የፓርኪንሰን ህመምተኞች በመድሃኒት ዋጋ ንረት ተቸገርን አሉ

Wednesday, 14 March 2018 12:34

 

በይርጋ አበበ

 

የፓርኪንሰን ታማሚዎች በኢትዮጵያ ያው መድሃት ስርጭት፣ ዋጋ ንረት እና ከገበያ አለመገኘት ስጋት እንደሆነባቸው ተናገሩ። 


ለህመምተኞቹ ችግር መባባስ ዋናው ምክንያት በኢትዮጵያ ፓርኪንሰንን የሚመለከት ጥናት አለመካሄዱ መሆኑን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገልጿል። የፓርኪንሰን በሽታ በባህሪው ታማሚዎቹን የአካል እንቅስቃሴ፣ የእጅ ተግባር እና ንግግር የሚያደናቅፍ በመሆኑ ተማሚዎቹ ለዘርፈ ብዙ ችግር ተጋላጭ ናቸው። 


በዚህ ዙሪያ ለመገናኛ ብዙሃን ሃሳባቸውን የሰጡት በኢትዮጵያ የፓርኪንሰን ፔሸንትስ ሰፖርት ኦርጋናይዜሽን መስራች ወይዘሮ ክብራ ከበደ፤ “በሽታው እኛን ታማሚዎቹን ከአካል እንቅስቃሴ ሃሳብን እስከመግለጽ ድረስ የሚገታ በመሆኑ ችግራችንን የሚያውቅልን የለም” ሲሉ ተናግረዋል። ወይዘሮ ክብራ አያይዘውም፤ በሽታው መድሃኒት የሌለው መሆኑን ተከትሎ ለህሙማኑ ተስፋ የሚሆነው በወዳጅ ዘመድ እንክብካቤ ማግኘት ቢሆንም በተለይ በኑሮ ደረጃቸው ዝቅ ያሉ ሰዎች በሽታው ሁሉንም ነገራቸውን እንደሚጎድልባቸው ገልጸዋል።


ፓርኪንሰን ህመም መሆኑ ታውቆ ለታማሚዎቹ የተለያዩ መድሃኒቶች (በሽታውን ፈጽሞ ማዳን ባይችሉም) መመረት እና ክትትል መደረግ ከጀመረ ከ200 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል። በዚህም በዓለም ላይ በአስር ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የበሽታው ተጠቂ መሆናቸው ሲታወቅ፤ በኢትዮጵያ ግን ምን ያህል ታማሚዎች እንዳሉ መረጃው የለም። እስካሁንም በፓርኪንሰን ዙሪያ መንግስት የሰራው ጥናት አለመኖሩን በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ዳይሬክተሩ አቶ አበባው አያሌው ተናግረዋል። 


በሽታው በሁሉም የዕድሜ ክልል፣ በሁለቱም ጾታ፣ በሁሉም የአካባቢ እና የአየር ንብረት የሚኖሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ቢሆንም እስካሁን በሽታው እንዳለባቸው አውቀው ማህበር መስርተው ህክምና እየወሰዱ ያሉ ዜጎች ብዛት 500 ብቻ ናቸው። እነዚህ ህሙማን ደግሞ ሁሉም የሚገኙት አዲስ አበባ ከተማ ብቻ መሆኑን ወይዘሮ ክብራ ተናግረዋል። በፓርኪንሰን ዙሪያ በኢትዮጵያ ጥናት ቢካሄድ የህሙማኑ ቁጥር እጅግ ከፍተኛ እንደሚሆን ግምታቸውን ገልጸዋል። 


በኢትዮጵያ የፓርኪንሰን ፔሸንትስ ሰፖርት ኦርጋናይዜሽን የ2010 አምባሳደር አርቲስት ደሳለኝ ኃይሉ በበኩሉ የበሽታውን አስከፊነት ገልጾ በተለይ በኢኮኖሚ ደረጃቸው አነስተኛ የሆኑ ታማሚዎች የሚኖሩት ኑሮ አስከፊ መሆኑን ተናግሯል። ለዚህ ደግሞ ሁሉንም የበሽታው ተጠቂዎች በአንድ ጣራ ስር የሚያሳርፍ መጠለያ ለመገንባት በማህበሩ በእቅድ ደረጃ መያዙን ገልጾ፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለዚህ በጎ አላማ ከታማሚዎቹ ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርቧል። 


ፓርኪንሰን ካጠቃቸው ታዋቂ ሰዎች መካከል በኢትዮጵያ ለረዥም ዓመታት የኖሩትና የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ደራሽ የሚባሉት የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓክረስት አንዱ ሲሆኑ፤ ታዋቂው ቦክሰኛ መሀመድ ዓሊ ደግሞ ሌላው ተጠቃሽ ነው። 


በኢትዮጵያ የፓርኪንሰን ፔሸንትስ ሰፖርት ኦርጋናይዜሽን ሚያዝያ 6 ቀን 2010 ዓ.ም የግንዛቤ ማስጨበጫ በአዲስ አበባ የእግር ጉዞ ያካሂዳል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1319 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1031 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us