ፕሬዝዳንት አልሲሲ የሰሞኑን የፖለቲካ ውጥረት የሚያለዝብ ንግግር አደረጉ

Wednesday, 17 January 2018 13:17

· ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በአንፃሩ ከግብፅ መልስ ዛቱ

· ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ወደ ግብፅ ሊያመሩ ነው

 

ከግብፅ ጋር በተያያዘ የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ውጥረት ውስጥ በገባበት በአሁኑ ወቅት የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ በድንገት የማረጋጊያ ድምፃቸውን ሰጥተዋል።


ግብፅ ለአካባቢው ፖለቲካዊ ውጥረት ምክንያት የሆነችው 20 ሺህ የሚሆነውን ጦሯን በኤርትራ ምዕራባዊ ግዛት ሳዋ አስፍራለች በመባሉ ነው። ውጥረቱ ማየሉን ተከትሎ የኢትዮጵያ፣የሱዳንና የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በየአቅጣጫው በሁለትዮሽ ውይይት ተጠምደው ከርመዋል።


በሱዳንና በግብፅ መካከል የተፈጠረውን ፖለቲካዊ ውጥረትና ወታደራዊ ፍጥጫ በማስከተሉ የሱዳኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢብራሂም ጋንዶር ወደ ካይሮ በማምራት ከግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚህ ሽኩሪ ጋር የተወያዩ መሆኑን የሱዳን ትሪብዩን ዘገባ ያመለክታል። በዚህም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የካይሮ ቆይታ ፕሬዝዳንት አልበሽር ለፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ የላኩትን ደብዳቤ ያደረሱ መሆኑ ታውቋል። በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ውይይት ወቅትም አንዱ የውይይት አጀንዳ የህዳሴው ግድብ ጉዳይ መሆኑን ዘገባው ጨምሮ ያመለክታል።


የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ በበኩላቸው ከሰሞኑ በካርቱም በመገኘት ከሱዳኑ አቻቸው ኢብራሂም ጋንዶር ጋር ወይይት አድርገዋል። ሆኖም የውይይቱ ርዕሰ ጉዳይ በምን ላይ ትኩረት እንዳደረገ ግልፅ ሆኖ የወጣ መረጃ የለም። በሌላ መልኩ በግብፅ ይፋዊ ጉብኝት ላይ የነበሩት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከጉብኝታቸው መልስ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የሰላ ትችትን በመሰንዘር እስከዛሬ የነበረውን ዝምታቸውን ሰብረዋል።


ኤርትራ በሳዋ የጦር ሰፈርን በመፈቀድ የግብፅ ጦር በአካባቢው እንዲሰፍር አድረጋለች የሚል ዜና በስፋት ሲናፈስ የከረመ ሲሆን ይሄንኑ ጉዳይ በተመለከተ ኤርትራም ሆነ ግብፅ በየግላቸው አስተባብለዋል። ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ማክተም ማግስት እስከዛሬም ድረስ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ብዙም ጠንከር ያለ ኃይለ ቃል ተጠቅመው ባያውቁም፤ ከሰሞኑ የግብፅ ጉብኝታቸው መልስ ግን በኢትዮጵያ ሥርዓትን እስከመቀየር የሚያደርስ እርምጃን የሚወስዱ መሆኑን የመናገራቸው ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል።


በዚህ ሰሞን በአካባቢውን የፖለቲካ ውጥረት በሰፈነበት ሁኔታ የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ሰኞ ዕለት ባደረጉት ንግግር ግብፅ ከኢትዮጵያም ሆነ ከሱዳን ጋር ጦርነት ውስጥ የመግባት እንደዚሁም በሀገራቱም የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የምትገባበት ሁኔታ አለመኖሩን ገልፀዋል። ፕሬዝዳንቱ ባሳለፍነው ሰኞ ጥር 7 ቀን 2010 ዓ.ም በርካታ የልማት ፕሮጀክቶችን ባስመረቁበት ዕለት ባደረጉት ንግግር የሰሞኑን የአካባቢው ፖለቲካዊ ውጥረትም አካተው ተናግረዋል።


