You are here:መነሻ ገፅ»ዜና

በቡድን ከባድ የስርቆት ወንጀል የፈጸሙ በእስራት ተቀጡ

Wednesday, 04 January 2017 14:22

ተከሳሾች…… 1ኛ. ቴዎድሮስ ይታገሱ እሸቴ 2ኛ .ዳዊት ንጉሴ አበበ እንዲሁም 3ኛ. ቃልኪዳን መንግስተ አብ ሀለፎም ናቸው፡፡ ሶስቱም ተከሳሾች በ7 ከባድ የስርቆት ወንጀል መከሰሳቸው በቀድሞ ፍትህ ሚኒስቴር በንፋስ ስልክ ላፍቶ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ጽ/ቤት አቃቤ ህግ የክስ መዝገብ ያብራራል፡፡

የክሱ መዝገብ እንደሚያትተው

1ኛ ክስ በሦስቱም ተከሳሾች ላይበ1996 ዓ.ም. የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1/ሀ/ እና 669/3/ሀ/ እና ለ/ ላይ የተመለከተዉን በመተላለፍ፡፡ተከሳሾች የማይገባቸውን ብልጽግና ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት አስበው ጥቅምት 11 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም. ከቀኑ በግምት 4፡3ዐ ሰዓት ሲሆን በን/ስ/ላ/ክ/ከ/ ወ/12 ክልል ልዩ ቦታው ላፍቶ ራሴድ ገበያ አካባቢ ከዚህ ቀድሞ በነበራቸው ስምምነት፣ ቡድንና የስራ ክፍፍል መሠረት ለስርቆት ተግባር የሚጠቀሙበትንና 1ኛ ተከሳሽ ያሽከረክረው የነበረውን የሠሌዳ ቁጥሩ ኮድ1-21341 አ.አ የሆነ ላዳ ታክሲ በመጠቀም 1ኛና 2ኛ ተከሳሾች ሦስተኛ ተከሳሽን ይዘው ዳግማዊትና ቤተልሄም ወደ ተባሉ ህፃናት  ተጠርጣሪዎች በመሄድና ከየቤታቸው በመውሰድ “ዛሬ የምንሰራው ስራ አለ” በማለት ወደ ግል ተበዳይ  አቶ ኃ/ጊዮርጊስ ተረፈ መኖሪያ ቤት አብረው በመሄድ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች መኪናውን  በግል ተበዳይ ቤት አካባቢ /አጠገብ/ በማቆምና አካባቢውን በመሰለል /በመጠበቅ/ ሰው መምጣት አለመምጣቱን በመቆጣጠር /በመከታተል/ 3ኛ ተከሳሽና ህፃን ዳግማዊትና ቤተልሄም የተባሉትን ወደ ግል ተበዳይ ቤት “ዘመዶች ነን” ብለው እንዲገቡ እና የሚያገኙትን ሰው /ሠራተኛ/ ህፃን ዳግማዊትና ህፃን ቤተልሄም የተባሉት እንዲያዋሩ ብሎም ንብረት ካለበት አካባቢ እንዲርቅ እንዲሁም ሁኔታውን በመጠቀም 3ኛ ተከሳሽ በቤት ውስጥ የተገኘውን ንብረት ይዛ እንድትወጣና እንድታቀብላቸው መመሪያና የስራ ድርሻ በመስጠትና የስራ ድርሻ በመከፋፈል 3ኛ ተከሳሽና ቀሪዎቹ ህፃናትም በተሰጣቸው የስራ ድርሻ በመስጠትና የስራ ድርሻ በመከፋፈል 3ኛ ተከሳሽና ቀሪዎቹ ህፃናትም በተሰጣቸው የስራ ድርሻ መሠረት ወደ ቤቱ በመሄድ ንብረትነታቸው የግል ተበዳይና የባለቤታቸው የሆኑከወርቅ የተሰሩ ጌጣጌጦች፣ ከዳይመንድ የተሰሩ ቀለበትና መስቀል  ከብር የተሰሩ ጌጣጌጦች፣ አስራ ሁለት ሺ ብር የሚገመት የሆነ ላፕቶፕ ከነአክሰሰሪዎቹ እንዲሁም በፖስታና በሳምሶናይት ውስጥ ተቀምጦ የነበረ ሁለት መቶ አርባ አንድ ሺ አምስት መቶ ብር፣ ወርቅ መሰል/ የጆሮ ጌጥና የአንገት ሀብል በአጠቃላይ የዋጋ ግምታቸው ሦስት መቶ ሰማንያ ሺ ስድስት መቶ አስር ብር የሆነ ንብረት ከተቀመጠበት ቦታ /ቤት ውስጥ/ 3ኛ ተከሳሽ አውጥታ ለ1ኛና 2ኛ ተከሳሾች በመስጠት የወሰዱና ለግል ጥቅማቸው ያዋሉ መሆኑን፡፡

