You are here:መነሻ ገፅ»ዜና

 

በይርጋ አበበ

 

የወልቃይት ህዝብ የማንነት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ እና ወይዘሪት ንግስት ይርጋ የተመሰረተባቸው ክስ ተቋርጦ ከእሥር ተፈቱ።


የጸረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ ሶስትን በመተላለፍ ተቃውሞዎችን በመምራትና ማደራጀት በሚል ክስ ተመስርቶባት የነበረችው ወጣት ንግስት ይርጋ ትናንት ክሷ መቋረጡ ተገልጿል። በ2008 ዓ.ም በጎንደር ከተማ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ በቁጥጥር ስር ውላ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት ጉዳይዋ ሲታይ የቆየችው ተጠርጣሪዋ፤ የቀረበባትን ክስ እንድትከላከል ቀነ ቀጠሮ ተሰጥቷት የነበረ ቢሆንም ከቀጠሮው በፊት ክሷ ተቋርጦ ትናንት አመሻሽ ከእስር ወጥታለች።


ከዚህ ጋር በተያያዘ በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳያቸው ሲታይ የቆዩት የወልቃይት ህዝብ የማንነት ጥያቄ ኮሚቴ አስተባባሪ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር ቤት የተፈቱት ባሳለፍነው ሰኞ አመሻሽ ሲሆን፤ ከእስር ከወጡ በኋላም በርካታ ቁጥር ያለው የጎንደር ከተማ ህዝብ አቀባበል አድርጎላቸዋል። ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ከአማራ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ‹‹የጎንደር ህዝብ እና የአማራ ክልል መንግሥት ከጎኔ ሆነው ለዚህ ስላደረሱኝና ከእሥር እንድፈታ ስለረዱኝም አመሰግናለሁ›› ብለዋል። ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ እጃቸው ከተያዘበት ሃምሌ 2008 ዓ.ም ጀምሮ እስካላፈው ሰኞ የካቲት 12 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ በእስር ላይ ቆይተዋል።


በሌላ ዜና በእነ ተሻገር ወልደሚካኤል መዝገብ በሽብርተኝነት ክስ ተስርቶባቸው ጉዳያቸውን በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጄል ችሎት ሲከታተሉ የነበሩ 32 ተጠርጣሪዎች ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር ተፈተዋል። እስከ ትናንት ማክሰኞ ምሽት ድረስ በእነ ተሻገር ወልደሚካኤል መዝገብ ክስ ከተመሰረተባቸው 35 ተጠርጣሪዎች መካከል ሁለተኛ ተከሳሽና ሁለቱ የዋልድባ ገዳም መነኮሳት ክሳቸው አልተቋረጠም ነበር። ሁለቱን መነኮሳት ጨምሮ በዚህ መዝገብ ጉዳያቸው ሲታይ የቆዩት ተጠርጣሪዎች ክስ የተመሰረተባቸው ባሳለፍነው ሰኔ 2009 ዓ.ም ነበር። 

 

በይርጋ አበበ

 

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና ሰማያዊ ፓርቲ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰሞኑን ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነቀፉ፡፡


ሁለቱ ፓርቲዎች ትናንት በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ‹‹አሁን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ የሚያስገድድ አስገዳጅ ምክንያት የለም፡፡ በተለይ የታሰሩ ፖለቲከኞች እየተፈቱ ባሉበት በዚህ ወቅት ይህን አዋጅ ማውጣት ለብሔራዊ መግባባት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ወደኋላ ይጎትተዋል›› ብለዋል፡፡ አሁን እረፍት ላይ ያለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ወደ ስራ ሲመለስ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚያቀርበውን አዋጅ ሊያጸድቀው አይገባም ብለዋል፡፡