በዚሁ ዙሪያም በሰጡት ማብራሪያ “ለኢትዮጵያና ሱዳን ወንድሞቼ የምነግራችሁ ነገር ቢኖር እኛ ከማንም ጋር ጦርነት ውስጥ አንገባም። ግብፅ በማንም ላይ ሴራን አትጎነጉንም ወይንም በሀገራቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አትገባም። እኛ በሀገራቱ መካከል ያለው መልካም ግንኙነት ተጠብቆ እንዲቀጥል እንፈልጋለን።” ብለዋል። ፕሬዝዳንቱ በዚሁ ንግግራቸው አክለውም “እኛ ከሱዳንም ሆነ ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ግንኙነት እንዲኖረን ቁርጠኛ አቋም ያለን ነን” ሲሉ ተናግረዋል።


አህራም ኦንላይን እንደዘገበው ከሆነ ፕሬዝዳንቱ አክለውም “ እኛ ከማንም ጋር ጦርነት ውስጥ የምንገባበት ሁኔታ የለም። ባለፉት ዓመታት በአካባቢው ለሆነው ሁኔታ አካባቢው ራሱ ምስክር መሆኑ በቂ ነው። እኛ የልማት ፖሊሲን ነድፈን ከመስራት ውጪ ሌላ አላማ የለንም፤ እያንዳንዱን ፓውንድ እንፈልገዋለን” ብለዋል።


የግብፅ፣ የኢትዮጵያና የሱዳን ግንኙነት ውጥረት ውስጥ የገባው በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ሲደረግ የነበረው የሶስትዮሽ ድርድር ከተቋረጠ በኋላ ነው።


የሱዳንና የግብፅ የሁለትዮሽ ግንኙነት እየሻከረ የመጣው በአንድ መልኩ በድንበር ግዛት ይገባኛል ጥያቄ ሲሆን በሌላ አቅጣጫ ደግሞ ከህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ሱዳን ድጋፏን ለኢትዮጵያ በመስጠቷ ነው። የሁለቱን ሀገራት ፖለቲካ ግንኙነት የበለጠ ውጥረት ውስጥ የከተተው ደግሞ ሱዳን ከቱርክና ከኳታር ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ እያጠናከረች ከመሄድ ባለፈ ሱአኪን በተባለች የሱዳን ደሴት ላይ ቱርክ የጦር ሰፈርን ፈቅዳለች የሚል ዜና በሰፊው ከተናፈሰ በኋላ ነው።


ቱርክም ሆነ ኳታር ፕሬዝዳንት አልሲሲ የሙስሊም ብራዘርሁድ አመራር የነበሩትን ሙሃመድ ሙርሲን ከስልጣን በማስወገድ ወደ ሥልጣን የመጡበትን መንገድ በግልፅ በመቃወም ድጋፋቸውን ለፓርቲው ሲሰጡ ቆይተዋል። ሙስሊም ብራዘርሁድን በስጋትነት የሚያዩት ግብፅና ሳዑዲ አረቢያ ሌሎች አጋሮቻቸውን በማስተባበር በኳታር ላይ ሁሉን አቀፍ ማዕቀብ የጣሉ ሲሆን አውሮፓዊቷን ቱርክ ግን ምንም ማድረግ አልቻሉም። ግብፅ የሱዳንን አማፅያን በመርዳት የአልበሽር መንግስት ከስልጣን እንዲወገድ እየሰራች ነው የሚል ክስ የሚቀርብባት ሲሆን በሌላ አቅጣጫ ሱዳንም ብትሆን ከኳታር ጋር በማበር የግብፁን ሙስሊም ብራዘርሁድ ታስታጥቃለች የሚል ክስ እየቀረበባት ነው።


በዚህ መሀል የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሪሲፕ ጣይፕ ኤርዶጋን በሱዳን ያልተጠበቀ ጉብኝት ማድረጋቸውና ሱዳንም ለቱርክ የጦር ሰፈር ለመስጠት ተስማምታለች መባሉ የግብፅንና የሱዳንን ግንኙነት የበለጠ ጡዘት ውስጥ ከተተው። አካባቢው ግልፅ ባልሆነ ተለዋዋጭ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ ባለበት በአሁኑ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ነገ ሀሙስ ወደ ካይሮ በግብፅ ይፋዊ ጉብኝት የሚያደርጉ መሆኑን የኮሙኑኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትሩ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ትላንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት በፕሬዝዳንት አልሲሲ ግብዣ መሆኑን ሚኒስትሩ ጨምረው ገልፀዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
226 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 154 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us