በ2ኛ ክስጥቅምት 19 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም. ከጠዋቱ በግምት 3፡ዐዐ ሰዓት ሲሆን በን/ስ/ላ/ክ/ከ/ወ. 4 ክልል ልዩ ቦታው አየር ጤና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካባቢ ከሚገኘው የግል ተበዳይ ወ/ሮ ፍፁም ጥሩሰው መኖሪያ ቤት በመሄድ ከላይ በ1ኛ ክስ በተጠቀሰው ሁኔታ በመስማማትና የስራ ክፍፍል በማድረግ 1ኛና 2ኛ ተከሳሾች ከመኖሪያ ቤቱ አካባቢ ሆነው አካባቢውን በመቆጣጠር /ሰው በማየት/ ና በመቃኘት 3ኛ ተከሳሽ፣ ቤተልሄም እንዲሁም ዳግማዊት የተባሉት ወደ ቤቱ “ዘመድ ነን” በማለት ሠራተኛዋን  በማስፈቀድ ወደ ቤት ገብተው ሠራተኛዋ ስራ ላይ እያለች በቤቱ ውስጥ የነበረውንና የግል ተበዳይ ንብረት የሆነውን ቴክኖ ሞባይልና ፣c-3 ኖኪያ ሞባይል፣ አንድ ላፕቶፕ የወርቅ  ጌጣጌጦች  በአጠቃላይ የዋጋ ግምታቸው ብር 83.ዐዐዐ /ሰማንያ ሦስት ሺ ብር/ የሚሆን ንብረት 3ኛ ተከሳሽ ከተቀመጠበት ቦታ ላይ በማንሳት ለ1ኛና 2ኛ ተከሳሾች በመስጠት የወሰዱና ለግል ጥቅማቸው ያዋሉ በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት የከባድ ስርቆት ወንጀል ተከሰዋል፡፡

3ኛ ክስ ከላይ በተጠቀሰው የወንጀል ህግ አንቀጽ በመተላለፍ ነሐሴ 18 ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም. ከጠዋቱ በግምት 3፡ዐዐ ሰዓት ሲሆን በን/ስ/ላ/ክ/ከ/ወ. 12 ክልል ልዩ ቦታው 58 ቀበሌ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ከሚገኘው የግል ተበዳይ ወ/ሮ አልማዝ ጉተማ መኖሪያ ቤት ውስጥ ከላይ በ1ኛ ክስ ላይ በተገለፀው ሁኔታ ተከሳሾቹ ከያሉበት ተጠራርተውና ተስማምተው 1ኛ ተከሳሽ በሚያሽከረክረው የሠሌዳ ቁጥሩ ኮድ 1-21341 አ/አ ላዳ ታክሲ በመሄድ 1ኛ ተከሳሽ ታክሲውን በአካባቢ በማቆም ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር አካባቢውን በመቃፕት ሰው መምጣት ያለመምጣቱን ሊቆጣጠሩና እና የግል ተበዳይን ቤት ለ3ኛ ተከሳሽና ከግብረ አበሮቿ ጋር ‹‹የአልማዝ ዘመዶች ነን›› በማለት ወደ ቤት ውስጥ ከገቡ በኋላ 3ኛ ተከሳሽ ንብረቱ ያለበትን ቦታ በማጥናትና በመፈተሽ የመኝታ ቤቱን ብፌ በመስበር ንብረትነቱ የግል ተበዳይ የሆኑ  ጥሬ ገንዘብ ብር አንድ ሺ ሁለት መቶ ብር፣የተለያዩ ከወርቅ የተሰሩ ጌጣጌጦች  በአጠቃላይ ግምቱ ብር ሀያ አምስት ሺ ሁለት መቶ ብር የሚገመት ንብረት ይዘው በመውጣት ለ1ኛና 2ኛ ተከሳሽ በመስጠት የወሰዱ መሆኑን ክሱ ይዘረዝራል ከዚህም በተጨማሪ  በ4ኛ ክስ ከላይ በተጠቀሰው የወንጀል ህግ አንቀጽ 