መኢአድና ሰማያዊ በመግለጫቸው አክለውም ‹‹ህዝቡ እየጠየቀ ያለው የስርዓት ለውጥ እንጂ የጠቅላይ ሚኒስትር መነሳት አይደለም፡፡ በመሆኑም ኢህአዴግ የህዝቡን ጥያቄ ሊቀበል እንጂ በለመደው ጥገናዊ ለውጥ ስልጣኑን ይዞ ለመቀጠል የሚያደርገው ጥረት ለአገሪቱም ለራሱ ለኢህአዴግም አይበጅም›› በማለት ገልጸዋል፡፡


ሁለቱ ፓርቲዎች ኢትዮጵያ አሁን ከገጠማት ችግር እንድትወጣ ሁሉን አቀፍ ውይይት እንዲደረግ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ‹‹ኢህአዴግ በያዘው መንገድ ለውጥ አይመጣም›› ብለዋል፡፡

 

በሰሞኑ በኢትዮጵያ የጣለውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ አውሮፓ ህብረት እንደዚሁም በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኢምባሲ መግለጫ አውጥተዋል። በአውሮፓ ህብረት ቃል አቀባይ በኩል የተለቀቀው ይሄው መግለጫ በኢትዮጵያ ያሉ ሥጋቶችን በማተት ምክሮችንም ለግሷል።

  የህዝቡን ቅሬታ ለመፍታት በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የተጀመረውን አዎንታዊ እንቅስቃሴን ለማስቀጠል አዲሱ መንግስት በሙሉ አቅሙ ሊሰራ የሚገባ መሆኑን መግለጫው አመልክቷል። ጉዳዩ በሚመለከታቸው ኃላፊዎች፣ ተቃዋሚዎች፣ የሚዲያ አካላት፣ ሲቪል ሶሳይቲ መካከል የሚደረግ ገንቢ ውይይትም በሀገሪቱ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም የሚያመጣ መሆኑን መግለጫው ጨምሮ ያትታል።

ሆኖም አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሀገሪቱ መልሶ መታወጁ ግን ሁኔታዎችን አስቸጋሪ የሚያደርግ መሆኑን ያመለከተው ይሄው መግለጫ በተቻለ መጠንም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጊዜ እንዲያጥር እንደዚሁም በዚሁ አዋጅ ውስጥም በኢትዮጵያ ህገ መንግስት የተቀመጡት የዜጎች ሰብአዊና መሰረታዊ መብቶች እንዲከበሩ የጠየቀ ሲሆን ሁከቶችም ቢሆኑ እንዲወገዱ ጠይቋል።

መግለጫው በማጠቃለያውየአውሮፓ ህብረት ሁሉም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ተዋንያን አካላት ለዲሞክራሲያዊና  የተረጋጋች ኢትዮጵያ በጋራ እንዲሰሩ ማበረታቱን ይቀጥላልበማለት ሀሳቡን አጠቃሏል።

በተመሳሳይ ዜና በኢትዮጵያ የተከሰተውን የፖለቲካ አለመረጋጋት እንደዚሁም የኢትዮጵያ መንግስት በተለያየ ምክንያት የታሰሩ ዜጎችን መፍታት መጀመሩን ተከትሎ በተከታታይ ድምፁን ሲያሰማ የነበረው በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኢምባሲ ከሰሞኑ የታወጀውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅንም በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መታወጅ ተከትሎ ኢምባሲው ያወጣው መግለጫ አዋጁ እንደ መሰብሰብና ሀሳብን በነፃነት መግለፅ በመሳሰሉ መሰረታዊ የዜጎች መሰረታዊ መብቶች ላይ ገደብን የሚጥል በመሆኑ በሀሳቡ ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በፅኑ የማይስማማ መሆኑን ገልጿል። ኢምባሲው በመግለጫው ጨምሮምከተፈጠረው ሁከት ጋር በተያያዘ የኃላፊዎችን ሥጋት የሚረዳ መሆኑን ገልፆ፤ ይሁንና መፍትሄው መብትን መገደብ ሳይሆን የበለጠ ነፃነትን መፍቀድ ነውብሏል።

