You are here:መነሻ ገፅ»ዜና

ኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የመንገድ ግንባታ ውል ተፈራረመ

Wednesday, 12 April 2017 11:56

 

-    አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን እና ራማ ኮንስትራክሽን በጋራ

የሁለት መንገዶች ግንባታ ተፈራርመዋል

 

ኦርኪድ ቢዘነስ ግሩፕ ከጋምቤላ ከተማ እስከ ኤሊያ ድረስ ያለውን መንገድ ለመገንባት በብር 1,029,229,136.43 (አንድ ቢሊዮን፣ ሃያ ዘጠኝ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሃያ ዘጠኝ ሺህ አንድ መቶ ሰላሳ ስድስት ብር ከአርባ ሦስት ሳንቲም) ከመንገዶች ባለስልጣን ጋር ተፈራርሟል። 

ከጋምቤላ ከተማ እስከ ኤሊያ ድረስ ያለውን መንገድ ቀደም ሲል መንገዱ በጠጠር ደረጃ የነበረ ሲሆን፤ በአስፋልት ደረጃ እንዲያድግ መደረጉን ባለስልጣኑ ገልጿል። 78 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውን የዚህን መንገድ ግንባታ ለማካሄድ ጨረታውን በብር 1,029,229,136.43 (አንድ ቢሊዮን፣ ሃያ ዘጠኝ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሃያ ዘጠኝ ሺህ አንድ መቶ ሰላሳ ስድስት ብር ከአርባ ሦስት ሳንቲም) አሸንፎ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር የውል ስምምነት የተፈራረመው ኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ ኃ/የተ/የግ/ማኅበር የተባለ የአገር በቀል የስራ ተቋራጭ ድርጅት መሆኑን ባለስልጣኑ ጨምሮ ገልጿል።

ለመንገዱ ግንባታ የሚውለው አጠቃላይ ወጪ በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ሲሆን፤ ግንባታውን ለማጠናቀቅም ሦስት ዓመት (36 ወራት) ተሰጥቶታል። በተጨማሪም የመንገዱን ግንባታ የማማከርና የቁጥጥር ስራ የሚያከናወኑ አማካሪ ድርጅቶች ለመምረጥ በጨረታ ሂደት ላይ ይገኛል ተብሏል። መንገዱ የመንገድ ትከሻን ጨምሮ በገጠር 10 ሜትር ሲሆን፤ በከተማ 21 ነጥብ 5 ሜትር ስፋት ይኖረዋል።

የመንገዱ ግንባታ በሚጠናቀቅበት ወቅት ከዚህ በፊት በአካባቢው የነበረውን የትራንስፖርት ችግር በመቅረፍ የአካባቢው ኅብረተሰብ በቀላሉ ወደፈለገው ቦታ የሚንቀሳቀስበትን ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ከመሆኑም ባሻገር፣ በመስመሩ በግብርናው ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለተሰማራው ሳዑዲ ስታር አግሮ ኢንዱስትሪ ዴቨሎፕመንት ፒኤልሲም ሆነ የሌሎች በኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶችን የግብርናና የኢንቨስትመንት ውጤቶችን ወደ ገበያ ለማውጣት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል ተብሎ ይታመናል።

ከዚህም በተጨማሪ አካባቢው ከፍተኛ የግብርና ምርት የሚመረትበት እንደመሆኑ መጠን በዚህ አካባቢ የውጭና የአገር ውስጥ ባለሃብቶች በግብርናው ዘርፍ ለመሰማራት ከወረዳው ቦታ የወሰዱ ሲሆን፤ እነዚህ አካላት የግብርና ምርት ማምረት ሲጀምሩ ያመረቱትን ምርት ወደ ገበያ ለማውጣት እንዲችሉና ሌሎች ባለሃብቶችም በአካባቢው ኢንቨስት ለማድረግ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር አኳያ የዚህ መንገድ መገንባት ጉልህ ሚና ይጫወታል ተብሏል።

 ኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማራ ሲሆን፤ በዘርፉ ከሚሰራቸው ሥራዎች መካከል የመንገድ ሥራ፣ የውሃ ቁፋሮ፣ የፓይል ፋውንዴሽን (የመሰረት ቁፋሮ) ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው።

የኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ ዋና ሥራአስፈፃሚ ወ/ሮ አኪኮ ስዩም፣ ከሁለት ዓመት በፊት በሲውድን በተደረገው አለም አቀፍ የሴቶች ኢንተርፕርነር ውድድር ከአፍሪካ ተሸላሚ በመሆን ሀገራቸውን በዓለም ዓቀፍ መድረክ ማስተዋወቃቸው ይታወሳል።

በተያያዘ ዜናም፣ የቱርሚ - ኦሞ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ 63 ነጥብ 35 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን፤ ግንባታውን በብር 897,005,974.61 (ስምንት መቶ ዘጠና ሰባት ሚሊዮን፣ አምስት ሺህ ዘጠኝ መቶ ሰባ አራት ብር ከስልሳ አንድ ሳንቲም) ለማካሄድ ጨረታውን አሸንፈው ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር የውል ስምምነት አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን እና ራማ ኮንስትራክሽን የተባሉ ሀገር በቀል የስራ ተቋራጮች በጋራ በመሆን ተፈራመዋል።

የማማከርና የቁጥጥር ስር የሚያከናውኑ አማካሪ ድርጅቶች ለመምረጥ በጨረታ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ባለስልጣን መስሪያቤቱ ገልጿል። ፕሮጀክቱ ከቱርሚ ከተማ አንስቶ እስከ ኦሞ ድረስ የሚዘልቅ ነው። ለመንገዱ ግንባታ የሚውለው አጠቃላይ ወጪ በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ሲሆን፤ ግንባታውን ለማጠናቀቅም ሦስት ዓመት ተሰጥቶታል። መንገዱ በገጠር የመንገድ ትከሻን ጨምሮ 10 ሜትርና በቀበሌ 12 ሜትር ስፋት አለው። የመንገዱ ግንባታ የበርካታ ፉካዎችና የአነስተኛ ድልድዮችን ሥራ እንደሚያካትትም ታውቋል። መንገዱ ቀደም ሲል ምንም የመንገድ መሰረተ ልማት ያልነበረበት ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ ይገነባል።

የመንገዱ ግንባታ በሚጠናቀቅበት ጊዜ በግንባታ ሂደት ላይ ካሉ ከሚገኙት የስኳር ፋብሪካዎች ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ ምርቱን በቀላሉ ወደገበያ ለማውጣት ያስችላል። በተጨማሪም አካባቢው የቱሪስት መዳረሻ መስመር በመሆኑ የቱሪስት ፍሰቱን ለማቀላጠፍ ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል ተብሏል።

በተጨማሪም አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን እና ራማ ኮንስትራክሽን ሁለተኛው የመንገድ ፕሮጀክት በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው የሮቤ - ጋሰራ የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ለመገንባት ከባለስልጣኑ መስሪያቤት ጋር ተፈራርመዋል።

 60 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውን የዚህን መንገድ ግንባታ ለማካሄድ ጨረታውን በብር 769,860,000.00 (ሰባት መቶ ስልሳ ዘጠኝ ሚሊዮን ስምንት መቶ ስልሳ ሺህ ብር) አሸንፈው ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር የውል ስምምነት አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን እና ራማ ኮንስትራክሽን የተባሉ ሃገር በቀል የስራ ተቋራጮች በጋራ ተፈራርመዋል። የፕሮጀክቱን የማማከርና የቁጥጥር ስራ የሚያከናውኑ አማካሪ ድርጅቶች ለመምረጥ በጨረታ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ታውቋል። 

