ለአራተኛ ጊዜ የተሻሻለው የቤተ ክርስቲያኒቱ ቃለ ዓዋዲ ጸድቆ ታተመ

Wednesday, 04 October 2017 12:20

Øበማዕከል ደረጃ በግእዝና በእንግሊዝኛ ተተርጉሞ በሥራ ላይ እንደሚውል ተጠቆመ

Øየውጭ አህጉረ ስብከት ከየሀገራቱ ሕግጋት ጋር እያጣጣሙ እንዲሠሩበት ይደረጋል

Øየሥራ አስኪያጅና አለቃ የሹመት መመዘኛንና የነጻ አገልግሎት ድንጋጌዎችን ይዟል

Øለውል እና የባንክ ብድር የጽሑፍ ማረጋገጫ ግዴታ ነው፤ የውጭ ኦዲትም ተካቷል

Øእስከ 30 ዓመት የነበረው የሰንበት ት/ቤት አባላት የዕድሜ ገደብ እስከ 35 ተሻሽሏል

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር የተደራጀበት የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ቃለ ዐዋዲ ደንብ፣ ለአራተኛ ጊዜ ተሻሽሎ የጸደቀ ሲሆን፤ ኅትመቱ ተጠናቆ ለሥርጭት መዘጋጀቱ ተገለጸ፡፡

ቋሚ ሲኖዶሱ፣ ባለፈው ዓመት ሰኔ ያጸደቀው መተዳደርያ ደንቡ፣ በ59 ገጾችና በ67 አንቀጾች ተዘጋጅቶና ተሻሽሎ እንደቀረበና ለሦስተኛ ጊዜ ተሻሽሎ እየተሠራበት የቆየውን የ1991 ዓ.ም. በመተካት ከሐምሌ ወር 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውል መወሰኑ ተገልጿል፡፡

ጊዜውንና የቤተ ክርስቲያኒቱን ዕድገት በማገናዘብ እንዲሁም፣ በመንግሥትና አጋር አካላት ተቀባይነት ሊያገኝ በሚያስችል ሁኔታ ተጠንቶ እንዲሻሻል፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ ጥቅምት 2004 ዓ.ም. ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት፣ በሕግ አግባብነት ያላቸውን አዳዲስ ሐሳቦች በማካተት መጽድቁ ተጠቅሷል፡፡

በምልአተ ጉባኤው በተቋቋመውና ስድስት ሊቃነ ጳጳሳትንና አምስት የጠቅላይ ጽ/ቤቱን ሓላፊዎች በአባልነት በያዘው ዐቢይ ኮሚቴ በተመራው የማሻሻል ሒደት፥ ከመምሪያዎች፣ ድርጅቶች፣ አህጉረ ስብከትና ማኅበረ ቅዱሳን፤ ሊሻሻሉ፣ ሊጨመሩና ሊቀነሱ ይገባል የተባሉ ሐሳቦችና ጽሑፎች በግብአትነት መሰብሰባቸው ተመልክቷል፡፡

በቃለ ዐዋዲው በተደነገገው መሠረት፣ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሥር፡- በመንበረ ፓትርያርክ፣ በመንበረ ጵጵስና ሀገረ ስብከት፣ በወረዳ እና በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በአራት ደረጃ ተዋቅሮ እንዲሠራ ተወስኗል፡፡

ቤተ ክርስቲያኒቱን፥ በዕውቀታቸው፣ በጉልበታቸው፣ በሀብታቸውና በአገልግሎታቸው መርዳት የሚችሉ ካህናት፣ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች የተደራጁበት ሲሆን፤ ሀብቱንና አገልግሎቱን በማስፋፋትና በመቆጣጠር ይሠራሉ፡፡

ለአራተኛ ጊዜ ተሻሽሎ በጸደቀው ቃለ ዐዋዲ፣ በቋሚነት ከተመደቡና ደመወዝ ከሚያገኙት አገልጋዮች ውጭ፣ በተለያዩ ድርጅቶች የሚሠሩ ካህናት፣ በትርፍ ጊዜያቸው፣ እንደየሞያቸውና እንደ ምርጫቸው፣ በሰበካው ልዩ ልዩ የሥራ ክፍሎች ውስጥ ተመድበው የነጻ አገልግሎት ማበርከት እንደሚችሉ ይፈቅዳል፤ ምእመናንም፣ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያንን በማይመለከቱ የሥራ መስኮች በነጻ ፈቃዳቸውና በትርፍ ጊዜያቸው የሚፈለግባቸውን አገልግሎት ማበርከት ክርስቲያናዊ መብታቸውና ግዴታቸው እንደኾነ ይደነግጋል፡፡

“ስለሚሾሙ፣ ስለሚቀጠሩና በበጎ ፈቃድ ቤተ ክርስቲያንን ስለሚያገለግሉ” በሚል በአንቀጽ 59 በሰፈረው በዚሁ ድንጋጌ፡- የደብር፣ የወረዳ ሊቃነ ካህናት እና የሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች የሹመት መመዘኛንም በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ ዕድሜ፣ የትምህርት ደረጃ፣ ሥነ ምግባር፣ የክህነት አገልግሎትና የአስተዳደር ሥራ ልምድ በመሠረታዊነት፣ የአካባቢ ቋንቋ ችሎታን በአማራጭነት ይዟል፣ መመዘኛው፡፡ በተጨማሪም፣ ለገዳማት፣ ለአድባራትና ለውስጥ አገልግሎት ምርጫና ሹመት የሚያስፈልጉ መስፈርቶችንም ደንግጓል፡፡

