የሰዓሊተ ምሕረት ምእመናን የካቴድራሉን አስተዳዳሪዎች ቢሮ አሸጉ

Wednesday, 03 January 2018 16:05

-  ገለልተኛና ከምዕመናንም ጭምር የተወከሉበት አጣሪ ኮሚቴ እንዲዋቀር ጠየቁ

 

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ቦሌ ክፍለ ከተማ፣ በደብረ ምጥማቅ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ካቴድራል ሓላፊዎች በደል በተቆጡና ምላሽ በተነፈጋቸው የአጥቢያው ምእመናን ርምጃ፣ ጽ/ቤቱ፣ ዓርብ ታህሳስ 20 ቀን 2010 ዓ.ም የአስተዳዳሪዎቹን ቢሮዎች አሸጉ። በዕለቱ ቢሮው በምዕመናኑ ከታሸገ በኋላ ምሽቱን፣ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ በማምራት ካልገባሁ ያሉት ዋና አስተዳዳሪው መልአከ ብርሃን ሩፋኤል በተቆጡት ምዕመናን መደብደባቸው ታውቋል። በአሁኑ ሰዓት ሕዝቡ በየጊዜው በድብሩ ኃላፊዎች እየደረሰ ያለ በደል አስመልክቶ ያቀረባቸው አቤቱታዎች ሰሚ ባለማግኘታቸው በራሱ ውሳኔ የደብሩ ሥርዓተ ቅዳሴና ዕለት ተዕለት አገልግሎት ሳይስተጓጎል የደብሩን አስተዳዳሪና ጸሀፊ ቢሮዎችን እንዲሁም መዝገብ ቤቱን ማሸጉን ጉዳዩ የሚመለከታቸው ምዕመናን ለሰንደቅ ጋዜጣ አረጋግጠዋል።

ትላንት ማክሰኞ ዕለት ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የተወከሉ እና በአጣሪ ኮምቴነት ተመድበናል ያሉ ግለሰቦች የአካባቢውን ምዕመናን ሰብስበው አነጋግረዋል። ምዕመናኑ የአካባቢው ሕዝብ በሠላማዊ መንገድ አቤቱታውን በየደረጃው ሲያሰማ መቆየቱን፣ የሀገረ ስብከቱ ኃላፊዎች ሕዝቡን አግኝቶ ለማነጋገር እንኳን ፈቃደኛ አለመሆናቸው፣ አሁን ለተፈጠረው ችግር አንድ መንስኤ ነው ብለዋል። አጣሪ ኮምቴውን በተመለከተ ነጻና ገለልተኛ የመሆኑ ጉዳይ ላይ ጥያቄ እንዳላቸውና በኮምቴው ውስጥ ምዕመናን ጭምር ተገቢ ውክልና ማግኘት ስላለባቸው ኮምቴውን ላይ እምነት እንደሌላቸው አስታውቀዋል። የአካባቢው ምእመናን አያይዘውም የደብሩ አስተዳዳሪዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከኃላፊነታቸው ተሰናብተው በምትካቸው ኃላፊ እንዲመደብ፣ የሚወክላቸው የሰበካ ጉባዔ እንዲመረጥ ጥያቄ አቅርበዋል።

 

የነገሩ አመጣጥ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የደብረ ምጥማቅ ሰአሊተ ምህረት ቅድስት ማርያምና ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ካቴድራል አንዳንድ አመራሮች ከሙስናና መልካም አስተዳደር ችግር ጋር ተያይዞ በደብሩ ምዕመናን የቅሬታ አቤቱታ ለቅዱስ ፓትርያርኩ ከሁለት ሳምንት በፊት አቅርበዋል።

አቤቱታ አቅራቢዎች ለብጹዕ ወቅዱስ አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ቃነጳጳሳት ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት ከሳምንት በፊት በጻፉት ደብዳቤ ደረሰብን ያሉትን በደሎች በጹሑፍ ዘርዝረው አቅርበዋል።

