ጋዜጠኞች ስለ ዶ/ር አብይ አህመድ የጠቅላይ ሚኒስትር ሹመት ምን ይላሉ?

Wednesday, 04 April 2018 13:52

በይርጋ አበበ

 

ዶክተር አብይ አህመድ በኢህአዴግ ዘመነ ስልጣን ሶስተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተመረጡ በኋላ ያደረጉትን ንግግር በተመለከተ ምን አዲስ ነገር ተመለከታችሁ? ከእሳቸውስ ምን ይጠበቃል? ከንግግራቸው የታዘቡት ምንድን ነው? ስንል በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ለሚሰሩ ጋዜጠኞች ጥያቄ አቅርበንላቸው ነበር። ጋዜጠኞቹ የሰጡንን ምላሽ ከዚህ በታች አቅርበነዋል።

 

*** **** ***

 

ጌታቸው ዓለሙ በራዲዮ ፋና ፍሪላንስ ዜና አንባቢ


“ዶክተር አብይን የማውቃቸው ከሁለት ዓመት በፊት የከተሞች ፎረም ጎንደር ላይ በተካሄደበት ወቅት ስለከተሞች እድገትና የከተማ ከንቲባዎች እንዴት መምራት አለባቸው በሚል ሀሳብ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበው ነበር። ከዚያ በኋላ በግልም ሳገኛቸው ጥሩ ነገር አይቼባቸዋለሁ። ችግሮችን ከመረዳት በዘለለ የመፍትሔ ሃሳቦችን እና መንገዶችን አመላካች ምሁር መሆናቸውን ተረድቻለሁ። በስራቸው ሁሉም ሰው ተሳታፊ እንዲሆን የሚያስችል ባህሪ ነው ያላቸው። በበዓለ ሲመት ንግግራቸው የተረዳሁትም ይህንኑ ነው። ለምሳሌ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን እና ዲያስፖራዎችን የገለጹበት መንገድ ለዚህ ማሳያ ነው። ብሔራዊ መግባባት የሚፈጠረው በዚህ መንገድ ነው “አባቶቻችን በመተማ፣ በአድዋ፣ በማይጨው እና በካራማራ የአሁኑ ትውልድ ደግሞ በባድመ ለሀገር የከፈሉትን መስዋዕት ከፍተኛ ነው። እኛ ስንኖር ኢትዮጵያያዊ ስናልፍ ኢትዮጵያ ነን። የሚለው ንግግራቸው ደስ ብሎኛል። በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች የሚደግፏቸው ከሆነ ለውጥ ይመጣል ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም ዶክተር አብይ በግላቸው ቀና አስተሳሰብ ያላቸውና ጥሩ እውቀት ያላቸው መሆናቸው ብቻውን ለውጥ ለማምጣት በቂ አይደለም። ስለዚህ በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች ሊግፏቸው ግድ ይላል። የአገሪቱን ሰፊ የቆዳ ሽፋን የሚሸፍነው በአርብቶ አደሮች የተያዘ ነው። ዘርፉ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው እና በርካታ ዜጎችን የሚያስተዳድር ከመሆኑ አኳያ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። እስካሁን ትኩረት ተነፍጎት የቆየ በመሆኑ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በኋላ ለዚህ ዘርፍ ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ ይሰማኛል”

 

*** *** ***

 

ናዕምን አሸናፊ ከሪፖርተር ጋዜጣ

 

“ዶክተር አብይ በበዓለ ሲመታቸው ያደረጉትን ንግግር አዳምጬዋለሁ። በእውነት ተስፋ ሰጪ ንግግር ነው ያደረጉት። በተለይ ለወጣቱ ትውልድ ትልቅ ተስፋ ሰጪ ንግግር ነው። ከዚህ በተጓዳኝ አገሪቱ ብዙ ጥያቄዎች ያላቸው ዜጎች ያሉባትና ችግሮቹም ሰፊ ከመሆናቸው የተነሳ በርካታ ስራዎች ይጠብቃቸዋል። ዶክተር አብይ አንድ ግለሰብ ናቸው ምንም እንኳን የፓርቲውና የአገሪቱ መሪ ቢሆኑም ኢህአዴግ ደግሞ የሚመራው በዴሞክራሲ ማዕከላዊነት ነው። በዚህ የተነሳም ውሳኔዎች የሚተላለፉት በቡድን (collective leadership) በመሆኑ ህዝቡ በሚጠብቀው ልክ ለውጥ ይመጣል ብሎ መጠበቅ ከባድ ይሆናል። ሆኖም ግን ፓርቲው ከጎናቸው ከሆነ እና ለመለወጥ ዝግጁ ከሆነ ለውጥ ሊመጣ ይችላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።