የወለኔ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ወ.ህ.ዴ.ፓ) የወለኔን የማንነት ጥያቄ በማቅረባቸው ብቻ ለእስር የተዳረጉ አባሎቹ መንግሥት በገባው ቃል መሠረት በይቅርታ ወይንም በምህረት እንዲለቀቁለት ጥያቄ አቀረበ።

 

ፓርቲው ጥያቄውን በጹሑፍ ለደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አስተዳደር የጸጥታና የፍትሕ ቢሮ በቅርቡ ማቅረቡን የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ አብዲ ተማም ለሰንደቅ ጋዜጣ አስታውቀዋል።


ወ.ህ.ዴ.ፓ በምርጫ ቦርድ በ1999 ዓ.ም ተመዝግቦ የሚንቀሳቀስ ሕጋዊ ፓርቲ መሆኑን ያስታወሱት አቶ አብዲ ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ የአገሪቱን የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ለማስፋትና ዴሞክራሲውን ከማጎልበት አንጻር እስረኞችን ለመፍታት የወሰደው እርምጃ ፓርቲያቸው እንደሚደግፈው ጠቁመዋል።


በክልሉ በጉራጌ ዞን በገደባኖ ጉታዘር ወለኔ ወረዳ በ2004 ዓ.ም የወለኔ የማንነት ጥያቄ መነሻነት ግጭት ተቀስቅሶ የተወሰኑ የፓርቲው ከፍተኛ አመራርና አርሶአደር አባሎቻቸው የመንግስት መዋቅር አፍርሰዋል፣ ሕዝቡን አሳምጸዋል፣ ያልተፈቀደ ስብሰባ አድርገዋልና የመሳሰሉ ምክንያቶችን በመጥቀስ ከ70 በላይ የፓርቲው አባሎች ታስረው እንደነበር አቶ አብዲ አስታውሰዋል። ሆኖም የፓርቲው ከፍተኛ አመራር በፍርድ ቤት በነበረው ክርክር በነጻ እንዲሰናበቱ መወሰኑን ተከትሎ የታሳሪዎች ቁጥር ቀንሷል ብለዋል። የተቀሩ ታሳሪዎች ከ3 እስከ 15 ዓመት እስር ተፈርዶባቸው የእስር ጊዜያቸውን ጨርሰው ከወጡት ሌላ የ65 ዓመት አዛውንት ጨምሮ 11 ያህል የፓርቲው አባላት አሁንም በእስር ላይ ናቸው ብለዋል።


በአሁኑ ሰዓት በወልቂጤ እና በወሊሶ ማረሚያ ቤቶች ከሚገኙ እስረኞች መካከል አቶ ደንበል መሀመድ፣ አቶ ታለግን አወል፣ አቶ ምላዙ ቲጃን፣ አቶ ናስር ሰኢድ፣ አቶ ዙቢር ሁሴን፣ አቶ ጀማል ገረመው፣ አቶ ሙሁዲን አብዱልበር፣ አቶ አረብ ቆሬቻ፣ አቶ በድሩ ኡመር፣ አቶ ምእራጅ ሁሴን፣ አቶ ዝይን ቦንሳ መሆናቸውን የፓርቲው ሊቀመንበር አረጋግጠዋል።


ወ.ህ.ዴ.ፓ በእስር ላይ የሚገኙ ስማቸው የተጠቀሱት አባሎቹ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት በመስጠት የይቅርታው ተጠቃሚ ያደርጉዋቸው ዘንድ በይፋ ጠይቋል።


የወለኔ ሕዝብ የራሱ ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ወግ ያለው ማህበረሰብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በሕገመንግሥቱ ለሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች የተፈቀደው ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንዲረጋገጥለት አሁንም ሠላማዊ ትግሉን መቀጠሉን አቶ አብዲ ጠቁመዋል። 

