የፌዴራል ዳኞች ምልመላ ቅሬታ አስከተለ

Wednesday, 02 May 2018 12:45


በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት የሚሠሩ ዳኞች የፌዴራል የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጽሕፈት ቤት ለሦስቱም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማለትም ለፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ፣ ለከፍተኛና ለጠቅላይ ፍርድ ቤቶች ዳኞችን ለመሾም ያደረገው ምልመላ ሕጉን ያልተከተለ፣ አድልኦና መገለል ያለበት አሠራር ሆን ብሎ ተግብሯል በማለት ቅሬታቸውን አቀረቡ።


ቅሬታ አቅራቢዎቹ የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጽሕፈት ቀደም ሲል አውጥቶት የነበረውን መስፈርት ሙሉ በሙሉ እንደሚያሟሉ ነገርግን ለጊዜው ግልጽ ባልሆነላቸው ምክንያት ከሌሎች እኩል ደረጃ ላይ ካሉ ጓደኞቻቸው በተለየ መልኩ ሳይመለመሉ መቅረታቸውን ተናግረዋል። የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባዔ በአዋጅ የተቀመጠውን መሥፈርት ወደ ጎን በመተው እና ቀደም ሲል ማስታወቂያ ሲወጣ የጠቀሰውን መስፈርት በመቀየር ሕጉን ያልተከተለ ምልመላ ማድረጉን፣ ቅሬታ አቅራቢዎች ለሰንደቅ ጋዜጣ አስረድተዋል።


የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ጽሕፈት ቤት ማስታወቂያ ሲያወጣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚወዳደሩ በዳኝነት ለስድስት ዓመታት የሠሩ ወይም በሌላ የሕግ ዘርፍ ለስምንት ዓመታት ያገለገሉ፣ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚወዳደሩ በዳኝነት ለአሥር ዓመታትና በሌላ የሕግ ሙያ ዘርፍ 12 ዓመታት ያገለገሉና ለመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ያለምንም ልምድ መመዝገብ እንደሚቻል መገለጹን ቅሬታ አቅራቢዎቹ አስታውሰዋል። ጉባዔው ያወጣውን መሥፈርት የሚያሟሉ በዳኝነት ላይ እየሠሩ የሚገኙ ዳኞች፣ ዓቃቤያነ ሕግ፣ ነገፈ ፈጅ፣ ጠበቆች፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ሌሎች የሕግ ባለሙያዎች ተመዝግበው እንደነበር የጠቆሙት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ ‹‹የተመረጡና ለፈተና የተጠሩ ዕጩዎች›› በማለት ዝርዝራቸውን በማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ ሲለጥፉ፣ እነሱ መዘለላቸውን አብራርተዋል።


በሥራ ላይ የሚገኙ ዳኞችንም ሲመለምሉ በ2006 ዓ.ም. ከተሾሙት የፌደራል ዳኞች የተወሰኑት ተጠርተው የተወሰኑት እንደተገለሉ ተናግረዋል። ይኼ ደግሞ ሕግን ያልተከተለ፣ በዘፈቀደ የተሰጠና አዋጅንም የሚጥስ መሆኑን አክለዋል። ጉባዔው መመርያውን ማሻሻል ከነበረበትም ዳኞችን ለመመልመል ማስታወቂያ ከማውጣቱ በፊት እንጂ፣ ማስታወቂያ ካወጣ በኋላ መሆን እንደሌለበትና በርካታ አቅም ያላቸውን ሰዎች የሚያገል፣ የሕግ የበላይነትን የሚጥስ፣ ግልጽነት የጎደለውና ለፍትሕ ሥርዓቱ ሊጠቅሙ የሚችሉ ሰዎችን የሚያስወግድ  መመርያ መሆኑን አቤቱታ አቅራቢዎቹ አስረድተዋል።

 

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የሚመለከታቸውን አካላት ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

አቤቱታ አቅራቢ ዳኞች ለሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ሚያዝያ 12 ቀን 2010 ዓ.ም ያቀረቡት የቅሬታ አቤቱታ እንደሚከተለው አስተናግደነዋል።

…………….

ለኢፌዲሪ ሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት

አዲስአበባ

ለኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር

አዲስአበባ

በፌዴራል ጠ/ፍ/ቤት የፌዴራል ዳኞች ምልመላ

ላይ ያለንን ቅሬታ ስለማቅረብ

እኛ… አመልካቾች በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በዳኝነት የሙያ ዘርፍ ከሚያዚያ 21 ቀን 2006 ጀምሮ ለ 4 ዓመታት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተሹመን ሕዝባችንን በማገልገል ላይ እንገኛለን። ወደዚህ የፌዴራል ፍ/ቤት ከመጣን ጀምሮ በመልካም ሥነ ምግባር እና በታማኝነት ሥራችንን ሕግን እና ሕግን መሰረት በማድረግ ብቻ ስናከናውን ቆይተናል።

