You are here:መነሻ ገፅ»ዜና

የግለሰብ መኖሪያ ቤት ያለአግባብ ስም በማዛወር የሸጡ ሹማምንት ታሰሩ

Wednesday, 04 January 2017 14:26

በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ንብረትነቱ የሟች ወ/ሮ ገላኔ ጫላ የሆነን የመኖሪያ ቤት ሕግ ከሚፈቅደው ውጪ ስም በማዛወርና በመሸጥ አለአግባብ ጥቅም አግኝተዋል፣ መንግሥታዊ ኃላፊነታቸውን ለግል ጥቅማቸው አውለዋል የተባሉ ተከሳሾች ተቀጡ።

 

ከተራ ቁጥር አንድ እስከ ሦስት የተጠቀሱት አቶ ሙሉጌታ ሽፈራው፣ አቶ ሙላቱ ተፈራ እና አቶ አለማየሁ በሪሳ የተባሉ ተከሳሾች በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ እና የጸረ ሙስና አዋጅ በመተላለፍ የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኘት አስበው አርሲ ዞን ሙኔሳ ወረዳ ቀርሳ ከተማ ውስጥ ሥልጣናቸውን ያለአግባብ በመጠቀም አንደኛ ተከሳሽ  በወ/ሮ ገላኔ ጫላ ስም ያለውን መኖሪያ ቤት የወራሽነት መብት ሳይረጋገጥ በሶስተኛ ተከሳሽ ስም ተዛውሮ እንዲሰራ በማዘዙ፣ ሁለተኛ ተከሳሽ መሐንዲስ ባለሙያ ሆኖ እየሰራ ሳለ በሟች ስም ያለውን የባለይዞታነት ማስረጃ ያለአግባብ ወደሶስተኛ ተከሳሽ ስም በማዛወሩ ተከሰዋል። በተጨማሪም ሶስተኛ ተከሳሽ የሟች የወ/ሮ ገላኔ ጫላ ልጅ ሲሆን ሌሎች ወራሾች መኖራቸውን እያወቀ ብቸኛ የመውረስ መብት እንዳለው በወረዳው ፍ/ቤት አረጋግጦ የተወሰነለት ውሳኔ ሳይኖር በሟች እናቱ ስም ተመዝግቦ የሚታወቅ መኖሪያ ቤት ወደራሱ በማዛወር ለአራተኛ ተከሳሽ ለነበረ ግለሰብ በመሸጥና ስሙንም በአራተኛ ተከሳሽ ተዛውሮ የባላይዞታነት ማስረጃ እንዲሰራለት በማድረጉ የሙስና ወንጀል መፈጸማቸውን ተጠቅሶ በአቃቤ ህግ ክሱ ቀርቧል።

 

ፍ/ቤቱ በጉዳዩ ላይ ግራና ቀኝ ወገኖችን ሲያከራክር ከቆየ በኃላ ከአንድ እስከ ሶስተኛ ያሉት ተከሳሾች በአንድ ዓመት ከሁለት ወር ቀላል እስራት እና እያንዳንዳቸው የአንድ ሺ ብር መቀጮ እንዲጣልባቸው በቅርቡ ውሳኔ ሰጥቷል።

 

አቃቤ ሕግ በተከሳሾች ላይ የተጣለው ውሳኔ ከጥፋታቸው አንጻር የሚመጥንና አስተማሪ አይደለም በሚል በቅርቡ የይግባኝ አቤቱታ ለኦሮሚያ ጠ/ፍ/ቤት የምስራቅ ምድብ ችሎት አቅርቧል። አቃቤ ሕግ በዚሁ የይግባኝ አቤቱታው የስር ፍ/ቤት የሰጠውን የጥፋተኝነት እና የቅጣት ውሳኔ የተቃወመ ሲሆን በተለይ አራተኛ ተከሳሽ የነበረው ግለሰብ ሶስተኛ ተከሳሽ ከህግ ውጪ ቤቱን እንደሸጠለትና ስምም እንዳዛወረለት እያወቀ ንብረቱን ከሶስተኛ ተከሳሽ በመግዛት ከሕግ ውጪ በሆነ መንገድ አረጋግጦ ባለንብረት ሆኖ ሳለ፤ የስር ፍ/ቤቱ የፈጸመው ወንጀል የለም በማለት በነጻ ማሰናበቱን አቃቤ ሕግ በመቃወም ይግባኝ መጠየቁ ታውቋል።  

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
523 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us