You are here:መነሻ ገፅ»ዜና

6ቱ ፓርቲዎች አሁን ያለው አገዛዝ ወደ አስተዳደራዊ ሥርዓት እስኪመጣ እንታገላለን አሉ

Wednesday, 08 February 2017 14:16

በይርጋ አበበ

 

በአገሪቱ በተከሰተው ህዝባዊ አመጽ ምክንያት ሰዎች ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው መስራት ከማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሷል ሲሉ  ሰማያዊ ኢዴፓ መኢአድ ኢራፓ መኢዴፓ እና ኢብአፓ አስታወቁ። አገሪቱም ከፍተኛ የህልውና ስጋት ውስጥ መውደቋን ተናግረዋል።

በቅርቡ ኢህአዴግ በጠራው የድርድር ፕሮግራም ላይ ተሳታፊ የሆኑት ስድስቱ አገር አቀፍ ፓርቲዎች ባለፈው ሰኞ ከቀትር በኋላ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ድርድሩ የተሳካ እንዲሆን ሁሉም ወገን የበኩሉን ይወጣ” ብለዋል። ፓርቲዎቹ ከድርድሩ የሚጠብቁትን ሲያሳውቁም “አንድን የፖለቲካ ኃይል አሸናፊ ሌላውን ተሸናፊ የሚያደርግ ድርድር ሳይሆን አገራቸን ከገባችበት የህልውና ስጋትና የፖለቲካ ቀውስ ተላቃ ህዝብ የስልጣን ባለቤት የሚሆንበትን ስርዓት እንዲያገኝ ማድረግ ነው” ያሉ ሲሆን ለዚህ ግብም “የድርሻችንን በሀቀኝነትና በቁርጠኝነት ለመወጣት ተዘጋጅተናል” ብለዋል።

በአገሪቱ የፈጠረው ህዝባዊ አመጽ አስመልክቶ “ከዴሞክራሲ ስርዓት መገለጫዎች ዋነኛ የሆነውን የምርጫ ስርዓት የስልጣን ዕድሜ ማራዘሚያ በማድረግ ከላይ እስከታች የሚገኙትን የምክር ቤት መቀመጫዎች ፍጹም ኢ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ጠቅልሎ መውሰዱ ይህ የገዥው ፓርቲ የስልጣን ስግብግብነትና አምባገነናዊ ባህሪ አሁን አገራችን የምትገኝበት አደገኛ ሁኔታ ወስጥ እንድትገኝ አድርጓታል” ሲሉ ተናግረዋል።

ለድርድር ለማቅረብ የተስማማችሁባቸው ነጥቦች የትኞቹ ናቸው ተብለው ከመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ጥያቄ ቀርቦላቸው የፓርቲዎቹ አመራሮች መልስ ሲሰጡ “የአደራዳሪውን ማንነትና ገለልተኝነት፣ ታዛቢን የጉባኤውን ስርዓት ምን መምሰል እንዳለበትና የመገናኛ ብዙሃንን በተመለከተ ነው” ብለዋል።

አባሎቻችሁና አመራሮቻችሁ በእስር ላይ ሆነው መደራደር ተገቢ ነው ትላላችሁ? ለሚለው ጥያቄ “ቢዘገይም ለድርድር እድል መከፈቱን መጠቀም አስፈላጊ ነው” ያሉ ሲሆን “የታሰሩት እንዲፈቱ ጠይቀናል። እንደራደር ከተባለ በድርድሩ ተሳታፊ የሆኑ አመራሮች ለምሳሌ እንደ ዶክተር መረራ ጉዲና አይነት ተደራዳሪዎች ታስረዋል። ስለዚህ ወደ ድርድር ስንገባ እነዚህ ሰዎች እንዲፈቱ እንሻለን” ብለዋል። የፓርቲ ኃላፊዎቹ አክለውም “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ካልተነሳ ፓርቲዎች ከደጋፊዎቻችንና አባሎቻችን ጋር መወያየት አልቻልንም” ሲሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለፖለቲካዊ እንቅስቃሴያቸው እንቅፋት እንደሆነባቸው ተናግረዋል።

በቅርቡ የመንግስትን አቋም ያስታወቁት የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሚኒስትር ዶክተር ነገሪ ሌንጮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተወሰነለት ጊዜ ቀድሞ እንደማይነሳ መናገራቸው ይታወሳል።¾

ይምረጡ
(5 ሰዎች መርጠዋል)
866 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us