን በሃገራችን ትኩረት ከተሰጣቸዉ እንደ ኢንዱስትሪና የማምረቻ ተቋማትን ማዘመንና የግብርና ስራን ከማሻሻልን ባሻገር ህብረተሰቡን ለማሳደግና ድህነትን ለማጥፋት የሚጠቅሙ ስራዎች በመላው ሃገሪቱ እንዲሰሩ አደረጉ። ከእነዚህም ዋነኞቹ ስፋት ያለው የአአካባቢ ጥበቃ ማድረግና የሸማቾችን መብት ማረጋገጥ፣ የጤና ኢንሹራንስን መስጠት፣ የትምህርት አገልግሎት እንዲሻሻል፣ የስደተኞች ፖሊሲ እንዲረቅ፣ የበጎ ፈቃደኝነት እንዲስፋፋ መስራት እና ሌሎች ተጀምረው የነበሩ ማኀበራዊ ስራዎች እንዲከናወኑ ማድረግ ነበር።

በጎ ፈቃደኝነት የወጣቶች ሥራ ፈጠራ

በጎፈቃደኝነትሰዎችያለምንምክፍያበሀገርፍቅርስሜትተነሳስተውበአካልናበአእምሮወገኖቻችንን የምያገለግሉበት መንገድነው።

በጎፈቃደኞችበሚሰጡት የነጻ ማህበራዊናኢኮኖሚያዊአገልግሎትእርካታንየሚያጐናፅፉሲሆን፣ህብረተሰቡደግሞከአገልግሎቱየሚያገኛቸውጥቅሞችዘርፈብዙገጽታአላቸው። በኢትዮጵያበጎፈቃደኝነትየረጅምጊዘታሪክያለውናሰዎችለሰዎችባላቸውቀናልቦናየሚያካሂዱትየመደጋገፍሂደትነው።በጎፈቃደኝነት አካባቢንናሀገርንበማሻሻልረገድየራሱአዎንታዊሚናአለው።

በመሆኑም የዩኒቨርሲቲ፣የኮሌጆች፣የቴክኒክናሙያተቋማት፣እንዲሁምየሁለተኛናየመሰናዶትምህርትተማሪዎችን እንዲሁም ሌሎችበገጠርምሆነበከተማየሚገኙበጎፈቃደኛወጣቶችምበሚሳተፉበትመልኩ ቢሰራ ዜጎች በሀገር ግንባታ ሂደት የበኩላቸዉን መወጣትይችላሉ። ጎን ለጎንም የተጀመሩት የወጣቶች ስራ ፈጠራ ተግባራት ተጠናክረዉ እንዲቀጥሉ ቢደረግም ይበልጥ ዉጤታማ መሆን ይችላል

ከዚህ አንጻር አሜሪካንን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ወጣቶችን ለማነቃቃትና ሀገራቸዉን ለመገንባት እንዲሁም ለወጣቶች ስራ ፈጠራ የተጠቀሙበትና ዉጤታማ የሆኑበት ስለሆነ እኛም በጎፈቃደኝነትን በስፋት ልንሰራበት ይገባል

የአካባቢ ጥበቃና የሸማቾች መብት

የጆንሰን “ታላቅ ማኀበረሰብ” የመፍጠር መርሃ-ግብር በዋናነት አጠቃላይ የአሜሪካ ህዝብ ኑሮ እንዲሻሻል ያለመ ሲሆን ይህንንም ለማስቻል ከፍተኛ የንቃተ ህሊና ሥራ እንዲሰራ ተደርጓል። በተለይም በዚያ ዘመን (በ1960ቹ) በሀገሪቱ የአካባቢ ጥበቃና የሸማቾች መብትን የተመለከቱ ምርጥ ምርጥ መፅሐፍት ታትመው ለገበያ እንዲቀርቡ መደረጉ የራሱ አስተዋፅኦ እንደነበረው ይነገራል።