በቅዱስ ፓትርያርኩ የሚሾሙ የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ አበምኔቶችና እመምኔቶች በሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቅራቢነት በቅዱስ ፓትርያርኩ የሚሾሙ ሲሆኑ፣ ተጠሪነታቸውን ግን ለሊቀ ጳጳሱ ማድረጉ በማሻሻያው የተጨመረ አንዱ ነጥብ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ማንኛውም የገዳማቱ ገቢና ንብረት፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የበላይ ተቆጣጣሪነትና በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ሓላፊነት በሚታተሙ ካርኒዎች ብቻ እንዲሰብሰቡም ያዛል፤ ማዕርገ ምንኩስና ስለሚቀበሉ አገልጋዮችና ካህናትም ዝርዝር መመዘኛዎችን አካቷል፡፡

ለልማት ሥራ ብቻ፣ ከባንክ ገንዘብ መበደር እንደሚቻል በቀድሞው ቃለ ዓዋዲ አንቀጽ 12 ንኡስ አንቀጽ 6 ተቀምጦ የነበረውና በቋሚ ንብረቶችና ግምታቸው ከፍተኛ በሆነ በማንኛውም ጉዳዮች ላይ ውል ለመዋዋል በንኡስ አንቀጽ 7 ተቀምጠው የነበሩት ድንጋጌዎች፡- የሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባኤ፣ በሊቀ ጳጳሱ ሰብሳቢነት ሲፈቀድና ሲጸድቅ በሚል ብቻ ተቀምጠው የነበሩ ሲሆኑ፤ በማሻሻያው መሠረት  “ሊቀ ጳጳሱ ፈቃዳቸውን በጽሑፍ ሲያረጋግጡ” ብቻ እንደሚፈቀዱ በማሻሻል አጥብቆታል፡፡

የአጥቢያን ቤተ ክርስቲያን ገንዘብና ንብረት ጠቅላላ ገቢና ወጭ፣ በበጀት ዓመቱ መጨረሻና በሌላም አስፈላጊ ጊዜ፣ በሀገረ ስብከቱ የሒሳብ ባለሞያ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝና በሀገረ ስብከቱ ሲፈቀድ በጠቅላይ ቤተ ክህነት እንዲሁም ሀገረ ስብከቱ አወዳድሮ በውጭ ኦዲተር እንዲመረመር እንደሚያደርግ ተደንግጓል፡፡

የሰንበት ት/ቤቶች፣ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ከሚቋቋሙትና ከሚደራጁት የሥራ ክፍሎች አንዱ ሲሆኑ፤ አባሎቻቸው፣ ከአራት እስከ ሠላሳ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሕፃናትና ወጣቶች እንደሆኑ በቀድሞው ድንጋጌ የነበረውን ገደብ እስከ ሠላሳ አምስት በማድረግ ተሻሽለዋል፡፡ ማሻሻያው፣ ለወጣትነት የዕድሜ ክልል የተቀመጡ ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ መግለጫዎችን መሠረት ማድረጉ የተገለጸ ሲሆን፣ “ወጣቱ ይበልጥ ቤተ ክርስቲያኑን እንዲያገልግል ያስችለዋል፤” ተብሏል፡፡

ገቢ ያላቸው ካህናትም ኾኖ ምእመናን፣ ለሚገለገሉበት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የሰበካ ጉባኤ አባልነት ብር ኻያ እንደሚከፍሉና የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ በአስተዳደር ጉባኤ እያስወሰነ ከኻያ ብር በላይ ሊያስከፍል እንደሚችል ተመልክቷል፡፡ ይህም የወቅቱን የሀገሪቱንና የቤተ ክርስቲያኒቱን ዕድገትና አገልግሎት መስፋፋት መነሻ ያደረገ ነው፤ ተብሏል፡፡

 ከዐብዮቱ ፍንዳታ ቀደም ብሎ፣ የለውጡን አዝማሚያ በመረዳት፣ ከጥቅምት 15 ቀን 1965 ዓ.ም. ጀምሮ በዐዋጅ የተቋቋመው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፣ በመሬት ሥሪት ላይ ተመሥርቶ የኖረውን የቤተ ክርስቲያኒቱን መተዳደርያ በመተካት ከመዳከም ታድጎ ለዛሬው ዕድገቷና ልማቷ ያበቃት እንደኾነ ተደርጎ ነው የሚወሰደው፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቱን ህልውና መጠበቅ፣ የአገልጋዮቿን ካህናት የኑሮ ሁኔታ ማሻሻልና የምእመናኗን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ማሟላት ዋና ዓላማው እንደኾነና አስተዳደሯን በማጠናከር በገቢ ራሷን በማስቻል የማይተካ ሚና እየተጫወተ እንዳለ ተጠቁሟል፡፡

ይምረጡ
(4 ሰዎች መርጠዋል)
892 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 578 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us