You are here:መነሻ ገፅ»ዜና

የእምቦጭ አረምን ለመከላከል ፌዴራል መንግስት የሚጠበቅበትን ያህል አልሰራም ተባለ

Wednesday, 13 September 2017 12:01

ከጣና ሀይቅ ባለፈ ወደአባይ ወንዝም የእምቦጭ አረም መስፋፋት እያሳየ መሆኑን በመጥቀስ አደጋውን ለመከላከል የፌዴራል መንግስት የሚጠበቅበትን ያህል አልሰራም ሲሉ የባህርዳር ከተማ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ በሰላም ይመኑ ለሰንደቅ ጋዜጣ ተናገሩ። በደቡብ ጎንደር አካባቢ ከጣና ጋር የሚገናኙ ወረዳዎች አረሙ በስፋት ታይቷል ያሉት ኃላፊው፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ በጣና ቂርቆስ ገዳማት አካባቢ የነበረው የቱሪስት ፍሰት መቀነሱንም ጠቁመዋል።

 

የአባይ ወንዝ በእምቦጭ አረም የሚደርስበት ጉዳት ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ይገኛል ያሉት ደግሞ የባህርዳር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ክብረት መሀመድ ናቸው። በአሁኑ ወቅት ከ25 ሄክታር በላይ የወንዙ ስፋት በአረሙ ተወሯል ሲሉ ያስታወቁ ሲሆን፤ በክልሉ መንግስትና በአካባቢው ወጣቶች ርብርብ ለመከላከል የሚደረገው ጥረት መቀጠሉንም የከተማ አመራሮች ያስረዳሉ። እንደከተማዋ የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ገለፃ  የክልሉ መንግስት ከህብረተሰቡ ርብርብ ባለፈ በሁለት የመከላከያ መንገዶች ለመጠቀም ከክልሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ ይገኛልም ብለዋል። የመጀመሪያው አረሙን ከስሩ ነቅሎ ማስወገድ የሚያስችል መሣሪያ መፍጠርን የሚመለከት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ አረሙን በምግብነት የሚገለገሉ ፌንጣዎችን በባዮሎጂካል መንገድ ማምረት ላይ ያተኩራል ብለዋል። በዚህም አካሄድ አሁን ላይ ከ700 በላይ የእምቦጭ አረምን የሚያወድሙ ፌንጣዎች መፈልፈላቸው የተጠቆመ ሲሆን፤ በቀጣይም ቁጥራቸውን አሳድገው ወደመከላከል ዘመቻው ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል።

 

የባህርዳር ከተማ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በተዘባ መልኩ ተጋኖ ሰላማዊ እንዳልሆነች እየተገለፀ እንደሚገኝ ያመለከቱት የከተማዋ ምክትል ከንቲባ፤ አሁን ላይ የተረጋጋች ናት፤ ሰላሟን ለማደፍረስ የሞከሩ አባላትም በህግ ቁጥጥር ስር ይገኛሉ ብለዋል። ባለፈው ዓመት ብቻ 28ሺህ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር ችለናል ያሉት ም/ከንቲባው በቀጣይም የከተማዋን ወጣቶች የስራ ጥያቄ ለመመለስ እየሰራን ነው ብለዋል።

በአዲሱ ዓመት የፌዴራሉ መንግስት በዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ የሚጠናቀቅ የኢንዱስትሪ ፓርክን ከከተማዋ አስተዳደር ባገኘው 250 ሄክታር መሬት ላይ እንደሚገነባ ተገለፀ ሲሆን፤ ከመሬቱ ለተፈናቀሉ አርሶ አደሮችም ተገቢው ካሳ ተከፍሏቸዋል ብለዋል። አክለውም የግል ባለሀብቶች በተለያዩ ዘርፎች ለመሰማራት በመቶዎች የሚቆጠሩ የኢንዱስትሪ ፕሮጀክት ግንባታዎች ጥያቄ ለአስተዳደሩ ማቅረባቸውንም ሰምተናል። እነዚህ የኢንዱስትሪ ግንባታዎች ሲጠናቀቁ ለበርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥሩ በመግለፅ ባህርዳር የበለጠ ለኑሮ ምቹና የተሻለች ከተማ ትሆናለች ሲሉ ምክትል ከንቲባው ስለመጪው የከተማዋ ተስፋ ይናገራሉ።  

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
243 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us