በዴር ሡልጣን ጉዳይ የእኅትማማቾቹ አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት እየተበላሸ መኾኑን ፓትርያርኩ ተናገሩ

Wednesday, 14 March 2018 12:56

• ገዳሙ እንዲታደስ የእስራኤል መንግሥት ቃል ቢገባም፣ ኮፕቶቹ ዕንቅፋት ኾነዋል
• “ልቀቁና በራሳችን እናድሰው” ያሉትን መንግሥትም ቤተ ክርስቲያንም ተቃውመዋል
• ፖፑ፥ “ጠቅላላ ገዳሙ የእኛ ነው፤ መመለስ አለባችሁ፤” ብለው ለኢትዮጵያ አቻቸው ጻፉ
• “ኢትዮጵያውያን የታሪክና የቅድስና አንጡራ ሀብታችን ነው፤ አያገባችሁም፤” /ፓትርያርኩ/
• በኢትዮጵያ ቅርስነቱ መንግሥት እንዲጠብቀው፣ ፓትርያርኩ ጠየቁ

በክርስትና አስተምህሮና ሥርዐት ባላቸው አንድነት፣ የ“ኦርየንታል ኦርቶዶክስ” ቤተሰብ የሚባሉት የኢትዮጵያ እና የግብጽ አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት፣ በጥንታዊቷ ኢየሩሳሌም ከሚገኘው የዴር ሡልጣን ገዳም እድሳት ጋራ በተያያዘ እየተበላሸ መኾኑን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ተናገሩ፡፡


ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የካቲት 24 ቀን ከተከበረው አምስተኛ ዓመት የፕትርክና በዓለ ሢመታቸው ጋራ በተያያዘ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ቴሌቪዥን ጋራ ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በከፋ እርጅና እየፈራረሰ የሚገኘው የዴር ሡልጣን ገዳምና የመነኰሳቱ ማረፊያ ቤት እንዳይታደስ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን እንቅፋት በመፍጠሯና ከዚያም አልፋ ጠቅላላ ይዞታውን ለመንጠቅ እየቃጣች በመኾኑ፣ የሁለቱ እኅትማማች አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት እየተበላሸ ነው፤ ብለዋል፡፡


የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ወቅት ገዳሙን ለማደስ ቃል መግባታቸውንና ይህንንም በጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የእስራኤል ጉብኝት ወቅት ቢያረጋግጡላቸውም፤ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ግን፣ “መንግሥት የሚላችሁን ትታችሁ እኛ እናድስላችሁ፤ በገንዘባችን፣ በመሐንዲሶቻችን በራሳችን እኛ እናድሰው፤” እያለች እንደኾነ ፓትርያርኩ ተናግረዋል፡፡


በጉዳዩ ላይ፣ “ዴር ሡልጣንን ለመጎብኘት ሔደን በኢትዮጵያውን መነኰሳት ተከልክለን ተባረርን፤” ካሉ ሁለት የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ወደ መንበረ ፓትርያርኩ መጥተው ስሞታ እንዳቀረቡላቸው የጠቀሱት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ “በእኛ ሥር ኹነው እንዲቀመጡ ንገሩልን፤ ንገሯቸውና መቆያ ቦታም እንሰጣችኋለን፤ ገዳሙን ልቀቁልንና እኛ እናድሰው፤” በማለት እንደጠየቋቸው አመልክተዋል፡፡


በፓትርያርኩ በኩል፣ “ያለፈው ይበቃችኋል” የተባሉት ሁለቱ ግብጻውያን ጳጳሳት፣ “ሳንመካከር፣ ሳንወያይበት እድሳት የሚባል ነገር እንዳይደረግ” በሚል ሊያስጠነቀቁ ቢሞክሩም ተቀባይነት ባለማግኘታቸው ለቤተ ክርስቲያኒቱ ፖፕ አባ ታዎድሮስ ማሳወቃቸውንና ፖፑም፣ የጳጳሳቱን አቋም በማጠናከር እድሳቱን ከመከልከላቸውም በላይ “ጠቅላላው ገዳሙ የእኛ ነው፤ መመለስ አለባችሁ፤” የሚል ደብዳቤ እንደጻፉ አቡነ ማትያስ በቃለ ምልልሱ አውስተዋል፡፡


ዴር ሡልጣን፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የታሪክና የቅድስና አንጡራ ሀብት እንደኾነ በመጥቀስ ለፖፑ ደብዳቤ ምላሽ የሰጠችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ እድሳት ከባለቤትነት ጋራ የሚያያዝ እስከኾነ ድረስ በቱሪስትነት እንጅ በባለቤትነት ታሪክ የማያውቃት የግብጽ ቤተ ክርስቲያን በእድሳቱም ጉዳይ የሚያገባት ነገር እንደሌለ መግለጿን አቡነ ማትያስ አስታውቀዋል፤ “ምንም ጸጸትና ርኅራኄ የሌላቸው ናቸው፤” በማለት ግብጾቹን ክፉኛ የወቀሱት ፓትርያርኩ፣ መንግሥት በኢትዮጵያ ቅርስነቱ ጥበቃ እንዲያደርግ በቃለ ምልልሳቸው ጠይቀዋል፡፡


ፓትርያርኩ ከሁለት ዓመት በፊት እስራኤልን በጎበኙበት ወቅት፣ “ምንም ቢሆን መነጋገር የማይፈታው ነገር የለምና እንነጋገርበታለን፤ ጉዳዩን እንፈታዋለን፤” የሚል ተስፋ ከሀገሪቷ ፕሬዝዳንት የተሰጣቸው ሲሆን፤ አምባሳደሩ አቶ ህላዌ ዮሴፍ ደግሞ፣ በኤምባሲው ዓመታዊ ዕቅድ ውስጥ የዴር ሡልጣን ጉዳይ ከዋነኛ ተግባራት አንዱ ኾኖ ተቀምጦ፣ ዋና መሥሪያ ቤቱም ክትትል እንደሚያደርግበት መግለጻቸው ተዘግቧል፡፡

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
2528 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 838 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us