You are here:መነሻ ገፅ»ዜና

“ከ99 በመቶ በላይ የደረጃ ‘ሐ’ ቅሬታ አቅራቢዎች ችግር ተፈቷል”

Wednesday, 26 July 2017 12:44

 

አቶ አትክልት ገ/እግዚያብሔር የአዲስ አበባ ከፍተኛ

ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ስራ አስኪያጅ

 

በአዲስ አበባ አማካኝ የቀን ገቢ ግምት ተሰጥቷቸው ቅሬታቸውን ካሰሙት 59 ሺህ 275 ግብር ከፋዮች መካከል 99 ነጥብ 2 በመቶዎቹ የግብር ማስተካከያ ተደርጎላቸው ችግራቸው እንዲፈታ አድርገናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አትክል ገ/እግዚአብሔር ትናንት ለመገናኛ ብዙሃን ተናገሩ። ቅሬታ ያላቸው ግብር ከፋዮች በወረዳ አለፍ ሲልም በክፍለ ከተማ ደረጃ ቅሬታቸውን እንዲያቀርቡ ዕድሉ ተመቻችቶ እንደነበር ያስታወሱት ኃላፊው፤ ከአጠቃላይ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች መካከል 24 በመቶዎቹ ብቻ ቅሬታቸውን ሲያሰሙ የተቀሩት ግን አምነው ግብራቸውን እየከፈሉ ነው ብለዋል።

ማንኛውም አይነት ከግብር ግምት ጋር የተገናኘ ቅሬታ ያለው ግብር ከፋይ በወረዳና በክፍለከተማ በቀረበለት ቅሬታ ሰሚ ማዕከላት ቀርቦ ጉዳዩን ማስረዳት ይችላል የተባለ ሲሆን፤ አሁን ላይ በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተው የንግድ ተቋምን መዝጋት መንስኤው የተሳሳተ መረጃ በመስጠት የሚቀሰቅስ አካል ይኖራል ብለው እንዲያስቡ እንዳያረጋቸውም ተናግረዋል። አያይዘውም ቀጥተኛ ያልሆነ ታክስ አሰባሰብን በሚመለከት የሂሳብ መዝገብ ማስረጃ የሚያቀርቡ ነጋዴዎች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ ለ2009 ዓ.ም ብቻ ባመኑበት እንዲከፍሉ መወሰኑን አስታውሰው ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ግን የሂሳብ አያያዛቸውን ተከታትለን ቀጥተኛ ያልሆነውን ታክስ ለመሰብሰብ ተዘጋጅተናል ብለዋል።

የተጋነነ አማካኝ የቀን ገቢ ግምት ተሰልቶብናል በሚል ካሳለፍነው ሰኞ ጀምሮ መርካቶን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የንግድ ተቋማትን መዝጋት ሂደት የታየ ሲሆን፤ አስተዳደሩ በበኩሉ ቅሬታን ለማቅረብ እስከመደበኛ ፍርድ ቤት በየደረጃው ተቀምጦ ሱቅ በመዝጋት የሚመጣ መፍትሄ የለም ብሏል። በግምት ሂደቱና በባለስልጣኑ ሰራተኞች ላይ ቅሬታ መነሳቱን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሥራአስኪያጁ በሰጡት ምላሽ፤ የአማካኝ የቀን ገቢ ግምት አሠራር ጋር በተገናኘ ለሠራተኞች ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል። የባለሙያ ስብጥር እንዲኖም ከፋይናንስ፣ ከንግድ እና ከገቢዎች ቢሮ የተውጣጡ ሰዎች መሳተፋቸው ተነግረዋል።

ይህም በመሆኑ ሱቅ በመዝጋትም ሆነ ሌሎች እንዲዘጉ በመገፋፋት የሚፈታ ችግር የለም ያሉት አቶ አትክልት፤ በመርካቶ አካባቢ ተዘጉ የተባሉት ሱቆች ቀጥታ ከአማካኝ የቀን ገቢ ግምቱ ጋር የተያያዘ ነው አይደለም የሚለውን በትክክል ማጣራት ያስፈልጋል ብለዋል። 

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
321 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us