በኢዴፓ ውስጥ ለተነሳው ውዝግብ፤ ምርጫ ቦርድ ለዶ/ር ጫኔ ከበደ እውቅና ሰጠ

Wednesday, 20 December 2017 12:59

- እውቅና የተነፈገው የእነ አቶ አዳነ ታደሰ ቡድን ለቦርዱ ምላሽ ሰጥቷል

 

በይርጋ አበበ

 

በኢዴፓ አመራሮች መካከል በተፈጠረው የህጋዊነት ውዝግብ መነሻ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት የፓርቲውን ሊቀመንበር ዶ/ር ጫኔ ከበደ ናቸው ሲል፤ እውቅና ሰጥቷቸዋል። በአንፃሩ የአቶ አዳነ ታደሰን ሊቀመንበርነት እወቅና ነስቷል እውቅና የተነፈገው የእነ አቶ አዳነ ታደሰ ቡድን በበኩሉ ከምርጫ ቦርድ ለተነፈሰገው እውቅና ለቦርዱ ምላሽ ሰጥቷል።


ምርጫ ቦርድ እና የእነ አቶ አዳነ ታደሰ ቡድን የተመላለሷቸውን ደብዳቤዎች ከዚህ በታች ለአንባቢያን እንዲመች አድርገንአቅርበነዋል።

የምርጫ ቦርድ ውሳኔ

- በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 20.2.1 “የብሔራዊ ምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ በአራት ወር አንድ ጊዜ ይሆናል። ሆኖም የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ሲወስን ወይም ከምድር ቤቱ አባሎች 1/3ኛዎቹ ሲጠይቁ የምክር ቤቱ ልዩ ወይም አስቸኳይ ስብሰባ ሊጠራ ይችላል” በሚል የተቀመጠ በመሆኑ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ስለመወሰኑ ወይም ከምድር ቤቱ አባላት 1/3ኛዎቹ ጠይቀው ልዩ ስብሰባ ስለመደረጉ የተያያዘ ሰነድ አለመኖሩ፤

- በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 9.3 “ብሔራዊ ምክር ቤቱ የራሱን ሰብሳቢ ይመርጣል…”፣ 9.3.1 ሰብሳቢው “የምክር ቤቱን ስብሰባዎች ይመራል” ይላል። ይሁንና ጥቅምት 12 ቀን 2010 ዓ.ም የተካሄደው የብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ በማን ሰብሳቢነት እንደተካሄደ በቃለ ጉባኤው ላይ ያልተገለፀ መሆኑ፤

- ጥቅምት 12 ቀን 2010 ዓ.ም የተካሄደው የብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ ቃለ ጉባኤ ላይ በተጓደሉት የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምክት የማሟያ ምርጫ መካሄዱን፣ 3 ሰዎች ተጠቁመው ሁለቱ 1ኛ/ ወ/ት ጽጌ ጥበቡ 12 ድምጽ፣ 2ኛ/ አቶ ጌታሁን ብሬ 10 ድምጽ እንዳገኙ ተገልጿል። ይሁንና የሦስተኛው ተወዳዳሪ ስም እና ያገኙት ድምጽ ያልተገለፀ መሆኑ፤

- ጥቅምት 12 ቀን 2010 ዓ.ም የተካሄደው የብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ በቃለ ጉባኤ ላይ “… በቀጣይም ከተሟላው ሥራ አስፈፃሚዎች መካል… አቶ አዳነ ታደሰን በፕሬዚዳንትነት፣ ወ/ት ጽጌ ጥበቡን በምክትል ፕሬዚዳንትነት መርጧል” ከማለት ውጭ ለፕሬዚዳንትነትም ሆነ ለምክትል ፕሬዚዳንትነት ስንት ሰዎች እንደተወዳደሩና ያገኙት ድምጽ ያልተገለፀ መሆኑ፤

