በዴር ሡልጣን ጉዳይ ኢትዮጵያውያን በኢየሩሳሌም ሰልፍ አካሔዱ

Wednesday, 18 April 2018 12:39
  • - የገዳሙ አስተዳደርና በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ ክትትላቸውን እንዲያጠናክሩ አሳሰቡ

 

የዘንድሮን የትንሣኤን በዓል ለማክበር ከመላው ዓለም በኢየሩሳሌም የተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን፣ በአወዛጋቢው የዴር ሡልጣን ገዳም ባለቤትነትና እድሳት ጉዳይ ሰላማዊ ሰልፍ አካሔዱ።

 

በእስራኤል የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ እና የዴር ሡልጣን ገዳም ባስተባበሩት በዚሁ ሰልፍ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ተጓዦች፤ በዕለተ እሑድ፣ ሚያዝያ 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ከጸሎተ ቅዳሴ በኋላ (ከጠዋቱ 4፡30)፣ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ቢሮ በማምራት አቤቱታቸውን አቅርበዋል።

 

ሰልፈኞቹ በአቤቱታቸው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የታሪክ እና የቅድስና ይዞታ በሆነው የዴር ሡልጣን ገዳም ላይ፣ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ይገባኛል በማለት እየፈጠረችው የምትገኘው ችግር እንዲገታ ጠይቀዋል፤ ከዚሁም ጋር በተያያዘ ጣሪያው በመሸንቆሩ ላለፉት ስምንት ወራት ተዘግቶ የቆየው የቅዱስ ሚካኤል ቤተ መቅደስ በአስቸኳይ ታድሶ አገልግሎቱ እንዲቀጥል እንዲደረግ፤ በማኅበረ መነኮሳቱም ላይ የሚደርሰው ተፅዕኖና አድልዎ እንዲቆምላቸው አመልክተዋል። ይህንኑ የሚገልጹና በዕብራይስጥ፤ በእንግሊዝኛ እና በአማርኛ ቋንቋዎች የተጻፉ መፈክሮችንም በጋለ ስሜትና በከፍተኛ ድምፅ አስተጋብተዋል።

 

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተወካይ በሰልፈኞቹ የተመረጡ ሦስት ልዑካንን ካነጋገሩ በኋላ በጽሑፍ የተዘጋጀውን አቤቱታ ተቀብለዋል፤ ምላሹንም በቅርቡ እንደሚያሳውቁ ለተወካዮቹ ቃል ገብተዋል። የገዳሙ አስተዳደርና በእስራኤል የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ክትትል እንዲያጠናክሩ ለሰንደቅ አስተያየታቸውን የሰጡ የሰልፉ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።

 

በዘንድሮው ክብረ በዓል ከአሜሪካ፣ ካናዳ፣ አውሮፓ እና በዋናነትም ከኢትዮጵያ በአጠቃላይ ከ11ሺሕ ያላነሱ ተሳላሚ ምእመናን በተለያዩ አስጎብኚ ድርጅቶች አማካይነት ወደ ኢየሩሳሌም የተጓዙ ሲኾን፤ በሰልፉም ከተጓዦቹና በእስራኤል ነዋሪ ከኾኑ ኢትዮጵያውያን መሳተፋቸው ተገልጿል፤ በቁጥር 350 ያህል ሰልፈኞች እንደኾኑ የዐይን እማኞች አረጋግጠዋል።

 

በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ይዞታ ከሆነው የዴር ሱልጣን ገዳም ባለቤትነት ጋር በተያያዘ ግብፅ የይገባኛል ጥያቄ በተደጋጋሚ በማንሳት፣ የእድሳት ሒደቱንም በማደናቀፍ እየተከሰቱ ባሉ አለመግባባቶች ሳቢያ፣ የሁለቱ ሀገሮች እኅት አብያተ ክርስቲያናት ታሪካዊ ግንኙነት እየሻገረ እንደሚገኝ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ በቅርቡ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ቴሌቭዥን የተናገሩትን ጠቅሰን መዘገባችን የሚታወስ ነው።                                                                

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
349 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 219 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us