 ሚያዚያ 2ዐ ቀን 2ዐዐ5 ዓ.ም. ከቀኑ በግምት 7፡3ዐ ሰዓት ሲሆን  በን/ስ/ላ/ክ/ከ/ቀ. ዐ2 ክልል ልዩ ቦታው  ቆሼ ሰፈር ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ከላይ በቀረቡት ክሶች ላይ በተገለፀው መኪና እና ሁኔታ ተጠራርተው ከያሉበት ወደ ግል ተበዳይ አቶ ኤፍሬም ዘወልድ መኖሪያ ቤት በመሄድና ተበዳይ ከቤት መውጣታቸውን በማረጋገጥ ቤት ትጠብቅ የነበረችውን ሠራተኛ “የኤፍሬም ዘመዶች ነን” በማለት አስፈቅደው ከገቡ በኋላ ቤተልሄም የተባለችው ተጠርጣሪ ሠራተኛዋን ሱቅ እንድታሳያት ጠይቃ ይዛት ስትወጣ 3ኛ ተከሳሽ የቤቱን ቁምሳጥን በመገንጠልና /በመስበር/ በውስጡ የነበረውን ዲጂታል ካሜራ፣ የኢራቅ መንግስት ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ ሲመነዘር ብር 15,ዐዐዐ /አስራ አምስት ሺ ብር/ ጥሬ ገንዘብ በአጠቃላይ ድምሩ ብር 2ዐ,ዐዐዐ/ሃያ ሺ ብር/ በማውጣት ከውጭ ሁኔታውን ሲከታተሉና ሲቆጣጠሩ ለነበሩት 1ኛና 2ኛ ተከሳሾች በመስጠት የወሰዱት በመሆኑ በአምስተኛ ክስ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 27/1/፣ 32/1/ሀ/ እና 669/3/ሀ/ እና /ለ/ ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ  ጥቅምት 28 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም. ከቀኑ በግምት 6፡ዐዐ ሰዓት ሲሆን በን/ስ/ላ/ክ/ከ/ቀ.ዐ2 ክልል ልዩ ቦታው  ህብር ት/ቤት አካባቢ ወደ ሚገኘው የግል ተበዳይ ወ/ሮ ለምለም አቡዩ መኖሪያ ቤት ከላይ በቀረቡት ክሶች ላይ በተጠቀሰው መኪና በመሄድ 1ኛና 2ኛ ተከሳሾች ከውጭ ሆነው ሲጠብቁ 3ኛ ተከሳሽ፣ ቤተልሄም እንዲሁም ዳግማዊት የተባሉት ጋር “ዘመዶች ነን” በማለት ወደ ግል ተበዳይ ቤት እንዲገቡ በ1ኛና 2ኛ ተከሳሾች አማካኝነት በተነገራቸው መሠረት  ከገቡ በኋላ የግል ተበዳይን የመኖሪያ ቤት መኝታ ክፍል በር ለመስበር ሲታገሉ ሰራተኛዋ ሰምታ በመጠራጠሯ ተከሳሾቹ ተያይዘው በመውጣት ያመለጡ ስለሆነ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን 6ኛ ክስ የወንጀል ህግ አንቀጽ 27/1/፣ 32/1/ሀ/ እና 669/3/ሀ/ እና /ለ/ ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ ጥቅምት 28 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም. ከጠዋቱ /ከረፈዱ/ በግምት 5፡3ዐ ሰዓት ሲሆን በን/ስ/ላ/ክ/ከ/ቀ.ዐ2 ክልል ልዩ ቦታው ህብር ት/ቤት አካባቢ ከሚገኘው የግል ተበዳይ ወ/ሮ አምሳል ኃይሉ መኖሪያ ቤት በመሄድ 1ኛና 2ኛ ተከሳሾች የሠሌዳ ቁጥሩ ኮድ 1-21341 አ/አ. የሆነ ላዳ ታክሲ ውስጥ ተቀምጠው አካባቢውን በመቃኘትና ለ3ኛ ተከሳሽና ለሌሎች ተጠርጣሪዎች የግል ተበዳይ ቤት ፈትሸው ያገኙትን ንብረት ይዘው እንዲወጡ መመሪያና ትዕዛዝ በመስጠት 3ኛ ተከሳሽም  ከሌሎች ተጠርጣሪዎች ጋር ይህንኑ ትዕዛዝ በመቀበልና በመስማማት ወደ ግል ተበዳይ ቤት በመግባትና የልብስ ቁም ሳጥኑን በመስበር /በመገንጠል/ በውስጡ የነበረውን የዋጋ ግምቱ ብር አስር ሺ ብር የሚገመት ዲጂታል ካሜራ በማውጣት ሊወስዱ ሲሉ ሰራተኛዋ ስታውቅባቸው ንብረቱን ሳይወስዱ ጥለውት የሄዱ በመሆናቸው በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት የከባድ ስርቆት ሙከራ ወንጀል ተከሰዋል፡፡