አቤቱታ አቅራቢዎቹ በዚሁ ደብዳቤያቸው ከጠቀሱዋቸው በደሎች መካከል የደብሩ አንዳንድ መሪዎች በቤተክርስቲያኒቱ እየተከናወነ ያለው የልማት ሥራ በቃለ ዓዋዲው መሠረት የልማት ኮሚቴ ተዋቅሮ በዕቅድና በሥርዓት ሊመራ ሲገባ ምንም እንኳን ለስሙ የልማት ኮሚቴ ተዋቀረ ቢባልም ያለ እቅድና ያለበቂ ጥናት በቤተክርስቲያኒቱ የአስተዳደር ኃላፊነት ላይ በሚገኙ ጥቂት ግለሰቦች የግል ፍላጎትና ሃሳብ ብቻ እየተከናወነ ስለመሆኑ፣ የቤተክርስቲያኒቱን የቦታ ይዞታ በሕዝብ የተመረጠ ሰበካ ጉባኤ በሌለበት፣ ግልጽነት በጎደለውና ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ በድብቅ ለግለሰቦችና ለተለያዩ ድርጅቶች ለረጅም ዓመት በኪራይ መልክ እየተሰጠ መሆኑን ይጠቅሳል። በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ የተገነቡት ሱቆች በህጋዊ መንገድ ሊከራዩና ለቤተክርስቲያኒቱ ተገቢውን ገቢ ሊያስገኙ ሲገባ በካቴድራሉ የአስተዳደር ኃላፊነት ላይ የሚገኙ ጥቂት ግለሰቦች ሱቆቹን በቤተሰቦቻቸውና በወዳጆቻቸው ስም በመቀራመትና የተከራየ በማስመሰል ለግል ጥቅማቸው እየተገለገሉበት ይገኛሉ ብሏል።

ጠቅላይ ቤተክህነት ለአድባራትና ገዳማት የቦታ ኪራይን በተመለከተ 2007 ዓ.ም ባወጣው መመሪያ መሠረት ገዳማትና አድባራት ቦታን ማከራየት የሚችሉት ለአንድ ዓመት ብቻ ሆኖ ሳለ ይህንን መመሪያ ወደ ጎን በመተውና ከሰበካ ጉባኤ እውቅና ውጪ የቤተክርስቲያኒቱን ቦታ ለሁለት የግል ድርጅቶች በራሳቸው ወጪ ሱቅ ሰርተው እንዲጠቀሙበት ለ10 ዓመት ቦታው በኪራይ መልክ እንዲሰጣቸው የተደረገበትን አሠራር ሕገወጥ ነው ሲሉ ተቃውመዋል።

በተጨማሪም የደብሩ አንዳንድ መሪዎች በቃለ-ዓዋዲው ላይ ከተቀመጠላቸው ሥልጣን ውጪ ከሀገረ ስብከቱ ምንም አይነት የተለየ መመሪያ ሳይሰጣቸው ቤተክርስቲያኒቱ በውርስ ያገኘችውንና በቤተክርስቲያኒቱ ስም ካርታ የወጣለትን ጉርድ ሾላ አካባቢ የሚገኝ ስፋቱ 169 ሜትር ካሬ የሆነ ቦታን በጨረታ አወዳድሮ በመሸጥ የቤተክርስቲያኒቱን ሀብት አባክነዋል ሲል ይከሳል።

ምዕመናኑ ይህንና ሌሎችም አቤቱታዎቻቸው በቅዱስ ፓትያርኩ እንዲጣራ ትዕዛዝ እንዲሰጡላቸውና አጥፊ በሆኑ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድላቸው በአካል ቀርበው መጠየቃቸውን አቤቱታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ በስልክ ጥያቄ ያቀረብንላቸው የደብሩ አስተዳዳሪ መላዕከ ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሃን ምላሽ ለመስጠት ቀጠሮ ይዘውልን የነበረ ቢሆንም በቀጠሮ ሰዓት በስልክ ማግኘት ባለመቻላችን ምላሻቸውን ለማካተት አልቻልንም።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ፓትርያርክ በቤተክርስቲያንዋ የተለያዩ መዋቅሮች የሚታዩ የመልካም አስተዳደር፣ የሙስናና ብልሹ አሠራር ችግሮችን ሕዝበ ክርስቲያኑ እንዲዋጋ በተደጋጋሚ ጥሪ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።¾

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
338 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 972 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us