You are here:መነሻ ገፅ»ዜና

ለሥራ ወደውጭ ሀገራት መጓዝን የሚከለክለው እገዳ ተነሳ

Wednesday, 31 January 2018 12:24

 

ወደመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ለሥራ የሚሄዱ ኢትዮጵያዊያን ላይ እየደረሰ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመቅረፍ ይረዳል በሚል ከጥቅምት ወር አጋማሽ 2006 ዓ.ም ጀምሮ ታግዶ የቆየው የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ከትናንትናው ዕለት ጀምሮ እንዲነሳ የሚኒስትሮች ም/ቤት ወሰነ።


ቀደም ሲል በሥራ ላይ የነበረው የግል ሥራና ሠራተኛ የሚመለከተው አዋጅ ቁጥር 632/2001 በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት የሚያደርጉ ወገኖቻችን መብትና ጥቅም በማስከበር ረገድ ጉድለቶች አሉበት በሚል እስኪሻሻል ድረስ የውጭ ጉዞው ታግዶ እንዲቆይ ተደርጓል።


በ2008 ዓ.ም አዲሱ አዋጅ ሲወጣ የሥራ ስምሪቱ ቢያንስ የስምንተኛ ክፍል የትምህርት ዝግጅት ያላቸው፣ ከጉዞ በፊት በቂ ሥልጠና የወሰዱ ዜጎች የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት እንዲያገኙ ደንግጓል። አዋጁ የሥራ ስምሪቱ የሚከናወነው ሀገሪቱ የሁለትዮሽ ስምምነት ከምታደርግባቸው ሀገራት ጋር ብቻ እንደሚሆንም በአስገዳጅነት አስቀምጧል።


እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች በአሁኑ ወቅት ባልተሟሉበት ሁኔታ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት መፈቀዱ ብዙዎችን ግራ ያጋባ ሆኗል።


የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚ/ር የሥራ ኃላፊዎች ነገ ሐሙስ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር ማብራሪያ ለመስጠት ማቀዳቸው ታውቋል።


የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት መታገዱ በዘርፉ የተሰማሩ ላኪ ድርጅቶችን ሠራተኞቻቸውን በትነው ከሥራ ውጪ እንዲሆኑ ያደረገ ሲሆን፤ በርካታ ዜጎች መሥራት እየቻሉ ያለሥራ እንዲቀመጡ፣ አንዳንዶቹም በሕገወጥ መንገድ ከፍተኛ ገንዘብ ከፍለው እንዲጓዙና ሕይወታቸውን አደጋ ላይ እንዲጥሉ አድርጓል በሚል መንግሥትን ሲያስተቸው መቆየቱ የሚታወስ ነው።

 

ይምረጡ
(3 ሰዎች መርጠዋል)
652 ጊዜ ተነበዋል

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us