- ጥቅምት 12 ቀን 2010 ዓ.ም የተካሄደው የብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ ተሳታፊዎች ብዛት 14 እንደሆነ የቀረበው ሰነድ ያሳያል። ከእነዚሁ ውስጥ አቶ ተስፋ መስፍን የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚቴ አባል ሲሆኑ አቶ ደረጀ ዘርጋው በቦርዱ ጽህፈት ቤት በሚገኘው የፓርቲው የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት ዝርዝር ውስጥ ስማቸው የማይገኝ በመሆኑ የተገኙት የብሔራዊ ምክር ቤት አባላት ብዛትን 12 ያደርገዋል። በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 9.2.1 መሠረት የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት አባላት 25 ናቸው። በመሆኑም በአንቀጽ 21.1 “ማንኛውም ስብሰባ ከግማሽ በላይ በሆኑ አባሎች ውክልና ሊካሄድ ይችላል” እንዲሁም “… በፓርቲው ውስጥ ውሳኔዎች የሚፀድቁት ከግማሽ በላይ በሆኑ አባሎች ሲደገፉ ነው” በሚለው መሠረት ምልአተ ጉባኤ ሳይሟላ የተካሄደ ስብሰባ በመሆኑ፤ የቀረበው ሰነድ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን እያሳወቅን አቶ አዳነ ታደሰ “የፓርቲው ፕሬዚዳንት” በሚል የደብዳቤ ልውውጥ ማድረግ የማይችሉ መሆኑን በአክብሮት እንገልጻለን።


ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ታህሳስ 6 ቀን 2010 ዓ.ም በም/ል ዋና ኃላፊው ወንድሙ ጎላ ፊርማ ለኢዴፓ የሰጠውን ውሳኔ ተከትሎም በእነ አቶ አዳነ ታደሰ የሚመራው የኢዴፓ አመራር ደግሞ ታህሳስ 9 ቀን 2010 ዓ.ም ምላሽ ሰጥቷል። የፓርቲው ምላሽም ከዚህ በታች ቀርቧል።

 

የ“ኢዴፓ” ምላሽ


በ05/03/2010 ዓ.ም ብሔራዊ ምክር ቤቱ ያደረገውን ልዩ ስብሰባ የስራ አስፈፃሚው ወስኖ የተካሄደ በመሆኑ፣ /በ12/03/2010 ዓ.ም የተካሄደው የብሔራዊ ምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባ ደግሞ የብሔራዊ ምክር ቤቱ አባላት በ5/03/2010 ዓ.ም ባካሄዱት ልዩ ስብሰባ በ12/03/2010 ዓ.ም ስብሰባ ለማድረግ የወሰኑ መሆኑን የሚያሳይ የቃለ-ጉባኤ ማስረጃ ስላለን ደንብ ጥሰን ያደረግነው ስብሰባ የለም።


በ05/03/2010 ዓ.ም ባካሄድነው ስብሰባ በሰብሳቢነት እንዲመሩ የተመረጡት አቶ ጌታሁን ብሬ የነበሩ ሲሆን (ይሄም በ05/03/2010 ዓ.ም በተያዘው ቃለ - ጉባኤ ላይ ተገልጿል) በ12/03/2010 ዓ.ም የሚካሄደው ስብሰባ የ05/03/2010 ዓ.ም ቀጣይ ስብሰባ በመሆኑ ሌላ ሰብሳቢ መምረጥ ምክር ቤቱ አስፈላጊ ነው ብሎ ባለማመኑ ነው።


