You are here:መነሻ ገፅ»ዜና

የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ ለወወክማ የቦርድ አባላት ምርጫ ዕውቅና መስጠቱ አወዛገበ

Wednesday, 16 August 2017 12:01

የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማሕበራት ኤጀንሲ  ለወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማሕበር (ወወክማ) አዲሱ ቦርድ ሕጋዊ እውቅና መስጠቱት በቀድሞ የቦርዱ አባላትና አዲስ ከተመረጡ የቦርድ አባላት መካከል የምርጫ አሰራር ሥርዓቱን ያልተከተለ ነው ሲሉ ለሰንደቅ ጋዜጣ ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም የተቃውሞው መነሻ፣ አዲሱ ቦርድ ከነባሩ ቦርድ በሕጋዊ መንገድ የንብረት፣ የሰነድ እና ሌሎች ቁሶችን ሳይረከብ ወደሥራ የገባበት አግባብ ለውዝግቡ አንዱ መነሻ ነው፡፡ እንዲሁም አዲሱ ቦርድ ከሕግ አግባብ ውጪ ተሰይሟል የሚል ተቃውሞ ተነስቷል፡፡ በአዋጅ 621 እና በ1943 የወወክማ ማቋቋሚያ አዋጅ መካከል የሕግ ትርጓሜ አስነስቷል፡፡ በእነዚህ ላይ የሚመለከታቸውን ሰዎች አነጋግረን በዚህ መልኩ አቅርበነዋል፡፡ 

የአዲሱ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ይርጋ በአጠቃላይ በፍሬ ነገሩ ላይ የሰጡት ምላሽ ፣ “እነዚህን መሰል ጉዳዬች እንዲዳኝ በመንግስት ኃላፊነት ለተሰጠው የበጎ አድራጎት ድርጅትና ማሕበራት ኤጀንሲ  ቅሬታቸውን ማቅረባቸውን አውቃለሁ፡፡ ከኤጀንሲው ያገኙት ምላሽ ስላላረካቸው ነው ወደ ጋዜጣ የመጡት? አላውቅም! ሕግና ሥርዓት ባለበት ሀገር የሚመለከተው አካል የሰጠውን ውሳኔ ተቀብሎ በቅንነት መሔድ አስፈላጊ ይመስለኛል፣ እንደግለሰብ፡፡ የሆኖ ሆኖ በየአመቱ ጉባኤ ይጠራል፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ ጉባኤው ሲጠራ የማሕበሩን ሕገ ደንብ መሰረት አድርጎ ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ በተወካዬቻቸው በኩል ተገኝተው የእግዚአብሔር መንፈስ የተሞላበት ጉባኤ ነው ማካሄዳችን የማውቀው፡፡ ሶስት አራት አጀንዳዎች ነበሩት፡፡ ከእነሱም መካከል አንዱ በተጓደሉ የቦርድ አባለት ምትክ መምረጥ ነው፤ ተደርጓል፡፡”

“ምርጫ ያደረጋችሁት በተጓደሉ የቦርድ አባለት ለመተካት ነው? ወይንስ አዲስ ቦርድ ለመሰየም ነው?” ለሚለው ጥያቄ ሲመልሱ፣ “ጊዚያቸውን ከጨረሱ ጎድለዋል ነው፡፡ የቃላት አጠቃቀም ችግር ካለ በኋላ አርሙት፡፡ ምርጫ ግን ተደርጓል፡፡ አጀንዳውን ከጽ/ቤት ማግኘት ትችላላችሁ፡፡ ቃለ ጉባኤውም ለመንግስት ቀርቦ ነው የጸደቀው፡፡ ኤጀንሲ ሄዳችሁ ማየት ትችላላችሁ፡፡ ምርጫው ከተከናወነ ሁለት ወር በኋላ በሌላ ስብሰባ ቀርቦ ተቀባይነት አግኝቶ ነው ወደሥራ የተገባው፡፡ ጥሩ ሥራ ነው እየተሰራ ያለው፡፡ ወወክማ ሕግ ጥሶ አይሰራም፡፡ ከሕግ ውጪ አይሰራም ብዬም አምናለሁ፡፡ የእግዚያብሔር ቤት ነው፡፡” ብለዋል አቶ ይርጋ፡፡