ለምሳሌም በወቅቱ በራቼል ካርሰን “Silent spring” (1962) በሚል ርዕስ የወጣው መፅሐፍ የኬሚካል ማዳበሪያና ፀረ-ተባይ እንዴት ሃገሩን እየበከለ እና ሸማቾች ላይ ተጽዕኖ እየፈጠረ እንዳለ ግልጽ ያደረገበት ሁኔታ እና በራልፍ ናዴር የተጻፈዉና “Unsafe at Any Speed” (1965) የተሰኘው መፅሐፍ የአውቶሞቲቪ ወይም የመኪና መጓጓዣው ኢንዱስትሪ በብክለት እንዴት ህዝቡን እየጐዳው እንዳለ የተገለፀበት ሥራ በሃገሪቱ የህግ ማዕቀፍ ውስጥ ለውጥ ማምጣት ችሎ ነበር።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም ከሀገሪቱ የንፁህ ውሃ አቅርቦት እና በትራፊክ ስነ ሥርዓት ጋር ዙሪያ “The Water Quality Act (1965)” “The Clean Water Restoration Act (1966)” እንዲሁም “ The National Traffic and Motor Vehicle Safety Act (1966)” የተሰኙ አዋጆች መዉጣታቸዉ በዘርፋ ከፍተኛ እድገት እንዲመዘገብ አግዟል። ከዚህ አንፃር በተለይ በሀገራችን ጥቅም ላይ የዋሉ መኪኖች ወደ ሀገር ውስጥ እየገቡ የሚፈጥሩት ችግርና በጣም ያረጁ መኪኖችና በሥራ ያሉበት ሁኔታ በሰውና በአካባቢ ደህንነት ላይ የሚያመጣው ተፅእኖ በቅጡ ያመላከታል። ለዚህም ተገቢ ምላሽ መስጠት ያሻል።

የትምህርት ጥራት

በጆንሰን “ታላቅ ማኀበረሰብ” የመፍጠር ሥራ ውስጥ ሌላ ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ለትምህርት ጥራት ነበር። በተለይም በአሜሪካ በዚያን ዘመን ድህነትን ለማስወገድና የማኀበረሰቡን ኑሮ ለማሻሻል ያስችላል የተባለው የ1965ቱ የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ድጋፍ አዋጅ መውጣቱ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደነበረው ይታመናል። ይህ “Elementary and Secondary Education Act” የተባለው የህግ ማዕቀፍ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ዜጐችን ጥራት ያለው ትምህርት እንዲያገኙ አስችሏል። በዚህም ኑሮአቸው እንዲቀየር ተደርጓል። ይህን አዋጅ ተከትሎም የፌደራል መንግስቱ በሀገሪቱ ላሉ በጣም በኑሮ ዝቅተኛ ለነበሩ ማኀበረሰቦች የተሟላ የትምህርት ቤቶች፣ ላይብረሪዎች፣ የቋንቋ ላቦራቶሪዎች እና ሌሎች የትምህርት አገልግሎቶች እንዲያገኙ ከፍተኛ ገንዘብ እንዲመደብ አስችሎ ነበር። በዚህም ሃገሪቱ የዜጐቿን የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻል በር ከፋች የሆነ ተግባር መፈጸም ችላ እንደነበር ይታያል።

የጤና ኢንሹራንስ

ፕሬዝዳንት ጆንሰን የማኀበረሰቡን የጤናና አጠቃላይ ደህንነት ለመጠበቅ ያደረጉት ሌላኛው ነገር ህብረተሰቡ የጤና መድህን ሽፋን እንዲኖረው ማድረግ ነበር። ይህም ጤነኛና ምርታማ ማኀበረሰብ እንዲፈጠርና አጠቃላይ ለውጥ እንዲመጣ በሚል ይህ “ታላቅ ማኀበረሰብ” የመፍጠር ራዕይ አካል የነበረው መርሃ ግብር በተለይ አዛውንቶችንና አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ ያደረገ ነበር።

አሁን አሁን በአገራችን የተጀመሩ መሰል የማኀበራዊ ደህንነት ተግባራት በተለይ ሙሉ ጊዜውን ምርታማነት ላይ ሊያውል የሚችለውን የወጣቱን ክፍልም በተዘዋዋሪ ያግዛል ተብሎ ስለሚታይ መጠናከር ይኖርበታል። በኛ ሃገር ማኀበራዊና ቤተሰባዊ ግንኙነቱ ጠንካራ በመሆኑ ብዙ ወጣትና አምራች ሃይል የሆኑ አዛውንትና አካል ጉዳተኞችን በጉልበትም በገንዘብም በመደገፍ ይሳተፋሉ። መንግስት ይህንን ጫና መካፈሉ ፋይዳው ከፍ ያለ ይሆናል።

ከላይ የተጠቀሱት ቁልፍ ተግባርት የጆንሰንን አስተዳደር “ታላቅ ማኀበረሰብ” ለማሳካት እንዳስቻሉ ሁሉ በኛም ሃገር በአሁኑ ወቅት በጠ/ሚ ዐብይ አህመድ ለሚመራው መንግስታችን ሙሉ በሙሉ በወቅቱ በአሜሪካ የተሰሩ ሥራዎች እዚህም ይሰራሉ ባይባልም አቅጣጫዎችን በማመላከትና ምሳሌ በመሆን ያገለግላሉ የሚል እምነት አለኝ።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
24 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 85 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us