በፍ/ቤቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የጉዳዮች መብዛት ከዳኞች ቁጥር ጋር ለማመጣጠን በተለያየ አስተዳደር ጊዜ የዳኞች ምልመላ በማድረግ በም/ቤቱ ዳኞችን ሲያሾም መቆየቱም ይታወቃል። በዚህም መሰረት የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ በሐምሌ ወር 2009 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ባወጣው ግልጽ የሥራ ማስታወቂያ እኛን አመልካቾችን ጨምሮ በርካታ የሕግ ባለሙያዎች ተፈላጊውን ችሎታ አሟልተን ተመዝግበን ነበር። ጉባኤው ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ የምልመላ ሂደቱን ሲያጓትት ቆይቶ የም/ቤቱ የሥራ ጊዜ ሊጠናቀቅ ሁለት ወር ብቻ እንደቀረው ሲያውቅ ስምንት ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በርካቶችን ያሳዘነ መስፈርት በማውጣት ከዘጠኝ ወራት ቆይታ በኋላ ሚያዚያ 03 ቀን 2010 ዓ.ም ለፅሁፍ ፈተና የሚቀርቡ እጩዎችን በማስታወቂያ ገልጿል።

ጉባኤው በመጀመሪያ የሥራ ማስታወቂያውን በጋዜጣ በሚያወጣበት ጊዜ ለፌ/ከፍ/ፍ/ቤት ለሚወዳደሩ በዳኝነት ለ6 ዓመት ያገለገለ/ች ወይም በሌላ የሕግ ሙያ ዘርፍ 8 ዓመት ያገለገለ/ች ለፌ/ጠ/ፍ/ቤት ለሚወዳደሩ ደግሞ በዳኝነት ለ10 ዓመት ያገለገለ/ች ወይም በሌላ ሕግ ሙያ ዘርፍ ለ12 ዓመት ያገለገለ/ች፣ ለፌ/መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ለሚወዳደሩ ደግሞ 0 ዓመት የሥራ ልምድ የሚል መስፈርት አውጥቶ ነበር። ለፅሁፍ ፈተና የተጠሩት እጩ ተፈታኞች ዝርዝር በሚለጠፍበት ጊዜ ግን ከዳኝነት ሙያ ውጭ ያሉ በሌላ የሕግ ሙያ ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙ ዐቃብያነ ሕጎች፣ ነገረ ፈጆች፣ ጠበቆች፣ የዩኒቨርስቲ የሕግ መምህራን እና ሌሎች የህግ ባለሙያዎችን በሙሉ ከውድድሩ ውጭ እንዲሆኑ ከማድረጉም በላይ በ2006 ዓ.ም የተሾምን የፌዴራል ዳኞችን ከፊሎቹን ለፈተና እንዲቀርቡ፣ ከፊሎቹን ደግሞ ለፈተና እንዳይቀርቡ የሚያደርግ ምልመላ ተከናውኗል። ይህ የምልመላ ሂደት ፈፅሞ ሕግን ያልተከተለ እና በዘፈቀደ የተሰራ ነው የምንልበት ምክንያቶች እንደሚከተለው እንጠቅሳለን።

 

1.  በተሻሻለው የፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 684/2002 አንቀጽ 11 ላይ ከተቀመጠው በዳኝነት ለመሾም ብቁ ከሚያደርጉ ሁኔታዎች መካከል “እውቅና ካለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም በሕግ ትምህርት ቢያንስ በመጀመሪያ ዲግሪ በከፍተኛ ውጤት የተመረቀ ሆኖ ዝርዝር አፈፃፀሙ ጉባዔው በሚያወጣው መመሪያ ይወሰናል” የሚል ሲሆን መጀመሪያ ማስታወቂያው ሲወጣ በነበረው የጉባኤው መመሪያ ብቁ ናቸው በሚል ከተመዘገብን በኋላ እንደገና አዲስ መመሪያ አውጥተናል በሚል ብዙዎችን ያሳዘነ ምልመላ ማከናወኑ ተገቢ አይደለም። ተገቢ አይደለም የምንለውም ጉባኤው መመሪያውን ማሻሻል ከነበረበትም ማስታወቂያ ከማውጣቱ በፊት እንጂ ማስታወቂያ ከወጣ እና በርካታ ሰዎች ለዳኝነት ካመለከቱ በኋላ በርካታ አቅም ያላቸውን ሰዎች የሚያገል መመሪያ ማውጣት የሕግ በላይነትን የሚጥስ እና ግልጽነት የጎደለው ነው። ለፍትሕ ሥርዓቱ ሊጠቅሙ የሚችሉ ሰዎችንም የሚያስወግድ (technical avoidance) ነው።