 “ጠቅላላ ጉባኤው ሲጠራ አጀንዳ ቀርፃችሁ የቦርድ ምርጫ እንደሚደረግ አሳውቃችሁ፣ ከአስራ አምስት ቀን በፊት እንዲደርሳቸው ነው ያደረጋችሁት” አቶ ይርጋ ሲመልሱ፣ “ይህ ጥያቄ መቅረብ ያለበት ለቀድሞ የቦርድ ሰብሳቢ ለዶክተር ፀጋዬ በርሄ እና ለድርጅቱ ሥራአስኪያጅ አቶ ዳግማዊ ሰላምታ ነው፡፡ ሶስተኛው ሰው ደግሞ የጠቅላላ ጉባኤው ሊቀመንበር ናቸው፡፡ እስከማውቀው ድረስ ምርጫው በሕጋዊ መንገድ ነው የተካሄደው፡፡ በቀናነት የምትጠይቀኝ ከሆነ፣ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ቅሬታ አለን፣ ጥሪ አልደረሰነም የሚለው ተቋም ቅሬታውን አቅርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ አካሄዱ ትክክል ነው ተብሎ ስብሰባው ቀጥሏል፡፡ አንዲ ሺ ኪሎሜትር አድዋ የደረሰ ደብዳቤ አዲስ አበባ አልደረሰም ከተባለ፤ የኮሚኒኬሽን ችግር እንጂ የአሰራር ተደርጎ የሚወሰድ አይደለም” ብለዋል፡፡

በወወክማ ማቋቋሚያ አዋጅ ከአዲስ አበባ ውጪ የቦርድ ሊቀመንበር እንዳይሆን ይደነግጋል፡፡ ከዚህ አንፃር ከአዲስ አበባ ውጪ ሆነው የቦርድ ሊቀመንበር መሆንዎን እንዴት ያዩታል ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ “አሁን ያለው ወወክማ በአዋጅ 621 የተቋቋመ ነው፡፡ በዚህ አዋጅ ላይ እንዲህ የሚል ሕግ የለም፡፡ አዲስ አበባ ላይ ካልሆንክ ሊቀመንበር አትሆንም የሚለው በራሱ ዴሞክራሲያው አስተሳሰብ አይደለም፡፡ ሰብዓዊ አስተሳሰብ ነውን? በርግጥ በውስጥ አሰራራችን በቅርብ ቢሆን ይሻላል የሚል አረዳድ አለ፡፡ ለፊርማ፣ ለአሰራር አዲስ አበባ ያለ ይመረጣል በአስተሳሰብ ደረጃ፡፡ እንደሕግ ግን አትገድብም፡፡ ሕገ ማሕበሩ ላይም የመንግስት አዋጅ ላይ የለም፡፡ ኢሰበዓዊ ሕግ የለንም፡፡ ቢሆርም ሕጋዊ አይደለም ዴሞክራሲያው አይደለም፡፡” ብለዋል፡፡

“ከቀድሞ ቦርድ ሕጋዊ ርክብክብ አድረገችኋል” “አዲስ ተመራጭ አይደለሁም፡፡ ሶስት ዓመት ምክትል ነበርኩ፡፡ የምረከበውም ነገር የለም፡፡ አዲስ አይደለሁም፡፡ ሌላ እንግዳ ቢሆን ያስደነቅ ነበር፡፡ በሁለት ወር ውስጥ እንዲረከቡ ተብሎ በውይይት የተዘጋ አጀንዳ ነው፡፡ የተለየነ ነገር እኔ እንድቀበል የሚፈለገው ነገር ምንድን ነው ሲሉ ጥያቄውን በጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የቀድሞ የወወክማ ቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር ፀጋዬ በርኸ በበኩላቸው “ምርጫውን በተመለከተ ክርክሮችና ተቃውሞዎች ተነስተው ነበር፡፡ በአቶ አስናቀ እና በአቶ ስብሃት የቀረቡ የአሰራር ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ ሌሎችም የራሳቸውን መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡ የተፈጠሩት ልዩነቶች መፍትሔ እስከሚያገኙ የቀድሞ ቦርድ በጊዜያዊነት እንዲቆይ ተስማምተን ደብዳቤ ፃፍን፡፡ ደብዳቤ የፃፍንለት የበጎ አድራጎት ድርጅትና ማሕበራት ኤጀንሲ ለደብዳቤያችን ምላሽ ሳይሰጠን ቀረ፡፡ ለጠየቅነውም ዳኝነት ምላሽ ነፈገን፡፡ ለምን እንደሆነ ግን እስካሁን ግልፅ አይደለም” ብለዋል፡፡

