የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን በአምስት ፌዴሬሽኖች ጥምረት ሊመሰረት ነው

Wednesday, 21 March 2018 12:36

 

· የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ጥሪውን አልተቀበለም

በይርጋ አበበ

 

ላለፉት ዘጠኝ ወራት በኮንፌዴሬሽን ምስረታ ላይ ጥናት ሲካሄድ ከቆየ በኋላ አምስት ፌዴሬሽኖችን ያቀፈ የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን ሊቋቋም ነው።


የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን አደራጅ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው ኃይሌ በተለይ ለሰንደቅ ጋዜጣ በሰጡት አስተያየት ኮንፌዴሬሽኑን የሚመሰርቱት አምስቱ ፌዴሬሽኖች ማለትም፤ የኢትዮጵያ ሆቴል መሰል አገልግሎት ሰጪ አሰሪዎች፣ የኢትዮጵያ ጥቃቅን አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች አሰሪዎች፣ የአማራ ክልል አሰሪዎች ፌዴሬሽን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሰሪዎች ፌዴሬሽን እና የኢትዮጵያ የከተሞች የመጠጥ ውሃ አገልግሎት አሰሪዎች ፌዴሬሽን መሆናቸውን ተናግረዋል።


ከ65 ዓመት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ የተመሰረተው የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን አሁንም እየተንቀሳቀሰ ሲሆን አሁን ከሚመሰረተው ኮንፌዴሬሽን ጋር ያለው ግንኙነትና ልዩነት ምንድን ነው? ለሚለው የሰንደቅ ጋዜጣ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ደግሞ፤ ‹‹አሁን በህግ እውቅና የተሰጣቸው ሁሉም ፌዴሬሽኖች እኩል የስልጣንና የኃላፊነት ደረጃ ያላቸው ሲሆን አንድ የበላይ የሆነ የጋራ ቤት ያስፈልጋቸዋል። ለዘጠኝ ወራት ያህል ውይይት ከተካሄደ በኋላ ይህ የአሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን ምስረታ ጫፍ ሊደርስ ችሏል። በዚህ ውስጥ እንዲሳተፍ ለኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ጥሪ ብናደርግም እስካሁን ምላሽ አልሰጡንም ወደፊት ምላሽ ይሰጡናል ብለን እየጠበቅን ነው›› በማለት ተናግረዋል።


‹‹ማህበራት ሲመሰረቱ በአዋጅ ቁጥር 377/97 እና በዓለም አቀፉ የአሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን መመሪያ መሰረት በፍላጎት እና በፈቃደኝነት እንጂ አስገዳጅ በሆነ መንገድ አይደለም›› ያሉት አቶ ጌታቸው፤ በአሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን ምስረታ ላይ የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ከአምስቱ የኮንፌዴሬሽን መስራች ፌዴሬሽኖች ጋር በጋራ እንዲሰሩ የሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሁለቱን አካላት ለማቀራረብ ሙከራ አድርጎ ነበር። አምስቱ የኮንፌዴሬሽን መስራች ፌዴሬሽኖች የሚኒስቴሩን ጥያቄ ለመቀበል ዝግጁ ቢሆኑም በኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን በኩል ግን እስካሁን ምላሽ አለመምጣቱን ተናግረዋል።


የአሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን አደራጅ ሰብሳቢ አያይዘውም ከአምስቱ መስራች ፌዴሬሽኖች በተጨማሪም ገና በምስረታ ላይ ከሚገኙት የተለያዩ ፌዴሬሽኖች ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ለአብነት ያህልም በማህበር ደረጃ ተደራጅቶ ለፌዴሬሽን አደረጃጀት ምዝገባ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ትራንስፖርት አሰሪዎች ፌዴሬሽን፣ በኮንስትራክሽንና በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፉ በምስረታ ላይ ያሉ የአሰሪዎች ፌዴሬሽኖች ኮንፌዴሬሽኑን የሚያጠናክሩ አባላት ሆነው ይቀጥላሉ ብለዋል። የኢትጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽንም እስካሁን ምላሽ አይስጥ እንጂ ወደፊት በአባልነት እንደሚቀላቀላቸው እምነታቸውን ገልጸዋል።


ከዚህ በተጨማሪም አዲሱ የሚመሰረተው የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማ) ጋር በጋራ ለመስራት በተለያዩ መንገዶች እንቅስቃሴ መጀመሩን ያስታወሱት አቶ ጌታቸው፤ በዓለም አቀፍ የሰራተኞች ኮንቬንሽን አንቀጽ 87 መሰረትም የዓለም አቀፉ ኮንፌዴሬሽን አባል ሆኖ የሚቀላቀል እንደሆነ አስታውቀዋል። ይህም ለኩባንያዎቹ እና ለባለሀብቶቹ ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
1210 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 189 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us