ለመንገዱ ግንባታ የሚውለው አጠቃላይ ወጪ በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ሲሆን፤ ግንባታውን ለማጠናቀቅም ሦስት ዓመት ተሰጥቶታል። መንገዱ በገጠር የመንገድ ትከሻን ጨምሮ 10 ሜትር፣ በቀበሌ 12 ሜትርና በወረዳ ከተማ 19 ሜትር ስፋት ይኖረዋል። የመንገዱ ግንባታ ሥራ ከ1784 በላይ ፉካዎችና የሁለት ድልድዮችን ሥራ እንደሚያካትትም ታውቋል።

የመንገዱ ግንባታ በሚጠናቀቅበት ጊዜ በአካባቢው በስፋት የሚመረቱትን የስንዴና ገብስ ምርቶችን ወደማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ከማስቻሉም ባሻገር፣ እንደ ድሬ ሸክ ሁሴን፣ የባሌ ሶፍ ዑመር ዋሻ፣ የዲንሾ እና የሰነቴ ፓርኮች የመሳሰሉትን የቱሪስት መስህቦች ለመጎብኘት ለሚመጡ ቱሪስቶች ምቹ የመንገድ መሰረተ ልማት ከማቅረብ አኳያ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል። ስለሆነም የቱሪስት ፍሰቱን በመጨመር ለክልሉም ሆነ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

በአጠቃላይ የመንገዶቹ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከዚህ በፊት በየአካባቢው የነበረውን የትራንስፖርት ችግር በመቅረፍ የአካባቢው ኅብረተሰብ በቀላሉ ወደፈለገው ቦታ የሚንቀሳቀስበትን ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ከመሆኑም ባሻገር፣ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶች ያመረቱትን ምርት ወደ ገበያ ለማውጣት እንዲችሉና ሌሎች ባለሃብቶችም በአካባቢው ኢንቨስት ለማድረግ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር እንዲሁም የቱሪስት ፍሰቱን ከማቀላጠፍ አኳያ ጉልህ ሚና ይጫወታል።

በተጨማሪ ለአካባቢው ነዋሪዎች ወይም ወጣቶች ሰፊ የሆነ የስራ ዕድል እንዲፈጠር በማስቻል፤ በየአካባቢው የሚገኙ ትንንሽ መንደሮችና ከተሞችን እድገት ከማፋጠን እንዲሁም የጤና፣ የትምህርት እና ሌሎች የማኅበራዊ አገልግሎት ተቋማት እንዲስፋፉ ከማድረግ አንፃር እንዲሁም በየክልሎቹ ውስጥ የሚገኙ ዞኖችንና ወረዳዎችን እርስ በርስ ያስተሳስራሉ። ከዚህም ባሻገር የመንገዶቹ መጠናቀቅ የተሽከርካሪዎችን የጉዞ ጊዜና ወጪን በከፍተኛ ደረጃ የሚቀንስ ከመሆኑም በተጨማሪ የምርትና የሸቀጥ ልውውጥ ያለምንም እንግልት በቀላሉ እንዲከናወን ለማድረግ ያስችላል ተብሎ ይታመናል።

የእነዚህ መንገዶች መገንባት በአገሪቱ ካለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲሁም መንግሥት ከያዘው የድህነት ቅነሳ ስትራቴጂ አንፃር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረከቱ ተገልጿል። ስለሆነም የመንገድ ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ውስጥ እንዲጠናቀቁ በአካባቢው የሚገኙ የመስተዳድር አካላትና፣ የክልሉ ነዋሪዎች ከፍተኛ ትብብር እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አሳስቧል። የባለሥልጣን መ/ቤቱም የክትትልና የድጋፍ ሥራውን ከመቼውም ጊዜ በላይ አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።  

የውል ስምምነቶቹን የተፈራረሙት በኢመባ በኩል አቶ አርአያ ግርማይ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሲሆኑ፤ በኦርኪድ ቢዝነስ ግሩፕ በኩል ኢንጂነር ኃይለዓለም ወርቁ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ፣ በራማ ኮንስትራክሽን በኩል አቶ ፍሬው ተድላ የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ እና በአፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን በኩል ደግሞ አቶ ሲሳይ ደስታ የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ናቸው።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
542 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us