በዚህች አገር ዴሞክራሲ እንዲኖር የዴሞክራሲ ምህዳሩ ሊስተካከል እንደሚገባ ግልጽ ነው። በዚህ በኩል በተለይ የበጎ አድራጎትና ማህበራት አዋጅ እና የሚዲያ ህጎች ላይ ማሻሻያ ቢደረጉ የሚል ሃሳብ አለኝ”

 

*** **** ***

 

ሐረገወይን ድረስ ከአሀዱ ሬዲዮ


“የዶክተር አብይ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ከሚያርጉት ጉዞ ጀምሮ ነበር ለዚህች አገር አስፈላጊ እንደሆኑ የተረዳሁት። የዚህ ስርዓት ባለስልጣናት በተደጋጋሚ አገሪቱ፣ አገሪቱ ሲሉ እንጂ ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል ሲጠሩ አይደመጡም ነበር። ዶክተር አብይ ግን በግማሽ ሰዓት ንግግራቸው ኢትዮጵያን ከ30 ጊዜ በላይ በመጥራት ኢትዮጵያን ከፍ አድርገዋታል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ማንም ሰው እንኳን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ደረጃ ቀርቶ ትንሽ ከፍ ወዳለ የስልጣን ደረጃ ከደረሰ ምስጋና አያውቅም። ‹በርካታ ውጣ ውረዶችን በጽናት አልፌ…. ወዘተ እዚህ ደረስኩ› ይላል እንጂ ጓደኛን፣ ሚስትን እና እናትን ሲያመሰግን አይታይም። ዶክተር አብይ ይህን ባህልም በመቀየር ማመስገንን አስተምረውናል። ወደ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ስንመጣ በዚህች አገር የተበላሸው ነገር ከመብዛቱ የተነሳ ለማስተካከል ሰፊ ጊዜ መውሰዱ አይቀርም። ዶክተር አብይም በዚህች አገር የተበላሸውን ነገር በሙሉ ለማስተካከል ጊዜ ያስፈልጋቸዋል ብዬ አምናለሁ። ነገር ግን በበዓለ ሲመት መግለጫቸው የህዝብን ችግር እና ጥያቄን በሙሉ ስለተናገሩ እና በህዝብም እምነት የሚጣልበት ንግግር ስላደረጉ አመኔታን ያገኛሉ። የህዝብን አመኔታ ያገኘ መሪ ደግሞ ህዝብን አስተባብሮ ለውጥ ለማምጣት ይቸግረዋል ብዬ አላስብም። የዶክተር አብይ ተስፋም ይህ ነው። ጊዜ መስጠት ግን አስፈላጊ ነው”

 

*** *** ***


ዳዊት በጋሻው ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ሰርቪስ (ኢቢኤስ)


“የተመራጩ ጠቅላይ ሚኒስትር ንግግር በፓርቲው ሹሞች ያልተባለ፣ በአድማጭ፣ በተመልካች እና በአንባቢያን ያልተሰለቸ እንዲሁም ተስፋ ሰጪም ነው። በተለይ አገር እና ህዝብ ምን ይፈልጋሉ የሚለውን በሚገባ ተናግረውታል። ምንም እንኳን በተግባር የሚታዩት ወደፊት ቢሆንም የተግባር ጅማሬው ወይም ሀሁ ንግግር ነው። የአንድን መሪ ባህሪ እና አቅድ ከምናውቅባቸው መንገዶች አንዱም ንግግራቸው ነው። በንግግራቸው ከዳግማዊ ምኒልክ ጀምሮ ያሉ መሪዎችን አመስግነዋል። አጼ ምኒልክ ብዙ ለፍተው ብዙ ሰርተው ግን ምንም እንዳልሰሩ በኢህአዴግ ሰዎች ሲብጠለጠሉ ነበር። የዶክተር አብይ ንግግር ግን ይህን የኢህአዴግ ሰዎች አስተሳሰብ የቀየረ ነበር። ስፋት ሰጥተው ከተናገሩባቸው አገራዊ ጉዳዮች ውስጥ 50 በመቶ የሚሆነው ወደ ተግባር ከተቀየረ በዚህች አገር ያለው ዘርፈ ብዙ እና መጠነ ሰፊ ችግር በብዙ መልኩ ይለወጣል”

 

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
826 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 158 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us