ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ምርጫ ያለፉ አምስት ዕጩዎች ታወቁ

Wednesday, 17 January 2018 13:11

 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ምርጫ ሂደት አካል የሆነው የቃለ-መጠይቅ ፓናል መርሀ-ግብር ተካሔደ። አምስቱ ለዩኒቨርስቲዉ ቦርድ የሚቀርቡ ተወዳዳሪዎችም ታወቁ።


የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ተወካዮች የቃለ-መጠይቅ ፓናል በማካሄድ ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንትነት የተወዳደሩና ሁለት ማጣሪያዎችን አልፈው የደረሱ ስምንት እጩዎችን በመገምገም ነጥብ ሰጡ። ውጤቱም ከጠቅላላው 20 በመቶ ሲይዝ ተወዳዳሪዎች ያገኙት ነጥብ ተወካዮች ባሉበት ወዲያውኑ ይፋ ሆኗል።


አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መመዘኛውን ከሚያሟሉ አመልካቾች መካከል ዩኒቨርሲቲውን የሚመራ ፕሬዝዳንት ለመምረጥ ህዳር 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ማስታወቂያ በይፋ ማውጣቱ ይታወቃል። ማስታወቂያውን ተከትሎ በነበሩት 16 የምዝገባ ቀናት 22 ተወዳዳሪዎች ማመልከታቸው ይታወሳል።
የመጀመሪያውን ማጣሪያ አልፈው ሁለተኛውን ዙር የተቀላቀሉ 13 ተወዳዳሪዎች እንደሆኑ፣ ከእነዚህም መካከል 12ቱ በተመደበላቸው ጊዜ የዩኒቨርቲው ቦርድ ላቋቋመው የምልመላ እና መረጣ ኮሚቴ ስትራቴጅያዊ እቅዶቻቸውን ማቅረባቸውን፣ ከእነዚህም መካከል ወደ ሶስተኛ ዙር ወይም ለቃለ-መጠይቅ ፓናል የደረሱ ስምንት እጩ ተወዳዳሪዎች እንደሆኑ በቀደሙት መግለጫዎቻችን ማስታወቃችን የሚታወስ ነው።


ጥር 4 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ትልቁ አዳራሽ በተሰናዳው መርሀ-ግብር የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ የሚወክሉ ሁሉም የሴኔት አባላት፣ መምህራን፣ የአስተዳደር ሰራተኞች፣ የቅድመ-ምረቃና ድህረ-ምረቃ ተማሪዎች፣ ሴቶች እንዲሁም ልዩ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች በተወካዮቻቸዉ አማካኝነት በቃለ-መጠይቅ ፓናሉ ላይ ተሳታፊ ሆነዋል። ከዩኒቨርሲቲው ቦርድ፣ ከመምህራን፣ ከሴኔት፣ ከተማሪዎች እና ከኢንዱስትሪው ተውጣጥቶ የተቋቋመው የመረጣና ምልመላ ኮሚቴ መርሀ-ግብሩን አስተባብሯል።


ለስምንቱ እጩ ተወዳዳሪዎች ለእያንዳንዳቸው ስምንት ደቂቃዎች ተሰጥተዋቸው ፕሬዝዳንት ሆነው ቢመረጡ ምን ሊሰሩ እንዳሰቡ በአጭሩ አቅርበዋል። ተወዳዳሪዎች የሚያቀርቡበት ቅደምተከተል በዕጣ ተለይቷል። በዚህም መሰረት ዶ/ር ማቲዎስ እንሰርሙ፣ ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ፣ ፕ/ር ማስረሻ ፈጠነ፣ ፕ/ር ኤማና ጌቱ፣ ፕ/ር በቀለ ጉተማ፣ ፕ/ር ጣሰው ወልደሀና፣ ዶ/ር ጀይሉ ዑመር እና ዶ/ር ዳዊት ወንድማገኝ በቅደም ተከተል ንግግር አድርገዋል።