 

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረንስ (ኦፌኮ) ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚደንት አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ሰባት የፓርቲው አባላት የተመሠረተባቸው ክስ ተቋርጦ በትላንትናው ዕለት ከእስር ተለቀዋል።


ከእስር የተለቀቁት የኦፌኮ አባላት አቶ በቀለ ገርባ፣ ጉርሜሳ አያና፣ አዲሱ ቡላላ፣ ደጀኔ ጣፋ፣ ጌቱ ጋሩማ፣ ተስፋዬ ሊበን እና በየነ ሩዳ ናቸው።


የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በቅርቡ በወሰነው መሠረት በሁከትና ብጥብጥ፣ በሽብር እንዲሁም በሀይማኖት አክራሪነት ተሳትፈዋል በሚል ተከሰው የተቀጡ እና ጉዳያቸው በክስ ሒደት ላይ ያሉ ተከሳሾች ክስ የማቋረጥ እና ይቅርታ የማድረግ ተግባር ሲከናወን መቆየቱ ከፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተገኘ ዜና ጠቁሟል።


የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በእነ አቶ በቀለ ገርባ ላይ የተጀመረው ክስ እንዲቋረጥ መወሰኑን ከትናንት በስቲያ ሰኞ ዕለት ማስታወቁ የሚታወስ ነው። ሆኖም ግን ተጠርጣሪዎቹ በችሎት ጉዳያቸውን በሚከታተሉበት ጊዜ በችሎት መድፈር እያንዳንዳቸው የአንድ ዓመት እና የስድስት ወር ቅጣት የተጣለባቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ጉዳያቸው በፌደራል የይቅርታ ቦርድ እንዲታይ ግድ ሆኗል። የይቅርታ ቦርዱ የውሣኔ ሃሳብ ለሀገሪቱ ርዕሰ ብሄር ቀርቦ በመፅደቁ እሥረኞቹ በትናንትናው ዕለት ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሊቀላቀሉ በቅተዋል።

 

ባለፈው ሰኞ እና በትላንትናው እለት የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በበርካታ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ተከታታይ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል፡፡ የተቃውሞ ሰለፍና አድማ ከተካሄደባቸው ከተሞች መካከልም ሻሸመኔ፣ ነቀምቴ፣ አምቦ፣ ወሊሶ፣ ጅማ፣ ሐረር እና ቢሾፍቱ ይገኙበታል፡፡ በዚህ ተቃውሞና አድማ አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የሚያመሩ ዋና ዋና ዋና መንገዶች ተዘግተዋል፡፡


በክልሉ ያሉ በርካታ የንግድ ተቋማትም አገልግሎት መስጠት አቁመዋል፡፡ ከተለያዩ የተቃውሞ አካባቢዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚለቀቁ ተንቀሳቃሽ ምስሎችና ፎቶዎች የተካሂዱት የተቃውሞ ሰልፎች ወደ ሁከት አምርተው ጎማ ማቃጠል፣ መንገዶችን በድንጋይ መዝጋት፣ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት ማድረስና አንዳንድ የማምረቻ ተቋማትን ማቃጠል እንደዚሁም ንብረትን የመዝረፍ አዝማሚያዎች ታይተዋል፡፡


ከንግድ ተቋማት ጋር በተያያዘ አንዳንዶች ተቃውሞውን በመደገፍ ሌሎች ደግሞ ሁኔታውን በመፍራት እንደዚሁም በየአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ወጣቶች በደረሳቸው ማስጠንቀቂያ ነጋዴዎች ሱቆቻቸውን የዘጉበት ሁኔታ እንዳለ ከተወሰኑ አካባቢዎች የደረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡


ተቃውሞዎቹ ከአንዳንድ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ባለፈ በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ ከተሞችና አካባቢዎችም ተካሂዷል፡፡ ወለቴ፣ አሸዋ ሜዳ፣ ዓለም ገና፣ሰበታ፣ ሱሉልታና ለገጣፎ መሰል የአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ከተሞች ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፎችን ያስተናገዱ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ ከተሞች የነበሩት ተቃውሞዎችና አድማዎች በዚያው አቅራቢያ ባሉ እንደ ጀሞና ሀይሌ ጋርመንትን የመሳሰሉ አካባቢዎችም የተቃውሞው ደመና እንዲያጠላባቸው አድርጓል፡፡


በተያያዘ ዜና የአሜሪካ መንግስት ዜጎቹ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል የሚያደርጉት ጉዞ በተመለከተ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳሰበ።


የአሜሪካ መንግስት የኮንሱላር ጉዳዮች ከትላንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ በሁለቱ ክልሎች አድማ መኖሩን፣ አዲስ አበባን ከሌላ ወደኦሮሚያ ከተሞች ጋር የሚያገናኙ መንገዶች መዘጋታቸውን፣ የትራንስፖርት አገልግሎት መቋረጡን በመጥቀስ ዜጎች ወደእነዚህ አካባቢዎች የሚያደርጉትን የጉዞ መርሃ ግብር ቢቻል ወደሌላ ጊዜ እንዲያስተላልፉ ሲል መክሯል።

 

“የሥራ ማቆም አድማን በማሳበብ በኦሮሞ ስም የግለሰቦች እና የመንግስትን ሀብት የመዝረፍና ማውደም ተግባራት እየተፈጸመ ነው”

ዶክተር አብይ አህመድ
የኦህዴድ ጽ/ቤት ኃላፊ

 

የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር አብይ አህመድ በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች መንገድና የንግድ ተቋማትን መዝጋት ከዛሬ ጀምሮ እንዲቆም ጥሪ አቀረቡ።


ዶክተር አብይ ትላንት በሰጡት መግለጫ፣ “ህዝብ አንድ ላይ በመደራጀት ሰላማዊ በሆነ መንገድ የራሱን መንግስት ማስገደድ እና ጫና በመፍጠር የተለያዩ ጥያቄዎችን ማንሳት በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ ወሳኙ ነገር ነው ብለዋል። አያይዘውም፣ ሆኖም ግን ማንኛውንም ጥያቄ በምን መልኩ መቅረብ እንዳለበት እንዲሁም ግራ እና ቀኙን አስተውሎ መመልከት እና ማሰብ ያስፈልጋል ነው ያሉት። ህዝብ እና የሀገርን ሀብት በማይጎዳ መልኩ መሆን ይገባዋል ሲሉ ዶክተር አብይ አሳስበዋል።


በአሁኑ ወቅት ከሥራ ማቆም ጋር ተያይዞ እየተነሱ ካሉ ጥያቄዎች ውስጥ “የታሰሩ ሰዎች ይፈቱልን” የሚል ጥያቄ እየተነሳ መሆኑንም ዶክተር አብይ አስታውሰው፤ ይህን ጉዳይ አመራሩ ከጥልቅ ተሃድሶው በኋላ ዋና ስራው አድርጎ በመውሰድ በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች ተለቀው በተለያዩ የልማት ስራዎች እንዲሰማሩ ለማድረግ መወሰኑንም ነው ይፋ አድርገዋል።


“እስር ከበዛ ህዝብ ይቸገራል፤ ማደግም ሆነ መለወጥ አይችልም” ያሉት ዶክተር አብይ፣ “ስለዚህም የእስረኞች መለቀቅ ጉዳይን ዋነኛ አጀንዳችን በማድረግ እየሰራን ቆይተናል” ብለዋል።


አጀንዳ ብቻ ሳይሆን ተጨባጭ ስራዎች መስራት እንደተቻለ ያስታወሱት ዶክተር አብይ፣ ከጥልቅ ተሃድሶው ወዲህ በኦሮሚያ ክልል ስልጣን ስር የነበሩን ከ30 ሺህ በላይ ሰዎችን ከእስር መፍታት መቻሉንም አስረድተዋል።