አቶ ተስፋ መስፍን በ12/03/2010 ዓ.ም በነበረው ስብሰባ ላይ ቃለ-ጉባኤም ላይ ይሁን የስብሰባ ተሳታፊዎች ስም ዝርዝር ፊርማ የፈረሙት በሰነዱ እንደሚታየው የኦዲትና ኢንስፔክሽን አባል መሆናቸውን በግልጽ አስፍረዋል። በስብሰባው ላይ የተገኙትም ስብስባውን ለመታዘብ ብቻ ነው። ስለዚህ አቶ ተስፋ መስፍንን እንደ ብሄራዊ ምክር ቤት አባልነት አድርገን እንዳቀረብን ተደርጎ የተወሰደበት ሁኔታ ተገቢ አይደለም። በመቀጠልም አቶ ደረጀ ዘርጋው እና የማናውቃቸው የብሄራዊ ምክር ቤት አባል በመሆናቸው በስብሰባው ላይ የተገኘውን የብሄራዊ ምክር ቤት አባላት ቁጥር 12 ስለሚያደርገው ምልዓተ-ጉባዔ ሳይሟላ ነው በሚል ውድቅ አድርጎታል።


አቶ ደረጀ ዘርጋው በብሄራዊ ምክር ቤት አባልነት በ22/06/2007 ዓ.ም ጀምሮ እየተሳተፉ ይገኛሉ። ይህንኑ የቃለ-ጉባኤ ማስረጃ በተጠየቅንበት ግዜ ለማቅረብ ዝግጁ ነን።


በሌላ በኩል ደግሞ በ3ኛ ተራ ቁጥር ላይ “ጥቅምት 12 ቀን 2010 ዓ.ም የተካሄደው የብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ ቃለ-ጉባኤ ላይ በተጓደሉት የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምትክ የማሟያ ምርጫ መካሄዱን፣ 3 ሰዎች ተጠቁመው ሁለቱ 1ኛ/ ወ/ት ጽጌ ጥበቡ 12 ድምጽ፣ 2ኛ/ አቶ ጌታሁን ብሬ 10 ድምጽ እንዳገኙ ተገልጿል። ይሁንና የሶስተኛው ተወዳዳሪ ስም እና ያገኙት ድምጽ ያልተገለፀ በመሆኑ የሚለው” እና በተራ ቁጥር 4 ላይ “ጥቅምት 12 ቀን 2010 ዓ.ም የተካሄደው የብሔራዊመ ክር ቤት ስብሰባ በቃለ ጉባዔ ላይ” በቀጣይም ከተሟላው ስራ አስፈፃማች መካከል… አቶ አዳነ ታደሰን በፕሬዝዳንትነት፣ ወ/ት ጽጌ ጥበቡን በምክትል ፕሬዚዳንትነት መርጧል። “ከማለት ውጭ ለፕሬዝዳንትነትም ሆነ ለምክትል ፕሬዚዳንትነት ስንት ሰዎች እንደተወዳደሩና ያገኙት ድምጽ የተገለፀ በመሆኑ” የሚለው በጊዜው በብሄራዊ ምክር ቤቱ ህገ ደንቡን ተከትሎ የተካሄደ ምርጫ ቢሆንም ቃለ ጉባዔ ላይ ሳይመዘገብ መቅረቱን እንደ ስህተት ተቀብለናል።


ስለሆነም ምርጫ ቦርድ በጉድለት የጠቀሳቸውን፣ ፓርቲውም ጉድለትነታቸውን ያመነባቸውን ጉዳዬች እንደገና ለማየት ታህሳስ 15 ቀን 2010 ዓ.ም ከጧቱ 3፡00 ሰዓት በቅሎ ቤት በሚገኘው የፓርቲው ጽ/ቤት ልዩ ስብሰባ እንዲካሄድ በህገደንቡ አንቀጽ 20.2.1 መሰረት በተጠየቀ ፔትሽን ስብሰባ ተጠርቷል።


በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ ጽ/ቤት በፓርቲው የውስጥ ጉዳይ የመግዛት መብት እንደሌለው ብናውቅም በፓርቲያችን ውስጥ የተፈጠረውን ችግር በግልጽነትና ህጋዊነት እንዲፈታ ፍላጎት ስላለን የኢዴፓ ብሔራዊ ምክር ቤት ልዩ ስብሰባ ላይ ቦርዱ ተወካይ ልኮ በታዛቢነት እንዲገኝልን በአክብሮት እንጋብዛለን።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
287 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1042 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us