“በእጃችሁ የሚገኙ የወወክማ ሰነዶች አስረክባችሁ ነው የለቀቃችሁት? ሪፖርት ለጠቅላላው ጉባኤ አቅርባችኋል?” ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ዶክተር ጸጋዬ በሰጡት ምላሽ፣ “ሰነዶች በጽ/ቤትም በእኛም እጅ አሉ፡፡ ከዚህ በፊት በነበረው አሰራር በሕጋዊ መንገድ ሰነዶችን ተረካክበን ነበር ወደሥራ የሚገባው፡፡ የተደረገው ግን ቦርድ ላይ ጠለፋ አድርገው፣ እውቅና አግኝተናል ብለው ነው ወደስራ የገቡት፡፡ እንዴት እንዲህ ሊሆን እንደቻለ አላውቅም፡፡  ቅሬታ የፈጠረብን ኤጀንሲው ነገሮችን እንዲያጣራ ደብዳቤ ጽፈንለት እያለ፣ ለምን ሕጋዊ ናችሁ ሲል እውቅና እንደሰጣቸው ነው፡፡ እነሱም ቀርበው ብትከሱንም ምንም አላመጣችሁም በማለት ወደሥራ መግባታቸውን አሳውቀውናል፡፡ ሁለት መሰረታዊ ነገሮችን አስቀምጠን ነው ከኃላፊነት ራሳችን ያገለልነው፡፡ አንደኛ፤ አሁን ያለውን ፀሐፊ አንጃ የፈጠረው ቡድን ነው ያመጣው፡፡

አመጣጡም ሕግን ያልተከተለ መሆኑን አሳውቀናል፡፡ ሁለተኛ፣ አጠቃላይ ጉባኤ ከመደረጉ በፊት ሁላችንም ለ70ኛው ዓመት ክብረ በዓል ስንሯሯጥ፤ አሁን በአንጃ የተሰለፈው ቡድን፣ ለብቻቸው በጊዮን ሆቴል ተሰብስበው ስለጠቅላላው ጉባኤ ቅስቀሳ ሲደርጉ እንደነበር በስብሰባው ላይ በግልፅ ተነግሯቸዋል፡፡ በአቶ ስብሃትና በአቶ የቀረበ ቅሬታ መኖሩም በስብሳበው ላይ ቀርቧል፡፡ እነዚህን ሁሉ ይዘን ረጋ ብለን ችግሮቹን ለመፍታት ነበር የታሰበው፡፡ በአድራጎት ድርጅትም ለጉዳዩ ክብደት ሳይሰጥ ዝም አለ፡፡ የሚገርመው በጣም ለወወክማ ጠቃሚ የሆኑት ዶክተር ሰሎሞን አሊ እና አቶ ጌታቸው በለጠ በአዲሱ ቦርድ ቢያካትቷቸውም፣ የአሰራር ሥርዓቱ የተከተለ ምርጫ አይደለም በማለት ከአዲሱ ቦርድ ለቀው ወጥተዋል፡፡ ምክንያታቸውም ሕጋዊ ርክብክብ ባልተደረገበት ሁኔታ በማናውቀው ውስጥ አንገባም የሚል ነው፡፡ ቦርዱን የጠለፉት ግን ድርጅታዊ ሥራ ሰርተናል በሚል ነበር ፍላጎታቸውን ሊያሟሉ የፈለጉት” ሲሉ አካሄዱን ተቃውመዋል፡፡