በመጨረሻም በ7ኛ ክስ በ1996 ዓ.ም.የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ27/1/፣ 32/1/ሀ/ እና 669/3/ሀ/ እና /ለ/ ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ ተከሳሾቹ የማይገባቸውን ብልጽግና ለራሳቸው ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ጥቅምት 28 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም. ከቀኑ በግምት 8፡3ዐ ሰዓት ሲሆን በን/ስ/ላ/ክ/ከ/ቀ. ዐ2 ክልል ልዩ ቦታው ቀጠና ዐ4 ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ከላይ በተመለከቱት ክሶች ላይ በተጠቀሰው የ1ኛ ተከሳሽ መኪና ወደ ግል ተበዳይ ወ/ሮ ሙሉ ተሾመ መኖሪያ ቤት በመሄድ 1ኛና 2ኛ ተከሳሾች ለ3ኛ ተከሳሽና ለሌሎች ተጠርጣሪዎች ቤቱን አንኳኩተው በመግባት ዘመድ መሆናቸውን ገልጸው እንዲገቡና ያገኙትን ንብረት ይዘው እንዲወጡ መመሪያና ትዕዛዝ በመስጠት ከቤቱ ውጭ አካባቢ በመጠበቅና አካባቢውን በመቆጣጠር /በመቃኘት/ ሲጠብቋቸው 3ኛ ተከሳሽና ግብረ-አበር ተጠርጣሪዎቹ ደግሞ በታዘዙት መሠረት ወደ ቤት በመግባት ቤተልሄም የተባለችው ተጠርጣሪ የቤት ሰራተኛዋን ከቤት ውጭ ይዛት ስትወጣ 3ኛ ተከሳሽ እና ዳግማዊት የተባለችው ሌላዋ ተጠርጣሪ የቁምሳጥኑን በር በመስበር ላይ እንዳሉ እጅ ከፍንጅ የተያዙ ሲሆን ይህንኑ ያወቁት 1ኛና 2ኛ ተከሳሾች ግን ያመለጡ ስለሆነ ተከሳሾቹ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት የከባድ ስርቆት ሙከራ ወንጀል ተከሰዋል፡፡

አጠቃላይ በቀድሞው ፍትህ ሚኒስቴር ንፋስ ስልክ ላፍቶ ፍትህ ጽ/ቤት ዐቃቤ ህግ በአርቲዲ ፈጣን ውሳኔ ማሰጠት 3ቱን ተከሳሾች በ7 ከባድ የስርቆት ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ክስ መስርቶባቸዋል፡፡

