You are here:መነሻ ገፅ»ዜና

በደረቅ ጭነት እና በሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ላይ የተጨመረው ግብር መጠን ባለቤት አጣ

Wednesday, 06 September 2017 13:30

·        ገንዘብ ሚኒስቴር እና ገቢዎች እየተወነጃጀሉ ነው ተባለ

 

በደረቅ ጭነት እና በሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ላይ የተጨመረው የ400 ፐርሰነት ግብር በምን መነሻ እና ማን እንደጨመረው ማወቅ እንዳቃታቸው የተሽከርካሪዎች ባለንብረቶች ለሰንደቅ ጋዜጣ ገለጹ፡፡ 

በአዲስ አበባ የሚገኙ በደረቅ ጭነት እና በሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ ማሕበራት ለሰንደቅ እንደገለጹት ከዚህ በፊት ከሚከፍሉት ስድስት ሺ እስከ ሰባት ሺ የግብር ክፍያ በአንድ ጊዜ ወደ አርባ ስምንት ሺ እንዴት እንደገባ የሚመለከታቸው ቢሮዎች አጥጋቢ ምላሽ መስጠት እንደተሳናቸው አሳውቀዋል፡፡

ገቢዎች በበኩሉ የገንዘብ ሚኒስቴር በ2008 ዓ.ም. ባወጣው አዋጅ እና ደንብ ማስከፈላቸውን፤ የጭማሪ ጥናቱ ሲደረግ ሁለት ጊዜ መድረክ ተመቻችቶ የትራንስፖርት ባለስልጣን ጥሪ ቢቀርብለትም አልተገኘም፣ ስለዚህም እኛ ባገኘነው መረጃ መሰረት ማስተካከያ አድርገናል፣ ለማስከፈል ተገደናል እንደተባሉ ማሕበራቱ ገልጸዋል፡፡  አያይዘውም፣ ማሕበራ በተገኙበት ውይይት የተደረገ ነው የመሰለን እንጂ አሁን እንደምትሉት እናንተን ያላሳተፈ ነው ብለን አልገመትንም ብለዋል፡፡

ገንዘብ ሚኒስቴር በበኩሉ በአቶ ብርሃኑ በኩል “በእኛ በኩል የተሻሻለው “ሐ” ግብር ከፋዮችን በተመለከተ ነው፡፡ የግብር “ሀ” እና “ለ” በተመለከተ ገቢዎች በተሰጠው ስልጣን ነው ያሻሻለው” የሚል ምላሽ እንደሰጣቸው ገለጸዋል፡፡  

በእኛ በኩል ያቀረብነው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ መፍጠር ነበረባችሁ፡፡ ማሕበራቱ እንደተለመደው ክፍያ ሊፈጽሙ ሲሄድ በ2008 ዓ.ም. የፀደቀ አዋጅና የማስፈጸሚያ ደንብ አለ ብላችሁ እንዴት ክፈሉ ትላላችሁ፡፡ ከምን ታሳቢ ነው ደረጃ “ሀ” እና “ለ” በዚህ ደረጃ የገመታችሁት ብለን ጥያቄ ብናቀርብም ምላሽ አልሰጡንም፡፡ ከአቶ ያሬድ ከሚባል ኃላፊ ጋር አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተን እንወያያለን ብለው የዛሬ ሶስት ሳምንት ቃል ቢገቡም ምላሽ አልሰጡንም ብለዋል፡፡ 

“ስብሰባው ሳይጠራ ማሻሻያ ተደርጓል ብለው አዲስ የግብር ክፍያ በትነዋል፡፡  በዚህ ሂደት ውስጥ ሰው መክፈል ጀምሯል፡፡ በተባለው ቀን ስብሳባ አልጠራ ሲሉን ሰኞ ዕለት ወደ ቢሮው ሄደን፡፡ ያሬድ የሚባለው ሊደበቀን ሞከረ፡፡ ሮጠን አገኘነው፡፡ አለቃዬን ተስፋዬን አናግሩት አለን፡፡ አቶ ተስፋዬ ደግሞ ገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር በሰጠን መሰረት ነው ማስከፈል ያለብን አለን፡፡ እንደሚባለው አላስከፈልንም ብሎ አዲስ ታሪፍ አውጥቶ አሳየን፡፡ የሰጠን ታሪፍ ይዘን ከከፈልነው ጋር አመሳከርነው፤ አንተ እንደምትለው አስልተን  ከስድስት ሺ ወደ አስራ አራት ሺ አካባቢ ነው የሚደርሰው፡፡ ይህንን የከፈልነው ደረሰኝ ተመልከተው፤ አርባ ስምንት ሺ ብር ነው የከፈልነው፡፡” አልነው

“እንዲህ ከሆነ ስህተት ነው፡፡ አሁን ማስተካከያ አድርገናል አለ፡፡”

 “እንዴት የመንግስት ተቋም በዚህ መሰል አለመመሪያ ሊያስከፍል ይችላል ስንል ጠይቅነው” የሰጠን ምላሽ “ሰራተኞቹ ረቂቅ ደንቡን ተከትለው ነው ያስከፈሏችሁ አለን፡፡ ስብሳባ ጠርተን ይፋዊ መግለጫ እንሰጣለን አለን፡፡ አቶ ብርሃኑ ውጭ ስለወጣ ነው፣ ሲመለስ ስብሰባ ጠርተን ክፍተቱ የቱጋ እንደተፈጠረ እንወያያለን አለን፡፡ የከፈላችሁት ለሚቀጥለው ግብር ክፍያ ይሆንላችኋል አለን፡፡ ይቅርታ እጠይቃለሁ አለ፡፡” ቢልም ሰኞም ማክሰኞም ጠበቅነው የተፈጠረ ነገር የለም ብለዋል፡፡ 

በዚህ ጉዳይ አቶ ያሬድን ለማነጋገር ፈልገን ስልካቸው አይነሳም፡፡ አቶ ብርሃኑን አነጋረናቸው ስለጉዳዩ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
307 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us