የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ

Wednesday, 09 May 2018 13:05

ከሚያዝያ 23 ቀን እስከ ሚያዝያ 29 ቀን 2010 ዓ.ም የተካሄደው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ ቅዱስ ሲኖዶስ የርከበ ካህናት ጉባዔ ለአገራችንና ለቤተክርስቲያኗ ጠቃሚ የሆኑ ውሣኔዎችን አሳልፏል፡፡ ከውሣኔዎቹ መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡

 

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶክተር ዓቢይ አሕመድ፣ ከተሠየሙበት ጊዜ ጀምሮ እያደረጉት ያለው ታሪካዊ ንግግር÷ ሀገራዊ አንድነትን፣ ፍቅርና ትሕትናን የሚያስተምር፣ ሰላምንና መረጋጋትን የሚያበሥር፣ የሩቁንና የቅርቡን የሚያስተባብር መንግሥታዊ ሓላፊነት የተሞላበት መልእክት በመኾኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በአክብሮት ተቀብሎታል፤


ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በየክልሉ እየተዘዋወሩ፣ በወንድማማች ሕዝብ መካከል የተፈጠረው መቃቃር ይቅርታ ባልተለየው መንፈስ ተወግዶ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን መመሪያ ከመስጠት ጋራ እያደረጉት ያሉት ጥረት ቅዱስ ሲኖዶስ በሙሉ ልብ ደግፎታል፤ የጥረቱም አካል በመኾን የበኩሉን ድርሻ እንደሚያበረክት ምልዓተ ጉባኤው ተስማምቷል፤


ሀገራችን ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የመጡት ክቡር የእሥራኤል ሀገር ፕሬዝዳንት ሪቨን ሪቢሊን፣ የርክበ ካህናቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ በሚጀምርበት ሚያዝያ 24 ቀን 2010 ዓ.ም.፣ በመንበረ ፕትርክናው ተገኝተው ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ጎብኝተዋል፡፡


በጉብኝታቸው ጊዜም፣ ስለ ዴር ሡልጣን ገዳማችን ኹኔታ ለ30 ደቂቃ ያህል ውይይት ካደረግን በኋላ በኢየሩሳሌም ያሉት ገዳማት በሙሉ እንደሚታደሱ፣ በተለይም አሁን በቅርቡ የመፍረስ አደጋ የደረሰበት የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በቅርቡ እንደሚታደስ የቃል ተስፋ በመስጠት አረጋግጠውልናል፡፡


የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የጉባኤ መክፈቻ ንግግር፣ ትምህርትና መመሪያ÷ የቤተ ክርስቲያኒቱንና የሀገሪቱን ኹለንተናዊ ገጽታ የዳሰሰ፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎትን የሚገነባ ተልእኮ ያለው በመኾኑ ምልአተ ጉባኤው በሙሉ ድምፅ ተቀብሎታል፤


ምልአተ ጉባኤው ከሚያዝያ 23 እስከ 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ለአንድ ሱባኤ ያህል ባደረገው ስብሰባ፣ ከግንቦት ወር 2009 ዓ.ም. እስከ ሚያዝያ 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እና በቋሚ ሲኖዶስ የተላለፉ ውሳኔዎች፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ አማካይነት ቀርበው በአፈጻጸማቸው ዙሪያ ከተወያየ በኋላ አስፈላጊውን መመሪያ በመስጠት ተቀብሎ አጽደቆታል፡፡


በተለያየ ምክንያት የሥራ ዝውውር እንዲደረግላቸው ጥያቄ ያቀረቡ አንዳንድ ሊቃነ ጳጳሳት እና ጳጳሳት፣ የጥያቄአቸው አስፈላጊነት በቅዱስ ሲኖዶስ ከተጠና በኋላ ዝውውሩ ተፈጽሞላቸዋል፤


እናት አባታቸው ሙተውባቸው ሰብሳቢ ያጡ ሕፃናትን እያሳደገና እያስተማረ ለቁም ነገር ያበቃ ዘንድ ቀደም ሲል ቤተ ክርስቲያኒቱ ያቋቋመችው የሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት፣ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር ርዳታ ለጋሾች ጋራ ያለውን የቅርብ ግንኙነት በበለጠ እያጠናከረ ሥራውን ይቀጥል ዘንድ ምልዓተ ጉባኤ መመሪያን ሰጥቷል፤


እግዚአብሔርን መፍራት የመጀመሪያው ጥበብ እንደኾነ እየተገነዘበ የመጣው ወጣቱ ትውልድ፤ ሀገሩንና ሃይማኖቱን፣ ባህሉንና ቋንቋውን፣ ሥርዓቱንና ትውፊቱን ከመጠበቅ ጋራ ሥራ የመፍጠር ክሂሎቱን በበለጠ አጎልብቶ ሀገሩን እንዲያለማ ቅዱስ ሲኖዶስ አደራውን ጥሎበታል፡፡


የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መሠረት ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያናችን የግንባታው ሥራ ማከናወኛ የሚኾን ገንዘብ እንዲያዋጣ ሕዝቡን ከማስተባበር ደረጃ ጀምሮ አስፈላጊውን የገንዘብ ድጋፍ ሁሉ ከመለገስ ወደኋላ ያለችበት ጊዜ እንደሌለ ቢታወቅም፣ የማጠናቀቂያው የደወል ድምፅ እስካልተሰማ ድረስ የማስተባበሩ ሥራም ኾነ የርዳታ ገንዘብ አሰባሰቡ ተግባር እንዲቀጥል ማድረግ ሀገራዊ ግዴታ መኾኑን ትገነዘባለች፡፡ ከዚህ አንጻር የግድቡን ሥራ ለማጠናቀቅ ሁሉም ኅብረተሰብ የጋራ ሓላፊነት ያለበት መኾኑን በመገንዘብና በውል በመረዳት የርዳታ እጁን እንዲዘረጋ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያስተላለፋል፡፡


የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ፣ ከዚህ በላይ በተገለጹትና በሌሎችም መንፈሳዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ሲወያይ ሰንብቶ አስፈላጊዎቹን በመወሰን ስብሰባውን በጸሎት አጠናቋል፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን፡፡


አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት


ሚያዝያ 29 ቀን 2010 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

 

ይምረጡ
(0 ሰዎች መርጠዋል)
635 ጊዜ ተነበዋል

ድርጅትዎ ያስተዋውቁ!

  • Advvrrt4.jpg

እዚህ ያስተዋውቁ!

  • Aaddvrrt5.jpg
  • adverts4.jpg
  • Advertt1.jpg
  • Advertt2.jpg
  • Advrrtt.jpg
  • Advverttt.jpg
  • Advvrt1.jpg
  • Advvrt2.jpg

 

Advvrrt4

 

 

 

 

Who's Online

We have 1081 guests and no members online

Sendek Newspaper

Bole sub city behind Atlas hotel

Contact us