“በወወክማ ውስጥ የተለየ ጥቅም በመኖሩ ነው ወይንስ በሌላ ምክንያት ነው መጠላለፍ ውስጥ የተገባው?” ለሚለው ጥያቄም ሲመልሱ፣ “እኛ እስከ ነበርንበት ድረስ፣ ከራሳችን አውጥተን እንደግፋለን እንጂ ጥቅም የሚባል የለም፡፡ የሚፈልግም የለም፡፡ አብዛኞቻችን በተሻለ የሥራ ልምድና ሕይወት ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ምንአልባት ጥቅም ከተባለ አሁን የቦርድ ሰብሳቢ ናቸው የተባሉት አቶ ይርጋ ከመቀሌ ሲመጡ ውሎ አበልና ትራንስፖርት ይከፈላቸው ነበር፡፡ ባደረግነው ስብሰባ አንዱ የተነሳው አቶ ይርጋ የቦርድ ሰብሳቢ ሆነህ ከመቀሌ እየተመላለስ የትራንስፖርትና አበል እየከፈልን ሥራውን ልታስተዳድረው አትችልም የሚል መቃወሚያ አቅርበናል፡፡ የቦርድ አባልም መሆን አትችልም፡፡ ከክፍለ ሃገር እየተመላለሱ ወወክማን ማስተዳደር መምራት እንደማይቻል በግልፅ ተናግረን ተስማምተናል፡፡

በዚህ አሰራር ከተስማማን በኋላ ግን ከዘጠኙ ክልሎች ጥቆማ ተቀብለን ሳለ፤ መቀሌ ላይ ሲደርስ አቶ ይርጋ መግባት አለበት በሚል በእጩነት እንዲቀርብ ተደረገ፡፡ አስመራጭ ኮሚቴ ሰይመን ከተስማማን በኋላ፣ ወደኋላ ተመልሰን ለምን እንዲህ ይደረጋል የሚል ክርክር ተነሳ፡፡ አንጃ አደረጅቶ ስለነበር ፈጽሞ አይቻልም አሉ፡፡ እዚህ ነጥብ ላይ ነበር የተጨነቅነው፡፡ አብዛኛው ሰው ጫና ተደርጎበት ተገዶ ነው የሚሰራው፡፡ እንዴት ዛሬ ላይ አንጃ ተመስርቶ የምረጡኝ ዘመቻ ውስጥ ተገባ የሚል ጥያቄ አሳደረብን፡፡ ይህ ቡድን ከአሰራር ውጪ የራሱን ፀሐፊ አስቀምጧል፡፡ አሁን ደግሞ አንጃው የቦርድ ሰብሳቢ ብሎ ሰይሟል፡፡ ይህንን ያህል እርቀት ለምን መሄድ እንደፈለጉ እስካሁን ግልፅ የሆነ ነገር የለም፡፡ ምን ፈልገው ነው የሚለው ጥርጣሬ ያደረብን ከእነዚህ መነሻ ነው፡፡ ”

የአራት ኪሎ ወወክማ የቦርድ አባል አቶ አስናቀ ደምሴ በበኩላቸው የጠቅላላ ጉባኤ አጠራር በተመለከተ እንዳስቀመጡት፣ “ከአስራ አምስት ቀን በፊት አጀንዳውና ቦታው ተገልፆ ጥሪ ይደረጋል ነው የሚለው፡፡ በአምስት ቀኑስ ደግሞ የተጠራው አባል የሚያሲዘው አጀንዳ ካለው ማቅረብ ይችላል፡፡ አስራ አምስት ቀን አይደለም ሶስት ቀን አልተሰጠም፤ ሰጥተናል ካሉ ጥሪ ያደረጉበትን ደብዳቤ ከፒ ማቅረብ ነው፡፡ የጠቅላላ ጉባኤው ሰብሳቢ የቦርዱ ሰብሳቢ አይደለም፡፡ ከጉባኤው የሚመረጥ ነው፡፡ ጥሪም ሲደረግ የጠቅላላ ጉባኤው ሰብሳቢ ነው መፈረም ያለበት፡፡ ሰብሳቢው ከምክትል ሊቀመንበሩና ከጸሃፊው ጋር በጋራ ነው አጀንዳ የሚቀርጹት፡፡ በጠቅላላው ጉባኤ በተባለውም ፀሀፊውም ም/ሊቀመንበሩም አልተሳተፉም፡፡ ሁለተኛ “ተበትኗል በሚሉት ደብዳቤ” ላይ የጠቅላላ ጉባኤው ሰብሳቢ ፊርማ የለም፡፡ ጠቅላላው ጉባኤ ሕገወጥ መሆኑን በጊዜው በስብሰባው ላይ አቅርበናል፡፡ ሁሉም የጠቅላላ ጉባኤ አባት ስለመሆናቸው የተያዘ ፊርማም የለም፡፡ በበዓሉ ምክንያት ቀኑ ያለፈ ምርጫ በመሆኑ ከኤጀንሲው ታዛቢ መኖር ነበረበት፡፡” 

