የብር ምንዛሪ መውረድ የሚያመጣቸው ቀጣይ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች

Wednesday, 11 October 2017 12:41

ሰኞ ጥቅምት 29 ቀን 2010 ዓ.ም በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ መክፈቻ ስብሰባ ላይ የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ንግግር ባደረጉበት ወቅት የምንዛሪ ማስተካከያ የሚደረግ መሆኑን ጠቆም ያደረጉ ሲሆን በትላንትናው ዕለትም ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የብር ምንዛሪ ማስተካከያ ተደርጓል።


እንደ ብሄራዊ ባንክ መረጃ ከሆነ የብር ከዶላር አንፃር የብር የመግዛት አቅም በ15 በመቶ እንዲወርድ ተደርጓል። በዚህም መሰረት ቀደም ሲል አንድ ዶላር በባንክ በአማካይ ሲመነዘርበት የነበረው 23 ነጥብ 4177 ብር ወደ 26 ነጥብ 93 ብር ከፍ ብሏል። ይህ የዶላር መግዣ ዋጋ መነሻው ሲሆን በጊዜ ሂደትም ከፍ እያለ የሚሄድ ከመሆኑም ባሻገር የጥቁር ገበያው ዋጋም ከዚህም በላይ እየናረ የሚሄድ ይሆናል።


መንግስት ይህንን እርምጃ ሲወስድ በዋነኝነት እየተዳከመ ያለውን የኤክስፖርት ገበያ ለማጠናከር በሚል ሲሆን ይህንን ሁኔታ ግን አንዳንድ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች አግባብነት የሌለው እርምጃ መሆኑን በመግለፅ ሀሳባቸውን ያስረዳሉ።


ከዚህ ቀደም የዓለም ባንክ በሰጠው ምክረ ሀሳብ መሰረት የኢትዮጵያን የኤክስፖርት ምርት በዓለም አቀፉ ገበያ ተወዳዳሪ ለማድረግ በሚል በ2002/2003 ዓ.ም የብር የመግዛት አቅም ከዶላር አንፃር በ17 በመቶ እንዲወርድ መደረጉ የሚታወስ ነው።


ይህ እርምጃ ከተወሰደም በኋላ ቢሆን በተባለው መሰረት የሀገሪቱ ኤክስፖርት ገቢ እድገት ሲያመጣ አልታየም። በጊዜው የሀገሪቱ ኤክስፖርት ገቢ ከ3 ቢሊዮን ዶላር ያልበለጠ ሲሆን ከስምንት ዓመታት በኋላ በ2010 ዓ.ም ያለው ውጤትም ከዚህ የተለየ አይደለም።


በመንግስት በተለይም በንግድ ሚኒስቴር ዓመታዊ የኤክስፖርት አፈፃፀም ሪፖርቶች ላይ በተደጋጋሚ እንሚመለከተው የሀገሪቱ የኤክስፖርት ምርት በዓለም አቀፉ ገበያ መወዳደር ያልቻለው በጥራት ጉድለት፣ በቂ የሆነ የኤክስፖርት ምርትን ማቅረብ ባለመቻል፣የኤክስፖርት ምርት ስብጥርን ከማሳደግ ይልቅ በውስን የግብርና ምርቶች ላይ የኤክስፖርት ገቢውን ማንጠልጠል ገበያን በማፈላለግ የኤክስፖርት ምርት መዳረሻዎችን ከማስፋት ይልቅ ቀደሞ በነበሩት ገበያዎች ላይ ተወስኖ መቅረትና የመሳሰሉት ይገኙበታል።


በዚህ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ገብሩ አስራት የኢትዮጵያ የኤክስፖርት ችግር የሀገሪቱ ምርት በውጭ ገበያ መወደድ ሳይሆን የምርታማነት ብሎም የሙስና ችግር መሆኑን ገልፀውልናል።


አቶ ገብሩ እንደምሳሌም ያነሱት የወርቅ ኤክስፖርትን ጉዳይ ነው። እንደሳቸው ገለፃ የወርቅ ምርት ገቢ ሊቀንስ የቻለው የመንግስት ባለስልጣናትና ነጋዴዎች ተመሳጥረው በኮንትሮባንድ ወደ ውጭ የሚልኩበት ሁኔታ መፈጠሩ ነው። ይህም ሁኔታ መንግስት ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን የውጭ ምንዛሪ እንዳያገኝ አድርጎታል። ይህ ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ ያለው የውጭ ምንዛሪም ወደ ውጭ የማሸሽ ስራ መከሰቱም አንዱ በሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዲከሰት ያደረገ መሆኑን ይገልፃሉ።


በመሆኑም በአቶ ገብሩ ገለፃ ኤክስፖርትን እናበረታታለን በሚል ምክንያት የብርን የምንዛሪ ዋጋ ማውረድ ፈፅሞ ሚዛን የሚደፋ ምክንያት አይደለም። እንደሳቸው ገለፃ ሀገሪቱ ወደ ውጭ ከምትልከው በላይ ከውጭ የምታስገባው ምርት በአምስትና ስድስት እጥፍ ስለሚልቅ ይህ የብር ዋጋ መውረድ የሚያመጣው ውጤት በገቢ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ጭማሪን በማስከተል የህብረተሰቡን የመግዛት አቅም ከማዳከም ያለፈ ሌላ ፋይዳ የለውም።


አቶ ገብሩ ምርታማነት እስካላደገ ብሎም በኤክስፖርቱ ዘርፍ ያለውን ሙስና ማስወገድ አስካልተቻለ ድረስ የብርን የመግዛት አቅም ማውረድ በህብረተሰቡ ኑሮ ላይ ጫና ከመፍጠር ባለፈ የሚመያጣው ለውጥ አለመኖሩን ገልፀውልናል።


በዚሁ ዙሪያ ያነጋገርናቸው ሌላኛው የኢኮኖሚ ባለሙያ ዶክተር ጫኔ ከበደ በበኩላቸው ለውጭ ምንዛሪ እድገት አንዱ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍስት መሆኑን ገልፀው፤ ይሁንና ባለፉት ሁለት ዓመታት በሀገሪቱ የተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ አለመኖሩ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዳይኖር ያደረገው በመሆኑ የውጭ ምንዛሬውም በዚያው መጠን እንዲወርድ ያደረገው መሆኑን ገልፀውልናል። እንደ ዶክተር ጫኔ ገለፃ መንግስት የብርን የምንዛሪ አቅም በማውረድ በሚፈጠረው የዋጋ ንረት ህብረተሰቡን ከመጉዳት ይልቅ በቅድሚያ ፖለቲካዊ መፍትሄው ላይ በመስራት የተረጋጋ የኢኮኖሚ ከባቢያዊ ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ ነበረበት። ዶክተር ጫኔ የአቶ አስራትን ሀሳብ በመጋራት አሁን የብርን የምንዛሪ አቅም ማውረድ በኢምፖርት ምርቶች ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ እንዲኖር በማድረግ ግሽበት እንዲፈጠር የሚያደርግ መሆኑን ገልፀውልናል።

 

ይምረጡ
(10 ሰዎች መርጠዋል)
1236 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 38 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us