You are here:መነሻ ገፅ»ዜና

የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት፤ አቶ አማረ አረጋዊን ሰብሳቢ አድርጎ መረጠ

Wednesday, 13 January 2016 14:26

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት መስራች ጉባኤ ትናንት ማክሰኞ ጥር 3 ቀን 2008 ዓ.ም በአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የስብሰባ አዳራሽ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ አምስት የሥራ አስፈፃሚ አባላትን የመረጠ ሲሆን፤ የሪፖርተር ጋዜጣ ባለቤት የሆኑት አቶ አማረ አረጋዊን የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አድርጎ መርጧል።

በሥራ አስፈፃሚ ውስጥ የተካተቱት ወ/ሮ መዓዛ ብሩ በም/ሰብሳቢነት፣ አቶ አብርሃም ገ/መድህን በዋና ጸሃፊነት እንዲሁም አቶ መሰረት አታላይ እና አቶ ታምራት ኃይሉ በአባልነት ተመርጠዋል። ይህ ሥራ አስፈፃሚ አካል ከሚያከናውናቸው ስራዎች መካከል በከፊል፣ የምክር ቤቱን ሥራ አስኪያጅ ይሾማል፣ ይሽራል። የምክር ቤቱን ፖሊሲ ለማውጣት ወይም ለማሻሻል ጽሕፈት ቤቱ የሚያቀርባቸውን ሃሳቦች ተቀብሎ አስፈላጊ ሲሆን የራሱን አስተያየት ጨምሮ ውሳኔ እንዲሰጣቸው ለጠቅላላ ጉባኤ ያቀርባል። ለምክር ቤቱ ሥራዎች ማስፈፀሚያ ገቢ መኖሩን ያረጋግጣል፣ ገቢ የሚገኝበትን መንገድ ይቀይሳል። አስቸኳይ የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ የሚጠራበትን ምክንያት ሲያጋጥም ጥሪ እንዲደረግ ይወስናል።

አቶ አማረ ከተመረጡ በኋላ ባሰሙት ንግግር ከአስር አመት በፊት መንግስት አንድ የሚዲያ ሕግ አውጥቶ ነበር። አንዱ አንቀጽ የነበረው የሚዲያ ካውንስል ይቋቋም የሚል ነበር። በጊዜው የሚዲያ ሰዎች ተሰብስበን እባክህን መንግስት አንተ አታቋቁም ራሳችን እናቋቁማለን በማለት ይህን አንቀጽ ሰርዝልን አልን። መንግስትም ጥያቄያችንን ተቀብሎ፣ እናንተ የምታቋቁሙ ከሆነ ሰርዤዋለሁ አለ። ባለፉት አስርት አመታት በሄድነው ሂደት ይህቺ የመንግስት ቃል ተከብራ ዛሬ ለማቋቋም በቃን። በዚህ አጋጣሚም መንግስትን እናመሰግናለን” ብለዋል።

የዕለቱ እንግዳ የነበሩት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት ለመመስረት በመብቃታችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል። ሚኒስትሩ አይይዘውም፣  የእናንተ መጠናከር መደራጀት በሚዲያው ዘርፍ መንግስት አሳካዋለው ለሚለው እቅድ የሚኖራችሁ አስተዋፅዖ ከፍተኛ ነው። ይህም ሲባል መንግስት በራሱ ጊዜ ጫና ሳያደርግ በራሳችሁ ፈቃድ መንግስትን የሚያካትት ሂደት በመከተላችሁ ነው። የእናንተ ስኬት ቢያንስ ቢያንስ ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ራሱን የቻለ ትልቅ ሚና ስላለው ያንን ከማሳካት አንፃር የእናንተ ድርሻ ግምት የሚሰጠው ነው። አሁን ከእናንተ የሚጠበቁ ስራዎች አሉ። ይሄውም ፊርማቸውን ለምስረታው ያኖሩት የሚዲያ ተቋማትና ማሕበራት ቁጥራቸው የሚናቅ ባይሆንም ስራዎቻቹሁን ወደ ከፍተኛ የሙያ ደረጃ በማድረስ በበለጠ ሁኔታ የሚስፋፋበት ሁኔታ ይኖራል ብለን እናምናለን። ስለዚህም ማሕበራችሁ በሂደት ሁሉን አቀፍ እንዲሆን የሚቀራችሁን ስራዎች ማከናወን ይጠበቅባችኋል ሲሉ አሳስበዋል።

በመጨረሻም አቶ ጌታቸው የማሕበሩ ስራዎች የተቃኑ እንዲሆኑ በመንግስት በኩል አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ጉባኤውም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤትን ለማደራጀት በወ/ሮ ሚሚ ስብሃቱ አስተባባሪነት ሲሰሩ ለነበሩ ሁሉ በሰብሳቢው በአቶ አማረ አረጋዊ በኩል ምስጋና ቀርቧል።¾

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
1000 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us