አቶ አስናቀ አያይዘውም፣ “በ1943 ዓ.ም ወወክማን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ የቦርዱ ሰብሳቢ ከአዲስ አበባ መሆን እንዳለበት በግልፅ ይደነግጋል፡፡ የአዋጁ መንፈስም ለአሰራር አመቺ በመሆኑ የቀረበ ነው፡፡ አዋጅ 621 ለኤጀንሲው ምዝገባ የሚያገለግል ነው፡፡ የኤጀንሲውን ስልጣን ነው የሚያሳየው እንጂ ሌሎች ድርጅቶች መፍረሳቸውን አይገልጽም፡፡ ኤጀንሲው የመንግስት ተቋም ነው፤ ወወክማ ደግሞ የበጎ አድራጎት ድርጅት ነው፡፡ ሁለቱም አዋጆች ራሳቸውን ችለው ለተለያዩ መስሪያቤቶች የወጡ አዋጆች ናቸው፡፡ በጠቅላላ ጉባኤ አስመራጭ ኮሚቴ የነበሩት፤ እጩዎችን ሲመርጡ ካስቀመጡት መስፈርት አንዱ ለሥራ አመቺነት እንዲረዳ የቦርድ ሰብሳቢው ከአዲስ አበባ መሆኑን እንዳለበት አሳውቀው ነበር፡፡ መቀሌ ላይ ሲደርስ የመቀሌው ተመራጭ እንዲወዳደር ድምጽ ይሰጥ ተብሎ፣ በድምጽ ብልጫ ሕግ ጥሰዋል” ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡

የቀድሞ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማሕበር አቶ ጌታቸው በለጠ በበኩላቸው “በሌለውበት ነው የአዲሱ የቦርድ አባል ተደርጌ የተመረጥኩት፡፡ ወወክማ ስላደግን ነው የመረጡት፡፡ ወደ ኃላፊነት ለመግባት ግን መቸኮል የለብንም የሚል  ልዩነት እንዳለኝ አሳውቄያለሁ፡፡ ይኸውም፤ ከቀድሞ የቦርድ ሕጋዊ ርክብክብ ሳናደርግ፣ የአዲሱ ቦርድ ራዕይ ምን እንደሆነ ሳያካፍሉን፣ የቀድሞ ቦርድ ድክመት ጥንካሬ ሳንሰማ፣ የተሰሩ ሥራዎች ሪፖርት ሳናዳምጥ፣ ያለው ንብረት ምን እንደሆነ ሳናውቅ ወደሥራ መግባት ጥሩ አይደለም፡፡ ትንሽ ታግሰን የወወክማ 70ኛ ክብረ በዓሉን  አክብረን ሰላማዊ የቦርድ ሽግግር እናድርግ የሚል ጥያቄ አቅርበን የነበረ ቢሆንም፤ አልሰሙንም፡፡ ስለዚህም ነገሮች ሰላማዊ እስኪሆኑ ራሴን ከጉዳዩ አርቄያለሁ” ሲሉ ያላቸውን ልዩነት አስቀምጠዋል፡፡

የበጎ አድራጎት ድርጅትና ማሕበራት ኤጀንሲ በተደጋጋሚ ደውለን በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሚሰጡት በኮሚኒኬሽን በኩል መሆኑን አስረድተውናል፡፡ የኤጀንሲው ኮሚኒኬሽን ቢሮ በተደጋጋሚ ብደውልም ስልክ የሚያነሳ የለም፡፡  

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
162 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us