የፌደራል መንግስት መስራት ባለበት ጉዳይ ላይም ድርጅታቸው ጠንካራ ትግል ማካሄዱን እና በፌደራል ደረጃ የተሰሩ ሥራዎች መኖራቸውን በማሳያ አስቀምጠዋል፤ ይኸውም፣ ጉዳያቸው በፌደራል ደረጃ እየታየ ካሉ ሰዎች ውስጥም ከግማሽ በላዩ ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር እንዲፈቱ መደረጉን አንስተዋል።


ዶክተር አብይ ከስራ ማቆም አድማ ጋር በተያያዘ እንደተናገሩት፣ “አሁን ላይ ድርጅቱ ህዝቡን የሚጠቅሙ ታላላቅ እርምጃዎችን መውሰድ በጀመረበት ወቅት የሥራ ማቆም አድማን በማሳበብ በኦሮሞ ስም የግለሰቦች እና የመንግስትን ሀብት የመዝረፍና ማውደም ተግባራት እየተፈጸመ መሆኑንም” ገልጸዋል።


ከዚህ ባለፈም በክልሉ የሚገኙ ብሄር ብሄረሰቦችን ላይ ጥቃት መፈጸም፣ የፀጥታ አካላት ላይ ጉዳት የማድረስ እና መሰል ተግባራት እየተፈፀሙ መሆኑንም በመግለጫቸው አንስተዋል። ይህ በማንኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የለውም ያሉት ዶክተር አብይ፣ ይህንን እንቅስቃሴ ከለላ በማድረግ ጉዳት እያደረሱ ያሉ አካላት እንዳሉና ጉዳዩ በህግ የበላይነት መስተካከል እንዳለበት አስረድተዋል።


በኦሮሚያ ውስጥ ማንኛውም ሰው ህጋዊ በሆነ መንገድ ሰርቶ የመኖርና የመንቀሳቀስ መብት እንዳለውም ነው የገለጹት ዶክተር አብይ፣ አሁን እየተነሱ ባሉ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የክልሉ መንግስት ትኩረት በመስጠት እየሰራ ነው፤ ውሳኔ ላይም ተደርሷል ብለዋል።


ስለዚህ ወጣቶች ሁሉንም ነገር በትዕግስት መጠባበቅ እንዳለባቸውና መንገድ መዝጋት እና ሰዎች የንግድ ተቋማቸውን እንዲዘጉ ማስገደድ ትክክል አይደለም ነው ያሉት ዶክተር አብይ።


ዶክተር አብይ በሰጡት ማሳሰቢያም፣ አሁን እየተካሄደ ያለው ተግባር በአስቸኳይ መቆም አለበት ብለዋል።


አሁን እየተካሄደ ያለው ተግባር ወዳልተፈለገ አላማ ሊለወጥና የኦሮሞ ህዝብ እና ወጣቶችን ሊጎዳ ስለሚችል፣ የክልሉ ህዝብ እና ወጣቶች ከዛሬ ጀምረው ከስራ ማቆም ጋር የተያያዙ እንቅስቃሴዎችን ማስቆም አለባቸው ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

ለሁለት ግዜያት ያህል የእሳት ቃጠሎ ውድመት የደረሰበት ዘመናዊ የሕንጻ ኢንዱስትሪ ኃ/የተ/የግል ማህበር ያከናወነውን የመልሶ ግንባታ የምረቃ ሥነሥርዓት ቅዳሜ የካቲት 3 ቀን 2010 ዓ.ም ኩባንያው በሚገኝበት ገላን ከተማ አከናወነ።

 

በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሥር የሚገኘው ዘመናዊ የሕንጻ ኢንዱስትሪ ኃ/የተወሰነ የግል ማህበር በገላን በሚገኙ ፋብሪካዎቹ ላይ በመጋቢት ወር 2007 ዓ.ም እና በሰኔ ወር 2009 ዓ.ም የቃጠሎ አደጋ ገጥሞት የነበረ ሲሆን የደረሱትንም ጉዳቶች መልሶ ለመጠገን ለመጀመሪያው ቃጠሎ 124 ሚሊየን ብር፣ ለሁለተኛው ቃጠሎ 16 ሚሊየን ብር በድምሩ 140 ሚሊየን ብር አውጥቷል።


ዶ/ር አረጋ ይርዳው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር በሥነሥርዓቱ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ኩባንያው የቃጠሎ አደጋ በገጠመው ወቅት ከፍተኛ ርብርብ ላደረገው የገላን ከተማ ሕዝብ፣ የአስተዳደር፣ የፖሊስና መከላከያ ሠራዊት አባላት እንዲሁም ለኩባንያው ሠራተኞችና የማኔጅመንት አባላት ምሥጋና አቅርበው ሠራተኛው በቀጣይ መሰል አደጋ እንዳይገጥም በንቃት ኩባንያውን እንዲጠብቁ አሳስበዋል።


የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ይድነቃቸው መኮንን በበኩላቸው ኩባንያው በሁለቱም ቃጠሎዎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት የነበረ ቢሆንም አንድም ሠራተኛ ሳይቀነስ፣ የክፍያ ችግር ሳይገጥም እና ለሠራተኛው የሚሰጠው ዓመታዊ ጭማሪም ሆነ ልዩ ጥቅም ሳይቋረጥ ዳግም ድርጅቱን ወደነበረበት ለመመለስ መቻሉን አስረድተዋል። ኩባንያው ችግር በገጠመው ወቅት አስተዋፅኦ ያደረጉ የኩባንያው ሠራተኞች፣ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ አባል ድርጅት ሠራተኞች እንዲሁም የሠራዊቱ አባላትና ለአስተዳደር አካላት የምሥጋና ሽልማት ሰጥቷል።


ዘመናዊ የሕንጻ ኢንዱስትሪ ኃ/የተ/የግል ማህበር በአፋር ክልል የሚገኘውን የፊለር ፋብሪካ በመያዝ በሚያዚያ ወር 1987 ዓ.ም በ21 ሚሊየን ብር የተከፈለ ካፒታል የተቋቋመ እና በ1992 ዓ.ም የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ በዶ/ር አረጋ ይርዳው ሲቋቋም ከመሥራች አምስት ኩባንያዎች አንዱ እንደነበር ተወስቷል። ኩባንያው በገላን ከተማ 50 ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ አራት ፋብሪካዎችን ማለትም የቀለም ፋብሪካ፣ የኳርትዝ የወለል ንጣፍ ፋብሪካ፣ የኮንክሪት ማምረቻ ፋብሪካ እና የቀለም ጣሳ ፋብሪካዎችን ይዟል።


ኩባንያው በአሁኑ ወቅት ከ500 በላይ ሠራተኞችን በማቀፍ የተከፈለ ካፒታሉን ወደ 250 ሚሊየን ብር ያሳደገ ሲሆን የዓመት ሽያጩም ከግማሽ ቢሊየን ብር በላይ ደርሷል።

 

የቀድሞ የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት አለን ጆንሰን ሰርዲፍ ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር በማድረጋቸው ብቻ በአርአያነት ተመርጠው የ 5ሚሊዮን ዶላር የሞ-ኢብራሂም ፋውንዴሽን ተሸላሚ ሆኑ።

 

የሞ- ኢብራሂም ሽልማት በአፍሪካ የመልካም አስተዳደር ዕውቅና ላገኙ የሚሰጥ መሆኑ ይታወቃል።


ሚስ ጆንሰን ሰርሊፍ እ.ኤ.አ. በ1944 ወዲህ ላይቤሪያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ የሥልጣን ሽግግር ለመጀመሪያ ጌዜ የታየበትን የሥልጣን ርክክብ ባለፈው ወር ማድረጋቸው አይዘነጉም።