2.  ከላይ እንደተጠቀሰውም አንዱ መስፈርት “እውቅና ካለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም በሕግ ትምህርት ቢያንስ በመጀመሪያ ዲግሪ በከፍተኛ ውጤት የተመረቀ” የሚል ሲሆን ቢያንስ CFPA 2.75 እና ከዚያ በላይ ያለው መሆን እንዳለበት መረዳት ይቻላል። ነገር ግን ጉባኤው የትምህርት ውጤትን ከግምት ውስጥ ሳያስገባ በጣም ዝቅተኛ ውጤት ያላቸው ሰዎች ተመልምለዋል። ከዚህም በላይ የወጣው መስፈርት ተገቢውን የሥራ ልምድና የትምህርት ዝግጅት ታሳቢ ያላደረገ እና የእኩልነት መርህን ግምት ውስጥ ያላስገባ ምልመላ ማድረጉ አቅምን እና እውቀትን ያላገናዘበ ከመሆኑም በላይ ከተለያዩ የህግ ተቋማት የሚመጡ ዐቃበያነ ሕጎች፣ ነገረ ፈጆች፣ ጠበቆች፣ የህግ ትምህርት ቤት መምህራን እና ሌሎች የህግ ባለሙያዎችን ያገለለ ነው።

3.  እኛ በዳኝነት የሙያ ዘርፍ ያለን ቅሬታ አቅራቢዎችም 10 ዓመት የሥራ ልምድ እያለን በዚህ በፌዴራል ፍ/ቤት ውስጥ ቢያንስ 5 ዓመት ማገልገል አለባችሁ በሚል የቃል መስፈርት በማውጣት በክልል ፍ/ቤቶች ያገለገልንበትን ጊዜ መና በሚያስቀር ሁኔታ ከምልመላ ውጭ እንድንሆን ተደርገናል። መመሪያን እንዲያሳዩን በምንጠይቅበት ጊዜም ከጉባኤው በቃል ነው የተነገረን በሚል በጉባኤው ጽ/ቤት ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያዎች ምላሽ ሰጥተውናል። ይህም ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ዳኞችን 5 ዓመት ባይሞላቸውም በምልመላው ውስጥ እንዲካተቱ በሚል በቃል እንደተነገራቸውም ባለሙያዎቹ ገልጸውልናል። ስለሆነም ጉባኤው እየተጠቀመ ያለው ድርብ መስፈርት (double standard) መርህ ፈፅሞ ሕግን ያልተከተለ ነው።

4.  ተመሳሳይ የሥራ ላምድ እያለን በክልል ፍ/ቤቶች ሲሰሩ የነበሩ ዳኞች ለምልመላ ሲቀርቡ እኛ ከክልል ወደ ፌዴራል ፍ/ቤቶች ቀድመን ከ4 ዓመት በፊት በመምጣታችን ባቻ የተሻለ ቅድሚያ ሊሰጠን ሲገባ በተቃራኒው የእኩልነት መርህን በሚጥስ መልኩ ከምልመላ ውጭ እንድንሆን ተደርጓል።

ከም/ቤቱ የምንጠይቀው መፍትሔ

·         ከላይ የጠቆምናቸውን የቅሬታ ነጥቦች መነሻ በማድረግ የተከበረው ም/ቤት የሚከተሉትን የመፍትሔ አቅጣጫዎች እንዲወስድልን በአክብሮት እንጠይቃለን።

1.  መጨረሻ ላይ ዳኞችን የሚሾመው ም/ቤቱ እንደመሆኑ መጠን ብቃት የሌላቸው ሰዎች ወደ ሹመት ከመምጣታቸው በፊት ከወዲሁ ከሕግ ውጭ የተደረገው ምልመላ ተገቢ አለመሆኑ ለጉባኤው እንዲገለፅለትና ምልመላው በድጋሚ በአግባቡ እንዲከናወን እንዲደረግ ትዕዛዝ እንዲሰጥልን፣

2.  አላግባቡ የተደረገውን ምልመላ ተከትሎ በጥድፊያ የሚደረገው የፅሁፍ ፈተና እንዲሰረዝ እና በም/ቤቱ ልዩ ክትትል በአግባቡ እንዲከናወን እንዲደረግ፣

3.  ይህ ሁሉ የሚታፍ ከሆነ ብቃት የሌላቸው ሰዎች ወደ ሹመት መምጣታቸው ስለማይቀር ወደፊት የሚደረገውን ሹመት እንዳያጸድቀው ም/ቤቱን እንጠይቃለን

ከክቡር ጠ/ሚኒስትሩ የምንጠይቀው መፍትሔ

1.  በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 81 መሰረት ለፌዴራል ፍ/ቤቶች የሚሾሙ ዳኞን ለም/ቤቱ የሚያቀርቡት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠ/ሚኒስትር እንደመሆናቸው መጠን ለም/ቤቱ ከማቅረባቸው በፊት ምልመላው ሕግን እና መመሪያን በተከተለ መልኩ በድጋሚ እንዲደረግ ለጉባኤው እንዲመልሱት በአክብሮት እንጠይቃለን።

የቅሬታ አቅራቢ ዳኞች ስምና ፊርማ ተካቷል፣

ይምረጡ
(1 ሰው መርጠዋል)
1461 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 762 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us