You are here:መነሻ ገፅ»ዜና

የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ሥርጭት እንዲያሻቅብ አድርጓል

Wednesday, 21 December 2016 14:07

የተመጣጠነ ምግብ በበቂ ሁኔታ ማግኘት ባለመቻሉ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች የመጋለጥ እድል እንዲጨምር አድርጎታል ተባለ፡፡

 

ዓለም አቀፉ የስነ-ምግብ እና የአካል እንቅስቃሴ ሁኔታ ጆርናል በኢትዮጵያ ያደረገውን ጥናት ይፋ ባደረገበት ዘገባ እንደገለፀው፣ በሀገሪቱ ያለው የተመጣጠነ እና በቂ የሆነ ምግብ የማግኘት እድል አናሳ በመሆኑ ተላላፊ ባልሆነ በሽታዎች የሚያዙ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡ ከተመጣጠነ ምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ እንደ ስኳር ህመም፣ የልብ እና ልብ ነክ ህመሞች እንዲሁም የካንሰር ህመም ስርጭት በፍጥነት እየጨመረ መጥቷል፡፡ በ2015 በግሎባል በርደን ኦፍ ዲዝስ የተደረገ ጥናትን ጠቅሶ የዘገበው ጆርናሉ፣ በዚህ ዓመት ብቻ 285 ሺህ 301 የሞት አደጋዎች የተከሰቱት በቂ እና ተመጣጣኝ ምግብ ካለማግኘት ጋር ተያይዘው በተከሰቱ በሽታዎች ሳቢያ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በዚሁ ዓመት በተመሳሳይ ምክንያት 14 ነጥብ 9 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥም በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት በሚከሰቱ በሽታዎች ሳቢያ ህይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች ቁጥር በ25 ነጥብ 1 በመቶ እንዲሁም ለአካል ጉዳት የሚዳረጉ ዜጎች ቁጥር በ36 ነጥብ 2 በመቶ መጨመሩ ተገልጿል፡፡

 

በቂ እና ጥራቱን የጠበቀ የምግብ እጥረት ቀደም ብሎ ከነበረው የምግብ እጥረት ጋር ተደማምሮ በሀገሪቱ ያለውን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ስርጭት እንዲያሻቅብ አድርጎታል ብሏል ዘገባው፡፡ በ2013 በተደረገ ጥናትም በሀገሪቱ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ከተከሰቱ የሞት አደጋዎች መካከል ሩብ ያህሉ ከስነ-ምግብ ችግሮች ጋር የተገናኙ ናቸው ያለው ዘገባው፤ ከስነ-ምግብ ጋር ተያይዘው ከተከሰቱ አስር የሞት አደጋዎች ውስጥ ዘጠኙ በልብ እና ከልብ ህመም ጋር በተያያዘ የተከሰቱ ናቸው ብሏል፡፡ በጥናቱ ማረጋገጥ የተቻለውም ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ጋር ተያያዥነት ያላቸው የምግብ እጥረቶች የፍራፍሬ፣ እና አትክልት እጥረት፣ የዘር እህል እጥረት፣ በሶዲየም የበለፀጉ ምግቦች እጥረት፣ የባህር ምግብ እጥረት እንዲሁም የፋቲ አሲድ ይዘት ያላቸው የምግብ አይነት እጥረቶች ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑም ተገልጿል፡፡ ለተመጣጠነ እና በቂ ለሆነ ምግብ እጥረት የሚዳርጉ ነገሮችም የእንስሳት ተዋፅኦን ለመጠቀም ያለው ባህላዊ እና ማህበራዊ ተፅዕኖ እንዲሁም የባህር ምግቦችን እንደልብ ማግኘት አለመቻል እና በቂ የሆነ ገቢ አለመኖር ዋና ዋናዎቹ ተብለው ተጠቅሰዋል፡፡ 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
415 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us