Print this page

ከ60 በላይ ጥናታዊ ጽሁፎች የሚቀርቡበት ጉባኤ ሊስተናገድ ነው

Wednesday, 04 January 2017 14:29

በስነተዋልዶ፣ በፅንስና ማህፀን ጤና ላይ ያተኮሩ ከ60 በላይ ጥናታዊ ጽሁፎች የሚቀርበት የአፍሪካ የፅንስና ማህፀን ሐኪሞች ፌዴሬሽን ጉባኤ በኢትዮጵያ ሊካሄድ ነው።

 

የኢትዮጵያ የፅንስና ማህፀን ሐኪሞች ማኅበር ባለፈው ቅዳሜ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው ጉባኤው፤ “ዘላቂ የልማት ግቦች በአፍሪካ ስነ-ተዋልዶ ጤና እድሎችና ተግዳሮቶች” በሚል መሪ ቃል ከጥር 25 እስከ 27 ቀን 2009 ዓ.ም ድረስ በካፒታል ሆቴል ይስተናገዳል። በጉባኤው በህክምናው ዘርፍ የሀገራችን ባለሙያዎች የላቀ ክህሎት እንዲያገኙ እና የምርምር ውጤቶችን እንዲያቀርቡ እድል ይሰጣል ተብሏል። በተለይ ከጉባኤው ከሁለት ቀናት አስቀድሞ በርካታ የሚካሄዱ ፕሮግራሞች እንዳሉ የገለፁት የአፍሪካ የፅንስና ማህፀን ሐኪሞች ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት ዶ/ር ይርጉ ገብረህይወት፤ ከእነዚህ ፕሮግራሞች መካከልም የማኅበሩ አባላት በዘርፉ የምርምር ስራዎችን ለመፃፍ የሚያስችላቸው የክህሎት ስልጠና ከአሜሪካ በሚመጡ ባለሙያዎች ይሰጣቸዋል ብለዋል። ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ጋር በመተባበርም ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች የአልትራሳውንድና የእርግዝና ክትትልን በላቀ ደረጃ ማከናወን የሚያስችላቸው ስልጠና ይሰጣቸዋል ብለዋል ዶ/ር ይርጉ። በተጨማሪም ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጋር በመተባበር በድንገተኛ ህክምና፣ በማህፀን ጫፍ እና በማህፀን ግድግዳ ካንሰር ላይ ለባለሙያዎች ስልጠና እንደሚሰጥ ዶ/ር ይርጉ ጨምረው ገልፀዋል። ጉባኤው ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች የህክምናው ዘርፍ የደረሰበትን ወቅታዊ እውቀትና ክህሎት እንዲቀስሙ ያግዛቸዋልም ተብሏል።

 

የኢትዮጵያ የፅንስና ማህፀን ሐኪሞች ማኅበር ፕሬዝደንት ዶ/ር ደረጃ ንጉሴ በበኩላቸው፤ የአፍሪካ የፅንስና ማህፀን ሐኪሞች ፌዴሬሽን ጉባኤ በሀገራችን በመስተናገዱ የሀገራችን ባለሙያዎች በጤናው ዘርፍ ከሌሎች ሀገራት ልምድ እንዲቀስሙ ጥሩ አጋጣሚ ነው ብለዋል። ጉባኤው በኢትዮጵያ የፅንስና ማህፀን ሐኪሞች ማኅበር እና በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ትብብር የሚካሄድ ሲሆን፤ በጉባኤው ላይም 300 የሀገር ውስጥ እና 200 የውጭ ሀገር ተሳታፊዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ ፕሬዝደንቱ ገልፀዋል። ማኅበሩም ከጉባኤው ጐን ለጐን 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓሉን ያከብራል። 

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
674 ጊዜ ተነበዋል

ተጨማሪ ጽህፎች ከ መስከረም አያሌው