You are here:መነሻ ገፅ»ዜና

በመሳለሚያ እህል በረንዳ በአደረጃጀት የተፈጠረው ልዩነት አወዛገበ

Wednesday, 28 December 2016 13:55

በመሳለሚያ እህል በረንዳ ተደራጅተናል በሚሉ እና አዲስ ማህበር በመሰረቱ፤ እንዲሁም በአብዛኞቹ ነባር ጫኝና አውራጆች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ከፍተኛ ውዝግብ ማስነሳቱን በስፍራው ተገኝተን ያነጋገርናቸው ሰራተኞች ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናገሩ። የወረዳው አስተዳደር በበኩሉ ከበረንዳው እህል ነጋዴዎች ጋር ማክሰኞ (ትናንት) በሚደረገው ስብሰባ ላይ ተመስርቼ ችግሩን ልፈታው ተዘጋጅቻለሁ ብሏል። እንደራጅ ብለው የሚቀርቡ ከሆነ በጥቃቅንና አነስተኛ መስፈርት መሠረት በፍጥነት እናደራጃቸዋለን ሲልም ምላሽ ሰጥቷል።

 

በእህል በረንዳው ለተፈጠረው ችግር መንስኤ ተብሎ የተቀመጠው 87 የሚሆን ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው በመምጣትና መንግስት ፍቃድ ሰጥቶናል በሚል ቀሪዎቹን የመጫንና የማውረድ ስራ የሚሰሩ የመሳለሚያ እህል በረንዳ ሰራተኞች ያገለለ ተግባር መፈፀማቸው፤ እንዲሁም እኛ ቀጥረን በስራችን እናሰራችኋለን በማለታቸው የተፈጠረ አለመግባባት እንደሆነ ባሳለፍነው ቅዳሜ (ታህሳስ 15 ቀን 2009 ዓ.ም) በአካባቢው በተደረገ የውይይት ስብሰባ ወቅት ሰምተናል።

 

የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የወረዳ 4 አስተዳደር በበኩሉ፤ ተደራጅተው ፍቃድ የሰጠዋቸው 87 ሰራተኞች በምንም አይነት የበላይ ሆነው እንዲሰሩ አላደረኩም ይላል። በአካባቢው በህገ ወጥነት የሚሰሩ አባላትን ማሳያ እንዲሆኑ ብለን ያደራጀናቸው 87 የሚሆኑ ወጣቶች ወደስራ ሲገቡ ነባሮቹን አስወጥተን አይደለም ሲሉ አቶ ሳሙኤል አባዲ የወረዳ አራት ምክትል ዋና ስራአስኪያጅ እና የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ኃላፊ ተወካይ ይናገራሉ።

 

በዕለቱ በተደረገው ውይይት ከ15ሺህ ያላነሱ ቤተሰቦችን ይወክላሉ የተባሉት ጫኝና አውራጅ ሰራተኞች ሁለት መሠረታዊ ሃሳብ አንስተዋል የሚሉት የወረዳው አስተዳደር ም/ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል አባዲ፤ ነባር ሰራተኞች ሆነን ሳለ፤ ተደራጅተን ብንመጣም ሰሚ በማጣታችን ተጎድተናል። በዚህም አዲስ ተደራጅተው በመጡ ሰዎች ስር እንድንሰራ ሆኗል። በዚህም የሚገባንን የጉልበት ጥቅም አላገኘንም የሚል ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ተደራጅተን ብንመጣም ተቀብሎ የሚያስተናግደን አካል አጥተናል የሚል እንደሆነ ሰምተናል። ይህንን የነባር ጫኝና አውራጅ ሰራተኞች ቅሬታ የወረዳው አስተዳደር እውነት ነው ብሎ የተቀበለው ሲሆን፤ በቀጣይም ግን ተደራጅተው ለመስራት ከመጡ በፍጥነት ለመቀበልና ለማስተናገድ ዝግጁ  መሆኑን ተናግሯል።

 

በአዲስ መልክ ተደራጅተው ወደስራ በመግባት በእህል በረንዳ ያለውን የእህል መጫንና ማውረድ ስራን በበላይነት በመስራት ፍቃድ አለን የሚሉት ወጣቶች በተለያዩ ጊዜያት ፀባያቸው ታርሞ ከማረሚያ ቤት የወጡ በመሆናቸውና ህጋዊ አሰራርን ተከትለው በመስራት የመጡ ናቸው። በአሁኑ ወቅት ግን በህጋዊ መንገድ ተደራጅተው ስራ ለመስራት በመፍቀዳቸው አደራጅተናቸዋል የሚለው አስተዳደሩ፤ ነገር ግን ነባሮቹን ሰራተኞች ዋጋ ተምነው የበላይ ሆነው እንዲያሰሩ አለመፍቀዱን አስተዳደሩ ደጋግሞ ይናገራል። ይህንንም ጉዳይ በጥልቀት ለመነጋገር በመሳለሚያ እህል በረንዳ ከሚገኙትና 350 በላይ ከሚሆኑት ነጋዴዎች ጋር ለመነጋገር በትናንትናው ዕለት(ማክሰኞ ታህሳስ 18 ቀን 2009 ዓ.ም) ስብሰባ የተጠራ ቢሆንም ያለምንም ውጤት መጠናቀቁን ምንጮች ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናግረዋል። የወረዳውን አስተዳደር አቶ ሳሙኤል አባዲን ለማነጋገር ያደረግነው ተደጋጋሚ የስልክ ሙከራም ሳይሳካ በመቅረቱ የአስተዳደሩን ቀጣይ እርምጃ ማካተት አልተቻለንም።  

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
335 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us