You are here:መነሻ ገፅ»ዜና

ታፍ ቢቢ ቢዝነስ እያስገነባ የሚገኘውን ዓለም አቀፍ ሆቴል ሒልተን ኢንተርናሽናል እንዲያስተዳድረው ተስማማ

Wednesday, 06 September 2017 13:35

በፍሬው አበበ እና በፋኑኤል ክንፉ

ታፍ ቢቢ ቢዝነስ ኃ/ተ/የግል ማኀበር እያስገነባ የሚገኘውን ዓለም አቀፍ ሆቴል ማኔጅመንቱን ለሒልተን ዓለም አቀፍ ለመስጠት የሚያስችለውን ስምምነት ከትላንት በስቲያ አከናወነ።

ስምምነቱ ሰኞ ነሐሴ 29 ቀን 2009 ዓ.ም በሒልተን ሆቴል ተገኝተው የፈረሙት በታፍ ቢቢ ቢዝነስ ኃ/የተ/የግ ማኀበር በኩል አቶ ተካ አስፋው የድርጅቱ መሥራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር፣ ሚስተር ማይክል ኩፐር የሒልተን ዓለም አቀፍ ንግድና ልማት ምክትል ፕሬዚደንት ናቸው።

አቶ ተካ አስፋው የታፍ ቢቢ ቢዝነስ ኃ/የተ/የግል ማህበር መሥራችና ማኔጂንግ ዳይሬክተር በሥነሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ከሒልተን ዓለም አቀፍ ግሩፕ (Hilton World Wide) ጋር ለረዥም ጊዜ በመወያየት እና ግንኙነት በማድረግ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውሰው፣ ከሒልተን ዓለም አቀፍ ሆቴሎች አንዱ እና ታዋቂ በሆነው “ደብል ትሪ” ብራንድ ተመርጠን እነሆ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ሆቴል በከተማችን ለመፍጠር በቅተናል ሲሉ የተሰማቸውን ደስታ ለታዳሚዎች ገልጸዋል።

አቶ ተካ አያይዘውም፣ በአዲስአበባ ቦሌ ብራስ ሆስፒታል አጠገብ በድርጅታቸው አማካይነት በመገንባት ላይ የሚገኘው ባለ 11 ፎቅ ሆቴል ዲዛይኑ በከፍተኛ ባለሙያዎች የተዘጋጀ፣ ውስጡም በአውሮፓ ዕቃዎች የተሟላና ከፍተኛ ውበት የተላበሰ ነው ብለዋል። የሆቴሉ ግንባታ በአሁኑ ሰዓት 70 በመቶ መጠናቀቁንና ቀሪ 30 በመቶ ሥራዎቹ በስምንት ወራት ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጹት አቶ ተካ፣ የግንባታው ጠቅላላ ወጪው 300 ሚሊየን ብር እንደሚፈጅ አስታውቀዋል። በግንባታው ሥራ ውስጥ እስከ 500 የሚደርሱ ወገኖች የሥራ ዕድል መፈጠሩን፣ ሆቴሉ ሥራ ሲጀምርም እስከ 500 ለሚደርሱ ወገኖች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

አቶ ተካ የሆቴሉ ግንባታ በከፍተኛ ውጣውረድ ውስጥ አልፎ ለዚህ በመብቃቱም የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው በሥራው ሒደት ከጎናቸው ለነበሩ አካላት፤ የዚያስ ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ደረጀ አሰፋ እና የድርጅቱ ባለሙያ የሆኑት አቶ ደረጀ ደስታን፣ በሆቴሉ የማማከር ሥራ የተሰማሩትን አቶ ፍስሃ አስረስን፣ የኮንስትራክሽን ሥራውን በማከናወን ላይ የሚገኙትን አቶ ሲሳይ ሰብስቤን እና የድርጅታቸውን ሠራተኞች እና  የሒልተን ቢዝነስ ዴቭሎፕመንት ምክትል ፕሬዝደንት ሚ/ር ማይክል ኩፐር ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል። እንዲሁም ለፕሮጀክቱ ብድርና  ሌተር ኦፍ ክሬዲት አገልግሎት በመስጠት እገዛ ያደረጉትን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አቢሲኒያ ባንክ አቶ ተካ አመስግነዋል።

 በመጨረሻም “ይህንን ታላቅ ሥራ ጀምሮ ለመጨረስ ያለውን ከባድ ጫና እና ትግል ተወጥቼ ፕሮጀክቱ እውን ይሆን ዘንድ ለዚህ ደረጃ ይበቃ ዘንድ ከጎኔ ሆነው ከፍተኛ አቅም የሆኑኝን ያበረታቱኝን እና ሞራል የሰጡኝን ምንጊዜም ውለታቸውን የማይረሳውን ታላቅ ሰው በዚህ አጭር ፅሁፍ መግለፅ አልችልም፤ ሆኖም ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለወገን ለሀገር አለኝታ ለሆኑት ለክቡር ዶ/ር ሼክ ሙሐመድ ሁሴን ዓሊ አል አሙዲን ምስጋናዬ ከፍ ያለነው፣ እድሜ እና ጤና ለእርሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው እመኛለሁ” ሲሉ ለአጋራቸው ያላቸውን ከበሬታ ገልጸዋል።

ሚስተር ማይክል ኩፐር በበኩላቸው ሒልተን ዓለም አቀፍ በመላው ዓለም ከ500 በላይ ቅርንጫፎችና ከ100ሺ በላይ የመኝታ ክፍሎች ያሏቸው ሆቴሎች በሥሩ መኖሩን አስታውሰው ወደኢትዮጵያ መጥተው ተጨማሪ ሥራ ለማከናወን ዕድል በማግኘታቸው አቶ ተካ አስፋውን አመስግነዋል። በቀጣይም ውጤታማ ሥራ እንደሚያከናውኑ እምነታቸውን ገልጸዋል።¾

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
377 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us