ሶስቱ ተከሳሾች ክደው የተከራከሩ ሲሆን ዐቃቤ ህግ በበኩሉ ጉዳዩን ያስረዱልኛል ያላቸውን የሰነድ እና የሰዎች ምስክር አሰምቷል፡፡ በመሆኑም 2ኛ ተከሳሽ ዳዊት ንጉሴ አበበ እና 3ኛ ተከሳሽ ቃልኪዳን መንግስተ አብ ዐቃቤ ህግ ያቀረበውን ማስረጃ ማስተባባል ባለመቻላቸው ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ናችሁ ብሏቸዋል፡፡

በአንጻሩ አንደኛ ተከሳሽ ቴዎድሮስ ይታገሱ እሸቴ በጊዜው መከላከያ ማስረጃ አቅርቦ ሲያሰማ የአንደኛ ተከሳሽ የክሱ መዝገብ የካቲት 3ቀን 2006 ዓ/ም እንዲቋረጥ የተደረገ ሲሆን በ2ኛእና በ3ኛ ተከሳሾች ላይ ሚያዝያ 3 ቀን 2008 ዓ/ም በዋለው ችሎት 2ኛ  ተከሳሽዳ ዊት ንጉሴ አበበ በ18ዓመት እንዲሁም ቃልኪዳን መንግስተ አብ  በ16 ዓመት ከ6ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን አስተላልፏል፡፡

ነገር ግን 1ኛ ተከሳሽ ቴዎድሮስ ይታገሱ እሸቴ ላይ የካቲት 3ቀን 2006 ዓ/ም ተቋርጦ የነበረውን የክስ መዝገብ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የንፋስ ስልክ ላፍቶ  ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ጽ/ቤት ዐቃቤ ህግ ለሚመለከተው አቤቱታ በማሰማት ጉዳዩን በድጋሚ እንዲቀሳቀስ በማድረግ  ክሱን በማጠናከር የሰነድ እና የሰው ምስክር በማቅረብ በአንደኛ ተከሳሽ ላይ ተቋርጦ የነበረውን መዝገብ  ፍርድ ቤቱ በድጋሚ እንዲያይለት ጠይቋል፡፡

ግራ ቀኙን የተመለከተው ፍርድ ቤትም ተከሳሹ ተከላል ቢለውም ዐቃቤ ህግ ያቀረባቸውን የሰው እና የሰነድ ማስረጃ ሊያስተባብል ባለመቻሉ ጥፋተኛ ነህ ሲል ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡

የቅጣት አስተያየት እንዲሰጥለት የተጠየቀው ዐቃቤ ህግ በበኩሉ አስተማሪ ቅጣት እንዲሰጥ አመልክቷል፡፡ ተከሳሹ በበኩሉ 5 ነጥቦች በመዘርዘር የቅጣት ማቅለያ እንዲደረግለት ጠይቋል፡፡ በመሆኑም የተወሰኑ ክሶች ላይ ወንጀሉ በሙከራ የቀረ መሆኑን፣ ተከሳሹ ከዚህ በፊት ወንጀል ፈጽሞ እንደማያውቅ፣ በማህበራዊ ግዴታውን የተወጣ በመሆኑ፣ ከሚሰራበት መስርያ ቤት ተከሳሹ ታማኝ ሰራተኛ መሆኑን የሚገልጽ የጽሁፍ ማስረጃ የቀረበውን በመመርመር  የመጀመርያ ደረጃ በንፋስ ስልክ ላፍቶ  አርቲዲ ችሎት  ታህሳስ 17 ቀን 2009 ዓ/ም በዋለው ችሎት በ14 ዓመት ከ3ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጣ  ሲል ውሳኔውን አስተላልፏል፡፡

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ጽ/ቤት አቃቤ ህግ አቶ ጌቱ ታደሰ  ሁሉም ሰው ባጠፋው መጠንና ልክ ከተጠያቂነት እንደማያመልጥ ገልፀው ቅጣቱ አስተማሪ መሆኑን እና አጥፊዎች ከጥፋታቸው የሚያስተምር ውሳኔ መወሰኑን ተናግረዋል፡፡

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
583 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us