ተወዳዳሪዎች በተሰጣቸው ጊዜ ሀሳባቸውን ካቀረቡ በኋላ ከእያንዳንዱ ተወዳዳሪ ንግግር ቀጥሎ ከመድረኩ ተሳታፊዎች ጥያቄዎች ቀርበዉ መልስ እንዲሰጡባቸዉ ተደርጓል። ተወዳዳሪዎች የንግግር ጊዜያቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የመረጣና ምልመላ ኮሚቴው ሰብሳቢ መድረኩን በመረከብ ተሳታፊዎች ጥያቄዎችን እንዲያነሱ እየጋበዙ፣ ለአንድ ተወዳዳሪ ስምንት ተሳታፊዎች ጥያቄ እንዲጠይቁ እድል ሰጥተዋል። በዚህም መሰረት ተወዳዳሪዎች ጥያቄዎችን ከመርሀ-ግብሩ ተሳታፊዎች ተቀብለዋል፤ መልሶቻቸውንም ሰጥተዋል። የተወዳዳሪዎች ንግግሮች፣ ጥያቄዎች እና መልሶች ካበቁ በኋላ ተወዳዳሪዎች እያንዳንዳቸው በሁለት ደቂቃ ውስጥ የማጠቃለያ ሀሳብ እንዲሰጡ ተጋብዘው፤ የማጠቃለያ ሀሳቦቻቸውን አቅርበዋል። በዚህም የመርሀ-ግብሩ ወሳኝ ሁነት ወደሆነው የነጥብ አሰጣጥ ስነ-ስርዓት ሽግግር ተደርጓል።


የመድረኩ ተሳታፊዎች ተወዳዳሪዎችን እንዲገመግሙበት የተዘጋጁ ስምንት ዋና ዋና መመዘኛ መስፈርቶች ነበሩ። እነዚህም ስትራቴጂያዊ አቅጣጫን የማዘጋጀት ችሎታ፣ የስትራቴጂያዊ አስተዳደር እውቀት፣ የሀገር አቀፍ ፖሊሲዎች እውቀትና ቁርጠኝነት፣ የአካዳሚያዊ አመራር ችሎታ፣ መልካም ስምና ሐቀኝነት፣ የግል ተነሳሽነት፣ የሕዝብ ግንኙነት ክህሎት እና የግንኙነት መረብ የመዘርጋት ችሎታ ነበሩ።


የእያንዳንዱ የተወዳዳሪ የትምህርት ዝግጅት፣ አካዳሚያዊ ማዕረግ፣ የስራ ልምድ እና ሌሎች ደጋፊ ሰነዶች መርሀ-ግብሩ ከመጀመሩ አስቀድሞ ታድሏል። ለተወዳዳሪዎች ለእያንዳንዳቸው በስማቸው የተዘጋጀ የነጥብ መስጫ ቅፅ ተዘጋጅቶ ከስምንቱ መመዘኛ መስፈርቶች ጋር ለሁሉም የመድረኩ ተሳታፊዎች ታድሏል።


በአጠቃላይ 302 ተሳታፊዎች ተወዳዳሪዎችን ገምግመው ነጥብ ሰጥተዋል። የነጥብ አሰጣጥ ስነ-ስርዓቱ እንደተጠናቀቀ ሂደቱን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለመጨረስ ለእያንዳንዱ ተወዳዳሪ አንድ ኮሚፒውተር በማዘጋጀት፣ በጠቅላላ ስምንት ኮሚፒውተሮችን ስራ ላይ በማዋል፣ ሁሉንም ነጥቦች ወደ ኤክሴል በፍጥነት በማስገባት፣ ለእያንዳንዱ ተወዳዳሪ የተሰጡትን ነጥቦች በመደመር የመድረኩ ተሳታፊዎች በተገኙበት አማካኝ ውጤቶች ይፋ ሆነዋል።


የምልመላና መረጣ ኮሚቴው የፓናል መጠይቁን ጨምሮ እስካሁን የተካሄደዉን ዉድድር ዉጤት አጠቃሎ የመጨረሻ አምስት እጩዎችን ይፋ ያደረገ ሲሆን ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አመራር ቦርድ እንደሚያቀርብ ይጠበቃል።


በዚሁ መሰረት ለቦርዱ ዉሳኔ የሚቀርቡት ተወዳዳሪዎች የሚከተሉት ሆነዋል።


1. ፕ/ር በቀለ ጉተማ ጀቤሳ
2. ፕ/ር ፍቅሬ ደሳለኝ ቦሼ
3. ዶ/ር ጀይሉ ዑመር ሁሴን
4. ፕ/ር ማስረሻ ፈጠነ ወርቅነህ
5. ፕ/ር ጣሰው ወልደሀና ካህሳይ


የዉድድሩን ቀጣይ ሂደት በተመለከተ የዩኒቨርስቲዉ ቦርድ ከአምስቱ ተወዳዳሪዎች ሶስት እጩዎችን ለኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር የሚያቀርብ ይሆናል። ትምህርት ሚኒስቴር ከቀረቡለት የመጨረሻ እጩዎች መካከል አንዱን ለስድስት አመታት እንዲያገለግል በፕሬዝዳንትነት እንደሚሰይም ይጠበቃል።


በዚህ ጉዳይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕዝብ ግንኙነት ጽህፈት ቤት ሂደቱን እየተከታተለ መረጃዎች ማቅረቡን ይቀጥላል ሲል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕዝብ ግንኙነት ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
276 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1047 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us