You are here:መነሻ ገፅ»ዜና

አካል ጉዳተኞችን የሚያስተባብር ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

Wednesday, 04 January 2017 14:27

አካል ጉዳተኛ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ዐብይ በሆኑ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ዘርፎች እንዲካተቱ ግፊት የሚያደርግ አዲስ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ። አካል ጉዳተኞች የሚያጋጥሟቸውን መሰናክሎች በኅብረት በመፍታት፤ ግንዛቤን በማስጨበጥና በአገር አቀፍ ደረጃ የረቀቁ ሕጐችና ፖሊሲዎች ተፈፃሚ እንደሆኑ በማስተባበር ይሰራል የተባለው ይህ ፕሮጀክት በአውሮፓ ኅብረት ሲቪል ሶሳይቲ ፈንድ ድጋፍ ኖቪብ እና ኢንዳን የተሰኙ በአካል ጉዳተኞች የተቋቋሙ ማኅበራት ኔትዎርክ ይፋ መደረጉን ትናንት (ታህሳስ 25 ቀን 2009 ዓ.ም) በአዜማን ሆቴል በተከፈተው አውደ ጥናት ተነግሯል።

 

በአገር አቀፍ ደረጃ በሚከናወኑ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ አካል ጉዳተኞች የድርሻቸውን እንዲሳተፉ ማትጋት የፕሮጀክቱ ዐብይ ዓላማ መሆኑን የኔትወርክ ኦፍ ኦርጋናይዜሽንስ ፎር ዘ ቪዥዋሊ ኢምፔርድ ኤንድ ዘ ብላይንድ (ኖቪብ) ስራ አስኪያጅ አቶ ጌቱ ሙላቱ በመክፈቻ ፕሮግራሙ ላይ ባደረጉት ንግግር አስረድተዋል። በአውደ-ጥናቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር እንዲያደርጉ በክብር እንግድነት የተገኙት የሰራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማኅበራዊ ጉዳይ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ወ/ሮ ታደለች ዳለቾ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት በሀገራችንም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአካል ጉዳት የሚዳርጉ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ አደጋዎች መበራከታቸውን አስታውሰው፤ አካል ጉዳተኞች ከሚደርስባቸው ጫና ይወጡ ዘንድ መንግስት ባወጣቸው መመሪያዎችና ፖሊሲዎች ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረው፤ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አውስታውቀዋል።

የአካል ጉዳተኞች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲከበር መንግስት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነቱን ያሳየ ቢሆንም፤ የትግበራውን መጠን በሚመለከት ግን ለውይይት መቅረብ እንደሚገባው የጠቆሙት ሚኒስቴር ዴኤታዋ፤ ይህ ተግባር በመንግስት ብቻ ሳይሆን በአጋር አካላት ትብብር መሠረት እንደሚገባውም አሳስበዋል። በመሆኑም በአውደ-ጥናቱ በውይይት የሚቀርበው የአካል ጉዳተኞች የአካታች ልማት ትግበራ ፕሮጀክት ለውጥ እንደሚያመጣ በተቋማቸው በኩል ያላቸውንም ተስፋ እና ድጋፍ ገልፀዋል።

 

የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች ኔትዎርክ ኦፎ ኦርጋናይዜሽንስ ፎር ዘ ቪዥዋሊ ኢምፔርድ ኤንድ ብላይንድ (ኖቪብ) እና ኢትዮጵያን ናሽናል ዴሲቢሊቲ አክሽን ኔትወርክ (ኢንዳን) ዋና ዓላማቸው ግንዛቤን በመፍጠር አካል ጉዳተኞችም የሚገባቸውን እንዲጠይቁና የኅብረተሰቡም ግንዛቤው እንዲሰፋ ማስቻል እንደሆነ በዐውደ ጥናቱ ላይ ተነግሯል። ፕሮጀክቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የአካል ጉዳተኞችና የነጭ ብትር ቀናትን በማስመልከት የሚተላለፉ መልዕክቶችን በትብብር በመስራት ለታቀደው አገር አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ፎረም ምስረታ መረጃዎችን ይሰጣል ተብሎለታል።

 

በአውደ-ጥናቱ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጥና በወጡ ሕጐችና ፖሊሲዎች ላይ ተፈፃሚ ይሆኑ ዘንድ ግፊት ከማድረግ ባለፈ፤ በፕሮጀክቱ ስለታቀዱ ዋና ዋና ስራዎችና ስለሚጠበቁ ውጤቶች ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን፤ ከባለድርሻ አካላት ምን እንደሚጠበቅም ውይይት ተደርጐበታል። በዚህ ፕሮጀክት ስር በኔትዎርክ አባልነት የታቀፉት ድርጅቶች ስድስት መሆናቸውን የተነገረ ሲሆን፤ በጋራ በመስራት ተገቢውን ለውጥ ለማምጣት የበኩላቸውን እንደሚወጡ በአውደ-ርዕይው ላይ የተገኙ የተለያዩ አካላት ተናግረዋል። 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
402 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us