ላይቤሪያን ለ12 ዓመታት (ለሁለት የሥልጣን ዘመን) የመሩት ጆንሰን ሰርሊፍ የኖቤል ሠላም ሎሬት በመሆን የመጀመሪያዋ ተመራጭ አፍሪካዊት መሪ ሴት ተሸላሚ ሆነዋል።


እ.ኤ.አ. በ2006 የመሠረተው ሞ- ኢብራሂም ፋውንዴሽን ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር ለሚያደርጉ መሪዎች የተደላደለ ሕይወት እንዲመሩ የዳጎሰ የገንዘብ ሽልማት የሚያደርግ ቢሆንም ከጥቂት መሪዎች በስተቀር አብዛኛው ጊዜ ይህን የሚያሟሉ መሪዎች ማግኘት አዳጋች ሆኖበት ቆይቷል።

 

በይርጋ አበበ

 

“ማይንድ ፕላስ ማትስ” የተሰኘ የአካዳሚ ተቋም በስድስት ክልሎች የሂሳብ ትምህርት ውድድር ማዘጋጀቱን ገለጸ።


ድርጅቱ ለሰንደቅ ጋዜጣ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በውድድሩ አሸናፊ ለሚሆኑ ተማሪዎች እስከ አስር ሺህ ብር ሽልማት አዘጋጅቷል።


ውድድሩ በቅድሚያ በአዲስ አበባ ተጀምሮ በአምስት የክልል ከተሞች ማለትም መቀሌ፣ ባህርዳር፣ ድሬዳዋ፣ አሰላ እና አዳማ ውድድሮቹ የሚካሄዱባቸው ከተሞች ናቸው።


ማይንድ ፕላስ ማትስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሂሳብ ትምህርት ክፍል አንጋፋ ምሁራን የሚመሩት ሲሆን ስልጠናውን በተለያዩ የግል ትምህርት ቤቶችና የመንግስት ተቋማት ይሰጣል። “ከዚህ ቀደም በአውሮፓ እና ሩቅ ምስራቅ ሀገራት በሰፊው ጥቅም ላይ ውሎ ውጤት ያጣውን የሳሮባ (የሂሳብ ቃላዊ ስሌት) ስልጠና በመንግስት እና በግል ትምህርት ቤቶች በማስተዋወቅ ተማሪዎች በቀላሉ ውጤታማ የሚሆኑበትን ስራ ሰርቷል” ሲል ተቋሙ ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ አክሎ ገልጿል።


ተቋሙ አሁን ለማዘጋጀት ካሰበው አገር አቀፍ ውድድር በተጨማሪ ከዚህ ቀደም ለሁለት ጊዜያት በትምህርት ቤቶች መካከል አዘጋጅቶ ለአሸናፊዎች ሽልማት ማበርከቱን አስታውቋል።


በዚህ ውድድር ለመሳተፍ በየክልል ከተሞቹ የሚገኙ የግል እና የመንግስት ትምህርት ቤት ተማሪዎች በትምህርት ቤቶቻቸው በኩል ተመዝግበው የክልሎቹ ትምህርት ቢሮዎች ደግሞ የተወዳዳሪዎችን እና የትምህርት ቤቶቹን ስም አያይዞ ለአወዳዳሪው ተቋም በመላክ ነው። በዚህ መሠረትም በውድድሩ የሚሳተፉ ተማሪዎች በአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር አንደኛ ለሚወጣው ተማሪ አስር ሺህ ብር የሚሸለም ሲሆን ሁለተኛ ለሚወጣው ሰባት ሺህ ብር ሶስተኛ ለሚወጣው ደግሞ አምስት ሺህ ብር ተሸላሚ ይሆናሉ።

Page 1 of 102

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us