You are here:መነሻ ገፅ»ዜና

ሚኒስትሩ፤ በጋምቤላ በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ሆን ተብሎ ምዝበራ መፈጸሙን አረጋገጡ

Wednesday, 28 December 2016 14:19

የግብርና ኢንቨስትመንት ሀገራዊ ንቅናቄ መድረክ በሚል በአዲስ አበባ ጊዮን ሆቴል ቅዳሜ 15 ቀን 2009 ዓ.ም. በተዘጋጀው አውደ ጥናት ላይ የተገኙት እርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትር ዶ/ር ኢያሱ አብርሃ በጋምቤላ በግብርና ኢንቨሰትመነት ዘርፍ ሆን ተብሎ ምዝበራ መፈጸሙን ለሰንደቅ ጋዜጣ አረጋገጡ።

“በጥናቱ ላይ የቀረበው በደላሎች ይሁን በኪራይ ሰብሳቢዎች የተፈጠረው የአሰራር ክፍተት ከእውቀት ማነስ የመጣነው ተብሎ የሚወሰድ ነው? ወይንስ ሆን ተብሎ የሕዝብና የመንግስት ሃብትን ለመቀራመት የተዘረጋ የተቀራማች ቢሮክራሲ ተደርጎ ነው የሚወሰደው?” ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሚኒስትሩ የሰጡት ምላሽ፣ “ጥናቱ የሚያሳየው ሆን ተብሎ ምዝበራ መፈጸሙን ነው። ጥናቱ የሚያሳየው አንደኛ የመንግስት አስፈፃሚ አካል ሆነው ሆን ብለው ኪራይ የሚሰበስቡ እንዳሉ አይተናል። ሁሉም አስፈፃሚ ግን ደላላ ነው ማለት አይደለም። በቀናነት ሥራቸውን አክብረው የሚሰሩም እንዳሉ ጥናቱ ያሳያል። እንዲሁም ከባለሃብቱ በኪራይ ሰብሳቢነት ላይ ሆን ብለው የተሰማሩ እንዳሉ አይተናል። ውጤታማ ባለሃብቶችም እንዳሉ በጥናቱ ተመልክቷል ብለዋል።”

አያይዘውም “ሁሉም አካል በየደረጃው ለፈጸመው ጥፋት ይጠየቃል። የህግ የበላይነት ያለበት ሀገር በመሆኑ ሁሉም በሕግ ይጠየቃሉ። በተገኘው ጥናት መሰረት አስተማሪ የሆነ እርምጃ ይወሰዳል። ይህንን ለመፈጸም ደግሞ የመንግስት ቁርጠኝነት አለ። ተሀድሶ የሚደረገውም በየደረጃው ያለውን ችግር ለመፍታት ነው። አሁን ባለው ደረጃ የተሰጠው መፍትሄ መሬት በክልሎች እንዲተዳደሩ ተደርጓል። ሁለተኛ፣ አደረጃጀትን በተመለከተ የመፍትሄ አቅጣጫ ተቀምጧል። ሶስተኛ፣ በሕግ እንዲጠየቁ ተወስኗል” ሲሉ አጥፊዎች በሕግ እንደሚጠየቁ አረጋግጠዋል።

“በጥናቱ መሰረት ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ከታለመለት ዓላማ ውጪ መዋሉ ታውቋል። መንግስት የቀድሞውን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝደንት ከኃላፊነት ከማንሳት ውጪ በተግባር ያደረገው ነገር የለም። ከዚህ አንፃር እርስዎ ቁርጠኝነት አለን ሲሉ የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ወይም ዝንባሌን በማስቀረት በሚደረግ ግምገማ የሚታለፍ ነው? ወይንስ አጥፊውን ለሕግ አቅርባችሁ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ እና የሕዝብ ሃብት እንዲመለስ ነው የምታደርጉት?” በሚል ሚኒስትሩ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ “መንግስት እያለ ያለው ኪራይ ሰብሳቢ እና መልካም አስተዳደር ችግር በተግባር አለ። ይህንን መፍታት ካልቻልን ሁሉንም ነገር ጠርጎ ይወስደዋል። ስለዚህም ሁሉንም ነገር በየደረጃው እንሄድበታለን። የተቀመጠ አቅጣጫ ነው፤ በሕግ ይጠየቃሉ” ሲሉ አረጋግጠዋል።

እስከ 2008 መጨረሻ ድረስ 134 የሀገር ውስጥና የውጭ አገር ባለሀብቶች በፌደራል ደረጃ ተመዝግበው ከ500ሺ ሔክታር በላይ መሬት ተረክበው ወደ ተግባር ገብተዋል።

በክልል ደረጃም የኢንቨስትመንት ፈቃድ በማውጣት ከ5ሺ 400 በላይ ባለሃብቶች ከ1 ነጥብ 95 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ተላልፎላቸው እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በተጨማሪም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለባለሃብት ከተላለለፈው 2 ነጥብ 45 ሚሊዮን ሔክታር መሬት እስካሁን 863ሺ ሔክታር መሬት ወደ ልማት የገባ ሲሆን ይህም በአጠቃላይ እስከ አሁን ከተላለፈው መሬት 35 በመቶ የሚሆነው ወደ ምርት ሂደት እንደገባ እና በአማካይ ከ8 እስከ 10 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚገኝ ከመድረኩ ተገልጿል።

(በዚህ ጉዳይ ላይ ዝርዝር መረጃ በፖለቲካ ገፅ  4 ላይ ይመልከቱ)¾

ይምረጡ
(2 ሰዎች መርጠዋል)
728 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us